Sunday, 11 September 2016 00:00

ፖለቲካዊ ቀውሱ እንዴት ይፈታል?

Written by  በአበበ ተክለሃይማኖት( ሜጄር ጄኔራል)
Rate this item
(5 votes)

• ከገዢው ፓርቲ፣ከተቃዋሚዎችና ከሌላው ምን ይጠበቃል?
• ብሔር-ተኮር ጥቃቶች የጥፋት መንገዶች ናቸው
• ዴሞክራሲን ማዕከል ያላደረገ ተሃድሶ ጥፋት ነው


የኦህዴድ፣ ብአዴንና ህውሓት ጥፋት
በዚህ ዓመት የተከሰቱት ችግሮች በህዝቦች መካከል ሲወርድ ሲዋረድ አብሮ የዘለቀውን ባህል አጉልቶ ያሳየበት ሲሆን የኢህአዴግ ድርጅቶች ግን ትዝብት ውስጥ የወደቁበት ነው። የኦሮሞ ፕሮቴስት ፅንፈኞች፤ ከኦሮሞ ውጭ ባሉ ብሄርና ብሄረሰቦች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ቢጎተጉቱም፣ ወንጀለኞችና ወረበሎች ከፈፀሙት ውጭ ህዝቡ ራሱ ተከላክሎታል፡፡ ኦህዴድ /ኢህአዴግ ግን ይሄን ብሄር ብሄረሰቦች ላይ  ያነጣጠረ ጥቃት አበክሮ ሲኮንን አልታየም። በጎንደርና አካባቢዋ ፅንፈኞች የትግራይ ተወላጆችን ዒላማ አድርገው በመንቀሳቀስ፤ ሲገድሉ፤ ንብረት ሲዘርፉና ሲያወድሙ የአማራ ክልል ምን እየሰራ እንደነበረ ለመገመት ያዳግታል፡፡ አንድን ብሄር ዒላማ ያደረገ ጥቃት ሲፈፀም ብአዴን በአጠቃላይ ማዘኑን ከመግለጽ ውጭ ማናቸውም ብሄሮችን ዒላማ ያደረገ ጥቃትን በቅጡ አልኮነነም።
 መሪዎች መጥፎ ሽታ ካለው ንፋስ ጋር አይነጉዱም፤ ሽታውን ያጠራሉ እንጂ። በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በሚኖሩባት ጎንደርና አካባቢዋ ዕድሜ ለጨዋው የጎንደር ህዝብ፣ ፅንፈኞችና ወረበሎች ያሰቡትን መፈጸም አልቻሉም። የአማራ ብሄራዊ ክልል አስተዳደር ይሁን ብአዴን ግን እንዲህ መሰል ተግባር በወንድም ህዝብ ላይ እንዳይፈፀም ምንም ዓይነት መልእክት ወይም ማሳሰቢያ አላስተላለፉም። ይልቁንም የመላውን ህዝብ ጥያቄና የፅንፈኛውን ሃይል ዘረኛ ድርጊት ሳይነጣጥሉ በጅምላ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው በማለት አድበስብሰውት አልፈዋል። የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከሆነ በአማራ ክልል በተለይም በጎንደር የሚኖረው ቁጥሩ የማይናቅ የትግራይ ተወላጅ የተመሳሳይ ችግር ሰለባ አይደለምን? ታድያ በእነሱ ላይ ብቻ ያነጣጠረውና በተወሰኑ ቡድኖች የተከናወነው የንብረትና የህይወት ጥፋት እንዴት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው ሊባል ይችላል? ይህን ለአንባቢ የህሊና ፍርድ ትቸዋለሁ።
ህወሓትም በበኩሉ፤ ለ25 ዓመታት ያህል “የትግራይ የበላይነት” አለ የሚል ወሬ ሲናፈስና በብዙ ህዝቦች ዘንድ የተዛባ አረዳድ (perception) ሲፈጠር (ስልጣናቸው ስላልተነካ) ይህን የማስመሰል የፕሮፓጋንዳ ስራ ለማስተባበልም ሆነ ለመከላከል ምንም የሰራው ስራ አልነበረም። ባለቤቱ ካላስተባበለ ደግሞ የሚናፈሰው ወሬ እንደ ሃቅ መቆጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
ህውሓቶች በ1997 ዓ.ም የስልጣን ዙፋናቸው መነቃነቅ ሲጀምር ግን “ኢንተርሃሞይ” ወይም “የዘር ጭፍጨፋ ሊደረግብህ ነው” በማለት ህዝቡን መቀስቀስ ጀመሩ። አሁን ደግሞ “ትምክህት” እና “ጠባብነት” በሚል መቀስቀስ ይዟል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ወያኔ ማለት ህወሓት፤ የትግራይ ህዝብና ህወሓት ደግሞ የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች እንደሆኑ አድርገው እንደሚያስቡት ሁሉ፤ ትምክህትና ጠባብነት የሚለውንም ፍረጃ ከየትኛውም ብሄር ጋር ማያያዝ የኋላ ኋላ ውጤቱ አደገኛ እንደሚሆን ማወቅ ይገባል፡፡
ከ25 ዓመት በፊት በተገኘው የትጥቅ ትግል ድል አድራጊነት ታሪክ አልያም መንፈስ እየተኩራሩና እየተኮፈሱ መኖር አይቻልም። አንዳንድ ወገኖች፣ የትግሉ ድል ህዝቦች በጋራ ያመጡት መሆኑን ክደው (የትግራይ ህዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ መሆኑ ሳይዘነጋ) “እኛ ያመጣንላችሁ ነጻነት ነው” በማለት ሲኮፈሱና ከአንዳንድ ባለስልጣናት ጋር በመሞዳሞድ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ሲያገኙ ህወሓትም ሆነ ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አልታገሉም። ከባለስልጣናት ጋር ተጠግቶ የማይገባን ጥቅም የማግበስበስ ባህሪና ድርጊት በሁሉም የተለያዩ የብሄር አባላት ዘንድ የሚታይ ቢሆንም ይህንን ለመሸፈን ሌላውን የማጉላት እንቅስቃሴ ይታያል። የጥቅም ትስስር ማንኛውንም ብሄር፤ ሃይማኖት ይሁን ሌላ አይለይም። በጥቅም የተሳስረ ማንኛውም ቡድን የቡድኑን ጥቅም እንጂ የወንድሙ ይሁን የእህቱ ጥቅም ቢሆን ጉዳዩ ላይሆን ይችላል። በመሆኑም በአሁኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ስርዓት የሚጠቀሙት በቡድን የተደራጁ፣ ከተለያዩ አካባቢዎችና ህዝቦች የተውጣጡ ሰዎች ናቸው። ሌባ ዘርና ሃይማኖት የለውም፤ዓላማውን የሚያሳካው ከአምሳዮቹ ጋር በመሆን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ሃቅ በሚፃረር መልኩ የትግራይ ሰዎችን ብቻ እንደ ተጠቃሚ አድርጎ ማሰብና መቁጠር በስፋት የሚታይ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ ይህ አስተሳስብ በተለይም ባህር ማዶ  በከተመው የፅንፈኛ ቡድን የሚናፈስ ሲሆን በተደጋጋሚ በመነገሩ ብቻ በህዝቦች ዘንድ የሃቅ ያክል ቁመና እንዲኖረው ተደርጓል። ክፋቱ ደግሞ አሁንም ይህንን የሚያስተባብልና ሃቁን የሚያስገነዝብ አካል አልተገኘም፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ግን ከተልባ የተገኘ ሰሊጥ እንደሚባለው በላባቸው፤ በትጋታቸውና ያለምንም የኢህአዴግ ልዩ ትብብር የበለፀጉ አብዛኞቹ ባለሃብቶች የዚሁ ሃሜት ተጠቂ መሆናቸው ነው።
የማንኛውንም ቡድን፤ ብሄር ይሁን ግለሰብ ጥቃት መከላከል የሚቻለው ዴሞክራት በመሆን ነው። አቶ ሌንጮ ለታ ከኦሮሞ ፕሮቴስት ጋር ተያይዞ ለህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፡- “ኦሮሞን የሚጨቁን ብሄር የለም። አሁን ያለው መንግስት የሚወክለው ብሄር የለም” በማለት ብሄር-ተኮር ጥቃት እንዳይፈፀምና ከተፈፀመም ያለማቅማማት እንዲያወግዙት ጥሪ አስተላልፈዋል። በአንዳንድ ፅንፈኞች ግፊት ሳቢያም የወገኖቻችንን ህይወትና ንብረት በማጥፋት ወንጀል ላይ እንዳይዘፈቁም መክረዋል፡፡
እውን የትግራይ የበላይነት አለ?  
ለመሆኑ በአንዳንድ ጽንፈኞች እንደሚናፈሰው፣ የትግራይ የበላይነት አሁን ባለው የፌዴራል ስርዓት ሊኖር ይችላል? የትግሪኛ ቋንቋ የበላይነት አለ? የትግሪኛ ባህል የበላይነትስ? በአገር ደረጃ የሚወጡት ፖሊሲዎች እቅዶች ወ.ዘ.ተ የትግራይን የበላይነት ለማረጋገጥ ታሳቢ ተደርገው ነው የሚወጡት? ግብርና-መር ኢንደስትራላይዜሽን፣ ጂቲፒ1፣ ጂቲፒ 2… ወዘተ ትግራይን ብቻ ለማልማት ነው እንዴ የተነደፉት? መልሱ ግልፅ ነው:: ከ86% በላይ ለድሃ ተኮር ወጪዎች ኢንቨስት የሚያደርግ መንግስት፤ የበጀት ስሌቱ በግልፅ መስፈርት በሚቀመጥበት አገር ትግራይ ልዩ እንክብካቤ እንደሚደረግላት አድርጎ ማቅረብ ውሸት ብቻ ሳይሆን ከህሊናም ከሞራልም አዃያ ነውር ነው።
 የሥራ አስፈፃሚው፣ የፓርላማዎቹ፣ የፍርድ ቤቶች ሹመትና ስብጥር የትግራይን የበላይነት ያሳያል? በፌዴራል፣  በአዲስ አበባና በድሬዳዋ መስተዳድር ያለው ፖለቲካዊ ሹመትና የሲቪል ስርቫንት አደረጃጀት ትግራይን ለይቶ በሚጠቅም መልክ ነው እንዴ የተዋቀረው? አሁንም መልሱ ግልፅ ነው:: ትግራይ ሩብ የሚያክለው ህዝብዋ በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ውስጥ ነው፡፡ ከቁጥሩ ጋር የማይመጣጠን ህዝቧ ስደተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች በስፋት በልመና ላይ ተሰማርቶ ይታያል፡፡ እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ በስሚ ስሚና በአሉባልታ የትግራይ የበላይነት አለ ማለት የግፍም ግፍ ነው። በተለይ ምሁራን የዚህ ዓይነት ወሬ ሰለባ ሲሆኑ እንደማየት የሚያሳቅቅ ነገር የለም።
ከትግራይ ውጪ ያለው መሬት በማን ይዞታና መስተዳድር ነው ያለው? ወ.ዘ.ተ በመጠየቅ የትግራይ የበላይነት ያለመኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል። ሆኖም በካቢኔ ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ኤታማዦር ሹምና የአገር ደህንነት መስሪያ ቤት ርስት እስኪመስል ድረስ በትግራይ ተወላጆች ለ25 ዓመታት የተያዙ በመሆናቸው የሚነሱ ተገቢ ጥያቄዎች አሉ። ከሌላ ብሄር እነዚህ ቦታዎችን መምራት የሚችል የለም የሚል አንድምታ ስላለው በአስቸኳይ መስተካከል አለበት፡፡
ተቃዋሚና “አጋር” ድርጅቶች
በአገራችን ፖለቲካዊ ምህዳሩ በስብሷል (corrupted ሆነዋል)። ለዚህ ገዥው ፓርቲ የአንበሳውን ድርሻ ቢወስድም ከተወሰኑት በስተቀር በሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ዝቅጠት መኖሩ ግልፅ ነው። ተቃዋሚዎች፤ ኢህአዴግን እያማረራችሁ አትኑሩ፤ ህዝቦች በነቂስ ወጥተው መብታቸውን ለማረጋገጥ በተንቀሳቀሱበት ሁኔታ “የሽግግር መንግስት” እያላችሁ ከኢህአዴግ ምፅዋት አትለምኑ። ሃቀኛ የፖለቲካ ዓላማ ካላችሁ ከአሁን የተሻለ የተመቻቸ ጊዜና ሁኔታ የለም። በአሁኑ ወቅት ፍራቻ ወግድ እየተባለ ነው፡፡ ትክክለኛ አላማ ካላችሁ ህዝቦች ከናንተ ጎን መሰለፋቸው አይቀርም። ዋናው ስራችሁ ህዝቦችን ማንቃት፣ማደራጀትና ማታገል ይሁን። የኤምባሲዎችን ግርግር በሁለተኛ ደረጃ ተመልከቱት። ህዝቦችን ለማሳመን ግን ትክክለኛ የፖለቲካ ዓላማ፣ ከጊዜው ጋር የሚሄድ አደረጃጀትና እንቅስቃሴ ያስፈልጋችኋል። ለፖለቲካ ትግሉ ያመፀው ትውልድ ምክር አስፈላጊ ቢሆንም ዋናዋ ሃይል ወጣቱ መሆኑን አምናችሁ ተቀበሉ፡፡
አሁን ምን ይደረግ?
የእውነት ተሃድሶ ያስፈልጋል። ዴሞክራሲን ማዕከል ያላደረገ ተሃድሶ ጥፋት ነው። በብዙ ትግል የተገኘው ሰላምና እድገት እየደፈረሰ ነው። አሁን በተዳፈነ እሳት ላይ ስለመቀመጣችን ምልክቶች እያየን ነው። ችግሮቹ ስርዓታዊ መሆናቸው ታውቀዋል፤መፍትሄውም ሌላ ሳይሆን የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማረጋገጥና ሕገመንግስቱን ማክበር ብቻ ነው፡፡  
ከሁሉም በፊት ግን በድርጅቶችና በህዝቦች መካከል እየጠፋ ያለውን ያለመተማመን (mis-trust) ደረጃ በደረጃ መገንባት አስፈላጊ ነው። እየተጠራቀመ የመጣው አለመተማመን በ100% የምርጫ ‘አሸናፊነት’ እና ይሄን ተከትለው  በተቀሰቀሱት ተቃውሞዎችና አያያዛቸው ተባብሷል፡፡  
 ከዚህ አንጻር ህዝቦች የተወሰነ ተስፋ እንዲኖራቸው መተማመንን መፍጠር የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ የህዝብ ጥያቄዎች መልስ እንደሚያገኙና ፍትሐዊነት እየተረጋገጠ እንደሚሄድ የሚጠቁሙ ፍንጮች ማሳየት ያስፈልጋል። መተማመኑና አብሮነቱ የሚጠበቀውና ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ሊል የሚችለው ህዝቡን እንደ ኮላ ሆኖ እርስበርሱ የሚያስተሳስረውን ማሕበረሰባዊ እሴቶች ስንጠቀም ነው።
“ከሰው ልብ እምነት (መተማመን) ቢጠፋ አንዳችም ስራ አይሰራም” ይላሉ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ። ስቲግሊዝ ደግሞ ማሕበራዊ ካፒታልን በሚመለከት እንዲህ ይላል፡- “Social Capital is a broad concept that includes those factors that contribute to good governance in both the public and the private sectors, but the idea of trust underlines all notions of social capital”. ለዚህም ነው መንግስት መተማመንን የሚያጠናክሩ እሴቶችና ተግባራት ላይ በሰፊው መስራት አለበት የምለው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በተጠናከረ መንገድ የሚካሄድ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶች ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል።
ከገዥው ፓርቲ ምን ይጠበቃል?
ሕገመንግስቱ እንደሚያከብር በማያወላውል ሁኔታ በሃሳብም በተግባርም ግልፅ ማድረግ፤ ሁኔታዎችን ለመቀየር ቁርጠኝነት እንዳለው በግልፅ ምልክት ማሳየት:: እንደ መንግስትም የስርዓት ጤንነት የሚረጋገጠው በሰዎች በጎ ፍላጎት ሳይሆን በአግባቡ በሚናበብ የቁጥጥርና የሚዛን ጥበቃ ስርዓት በመዘርጋት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕገ መንግስታችን ያስቀመጣቸውን ድንጋጌዎች ሳያወላውሉ ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል፡፡  
ተቃዋሚዎች ድርጅቶች ይነስም ይብዛም የህዝቦችን የተለያዩ አመለካከቶች ይወክላሉ። የህዝቦች መብት ማስከበር የሚቻለውም አመለካከታቸውን በማክበር መሆኑን በማመን፣ ፖለቲካዊ ምህዳሩን መክፈትና ማስፋት:: የተቃውሞ ፖለቲካውን ሃላፊነት ከማይሰማው ፅንፈኛ ሃይል መቀማት የሚቻለው የሃገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶች የራሳቸውን መሪ ሚና እንዲጫወቱ በማስቻል ነው። ይህ ለነገ የማይባል ስራ ነው።
አፋኝ ህጎችና አደረጃጀቶችን ማሻሻል ወይም ማስወገድ
የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት
ሕገመንግስቱን በግላጭ በሚጥሱትና ከፍተኛ ሙስና ውስጥ በተዘፈቁት ላይ አብነታዊ የሆነ እርምጃ መውሰድ
የተከሰተውን ችግርና ወደፊት የሚመጣውን ውስብስብ ጣጣ ኢህአዴግ ብቻውን መፍታት እንደማይችል አምኖ፣ ከተለያዩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስብስቦች፣ ተቋማት፣ ማህበራት፣ የሙያ ስብስቦችና በተለይም ከሰፊው ህዝብ ጋር በመሆን ሃገሪትዋን ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ።
 ከተቃዋሚዎችና ከሌሎች ምን ይጠበቃል?
ተቃዋሚዎች “ኢህአዴግ ከወደቀ በኋላ ቀጣዩን እናስብበታለን” በሚል የማያዛልቅ ፀረ-ኢህአዴግ ‘ግንባር  ጥምረት፣ ውህደት’ ለመፍጠር ከመዳከር ይልቅ አቅማቸውን አስተባብረው፣ ከኢህአዴግ ጋር ተወያይተው ለመስራት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
ከሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ውጪ ሌላ መንገድ እንደሌለ አምነው፣ሰላማዊና ሕገ መንግስታዊ መንገዶችን ብቻ መከተል አለባቸው፡፡
ህዝቡም ወደ ሁከትና እልቂት እንዳይሄድ በጊዜ ማስተማር ወሳኝ ነው፡፡
ጊዜያዊ የስልጣን ጥያቄና ሃገራዊ ደህንነትን ለያይቶ በማየት ሃገራችንን ሊበትኑ ከሚችሉ የውጭ ሃይሎች የሚመጣን ፈተና በአግባቡ ማክሸፍ:: ከእስካሁኑ ጥፋት ትምህርት ያልወሰዱ ፅንፈኞችም ሃይ ባይ ያስፈልጋቸዋል። ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ፤ “ያልተማረ ሰው የራሱን እንጂ ያገሩን፣ የመንግስቱንም ጥቅም ሊያስብ አይችልም፣ስለዚህ በገንዘብ ይታለላል፣ ቢያኮርፍም ይሸፍታል፣ ስለ መንግስቱም ልማት መከራንም ችሎ ተዋርዶ ከሚኖር ብዙ ሰውን ፈጅቶ፣ አገርንም አጥፍቶ ቢሞት ወይም ቢታሰር ስም ይመስለዋል” ይላሉ። ነጋድራስ ይህን ያሉት ከመቶ ዓመት በፊት ነበር፡፡ አሁንም በተወሰነ መልኩ እዚህ አዙሪት ውስጥ ሊያስገቡን የሚዳዱ ሃይሎችን ፊት መንሳት ያስፈልጋል፡፡
የተለያዩ የሙያ ማሕበራትም በየዘርፋቸው ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለአብሮነት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ አለባቸው። ምሁራንም የገጠመንን ችግር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናትና ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ በማተኮር፣ ታላቁና ኩሩው ህዝባችን በበለፀገችና ዴሞክራስያዊ በሆነች አገር የመኖር ተስፋው እንዲለመልም ሳይታክቱ መስራት ይጠበቅባቸዋል፣
የተከበሩ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የማሕበረሰብ መሪዎችም በየፊናቸው ማሕበራዊ እሴቶቻችንን ለገጠሙን ችግሮች በመፍትሄነት የምንጠቀምበትን መንገድ በመጠቆም፣ አጥፊን በመውቀስ፣ ስሜቶችን በማብረድ፣ እርቅና መግባባትን በመስበክ የሚጠበቅባቸውን ሞራላዊና ሃይማኖታዊ ግዴታ መወጣት አለባቸው። ዘረኝነት፣ አሉባልታና ጥላቻ ሃገራችንን ለጥፋት እንደሚዳርጋት ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሰው ህይወት ክቡርነትን ከምንጊዜውም በላይ ማስተማር ያለባቸው ሰዓት አሁን ይመስለኛል።
የሚድያ ሰዎችም የዴሞክራሲ ሃይል በመሆን የህዝብን ብሶት በተገቢው መንገድ በማቅረብና ለእውነትና ለፍትሕ በመቆም፣ ሞያዊና ህሊናዊ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው። የሃሳብና ሌሎች ብዝሃነትን በማክበርና ዕድል በመስጠት የጋራ መግባባትን ለመፍጠር መጣር አለባቸው። በተመሳሳይ መንገድም፣ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ስለሆነ በርካታ ወጣቶች በማህበራዊ ሚድያ መረጃ ይቀበላሉ፤ መረጃ ያሰራጫሉ። ይህን በጎ አጋጣሚ ለመልካም ነገር በመጠቀም ለዴሞክራሲ ያላቸውን ጠበቃነት ማረጋገጥ ያለባቸው አሁን ነው። ስሜት የኋላቀርነት መገለጫ መሆኑን ተገንዝበው፣ ምክንያታዊ ውይይትን በማስቀደም፣ የዘመናቸው ሰዎች መሆንና ማንም በህይወታቸው ቁማር እንዲጫወት መፍቀድ የለባቸውም፡፡ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ትግላቸውን መቀጠልም አለባቸው።

Read 4469 times