Sunday, 11 September 2016 00:00

አርቲስቶች በአዲስ ዓመት ዋዜማ !!!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ሀዘንም ደስታም ያየሁበት ዓመት ነው”
    አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ
ዛሬ የምናጠናቅቀው 2008 ዓ.ም ሀዘንንም ደስታንም ያየሁበት ዓመት ነው፡፡ ከሀዘኑ ብጀምር፤ በዚህ ዓመት ውስጥ አያቴንም አባቴንም፣አሁን በቅርቡ ደግሞ የባለቤቴን አባት ያጣሁበት ከባድ ጊዜ ነበር፡፡ በህይወትሽ ሶስት ሰው በአንድ ዓመት ስትነጠቂ ከባድ ነው፡፡ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ያሳለፍኩበት ዓመት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድና የተፈጥሮም ህግ በመሆኑ መቀበል ግድ ነውና ተቀብዬዋለሁ፡፡ በሌላ ጎኑ 2008 ዓ.ም የስኬት ዓመት ነበር፤ምክንያቱም በርካታ ሽልማቶችን ያገኘሁበት ዓመት ነው፡፡ አራት አሪፍ አሪፍ ሽልማቶችን አግኝቼያለሁ፡፡ ለምሳሌ በ“ለዛ የሬዲዮ አድማጮች ምርጫ”፣ በ”ዛሚ የሬዲዮ አድማጮች ምርጫ.”፣ በ“10ኛው የኢትዮ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል” እና በ“ጉማ” አራት ሽልማቶችን አሸንፌያለሁ፡፡
ሌላው ትልቁ ስኬት እንግዲህ በናፍካ (አፍሪካን ኦስካር አዋርድ) ላይ እጩ ሆኜ፣ በ “ፒፒልስ ቾይዝ አዋርድ” አሸንፌያለሁ፡፡ “79” በተሰኘውና በህዝብ በተወደደው ፊልም ላይ መሪ ተዋናይ ሆኜ በስኬት ያጠናቀቅኩበት ዓመት ነው፡፡ እንግዲህ ዓለም ሁለት መልክ ነው ያላት፡፡ ሀዘንም ደስታም፡፡ በ2009 ዓ.ም እንደፈጣሪ ፈቃድ ብዙ ሀሳቦች አሉኝ፡፡ ለምሳሉ በቅርቡ የሰራሁት አንድ አጭር ፊልም አለኝ - “The shoe makers page” (የጫማ ሰፊው ገፆች) ይሰኛል፡፡ የ8 ደቂቃ ርዝመት ብቻ ነው ያለው፡፡ ድርሰትና ዝግጅቱን ነው የሰራሁት፡፡ አሁን ፊልሙ በተለያዩ አገራት በሚካሄዱ ፌስቲቫሎች ላይ እየተወዳደረ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ውድድር ላይ ከ25 ፊልሞች ምርጥ 15ቶቹ ውስጥ ገብቷል፡፡ በአሜሪካ ካሊፎርኒያም፣ የአፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ውስጥም እየተወዳደረ ይገኛል፡፡ ካናዳ ውስጥ ከ40 ፊልሞች ምርጥ ሶስቱ ውስጥ ገብቷል፡፡ በእንግሊዝ የአጭር ፊልሞች ውድድር፣የመጨረሻዎቹ አምስቱ ውስጥ ገብቷል፡፡ እንግዲህ እስካሁን 12 ፊስቲቫሎች ላይ ነው ለውድድር የላክነው፡፡ የሌሎቹንም ውጤቶች እንጠብቃለን፡፡ ይሄ ፊልም ከዓመቱ ስኬቶች ውስጥ መካተት ይችላል፡፡
በቅርቡ ደግሞ ሁለት ለንባብ የሚበቁ መፅሀፎች አሉኝ፡፡ አንዱ በ 2001 ላይ ለንባብ የበቃው “መሰረታዊ የትወና መማሪያ” የተሰኘው መፅሀፍ ቁጥር 2 ሲሆን በዚህኛው የራሴን ልምዶችና ተሞክሮዎች አካትቼበት፣ ገፁም ዳጎስ ብሎ ይወጣል፡፡ አሁን ማተሚያ ቤት ነው ያለው፡፡ ሁለተኛውና ቀጥሎ የሚወጣው ከሁለት ዓመት በላይ የሰበሰብኳቸው በዓለም ላይ እስከዛሬ ያልተሰሙ እውነታዎችን የያዘ መጽሀፍ ነው፡፡ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ መልሼ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ የናፍካውንም ሽልማት አሜሪካ ሄጄ የምወስደው ህዳር ላይ ነው፡፡
እንግዲህ እንደ ‹‹የጫማ ሰፊው ገፆች›› አይነት ለመጽሀፍ አስቤያቸው የነበሩ አጫጭር ታሪኮች ስላሉኝ እነሱንም ወደ ፊልም የመቀየር ሀሳብ አለኝ፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እነዚህ ሁሉ በ2፼09 ለመስራት ያቀድኳቸው ናቸው፤ትወናውም ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻ፤ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፡- እንኳን አደረሳችሁ መልካም አዲስ አመት ይሁንላችሁ እያልኩ፤ፈጣሪ ሰላማችንን እንዲያበዛልን እመኛለሁ፡፡

---------------------------------------------------

                    “ብዙ ለውጦች ያየሁበት አመት ነው”

          አርቲስት ሀረገወይን አሰፋ
ያጠናቀቅነው 2008 ዓ.ም ብዙ አዳዲስ ነገሮችና በህይወቴ ተጨባጭ ለውጦችን ያየሁበት መልካም አመት ነበር፡፡ መሆንና ማድረግ የምፈልጋቸውን ነገሮች ያከናወንኩበት ዓመት ነው፡፡  እግዚአብሔር ይመስገን!! ለምሳሌ ለረዥም ጊዜ የተለማመድኩትና የተፈተንኩበት ‹‹እንግዳ›› የተሰኘ ቴአትር ነበር፡፡ ይህን ቴአትር ሰርቼ ማየቴ በጣም አስደሳች ነበር፡፡ ቴአትሩ የትወና ችሎታዬን መለኪዬ ነበር፡፡ ገና ስክሪፕቱን ሳየው፣ ይሄንን ቴአትር ከሰራሁት በጣም ጎበዝ ነኝ ማለት ነው፤አልኩኝ ለራሴ፡፡ እኔ ሁሌም የምወዳደረው ከራሴ ጋር ነው፡፡ ሀገረገወይን ምን ሰራች? የቱ ተሳካላት? ምን ቻለች? ምን አቃታት? የሚለውን የምለካውና የማወዳድረው ራሴን ከራሴ ጋር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹እንግዳን››ን ሰርቼ ሳየው በራሴ ተደሰትኩ፡፡
ሌላው ‹‹የቴዎድሮስ ራዕይ››ን ለመስራት አሜሪካ ሄጄ ነበር፡፡ በዚህ ትያትር ላይ ደግሞ ብዙ ጊዜ ትረካ ላይ ያሉት ወንዶች ናቸው፡፡ ወንዶች የተረኩትን ስራ በተሳካ ሁኔታ ሰርቼ መጥቻለሁ፡፡ ለራሴ የትወና ደረጃዬን የለካሁበት አመት ስለነበረ ደስተኛ ነኝ፡፡ መንፈሳዊ ህይወቴን በሚመለከት በፊት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረኝ ቁርኝት ጥሩ አልነበረም፤ ላላ ያልኩ ነበርኩ፤በ2008 ግን ከፈጣሪ ጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት መፍጠሬ ይሰማኛል፡፡ በትክክል መፅሐፍ ቅዱስ ማንበብ፣እንደ እግዚአብሔር ቃል መኖር ጀምሬያለሁ፡፡ ይሄ ከሁሉም በላይ ትልቅ ስኬት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስትቆራኚ ስራም ይሳካል፤ሁሌም ይሰምራል፡፡
በአጠቃላይ ዓመቱ ውጤታማ ነበር፡፡ በሌላ በኩል የፓርኪንሰን ፔሸንትስ አሶሴሽን አምባሳደር በመሆን ተመርጬ፣ባደረግሁት እንቅስቃሴ፤ ማህበሩ በተወሰነ መልኩ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ሰዎች ድጋፍ አድርገውልኛል፡፡ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮም፣የምግብ መድሀኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ከመረጣቸው ሰዎች አንዷ ነኝ፡፡ በነዚህ አምባሳደርነቶች በርትቼ የምችለውን እሰራለሁ፡፡ በ2009 ካቀድኳቸው ውስጥ ፎርማቱ ለየት ያለ የቴሌቪዥን ሾው አንዱ ሲሆን በጥቅምት መጨረሻ ወይም ህዳር መጀመሪያ ላይ ብጀምረው ደስ ይለኛል፡፡ ሌሎችም ስራዎች ይኖሩኛል፡፡ በአዲሱ ዓመት አገሬ ሰላም ሆና ማየት እመኛለሁ፤ለዚህም ሁሌ እፀልያለሁ፡፡ የተነሳው ግርግርና ሰላም ማጣት ተሰብሮ አገሬ የቀድሞ ሰላሟ እንዲመለስ፣የሌለብንን ዘር ቀለም የምንለውን ትተን፣ እንደ ሰው ብቻ እንድንተያይ እመኛለሁ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!!

---------------------------------------

                               “ሁለተኛ ልጄን የወለድኩበት ዓመት ነው”

         አርቲስት ሩታ መንግስተአብ
2008 ዓ.ም ለእኔ የስኬት ዓመት ነበር፡፡ አንደኛ፤ሁለተኛ ልጄን የወለድኩበት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደምወደው የትወና ስራዬ የተመለስኩበት ዓመት ነው፡፡ በሌላ በኩል የናፍካ (አፍሪካን ኦካር አዋርድ) የህዝብ ምርጫ ሽልማት አሸናፊ የሆንኩበት፤የደስታና የስኬት ዓመት ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ በ2009 ዓ.ም ዋናው እቅዴ፤ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ መሰማራት ነው፡፡ በተለይ ከመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በአምባሳደርነት ለመስራት እየተነጋገርን ነው፡፡ ዋናው እቅዴ እሱ ነው፤ሌላው ሽልማቴን አሜሪካ ሄጄ እቀበላለሁ።  በሽልማቱ ላይ ከምናገኛቸው አርቲስቶች ጋር የልምድ ልውውጥና የስራ እድሎችን ለማመቻቸት አቅጃለሁ፡፡ እቅዴ ይህን ይመስላል፡፡ በተረፈ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ። ለእኛ ማሸነፍ የህዝቡ ድምፅ ነበር ወሳኙ፤ ህዝቡ ይህን አድርጓል፡፡ በጣም በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። እግዚአብሔር ያክብርልን፡፡ በተጨማሪ አዲሱ አመት፤ የሰላም የፍቅር --እንዲሆንልንና አገራችን ሰላሟ ተመልሶ፣አንድነታችን እንዲጠናከር እመኛለሁ፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፡- መልካም አዲስ አመት!!

-----------------------------------

                       “ህዝብና መንግስት ያልተስማሙበት ዓመት ነበር”

       ያሬድ ሹመቴ (የፊልም ባለሙያ)
2008 ለእኔ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለአገራችን ትንሽ ጨፍገግ ያለ ዓመት ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ረሀብ የነበረበት አመት ነው፡፡ ህዝብና መንግስት ያልተስማሙበት ዓመት ነው፡፡ ብዙ ሰውም የሞተበት በመሆኑ ክፉ ጥላ ያለው ዓመት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የሁላችንንም ስሜት የሚቀይሩ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡ ለምሳሌ በቤተሰባችን ውስጥ ችግር ቢፈጠር ትልቅ ሀዘን ውስጥ እንደምንገባው ሁሉ አገራችንም ላይ የተከሰተው ነገር የራሳችን ሀዘን ነው፡፡ በጥቅሉ 2008 ዓ.ም የግል አመለካከትን ሁሉ የሚጫን ስለሆነ ቶሎ ባለቀ የተባለ ዓመት ነው፡፡
 በግሌ እስካሁን የምለው “ጉዞ አድዋን” ነው፡፡ 12 ሰዎች 120ኛውን የአድዋ በዓል ለማክበር ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ በእግር ተጉዘዋል፡፡ ይህ ደግሞ በዓሉ ከቀደሙት በዓላት በተለየና በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር የጉዞ አድዋ አዘጋጆች ትልቅ ስራ የሰሩበት ውጤታማ አመት ነበር፡፡
የ2009 የመጀመሪያ ዕቅዴ፤ከመታወቂያዬ ላይ “ብሄር” የሚለውን ማስቀረትና ኢትዮጵያዊ የሚል መታወቂያ መያዝ ነው፤ይህ ካልሆነ ደግሞ ፓስፖርቴን ለመጠቀም ነው ያቀድኩት፡፡ በአዲሱ ዓመት ይህን አደርጋለሁ ብሎ ሌላ እቅድ ለመያዝ፣ ዓመቱ ምን ዓይነት እንደሚሆንና ምን ይዞ እንደሚመጣ ለመገመት አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ፣በእርግጠኝነት ለማቀድ ይከብዳል፡፡ ዓመት በዓሉን እንዴት እንደምንውል እንኳን አናውቅም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አገራችንን ሰላም ካደረገልንና ሁሉም ነገር ከተስተካከለ፣ ሌሎች ብዙ ነገሮችን ማቀድ ይቻላል፡፡ አሁን እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም በጤና አደረሰን ማለት ስለማይቻል፣የምመኘው ለ2009 ሳይሆን ለ2010 ዋዜማ በሰላም ደርሰን፣መልካም ምኞታችንን ለመግለጽ ያብቃን፡፡ አሁንም በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን፣ህዝቡም በኢትዮጵያዊ አመለካከትና ፍቅር አንድ እንዲሆን፣  እየጠፋ ያለውን የአንድነት መንፈስም እግዚአብሄር እንዲመልስልን እመኛለሁ፡፡

-------------------------------------

                            “ዓመቱን በሀዘንና በቅሬታ ለመሸኘት ተገደናል”
           
        ገጣሚ አበባው መላኩ
2008 በስራ በኩል የታየ እንደሆነ በጋራ እየሰራን ያለነው የኪነ-ጥበብ የሬዲዮ ፕሮግራም የተሳካ ነበር ብለን እናምናለን፡፡ በመቀጠል በአንድ ሰው ብቻ የተተወነው የሙሉ ጊዜ ቴአትራችን “እያዩ ፈንገስ” በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዴት ሊያገኝ ይችላል የሚለው የውስጣችን ጥያቄ ነበር፤ ነገር ግን በጣም በተሳካ ሁኔታ ህዝቡ ለ2፡30 በእርጋታ፣ በደስታና በእርካታ፣ስለተመለከተው አመቱ ለእኛ ስኬታማ ነበር፡፡ የዓመቱ ጀንበር እያዘቀዘቀ ካለበት ማለትም ከአመቱ አጋማሽ በኋላ በነበረው ሁኔታ፣የሁላችንም ሀዘን የሆነ ጉዳይ በአገራችን ተከስቷል፡፡ 2008ን ስናብስ ይህንን መርሳት አይቻለንም፡፡ በተለይ በተለይ ደግሞ የአገሪቱ አንጋፋ ዜጎች ላለመኖራቸው፣ምሁራን ላለመታየታቸው፣የሀይማኖት አባቶች ቦታቸውን ላለመያዛቸው፣ ሽማግሌዎች በአገሪቱ ስለመጥፋታቸው መገለጫ ሆኗል፡፡ እነዚህ ወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታዎች ዓመቱን በሀዘንና በቅሬታ እንድንሸኘው አድርጎናል ማለት እችላለሁ፡፡ 2009 ዓ.ም ደግሞ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን? ከሚል ፍራቻና ሰቀቀን ጋር ነው እየተቀበልነው ያለው፡፡ በአዲሱ ዓመት በግሌ “ሀገሬ” የተሰኘ ግጥም በሲዲ ለግጥም ወዳጆች ለማቅረብ ዝግጅት እያደረግሁ ነው፡፡ ምኞቴን በተመለከተ አንድ ግጥም አለኝ፤“ሽማግሌ የሌላት አገር” የሚል፡፡ የሀገሬ ሽማግሌዎች ተግባራቸውን በስፋት መርምረው፣የማሸማገልና የማረጋጋት ሀላፊነታቸውን ሲወጡ ማየት እናፍቃለሁ፡፡
ምሁራንና አንጋፋ የአገሪቱ ዜጎች እንዲሁ ለቀጣይ ትውልድ የተረጋጋችና ሰላማዊ የሆነች አገር የማስረከብ ተግባር የሚወጡበትና የሚንቀሳቀሱበት አመት እንዲሆን በመመኘት፣አዲሱን ዘመን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡
ለሁሉም መልካም አዲስ ዓመት እመኛለሁ፡፡  

Read 6476 times