Sunday, 11 September 2016 00:00

ለኢህአዴግ የቀረቡት ምርጫዎች የእባብ ወይስ የንስር ተሃድሶ?

Written by  ሙሼ ሰሙ
Rate this item
(12 votes)

 ኢህአዴግ በ2007 ምርጫ መቶ ፐርሰንት ተመረጥኩ ባለ ማግስት መሬት አንቀጠጥቅጥ ሕዝባዊ ቁጣ እየናጠው ይገኛል፡፡ ህዝባዊ አመጹ በይዘቱም ሆነ በስፋቱ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ገጽታን የተላበሰና በክልልና በጊዜ ያልተገደበ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ከዝቅተኛው የደህንነትና መለዮ ለባሽ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የመንግስት አካላት ድረስ ህዝባዊ ቁጣው እንዲቆም የተለያየ ማስፈራሪያና ዛቻ ቢቃጣም ህዝቡ ግን “ውሻዎቹ ይጮሃሉ ግመሎቹ ጉዟቸውን ቀጥለዋል” እንዳለ ከርሟል፡፡
ቁጣው የተቀጣጠለው በአዲስ አበባ ዙርያ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ድንበረተኞችን መሬት ለመጠቅለል ያቆበቆበውን ተስፋፊነትና በጎንደር የወልቃይነት ጥያቄ ላይ አጠንጥኖ ቢመስልም ዛሬ ላይ ግን ጉዳዩ በራሱ ጊዜ አድጎ “ሃያ አምስት ዓመት ወደ ወለደው ሕዝባዊ ብሶት” ተሸጋግሯል። በአንድም መልኩ ሆነ በሌላ ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግማል›› ይሏል እንግዲህ ይህ ነው፡፡
አብላጫው ሕዝብ፤ ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ በሰላ ፕሮፓጋናዳ እየተሰነገ፤ ቀቢጸ ተስፋ ሰንቆ የተዘመረለት እድገትና ብልጽግናው ከዛሬ ነገ በሬን ያንኳኳሉ በሚል ምኞት፤ በርን በሩን እያያ በትዕግስትና በጽናት ቢዘልቅም፤ ልማቱ በበሩ ከማለፍ ባሻገር እንደተለመደው ከበይ ተመልካችነቱ ተላቆ ከሃረጋዊ ሃብቱ ተቋዳሻ ለመሆን አለመታደሉ፤ አሁንስ በዛና በቃ፤ እንዲል አድርጎታል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ፤ ዛሬም የልማታዊ መንግስት መጽሃፍትን እየጠቀሱ፤ ህዝቡን ያስቆጣው፤ “ልማት ያመጣው ቅንጦት” እንደሆነ አልያም ‹‹ለአፍሪካ ምሳሌ ይሆናል የተባለው የተንበሸበሸ ዲሞክራሲ” ወይም ዓለምን ያስደመመው ኢኮኖሚያዊ እድገትና በአጋፋሪ የሚመራው የፊደራሊዝም አደረጃጀት እንደሆነ አስመስሎ  አደባባይ መውጣት አልተግባብቶም ከሚባል ውጭ ሌላ ትርጉም ለመስጠት የሚያዳግት ነው፡፡
ይህን ሁሉ ቁጣ ተከትሎ የተቀጠፈው ሕይወትና  የወድመው ንብረት የጥቂቶች አጀንዳ ነው በሚል መንስኤ፣ መፍትሔ መሻት ወይም ለተሃድሶ መነሳት ላይ የሚጋብዘው አደጋ ላይ ስጋት አለኝ። ለዚህም በርዕሴ ላይ ያነሳሁት የእባቡና የንስሩ ትውፊት ለወቅቱ “የኢህአዴግ ዱብ እንቅ” መራራ ምሳሌ ቢመስልም፣ ትምህርት የሚሰጥ እውነትን ያዘለ ስለሆነ አስተያየቴን መሰጠት አሰስላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ዛሬም ቢሆን ሃይማኖት የግል፣ ሃገር የጋራ ነው ከሚለው ፍልስፍና ጋር የተቆራኘሁ ነኝ፡፡
ወደ ርዕሴ ልመለስ፡፡ ሳይንስ ለምን እንደሆነ ለመረዳት ቢያዳግተውም በዓለም ላይ ካሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእንስሳ ዝርያዎች መካከል እባብና ንስር አሞራ እራሳቸውን በማደሰ  እድሚያቸውን ለማራዘም እድል ከተሰጣቸው ፍጡራን መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ልብ በሉ፤ እንግዲህ በአምላክ አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ እንኳን ይህ እድል አልተሰጠውም፡፡
ይህም ሆኖ እባብና ንስር አሞራ ተሃድሷቸው ለየቅል ነው፡፡ እባብ የቆዳ ተሃድሶ ነው የሚያካሂደው። ንስር አሞራ ደግሞ ሁለንተናዊ ተሃድሶ ያካሂዳል፡፡ እባብ ለስላሳነቱን፣አከርካሪ የለሽነቱንና ተጣጣፊነተን ተጠቅሞ በጣም ጠባብ በሆኑ መንታ ድንጋዮች መሃል ታኮ ሾልኮ በማለፍ፣ የቆዳ ተሃድሶውን አድርጎ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ይሸጋገራል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ የንስር ተሃድሶ ፈተናው ብዙ ነው፡፡ ሁለት አማራጭ አለው፡፡ አንዱ አማራጭ የኖረውን ያህል ኖሯልና ቦታውን ለአዲሱ ትወልድ በመልቀቅ፤ሞትን ጠብቆ መሰናበት ሲሆን ሌላኛው አማራጭ ደግሞ በራሱ ላይ አሰቃቂ ጦርነት አውጆ እራሱ ድል ማድረግ ነው፡፡ በዚህ የራስ በራስ ትግል ውስጥ በመጀመርያ መንቁሩን በማፍረስ፣ ስልና ጠንካራ ጥፈሮቹን ቆርጦ በመጣል፣ ገላውንና ክንፉን ነጭቶ ለወራት በረሃብ በመቀጣት ተሃድሶውን አጠናቆ ወደ አዲስ ምዕራፍ ይሸጋገራል፡፡ ከዚህ አሰቃቂ  ተሃድሶ በኋላም ቢሆን እንደ እባብ እድሜው በመቶዎቹ የሚቆጠር አይደለም፡፡ ምርጫው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከተሃድሶው በኋላ አላግብብ የተንሰራፉ  ስል ጥፍሮቹን አራግፎ ይመጣል ወይስ ልብሱን ብቻ ለውጦ ይመጣል ነው ጥያቄው፡፡
ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ሆነ በሕዝብ ሃብት፣ ጊዜና ሕይወት ላይ እየወሰነ፣ ሃገር አፍርሶ ለመስራትና ተደጋግሞ ለመታደስ መብት እንዳለው የሚያምን በዓለም ላይ ብቸኛው ድርጅት ቢኖር ኢህአዴግ ብቻ ነው የሚል ግምት አለኝ፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ የሰጠው እድሜ በጊዜና የተገደበና  በሰዓት የተከፋፈለ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሃብታችንም በጊዜና በቦታ የተወሰነ (Scarce) ነው፡፡ የሰው ልጆች ዕድሜ ገደብ መሻሻልና መታረም የሚችል አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ሃብትንም ቢሆን መተካት አይቻልም፣ ከመታደግ ውጭ፡፡ ሁለቱም  አላቂ ናቸው፡፡
በማይተካ እድሜና በቁጠባ ለትውልድ በሚተላለፍ ሃብት ላይ የሚወስን መንግስት፤ አደባባይ ላይ ወጥቶ በተደጋጋሚ ‹‹የመሳሳትና የመታረም መብት›› አለኝና  የመሳሳት እድል ተደጋግሞ ሊሰጠኝ ይገባል ሲል የትኛውን ተሃድሶ እንደመረጠ ለመረዳት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡
ኢህአዴግም ሆነ ሌላ ፓርቲ በራሱ ተነሳሽነት አስሶ ወይም ከዓለም ተሞክሮ ቀስሞ አሊያም እንደ ኢህአዴግ “ከራሱ ዓዕምሮ አፍልቆ” ያመጠው የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም አስተዳደራዊ ፍልስፍና አልሰራ ብሎ ስራ-አጥነት ሲባባስ፣ልማቱንም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ በተገቢው መንገድ መሳለጥ ሲያቅተው፣ ፌደራሊዝሙ እንደተቀበረው ቦንብ ጊዜው እየፈነዳ አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን ሲያባበስ፣ አስተዳደራዊ መዋቅሩ ፍትህና ርትዕን ሳይሆን ሙስናና በስልጣን መባለግን አልፎ ተርፎም አስተዳደራዊ በደልን ሲያበረታታ እየታየ ራስን ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ ‹‹ፍልስፍናዬ ስላልገባኝ እየተሳሳትኩ በረሃብና በስራ አጥነት፣ በኑሮ ውድነትን በአስተዳደራዊ በደል እየተቀጣችሁ፣ ልማርባችሁ›› ማለት ለሰሚው አይደለም ለተነጋሪውም ግራ የሚገባ ነው፡፡
የኢህአዴግ ባለስልጣናት በግላቸውና ድርጅቶቻቸው ባላቸው ጊዜ፣ ሕይወትና ሃብት ላይ ለመወሰን ሲሉ ትምህርት ቤት እየገቡና እየወጡ ደጋግመው መሳሳትና  ደጋግመው መማር መብታቸው ነው፡፡ በኛና በልጆቻችን ተወስኖ በተሰጠን እድሜ፣ ጊዜና ሕይወት ላይ እንዲሁም በሃገራችን የጋራ ሃብትና ንብረት ላይ ሙከራ ማድረግንና መሳሳትን የሚያጎናጽፍ አንዳችም ምድራዊም ሆነ ሰማያዊም ወይም ሕጋዊና ሕገ-መንግስታዊ አልያምነባራዊ ሁኔታ የለም፣ አልተፈጠረምም ፡፡
ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት ከሳሽም ሆነው አለያም ተከሳሽ ሆነው ሲቀርቡ እኩል ናቸው፡፡ ባለስልጣን ይሁን ታጋይ ወይም ባለጸጋ ይሁን ድሃ ሕግን አላውቅም አሊያም እየሰራሁና አያስተዳደርኩ ስለሆነ፣ የመሳሳትና የማጥፋት መብት አለኝ ማለት እንደማይቻል። ሃያ አምስት ዓመት ስለሰብአዊ መብትና ስለ እኩልነት ሲሰብኩ  የኖሩት ኢህአዴጎች በተለይ ሊስቱት የሚገባ ጉዳይ አልነበረም፡፡
የምርጥ ዜጎች የመብት ጉዳይ ከቀድሞ ስርዓቶች ጋር ተቀብሯል እየተባለ ለአሰርት ዓመታት  ከተዘመረ በኋላ እንደገና እንደ መብት ተቆጥሮ በአደባባይ መቅረቡ አስደማሚ ነው፡፡ ኢህአዴጎች ደርግን ታግለው ስለጣሉ ከሌላው ዜጋ ተነጥለው በተለይ የመሳሳት መብት ከስልጣን ጋር መጎናጸፍ እንደሚችሉ አምነው፣ ይህንኑ የምርጥ ዜጋ ወይም የመለኮታዊ ስርዓት ለራሳችው አጎናጽፈው ከሆነም፣ አሁንም የተሃድሶ መንገድ ምርጫቸው ከየትኛው ጎራ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግተም፡፡ ብሳሳትም፣ ባጠፋም ሕግና ስርዓት እኔ ላይ ሲደርስ፣ ፊቱን ይሸፍን ማለት አስከፊ በመሆኑ ታግለነዋል ከሚሉት “የአጼው ስርዓትም” ሆነ ከደርግ የከፋ የፕሉቶክራሲና የአውቶክራሲ አስተሳሰብ ድምር ውጤት ነው፡፡
ማብቂያ ያጣው የኢህአዴግ የተሃድሶ ጉዞ፤ የትኛውን የተሃድሶ መንገድ እንደወሰደ ሌላ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሰሞኑን የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ሆነ የማዕከላዊ ምክር ቤቱ ያወጡት መግለጫም ሆነ በተከታታይ ለአራት ቀናት የቀረበው የነባር አመራሮች ውይይት፤ እራስን እንደመፈተሽ ወደ ውስጥ ሲመለከት፤ ጣቱን የሚቀስረው የበላይ አመራር በሚባሉት ላይ ነው። በተዋረድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሚኒስትሮችና ቀሪዎቹ ተሿሚዎች ከፍተኛ አመራሩ ላይ ሹም ሽር እንደሚኖርና እርምጃ እንደሚወሰድ ሲናገሩ ይደመጣል። ይህ የሚጠቀሰውና የሚባልለት እርምጃ የሚወሰድበት ከፍተኛ ወይም የበላይ አመራር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ አቶ አባይ ጸኃዬ፣ አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ አባ ዱላን ወይም አቶ ካሱ ኢላላ … ቀጥሎም ሌሎች ሚኒስትሮችና በተዋረድ ያሉ ተሿሚዎች ካልሆነ እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ያደረጉት ሙከራ ሊሳካልኝ አይችልም።
ምክንያቱም እስከ አሁን በምናውቀው ደረጃ ሃገሪቱ የምትመራው በነዚሁ ከፍተኛ ባለስልጣን ነው።  ሻዶ ካቢኒ አቋቁመው እኛ ሳናውቅ እየተመራን ከልሆነ በስተቀር ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ፣ ከሚኒስትሮችና ከማዕከላዊ ምክር ቤቱ ውጭ እንዲሁም ከተስብሳቢዎቹና ከተናጋረዎቹ ሌላ የማይታወቁ ተጠርጣሪዎቹ የት እንደሚገኙና ማን ሊሆኑ እንደሚችል ለመገመትም ያዳግታል። ይህ መቼም ድንቅ ድራማ ከመሆን አይዘልም። ሁሉም ከፍተኛ ባለስልጣን በሰነድም ሆነ በምርጫ ያልተመዘገበውን ከፍተኛ ባለ ሰልጣን ‹‹ጥፋተኛ ነው መጠየቅ ያለበት እሱ ነው እያሉ መቀጠል ዛሬም ላይ ሆኖ የኢህአዴግ ተሃድሶ በየትኛው ጎዳና እየነጎደ እንደሆን አመላካች ነው፡፡
ሌላው የታዘብኩት ነገር ያለመደማመጥ ወይመ ለማደማመጥ ያለመፈለግ አባዜ ነው፡፡ በሃገራችን ታሪክ እንደምናውቀው፤ ሕዝብ ሲናገር መንግስት ያዳምጣል። መንግስት ሲናገር ሕዝብ ያዳምጣል፡፡ ኢህአደግ ግን ሕዝብ ዝም ሲልም ሆነ ሲናገር ወይም ሲቆጣ እኩል ከመናገርና ከመጮኽ ውጭ ዛሬ ላይ ሕዝቡ ምን እያለ ነው የሚለውን ለማወቅ ድፍረቱም ሆነ ባህሉ ያለው ድርጅት አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን መናገር እንጂ ማዳመጥ የሌለበት አስተዳደራዊ ዘይቤ ኢህአዴግ ከየት እንዳመጣው ለማወቅ የሚያዳግት ነው፡፡
ሕዝብ ሲቆጣና መብቱን ሲጠይቅ፤ ጥያቄው ምንድን ነው ከማለት ይልቅ ታፔላ መለጠፍ ይቀድማል፡፡ አጀንዳ የማስጣሉ ርብረብ በቲቪና በሬድዬ አማካኝነት፤ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ምሁራን አስከትሎ”፤ ተረት ተረቱ ይቀላጠፋል፡፡ ይቀጥልና ከቢንላደን አስከ አይሲስ የተሳሰረ የስለላ መረብ በዘጋቢ ፊልሙ ይቀርባል። ጸረ ሰላም ኃይሎች፣ ጠባቦች፣ ትምክህተኞች… ብቻ ማብቂያ የሌለው እነ… ኞች፣ ኞች በማሻማቀቂያነት ይከተላሉ። በመቀጠል ‹‹ያለፈውን ስርዓት ናፋቂዎች መጡብህ፤ እራስህ ተከላከል በሚል እርስ በርስ ስጋትና ጥርጣሬ ውስጥ በሚከት መፈክር አጀንዳው በይዋል ይደር ይዘጋል፡፡
ይህ አካሄድ እንግዲህ ላለፉት 25 ዓመታት የታዘብነው ተደጋግሞ የተሞከረ ግን ያልተሳካ ስልት ነው። መንስኤውም ሌላ ሳይሆን የተለያዩ ማህበረሰብ አካላት ያቀረቡትን ጥያቄ በቅጡ አድምጦና በአግባቡ መርምሮ መልስ ከመስጠት ይልቅ እውነታውን በመሸሽ ሕዝቡን ለሌላ ጥያቄ እንዳያነሳሳ አንገትን ማስደፋት ነው፡፡
ይህ ስልት ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በይዋል ይደር ሰርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ እለት በእለት እየታዘብን የመጣነው ነገር ግን አንገት የማስደፋቱ ሂደት የተፈለገውን ግብ እንዳልመታ ብቻ ነው፡፡ ይልቁን ጥያቄው ይበልጥ እየጠነከረ፤ ቁጣው ታይቷል፡፡ እየከረረ፣ ጉልበት እየተቀላቀለበትና ጥይትን መፍራት እያቆመ እንደሆነ ነው፡፡ አመጽ ለተረጋጋ ለውጥ መሳሪያ ሆኖ እንደማያውቅ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ ሕዝብን አለማዳመጥም ሆነ ማሸማቀቅ የሕዝብ ጥያቄን ከመጉረፍ አግዶ አያውቅም፡፡
ተሃድሶ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚችለው ከፍረጃና ታፔላ ከመለጠፍ በፊት  የሕዝብን እውነተኛ ጥያቄን ከማዳመጥና ከመረዳት በመነሳት  ነው፡፡ እራስን በራስ ጠይቆ፣ መልሶ ለራስ መልስ  በመስጠት መርካት ብዙ ርቀት የሚወስድ መንገድ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ በውስጥ ችግር የሚናጥ ፓርቲ መሆኑ ከራሱ አንደበትም ሆነ አፈተልከው ከሚወጡ መረጃዎች መገመት ይቻላል። የራሱን ችግር ወደ ሕዝቡ መውሰድ ወይም በራሱ ችግር በመተብተቡ ምክንያት የሕዝብን ጥያቄ መሸሽ፣ ማጣጣል ወይም በርግጎ አርምጃ በመውሰድ ለመቅጨት መሞከር ያልተጠበቀ የዞረ ድምር እንዲከሰት በር መክፈቱ አይቀሬ ነው፡፡ የኢህአዴግ ተሃድሶ ከጅምሩ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን ለማስረዳት የሚያግዙ በርካታ ተምሳሌቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በእኔ እምነት ግን ራስን ከሁሉ በላይ አድርጎ ማሰብና የተአምረኝነት ዝንባሌ፣ በሕዝብ ሃብት እድሜና ሕይወት ላይ “ተደጋጋሚ ስህተት እየሰሩ” ተደጋጋሚ እድል መሻት፣ ሕዝብ ፊት  በግንባር ቀርቦ ጥያቄውን ለመረዳት እንደ አለመሞከር በቂ ምልክቶች የሉም የሚል እምነት አለኝ፡፡
እስከ ዛሬ ሁሌም ጊዜና ጉልበት ከኢህአደግ ጋር ነበሩ፡፡ ዛሬ ላይ ግን ይህ ተለውጧል፡፡ ሕዝብ ተስፋውና ትዕግስቱ ይበልጥ እየተሟጠ መጣቷል፡፡ ስለ ዳቦ እያወራ ስለ ኬክ ሰምቶ ወደ ቤቱ የሚገባበትን ጊዜ አርቆ ቀብሮታል፡፡ ኢህአዴግም ኳሷ በእርሱ ሜዳ ላይ ነች። ለግል ስልጣንና ጥቅም ወይም ለድርጅት ዝናና ክብር ሳይሆነ ለሃገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል አስቦና አስተውሎ ይመርጥ ዘንድም  የእባብ ተሃድሶ ሆነ  የንስር ተሃድሶ ከፊቱ ተዘርግተዋል፡፡

Read 13440 times