Sunday, 11 September 2016 00:00

የወልቃይት ችግር መፍትሔ፡- ህጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ?

Written by  አዲስ - ከድሬዳዋ
Rate this item
(38 votes)

 ወልቃይት ላይ እየተነሳ ያለውን የማንነት ጥያቄ ከምሁራን እስከ ሚኒስትሮች ድረስ ልክ እንደ ስልጤ የአዲስ ማንነት ጥያቄ ወይም ልክ በኦሮሚያና ኢትዮ- ሶማሌ ክልል እንደነበረው የድንበር ክርክር አድርገው ሲናገሩና ከዚህ አንፃር የመፍትሔ ሃሳቦችን ሲያስቀምጡ ይሰማል፡፡
እንደሚታወሰው የስልጤ ህዝብ፤ ቀድሞ የሚታወቅበት የጉራጌ ማንነቱ ትክክል አይደለም፤ እኔ የራሴ ማንነት ያለኝ ብሔረሰብ ነኝ ብሎ የማንነት ጥያቄ አንስቶ፣ በህገመንግስቱ አንቀፅ 39 አማካኝነት አዲስ ማንነቱ እውቅና አግኝቷል፡፡
በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል መካከልም የይገባኛል ጥያቄዎች ተነስተው በበርካታ ቀበሌዎች ላይ በህገመንግስቱ አንቀፅ 42 መሰረት፣ ሪፈረንደም ተካሂዶ መፍትሔ ተበጅቶለታል፡፡
ወልቃይት ላይ እየተነሱ ያሉ የማንነት ጥያቄዎችም ከዚህ አንፃር መፍትሔ ሊያገኙ ይችላሉ ባዮች ብዙ ናቸው፡፡ ወልቃይት ላይ ግን ሁለቱም መንገዶች ለውሳኔ መነሻ ይሆኑ ካልሆነ ዘላቂ መፍትሔ ግን የሚያስገኙ አይመስለኝም፡፡
ወልቃይት ላይ እየተነሳ ያለው ጥያቄ እንደ ስልጤ የአዲስ ማንነት ጥያቄ አይደለም፡፡ ወልቃይት አማራ ነው ሲባል አዲስ ማንነት መፈለግ አይደለም፤ አማራ ብሔር በሀገሪቱ ከሚታወቁ ብሔር ብሔረሰቦች አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም ወልቃይት አማራ ነው የሚል ጥያቄ ካለ እንደ ስልጤ አዲስ ማንነት የሚፈልግ አይደለም ማለት ነው፡፡
ድንበርን በተመለከተም በተደጋጋሚ እየተጠቀሰ ያለው በጠገዴ እና ፀገዴ ወረዳዎች መካከል የሚያከራክሩ አንድ ወይም ሁለት የገጠር ቀበሌዎችን መፍትሔ ለመስጠት በኦሮሚያና ኢትዮ ሶማሌ ክልሎች መካከል የተወሰደውን እርምጃ እንደ ተሞክሮ ማቅረብ ይቻላል። ሆኖም የወልቃይት ጥያቄ በዚህ መልስ የሚያገኝ አይደለም፡፡ ወልቃይት ላይ በመንግስታዊ መረጃዎች ላይ እንደተመለከተው፤አብዛኞቹ ነዋሪዎች ብሔራቸውን ሲጠየቁ ትግሬ ነን ብለው ነው ያስመዘገቡት፡፡ ሆኖም ትግሬነታቸው ከአድዋው ወይም ከመቀሌው ትግሬ የተለየ ነው፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ በሰፈራ፣ ለቢዝነስ ወይም ለፖለቲካ ከተከዜ ማዶ የመጡትን ትግሬ ሲሉ ራሳቸውን ግን ወልቃይቴ ብለው እንደሚለዩ ነው የሚነገረው፡፡ በባህላቸውም ከስም አወጣጥ እስከ ሃዘንና ደስታ አገላለፅ ከአማራ ጋር ብዙ የሚጋሯቸው ነገሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በአንዳንድ ሁነቶች ላይ አማርኛን፣ በሌሎች ሁነቶች ላይ ደግሞ ትግርኛን የመጠቀም ልምድ ነው ያላቸው፡፡ የስጋ ዘመዶቻቸውም የሚገኙት ከሽሬ ይልቅ በአርማጭሆ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ባጠቃላይ በሁለት ብሔሮች ድንበር አካባቢ የተቀየጠ ማንነትን ካዳበሩ ሌሎች ብሔሮች አንፃር ሊታዩ የሚችሉ ህዝቦች እንደሆኑ ነው መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚያሳየው፡፡
ስለሆነም ወልቃይት ላይ እየተነሳ ያለው ጥያቄ፤መነፃፀር ያለበት ከስልጤ ወይም ከኦሮሚያ- ኢትዮ ሶማሌ ድንበር ውዝግብ ጋር ሳይሆን ከሌሎች ጋር ነው። ለምሳሌ፡-
ቀድሞ በሃገራችን ሶዶ፣ ጉራጌ እንደሆነ ነበር የሚታወቀው፡፡ ሆኖም ከሶዶ ጎሳዎች አንዱ የሆነው ሶዶ ጂዳ፣ እኛ ጉራጌ ሳንሆን ኦሮሞ ነን ብለው ወደ ኦሮሚያ ተጠቃለሉ፡፡ ይህ ሲሆን እንዴት ተደርጎ በሚል የተነሳ አቧራም አልነበረም፣ የቀለጠ እልልታም አልነበረም፡፡ ጉራጌ ሶዶ ጂዳን በሰላም ሸኘ፡፡ ኦሮሚያም ኦሮሞነታቸውን በሰላም ተቀበለ። አለቀ፡፡
ቀደም ሲል በሽግግር መንግስቱ ወቅት በቦረና ዞን ካሉ የኦሮሞ ጎሳዎች አንዱ የሆነው የገሬ ጎሳ፣ በተወካዮች ምክር ቤት በኦህዴድ ተወክለው የነበሩ ሲሆን የጎሳው ሽማግሌዎች ግን ከመከሩ በኋላ፤ እኛ ኦሮሞ ሳንሆን ሶማሌ ነን በማለታቸው ሶማሌ ሆነዋል፡፡ ኦሮሚያ በሰላም ሸኘ፤ ሶማሌ በሰላም ተቀበለ፡፡ እዚህም የተነሳ አቧራ አልነበረም፡፡
ያለኝ መረጃ እንደሚያመለክተው፤የወልቃይት አማራነት ኮሚቴን ከሚያስተባብሩት አንዱ የሆነው ኮለኔል ደመቀ፣ቀድሞ የህወሓት ታጋይ የነበረ ሰው ነው፡፡ ሐሳቡን ከሚያራምዱ ሰዎች መካከልም አብዛኞቹ ቀድሞ ብሔራቸውን ሲጠየቁ፤ ትግሬ ነን ይሉ የነበሩ ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ስለሆነም የወልቃይት አማራነት ጥያቄ በብዙሀኑ ወልቃይቴ የሚደገፍ መሆኑ ከተረጋገጠ የሚሰጠው የመፍትሔ እርምጃ የስልጤን የመሰለ ሳይሆን ከላይ ያስቀመጥናቸውን ሁለት ምሳሌዎች የተከተለ መሆን አለበት፡፡
ሐገራችን አዲስ የብሔር ፌደራሊዝምን መከተል ስትጀምር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ማንነቱን በቀላሉ መለየት የሚችሉ ሲሆን ድንበርተኛ አካባቢ የሚኖሩና የተቀላቀለ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ግን ዛሬ ይሄንን ነን፣ ነገ ያንን ነን ሊሉ መቻላቸው የታወቀ ነው፤ በወልቃይት የተከሰተውም ይሄው ነው፡፡
መፍትሔው
መፍትሔው የወልቃይት ፀገዴ (ምዕራብ ትግራይ ዞን) ነዋሪዎች ነፃ ሆነው ማንነታቸውን እንዲወስኑ እድል መስጠት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ግን ሊነሱ የሚችሉ ሶስት ስጋቶች አሉ፡፡ በመፍትሔ ፍለጋው ሂደት ሊያጋጥም የሚችለው የመጀመሪያው ችግር፤ ወልቃይቴዎች ትግርኛ ተናጋሪ ከሆኑ  ትግሬ ናቸው የሚለው አስተሳሰብ ነው። ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የብሔር ማንነቱና የሚናገረው ቋንቋ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለአንዳንዶቹ ግን አይደለም፡፡ በቅርቡ በአማራ ክልል የማንነት ጥያቄው መልስ ያገኘው የቅማንት ማህበረሰብ አማርኛ ተናጋሪ ነው፡፡ ግን አማራ አይደለሁም ብሏል፡፡
በድሬዳዋ ዙሪያ ያሉት የጉርጉራ ጎሳዎችም ቀላል የማይባሉት ኦሮምኛ ተናጋሪ ናቸው፡፡ ግን ጉርጉራ ሶማሌ ነው፡፡ እንግሊዘኛ ተናጋሪን ሁሉ እንግሊዛዊ ነው እንደማንለው ወልቃይትም ትግርኛን በስፋት ስለተጠቀመ ትግሬ ነው ብሎ መደምደም ትክክል አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ይሄንን እውቅና ሰጥቶና አክብሮ፣ ማንነታቸውን በራሳቸው እንዲወስኑ ሊፈቀድላቸው ይችላል ወይ የሚለው አንዱ ስጋት ነው፡፡ ሰዎቹ አማራ ነን ካሉ እና ቀጥለው ደግሞ ወደ አማራ ክልል መካለል ከፈለጉ መብታቸው ነው፡፡ አማራ ክልልም ለአገው ህዝቦች፣ ለኦሮሞዎችና ለአርጎባዎች እንደሚያደርገው፣በፈለጉት ቋንቋ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ የሚከብደው አይመስለኝም፡፡ ይሄ የትኛውንም ፌደራላዊ ስርዓት አይሸረሽርም- ያጠናክራል እንጂ፡፡
በመፍትሔ ፍለጋው የሚያጋጥመው ሌላኛው ችግር ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ ወልቃይት ጸገዴ (ምዕራብ ትግራይ) ከ20 አመት በፊት ምንም ያልነበራቸው በርካታ ሚሊየነሮች የተፈጠሩበት አካባቢ ነው፡፡ ለትግራይ ክልልም ዋነኛው የውጭ ምንዛሪ ማግኛ፣ የግብር መሰብሰቢያና መሬት የሌላቸው የሚሰፍሩበት አካባቢ ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ሚና የትግራይ ክልል አካባቢውን ላለማጣት የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግ ሊያስገድደው ይችላል፡፡ በተጨባጭ በአካባቢው በመንግስት የተደገፉ ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፎች መደረጋቸው ይሄንኑ ሊያሳይ ይችላል፡፡
ሶስተኛው ችግር/ስጋት ከሰፋሪዎች ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ወልቃይት ፀገዴ (ምዕራብ ትግራይ ዞን) መሬት የሌላቸው፣ ወይም የመሬታቸው ምርታማነት የተሟጠጠባቸው በሺ የሚቆጠሩ የሌሎች የትግራይ ዞን ነዋሪዎች በመንግስት ድጋፍ ሰፍረውበታል፡፡ የኢፌዴሪ መንግስት የመከላከያ ሰራዊቱን የብሔራዊ ተዋፅዖ ለመጠበቅ በሺ የሚቆጠሩ የህወሓት ታጋዮችን ሲቀንስም በአካባቢው እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል አካባቢው ሐገራችን ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት የሰሊጥ ምርት በብዛት የሚመረትበት በመሆኑ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሚመጡትም በርካቶች ናቸው፡፡ ይሄ ሁሉ የፈጠረው የብሔር ተዋፅዖ (የዴሞግራፊ) ለውጥ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በመሆኑም የወልቃይት ማንነትን ለመወሰን ድምፅ መሰጠት ካለበት ተሳታፊ መሆን ያለባቸው ወልቃይቴዎች እንጂ በሰፈራና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ባለፉት 35 አመታት ወደ አካባቢው የመጡ የሌላ አካባቢ ተወላጆችም ጭምር መሆን የለባቸውም፡፡
ይህ ከህገመንግስቱ ጋር የሚጣረስ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ሪፈረንደም የሚካሄደው የወልቃይት ማንነትን ለመወሰን እስከሆነ ድረስ በሪፈረንደሙ መሳተፍ ያለባቸው ወልቃይቴዎች ብቻ መሆን አለባቸው፡፡ ባይሆን የወልቃይት አማራነት ጥያቄው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ በሰፋሪዎቹ የመኖር ዋስትና ላይ ምንም ስጋት የማይፈጥር መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡
በነገራችን ላይ በወልቃይት ማንነት፣ ወልቃይቴዎች ብቻ ይደመጡ ስንል ሃሳቡ እስከ ዛሬ ፌደራላዊት ሃገራችን ከተገበረቻቸው ተሞክሮዎቿ ላይ በመመስረት እንጂ አዲስ አቅጣጫ በመቀየስ አይደለም፡፡
ለምሳሌ፡-
የሐረሪ ክልል በታሪካዊቷ የሐረር ከተማ ሐረሪዎች ያላቸውን ታሪካዊ ባለቤትነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሀረሪዎች እንድትሆን ሲወሰን በክልሉ አብላጫው ነዋሪ ኦሮሞና አማራ መሆኑ እየታወቀ ነው፡፡
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከጎጃምና ከወለጋ ተቆርሶ ከአዲስ ሲመሰረት በቁጥር አማራ የሚበዛባቸው   ወረዳዎች ሁሉ ወደ ክልሉ እንዲጠቃለሉ ተደርጓል። የውሳኔው መነሻ ደግሞ አማሮቹ በመንግስት ወይም በራሳቸው የሰፈሩ እንጂ ነባር ነዋሪዎች አይደሉም በሚል ነው፡፡
ድሬዳዋ ላይ በኦሮሚያና ሶማሌ የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳ መፍትሔ መስጠት ባለመቻሉ ድሬዳዋ ተረስታ የቆየች ሲሆን ከተማዋ ራሷን በራሷ የምታስተዳድርበት ቻርተር ባለቤት እንድትሆን ሲወሰን እስከ አወዛጋቢው የ1999 ቆጠራ ድረስ በከተማዋ አብላጫ ቁጥር ያለው አማራ፣ ቁጥሩን የማይመጥን ውክልና ተሰጥቶት፣ 40 ፐርሰንት ኦሮሞ፣ 40 ፐርሰንት ሶማሌ፣ 20 ፐርሰንት “ሌሎች” (ማለትም አማራ፣ ደቡብ፣ ትግሬ፣ ሀረሪ) ፖለቲካዊ ውክልና እንዲኖራቸው ሲደረግ መነሻው ይሄው ነባር ህዝብነት መሆኑን ማስታወስ ይቻላል፡፡
ጋምቤላ ክልልም ቢሆን አሁን የክልሉ ፕሬዚደንት የሆኑትን ጨምሮ በርካታ ኑዌሮች ከደቡብ ሱዳን ወደ አሁኑ ጋምቤላ ክልል መጥተው በክልሉ አብላጫውን ቁጥር እስከሚይዙ ድረስ በከተማዋና አካባቢው በሰፈራና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሄዱት ደገኞች አብላጫውን ቁጥር ይይዙ ነበር፡፡ ሆኖም የክልል ምስረታውም ሆነ የስልጣን ድልድሉ፣ ነባር ህዝቦችን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው የተካሄደው፡፡. . . . ሌላም . . . . . ሌላም. . . . .
እነኚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ምሳሌዎች ተግባራዊ የተደረጉትና አሁንም እየተተገበሩ ያሉት ይሄንን አሰራር የሚደግፍ አንዳች እንኳ የህገመንግስት አንቀፅ ስላለ ሳይሆን በትምህርትም፣ በአስተዳደርም፣ በኢኮኖሚውም፣ በሀገር ባለቤትነት ስሜትም . . . . ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ደረጃ ላይ ስላልሆኑ ወደ ኋላ የቀሩትን መደገፍ ይገባል በሚል ታሳቢ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር “ህጋዊ ሳይሆኑ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች” በብዙ ቦታዎች ላይ ተግባራዊ ተደርገዋል፤ እየተሰራባቸውም ነው፡፡
ይህንን እያደረገ ያለ መንግስት፤ ወልቃይት ላይም ተመሳሳይ ፖለቲካዊ ውሳኔ ቢወስን፣ ለምሳሌ ማንነታቸውን ራሳቸው እንዲወስኑ ቅድሚያ ቢሰጣቸው አዲስ ነገር አይሆንም፡፡ እንደውም በሐረሪ ጉዳይ ከሐረሪ ክልል ውጭ የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች ድምፅ እንዳላቸው ሁሉ በወልቃይት ጉዳይ ወልቃይትን በተለያዩ ምክንያቶች የለቀቁ ወልቃይቴዎች ጭምር ድምፃቸው የሚሰማበት ሁኔታ ቢመቻች ተገቢ ነው፡፡
ባጠቃላይ እነኚህ ሶስት ስጋቶችን ግምት ውስጥ አስገብተን ስናይ፣ ለወልቃይት የማንነት ጥያቄ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ሊከብድ ይችላል፤ የፌደራል መንግስት የወሰነው የወልቃይት ማንነት፣የስልጤ የማንነት ጥያቄ በተፈታበት መንገድ የትግራይ ክልል ብቻውን እንዲፈታው የቤት ስራ መስጠቱ መፍትሔ የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡ የማንነት ጥያቄዎችን እያነሱ ያሉት ወልቃይቴዎች አዲስ ማንነት ፍለጋ ሳይሆን አማራ ነን የሚል ጥያቄ በመሆኑ አማራ ነን የሚሉ ሰዎችን ብአዴን ሊያናግራቸው፣ ሊያደራጃቸውና መብታቸው እንዲከበር ሊታገልላቸው ይገባል፡፡ በኦሮሚያ ወይም አዲስ አበባ ያሉ አማሮችን ብአዴን በፖለቲካ አደራጅቶ እንደሚያታግላቸው፣ አማራ ነን የሚሉ የወልቃይት ተወላጆችንም ሊያደራጅና መብታቸውን ሊያስከብር የሚገባው ብአዴን ነው (ወይ ሌላ የአማራ ድርጅት ካለ)፡፡ የማንነት ጥያቄው መፍትሔ እንዲያገኝ በማድረግ ረገድም ህወሓትና ብአዴን በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ መመቻቸት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሁኔታው ከድርጅት ማለፍ ካለበትም ሁለቱ ክልሎች በጋራ ሊወስኑት የሚገባው ነው የሚሆነው፡፡ ትግራይ ክልል በተናጥል የሚያስፈፅመው የማንነት ጥያቄ ተዓማኒነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳና ከውሳኔ በኋላ ሌላ ተቃውሞ ሊከተል ይችላል፡፡ በዚህ ሂደት ክልሉ በገለልተኛነት ያለ ጫና የማንነት ጥያቄው መልስ እንዲያገኝ ሊያደርግ ይችላል የሚለው ብዙዎች በጥርጣሬ የሚያዩት ነው፡፡ ወልቃይቴዎች ልክ እንደ ኩናማ ወይ ኢሮብ አዲስ የብሔር ማንነት ጥያቄ አቅርበው ቢሆን ነበር ህወሓት ብቻውን ይፍታ የሚባለው፡፡

Read 25719 times