Saturday, 10 September 2016 14:07

አነጋጋሪው የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ምጥን ዳሰሳ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(16 votes)

• የአማራ፣ የትግሬ ወይም የኦሮሞ ስርወ - መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም
• ‹‹ምኒልክ ጡት ቆርጠዋል” ብለው ሀውልት ያቆሙ በድርጊታቸው ማፈር አለባቸው
• በ21ኛው ክፍለ ዘመን የግዕዝ ፊደላትን ጠልተን ላቲን ፍለጋ የሄድንበት ምክንያት
ምንድን ነው?


(ካለፈው የቀጠለ)
ባለፈው ሳምንት “አነጋጋሪው የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ምጥን ዳሰሳ” በሚል ርዕስ ደራሲው “የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” በማለት ለንባብ ባበቁት አዲስ መጽሐፍ ላይ የተደረገ ምጥን ዳሰሳ ማቅረባችን ይታወቃል፡፡ ቀሪውን ክፍል እነሆ፡
ጥንት፣ ከዛሬ 5 እና 6 ሺህ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ እንደ ዛሬው ሳይሆን ኃያልና ገናና ነበረች። አብዛኛው የዓለም አገራት (አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያ…) ባልሰለጠኑበትና በማይታወቁበት ጊዜ ኢትዮጵያ ታዋቂ፣ ሥልጡንና ገናና ነበረች፡፡ መርከቦች ሰርታ ከሩቅ ምስራቅ አገሮች ጋር ትነግድ ነበር፡፡ የአፍሪካ አገሮችን ሱዳን፣ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ … በቅኝ ገዢነት ታስተዳድር ነበር፡፡
ፈርኦኖች ሆነው ግብፅን ካስተዳደሩ 14 እንስት ነገሥታት ውስጥ፣ ግብፆች አራቱን ብልሆችና የተዋቡ ንግሥቶች የፍቅር አማልክት ናቸው በማለት ያመልኳቸው ነበር፡፡ ንግሥት ሳባ (ኢትያኤል) የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ንግሥት አልነበረችም። ከእሷ በፊት ኢትዮጲስ 3ኛ፣ ልጁን አቲግዚያን በጣም ይወድ ስለነበረ ሰንደቅ-ጃን በሚል የንግሥና ስም ንግሥተ-ሳባ ከመወለዷ ብዙ ዓመታት በፊት አንግሶአት ንግሥተ- ነገሥት ሆና ኢትዮጵያን ለ45 ዓመታት ገዝታለች፡፡ ኢትዮጲስ ሌሎች ሁለት ሴት ልጆቹንም ንግሥቶች አድርጎ አንግሷቸዋል፡፡ አንዷ አሊና የተባለችው የኤደን ንግሥት ነበረች፡፡
ከ2900 ዓመት በፊት ደግሞ አክሱማይት የተባለው የንግሥተ-ሳባ የልጅ ልጅ፣ ኢትዮጵያውያን ንግሥቶችን ‹‹ሕንደኬ›› በሚል የማዕረግ ስም በኑቢያ (ሱዳን) በግብፅና በሊቢያ አንግሶ ነበር፡፡ በ1000 ዓመታት ጊዜ ውስጥ አክስቱን ጨምሮ የ13 ሴት ንግሥታት በታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኝ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ገልጸዋል፡፡
አረቦች እነዚህን የመሳሰሉ ንግስቶች ጨርሶ አልነበራቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ንግስቶች ነበሩ ሲገዟቸው የኖሩት ይላሉ ፕሮፌሰር፡፡ አረቦች፣ በኢትዮጵያውያን ሴቶች መገዛታቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ጣዖታት ያመልኳቸውም ነበር፡፡ ዛሬ የእነዚያ አስደናቂ ነገስታት ዝርያ የሆኑ ቆነጃጅት ኢትዮጵያውን ሴቶች፣ የአረቦች የቤት ውስጥ አገልጋይ ሆነዋል፡፡ አይ ጊዜ! ይህ ለኢትዮጵያ አሳዛኝና አሳፋሪ ውርደት ነው በማለት ቁጭታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጥንት ጊዜ የመን ለብዙ ዓመታት የኢትዮጵያ ግዛት እንደነበረች በታሪክ ድርሳናት ሰፍሮ ይገኛል። ያን ጊዜ የመን ስሟ “ናግራን” ነበር፡፡ ናግራ “ና በግራ በኩል” ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የመንን ቅኝ በሚገዙበት ወቅት የወታደራዊ ማዘዣ ቃል እንደነበር፣ የመን የሚለው ቃል “የማን?” ከተሰኘው አማርኛ የፈለቀ መሆኑንም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ያብራራሉ፡፡
ደራሲው በፅኑ የተቃወሙትና ጥልቅ ትንታኔ የሰጡበት ጉዳይ ስለ ዳግማዊ ምኒልክ የሚነገረውን አፈ-ታሪክ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ርካሽ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊያደርጓቸው፤ ‹‹አፄ ምኒልክ ጡት ቆረጡ፤ 5 ሚሊዮን ኦሮሞዎች ገደሉ›› እያሉ የሚነዙት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ፣ ከእውነት የራቀ ነው በማለት ማስረጃ ጠቅሰው ይሞግታሉ፡፡ ይህ ሁሉ የምኒልክን ባህርይ ካለማወቅ የመጣ ነው ይላሉ፡ ‹‹ምኒልክ ተበቃይ አልነበሩም፡፡ ይቅር ባይ፣ በተጨባጭ እውነታ ላይ የተመሠረተ ምክንያታዊ አስተሳሰብ የነበራቸው፣ ራሳቸውን እንደ ጥሩ ክርስቲያን የሚያዩ ነበሩ፡፡ በጦርነት ላይ የሴት ጡት መቁረጥ ፍጹም ከባህርያቸው ውጪ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ውንጀላ መሠረተ-ቢስና ከተንኮለኞች የመነጨ ነው፡፡”
ይህንንም አባባላቸውን በምሳሌ ሲያስረዱ፡- ‹‹የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አምፀው ጦርነት አነሱና ቆስለው ተማረኩ፡፡ ምኒልክ የቆሰለውን ምርኮኛ ገድሎ በመጨረስ ፈንታ ቁስላቸውን ራሳቸው አክመው፣ አጠገባቸው አስቀምጠው አብረዋቸው እንዲመገቡ በማድረግ ፍቅር ነው ያሳዩዋቸው፡፡ ሥልጣናቸውንም አልወሰዱባቸውም፤ ያለማመንታት መልሰውላቸዋል፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በእርግጥ ሩህሩህ ነበሩ፡፡ አገራቸውን ለመውረር የመጡ የኢጣሊያ ምርኮኞችን እንኳ በርህራሄና በደግነት ነበር የያዟቸው፡፡ እኚህ ሰው ጡት ቆርጠዋል (አስቆርጠዋል) ብሎ መፈረጅ አግባብነት የሌለው ትንሽ የፖለቲካ ጠቀሜታ ለማግኘት የሚነዛ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ‹‹ምኒልክ ጡት ቆርጠዋል ብለው ለማስጠላት ሀውልት ያቆሙ አካላት በድርጊታቸው ማፈርና ያንን አሳፋሪ ሀውልትም ማፍረስ ይገባቸዋል… አብዛኞቹ የአፄ ምኒልክ ወታደሮች ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ እነዚያ ወታደሮች የገዛ ሀገራቸውን የተከበሩ ሴቶች ጡት ቆረጡ ማለት ፍፁም የፈጠራ ወሬና ለሰሚው ግራ ነው፡፡
‹‹እኔ ባደረኩት ምርምር ይህን ድርጊት የሚያረጋግጥ አንድም ማስረጃ አላገኘሁም። ርካሽ ጥላቻን ለመንዛት ይህን ለሕዝብ ምንም ጥቅም የሌለውን ሀውልት ያቆሙ ፖለቲከኞች፣ ይልቅስ ለሕዝባቸው የሚፈይዱ ፋብሪካዎች ቢያቆሙላቸው ከድህነት ይላቀቃሉ፡፡ ይህን የጥላቻ ሀውልት ነቅለው ፋይዳ ያላቸው ፋብሪካዎች ለሕዝባቸው እንዲተክሉላቸው በዚህ አጋጣሚ እመክራቸዋለሁ፡፡ ሌላው ስለ አፄ ምኒልክ የተነዛው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ‹5 ሚሊዮን ኦሮሞዎችን ፈጁ› የሚል ነው፡፡ ይህም ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው ጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብ 10 ሚሊዮን ቢሆን ነው፡፡ 5 ሚሊዮኑ ከተገደለ ምን ሰው ተረፈ? ደግሞስ ጀግናው የኦሮሞ ሕዝብ ዝም ብሎ አንገቱን ለእርድ የሚጋብዝ ነበር እንዴ? ቢያንስ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት አይዋጋም ነበር እንዴ? የኦሮሞ ሕዝብ የማይበገር ጦረኛና ጀግና ስለነበር ተዋግቶ ለራሱ ይመክታል፤ እንዲሁም ይገድላል እንጂ በዝምታ እንደ በግ አይታረድም ነበር፡፡ ስለዚህ “የአፄ ምኒልክ ሠራዊት 5 ሚሊዮን ኦሮሞዎችን ፈጅተዋል” የሚለው ወሬም ለርካሽ ፕሮፓጋንዳ የተተረተ ነው›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ የኦሮሞ ምሁራን ከኢትዮጵያ ፈደል ይልቅ የላቲን ፊደልን ሲመርጡ በፍፁም መሳሳታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ (ሰባዊ) ፊደላት የማንኛውም አንድ ነገድ የግል ንብረት ሳይሆኑ ኦሮሞን ጨምሮ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀብት ናቸው ይላሉ፡፡ በፊደሎቹ የሚጠቀሙ ሰዎች ራሳቸውን እንዲገልጹ፣ እርስ በእርስና ከሌሎች ጋር እንዲግባቡ ከመርዳት ውጭ ፊደሎቹ በራሳቸው፣ በማንም ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አላደረሱም ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ሚሲዮናዊ መምህር የነበሩት ፓስተር አናሲሞስ ነሲብ፤ ‹‹መጽሐፈ ቁልቁሉ›› በማለት የሰየሙትን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኦሮምኛ የተረጎሙት በግዕዝ ፊደላት ነው፡፡ እኚሁ ምሁር አስቴር ጋኖ ከተባለች የኦሮሞ ሴት ጋር በመሆን የኦሮምኛ መዝገበ ቃላት የጻፉ፣ መዝሙራትንና ምሳሌያዊ አባባሎችን የሰበሰቡ ሊቅ እንደነበሩ ጠቅሰው፣ ጠሊቁ ምሁር በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በግዕዝ ፊደላት አሳምረው ከተረጎሙ፣ እኛ ልጆቻቸው በ21ኛው ክፍለ ዘመን የግዕዝ ፊደላትን ጠልተን ላቲን ፍለጋ የሄድንበት ምክንያት ምንድን ነው? በማለት ይጠይቃሉ፡፡
በቅርቡ (ከ60 ዓመት በፊት) ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገሮች የራሳቸው ቋንቋና ፊደል ስለሌላቸው የላቲን ፊደላትን ለመዋስ ቢገደዱ አይፈረድባቸውም። እኛ (ኦሮሞ፣ አማራና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን) ግን ከ4000 ዓመታት በፊት አያት ቅድመ አያቶቻችን (እነ ኢትዮጵና ዘሮቹ) ለንግግር፣ ለጽሑፍና ለመንግሥት ሥራ ሲጠቀሙበት የነበረውን ቋንቋ ትቶ ላቲን ፍለጋ መሄድ አሳፋሪ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የዛሬዎቹ የኦሮሞ ምሁራን ቁቤን ያስጀመሩበት ምክንያት ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ (ሳባዊ) ፊደላት የአማራና የትግሬ ብቻ ስለመሰላቸው፣ በአማራ፣ በአማርኛና በግዕዝ ላይ በነበራቸው ጥላቻና ቁጣ ተገፋፍተው እንደሆነ ፕሮፌሰር  ፍቅሬ ገልጸዋል። የዛሬ 45 ዓመት አካባቢ ኃይሌ ፊዳ በወለጋ ለነበሩ ለአውሮፓ ወንጌላውያን ተመልምሎ ሲሰብክ፣ በፖለቲካ ጥላቻ ምክንያት የሀገሩን ክብር በመጥላትና በማንቋሸሽ፣ ኦሮሞዎች በላቲን ፊደላት እንዲከትቡ ፕሮፓጋንዳ ከሚያራምዱት መካከል ግንባር ቀደም እንደነበር አውስተዋል፡፡
ከላቲን ይልቅ በግዕዝ (ኢትዮጵያውያን ፊደላት) መጠቀም የበለጠ ምቹና ተስማሚ መሆኑን ፓስተር አናሲሞ ነሲብና ጊፍቲ አስቴር ጋኖ አሳይተውናል። ኦሮምኛን በኢትዮጵያ ፊደላት መጻፍ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ኦሮምኛ በግዕዝ ፊደላት ሲጻፍ ጊዜና ገንዘብን ይቆጥባል፡፡ ለምሳሌ በላቲን Adaamaa የሚለው ቃል 7 ፊደላት አሉት፡፡ በሳባ (ግዕዝ) ሲጻፍ ‹‹አዳማ›› ተብሎ በ3 ፊደላት ይጻፋል፡፡ ‹‹Uumamaa›› የሚለው ቃል በላቲን ፊደላት 7 ሆሄያት አሉት፤ በግዕዝ ‹‹ኡመማ›› ተብሎ በ3 ፊደላት ይጻፋል፡፡ Oromoo በላቲን 6 ፊደላት፣ በግዕዝ ‹‹ኦሮሞ›› ተብሎ 3 ሆሄያት፣ Ilmaan በላቲን 6፣ በግዕዝ ‹‹ኢልማን›› አራት ፊደላት ነው ያሉት፡፡ በዚህ ዓይነት አንድ መጽሐፍ በላቲን ሲጻፍ ሁለትና ከዚያም በላይ ሆኖ አሳታሚውን ላላስፈላጊ ወጪ ይዳርጋል፤ አንባቢን ደግሞ ጊዜውን ያባክናል፡፡ በገጽ ሲታሰብ በላቲን 100 ገጽ የሚፈጅ ፅሁፍ በግዕዝ  በ40 ገጽ ሊጻፍ ይችላል። በቁቤና በኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ የሠለጠኑ ወጣቶች ከክልላቸው ውጭ ሥራ ለማግኘት ሲቸገሩ ይታያሉ፡፡ ግዕዝ ሌሎች በርካታ ጥቅሞችም አሉት በማለት አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ላለፉት 4500 ዓመታት አራት ስርወ መንግሥት አስተዳድሯታል ይላሉ ፕሮፌሰር፡፡ እነሱም የመጀመሪያው ኩሻዊ ስርወ መንግስት፣ ሁለተኛው የኢትዮጵ፣ ሦስተኛው ሰለሞናዊ፣ አራተኛው የዛጉዬ ስርወ መንግስት ናቸው፡፡ አማራ እንደ ዘርና ጎሳ ብቅ ያለው የኢትዮጵ ስርወ መንግሥት ከተቋቋመ ከ400 ዓመታት ጀምሮ ስለሆነ ኩሻዊውን ስርወ መንግሥት አልደረሰበትም፡፡
ስርወ መንግሥት (Dynasty) የሚለው ቃል በመሪያም ዌብስተር መዝገበ ቃላት ትርጉም፤ በአንድ ሀገር ላይ ‹‹ሥልጣን እየተቀባበሉ የገዙ የአንድ ቤተሰብ አባላት” ማለት ነው፡፡ የሥልጣን ዘመናቸው በመቶዎች ወይም በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሊዘልቅ ይችላል። በዚህ ፍቺ መሠረት፤ ‹‹አማራው ኢትዮጵያን እንደ ስርወ-መንግሥት ገዝቷል›› ማለት ባለማወቅ ወይም በፖለቲካ መድልዎ ላይ የተመሰረተ አነጋገር ነው። በእርግጥ እንደ ግለሰብ ንጉሥ ሆነው የራሳቸውን ግዛት በሚገባ አስተዳድረዋል ይላሉ ደራሲው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር የራሳቸውንም ሆነ የሌላውን ስርወ መንግሥት ወክለው ንጉሠ-ነገሥትና ንግሥተ-ነገሥታት ሆነው ድፍን ኢትዮጵያን አልገዙም፡፡ ሌላው ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ፣ አማሮች ብቻ ሳይሆኑ ትግሬዎችና ኦሮሞዎችም በስማቸው ስርወ መንግሥት መስርተው መላ ኢትዮጵያን አላስተዳደሩም፡፡ ባለፉት 3000 ዓመታት ውስጥ የሰለሞናዊና የዛጉዌ ስርወ - መንግሥታት እንጂ የአማራ፣ የትግሬ ወይም የኦሮሞ ስርወ- መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም በማለት ማስረጃ አጣቅሰው አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይላሉ ፕሮፌሰሩ፤ በሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ውስጥ በጋብቻ ‹ሰርገው በመግባት›› ላለፉት 700 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩት የኦሮሞ ዝርያ ያላቸው ግለሰቦች ነበሩ፡፡ እነሱም ቢሆኑ በራሳቸው ስም አልነበረም፡፡ ዙፋን ሊነጥቁ ይችላሉ ተብለው “ወህኒ አምባ” ከታሰሩ የነገስታት ዘሮች አንዱን ልዑል ወይም ልዕልት አምጥቶ “አሻንጉሊት መንግስት” እነሱ የንጉሡ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ሆነው አገሪቷን ይገዛሉ፡፡ አማሮች በቋንቋቸውና በባህላቸው መስፋፋት፣ እንዲሁም ሀገራቸውን በንጉሥነት፤ በአስተዳዳሪነት፤ በአገረ-ገዥነትና በጦር አለቅነት በነበራቸው የተወሰነ ሥልጣን የተነሳ ዘውዳዊውን ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩ የመላዋ ኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥታትና ንግሥተ ነገሥታት መስለው ታይተዋል፡፡ በዚህ የተሳሳተ ግምት የተነሳ ያለ አግባብ የጥቃት ኢላማ ሆነው ሲሰቃዩ ኖረዋል፤ አሁንም እየተሰቃዩ ነው በማለት በአማሮች ላይ እየደረሰ ስላለው በደል ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ በጣም የሚወዱትና ስሙ ከአፋቸው እንዳይጠፋ የሚፈልጉት አንድ ሰው አለ፡፡ እሱም የኢትዮጵ ስርወ- መንግሥት የመጨረሻ ንጉሠ-ነገሥት የነበረውና ስመ ክህነቱ ‹‹እስያኤል›› የተባለው ልዕለ ሰብ ንጉሠ-ነገሥት፣ 480 ዓመታት በሕይወት የኖረው አፄ (እሴ) ይባል የነበረው ንጉሠ-ነገሥት ነው። እሱ የመጀመሪያው በራሄ-ጂን (ዘረ-መል) መሐንዲስ ወይም ጀኔቲክ ኢንጂነር ሲሆን አዝርዕትንና ዕፅዋትን እንዲሁም እንስሳትን እያዳቀለ አዳዲስ ዝርያዎችን በቤተ መንግሥቱ ያኖር የነበረ ፈላስፋ ነበር ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን አሁን ያለንን መልክና ቅርፅ እንዲኖረን ያደረገው አፄ ነው ይላሉ ደራሲው፡፡ ‹‹በሰው በራሄ ጅንና DNA ላይም ምርምር ያደርግ ስለነበር ኢትዮጵያውያንን ከእስያ፣ ከአረቦችና ከመካከለኛው ምሥራቅ ምርኮኞች ጋር እያጋባ ኢትዮጵያውያን ቅይጥይጥ የቆዳ ቀለም፣ የተለያየ የነገድ፣ አካላዊና ባህላዊ ቅርፀ መልክ እንዲኖረን አስችሏል›› በማለት ገልጸውታል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ ምናልባትም በዓለም የመጀመሪያ የሆነችውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከዛሬ 3300 ዓመት በፊት የፈጠረ፣ ዛሬ እስያ እያልን የምንጠራውን አኅጉር በጦር ኃይል አንበርክኮና አስገብሮ ‹‹እስያ›› ብሎ በስሙ የሰየመ፣ ንጉሠ-ነገሥታትና ንግሥተ-ነገሥታት በአንድ ጊዜ ለ10 ዓመት ብቻ እንዲገዙ በሕግ የደነገገ፣ በዚሁ ሕግ መሠረት ራሱም ለ10 ዓመት ብቻ ነግሶ ከሥልጣን የወረደ ሲሆን ብዙ ዕድሜ ስለኖረ 158 ዓመት ሲሆነው እንደገና ስመ-መንግሥቱን “አጋቦና” አሰኝቶ በመንገሥ ለ130 ዓመት መምራቱን አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ስለንግሥተ ሳባና ስለ ልጇ ቀዳማዊ ምኒልክ እውነተኛ ታሪክ ማስረጃ አስደግፈው ጽፈዋል። ንግሥተ ሳባ የኖረችበትና የገዛችበት ዘመን ሩቅ (ከ3000 ዓመት በላይ) ስለሆነ ብዙ ኢትዮጵያውን ንግሥተ ሳባ በዚህ ምድር ያልኖረች አፈ-ታሪክ ትመስላቸዋለች፡፡ ንግሥተ ሳባ በእርግጥ በምድር የኖረች ኢትዮጵያን ለ51 ዓመታት የገዛች ኢትዮጵያዊት መሆኗን ፕሮፌሰር ፍቅሬ ማስረጃ አስደግፈው አቅርበዋል፡፡
ሌላው ፕሮፌሰሩ በጥልቀት ያብራሩት እንደ ኢትዮጵያዊ መገለጫ የምንጠቀምበትን ‹‹ሀበሻ›› የሚለውን ቃል ነው፡፡ ‹‹ሀበሻ›› የሚለው ቃል መጥፎ ትርጉም ስላለው አማራን አይወክልም ይላሉ፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች ‹‹ሀበሻ›› የሚለው ከየት እንደመጣ፣ እንዴት እንደተነገረና ትርጉሙ ምን እንደ ሆነ በትክክል ስለማያውቁ፤ ድርጅታቸውን ‹‹ሀበሻ ባርና ሬስቶራንት››፣ ‹‹ሀበሻ ሆቴል››፣ ‹‹ሀበሻ ቢራ›› ‹‹የሀበሻ ልጅ››… እያሉ ይሰይማሉ፡፡ ይህ አሰያየም ትክክል እንዳልሆነ ደራሲው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሀበሻ›› የሚለውን ቃል በመጀመሪያ የተጠቀሙት ፈላሻ አይሁዶች ሲሆኑ ኣግአዚ አይሁዶችን ለመስደብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡   
“ሀበሻ” ማለት የተጀመረው ቀዳማዊ ምኒልክን አጅበው ከኢየሩሳሌምና ከጋዛ እስራኤል የመጡት 40ሺህ አይሁዳውያን ኢትዮጵያ ደርሰው ከአገሬው ሕዝብ ጋር ተቀላቅለውና ተጋብተው መኖር ከጀመሩ 400 ዓመት በኋላ ነው፡፡ በ598 ዓ.ዓ ባቢሎናውያን እስራኤልን በወረሯት ጊዜ በርካታ እስራኤላውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ አግአዚዎቹ ከኢትዮጵያውያን ጋር እየተጋቡ በባህል ኢትዮጵያውያንን መስለው መኖራቸውን አዲስ መጤዎቹ አልወደዱላቸውም። “ካልተገረዙት ጋር ተቀላቅለው አይሁድነታቸውን አርክሰዋል” በማለት ነቀፏቸው፡፡ በዚህም የተነሳ “ሀበሻ” የሚል ስም አወጡላቸው፡፡ ትርጉሙም “ድቅል፣ ንፁህ ያልሆነ፣ የተከለሰ፣ የቆሸሸ” ማለት ነው፡፡ አግአዚዎቹ ደግሞ አዲስ መጤዎቹን “ፈላሻ” በማለት ጠሯቸው፡፡ ትርጉሙም “ስደተኛ”፣ “አገር-አልባ” ማለት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በሁለቱ የአይሁድ ቡድኖች መካከል የተፈፀመ አተካሮ ነው፡፡ ከአማራ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ራሱን እንደ ‹‹ሀበሻ›› የሚቆጥር ማንኛውም አማራ ካለ፣ ታሪኩን የማያውቅ ብቻ ሳይሆን ራሱን የሚያዋርድም ነው፡፡ “የተከበረውን ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ከእስራኤል ክልሶች ጋር ማምታታት ካላስፈለገ በስተቀር የአማራ ብዙኃን ህዝብ “ሀበሻ” አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵ ልጆች ስለሆኑ ኢትዮጵያውያን ተብለው ነው መጠራት ያለባቸው” በማለት በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡    
በዚህ ዳሰሳ ያነሳኋቸው ነጥቦች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ መፅሀፉ ‹‹እንዲህ ነው ለካ›› የሚያሰኙ በርካታ የማናውቃቸው አስገራሚና አስደናቂ የኢትዮጵያን ታሪኮች በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል። ቀሪውን ከመጽሐፉ ላይ እንድታነቡ እየጋበዝኩ ዳሰሳዬን እቋጫለሁ፡፡





Read 14724 times