Saturday, 10 September 2016 14:28

ፈንጂ ላይ የቆመው ሰው አጭር የሕይወት ታሪክ

Written by  በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር
Rate this item
(8 votes)

 አልሞተም፡፡ ፈንጂ ላይ እንደቆመ ነው። የህይወት ታሪክ ከባለታሪኩ ቀብር መልስ ብቻ የሚነበብ ነውን? አይደለም፤ የሕይወት ታሪክን በባለታሪኩ ፊት ማንበብስ ነውር ነውን? በጭራሽ፤ ስለሆነም የአገራችንን ባንዲራ ከፍ አድርገን፤ መፈክር አንግበን፤ በታላቅ ሐዘንና ቁጭት ተሞልተን፣ እነሆ የዚህን ሰው አጭር የሕይወት ታሪክ እንደሚከተለው እንተርካለን፡፡
ፈንጂ ላይ የቆመውን ሰው የህይወት ታሪክ፣ ‹‹ኗሪ ሳይኖር ኖረ ኖረ ኖረና ሞተ›› በምትል አጭር ሐረግ ማሳረግ የአገርን ታሪክ ማጉደል ነው፡፡ ‹‹በእንግልት ወረዳ በባሳዝን ቀበሌ፣ በ19… ምናምን ተወለደ›› ብሎ መጀመር ደግሞ፣ የሰኮንዶች ዕድሜ በቀረው በዚህ ሰው ነብስ ሥጋ ላይ መጫወት ነው፡፡
‹‹ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ ወደ ሱቅ ተላከ!›› ብለን ከጀመርን፣ ለዓመታት ያለ ድካም ከቤት ወደ ት/ቤት፤ በተመላለሰባቸውና ተምሮ ከጨረሰ በኋላ በሥራ አጥነት እቤት በዋለባቸው ጊዜያት ላይ መዘባበት ነውና ይህንንም ትተነዋል።
ስለ ውልደቱ ለመተረክ፣ ‹‹እናት አባቱ ተጠበቡ፤ ‹ጌታ ሆይ የዛሬውን የፆታ ግብግብ ከትግል ባለፈ ለፍሬ በልልን!?› በማለት ጸለዩ!›› ብለን አንጀምርም፡፡ የህይወት ታሪኩ ልብ በሚሰብር አኳኋን ፍፃሜውን ለሚያገኝ ሰው እንዲህ ባለ መንገድ መጀመር፣ ‹‹በኢኮኖሚ እድገቷ የዓለምን ቀልብ የሳበችው ረሃብተኛዋ አገር›› ብሎ እንደ መሳለቅ ነው፡፡
ምኑን ከምን አገናኘነው ጎበዝ!? የታሪካችንን አቅጣጫ እንዲህ ባለ ቅያስ እየወሰድን እኛም ወደ ፈንጂ ወረዳው ጉዟችንን አናደርግም፡፡ ይልቅስ ፈንጂ ላይ ወደቆመው ሰው አጭር የሕይወት ታሪክ እንደሚከተለው እናልፋለን፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊው ፈንጂ ላይ የቆመው ይህ ግለሰብ…›› ይቅርታ አድማጮቻችን ፈንጂ ላይ ለቆመው ሰው ክብር ስንል ይህን አረፍተ ነገር አስተካክለን ማንበብ እንጀምራለን፣ ‹‹የእምዬ ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነው ይህ ፈንጂ ላይ የቆመው ሰው…›› አሁንም ይቅርታ እንጠይቃለን፤ በእንዲህ ዓይነቱ መዘባዘብ ከጀመርን ታሪኩ ሳይቋጭ ሕይወቱ ይቋጭብናልና በዚሁ ትተነዋል፡፡
ፈንጂ ላይ የቆመው ጭቁን፣ ፈንጂ ላይ ከመቆሙ በፊት ቅን፣ የዋህ፣ ታዛዥ፣ ሽቁጥቁጥ፣ አገልጋይ፣ ‹ይህ ጎደለ፤ ይህ አነሰ፤ እንዲህ ደረሰብኝ፤ ኧረ እንዲህ ተበደልኩኝ› የማይል ነበረ… ብለን መልካም ባህርያቱን መዘርዘር፤ ‹‹አዬ ኤ! ፈንጂ ላይ ለመቆም የዳረገው ምን ሆነና?›› ባይ አሽሟጣጮች አፍ ውስጥ መግባት ነውና በዚሁ አልፈነዋል፡፡
ጠይም ነው፤ ጠቆር ያለ፡፡ ረዥም ነው ጥቂት አጠር ያለ… የሚለውን መዘርዘር ከሰከንዶች በኋላ በቆመበት ፈንጂ፤ ብዙ ትናንሽ ነገር በሚሆነው በዚህ ሚስኪን ማሾፍ ነውና ይህንንም ዘልለነዋል።
ባይሆን እናንተ አድማጮቻችንን፤ ወደ ሕይወት ታሪኩ እያዳፋን ከመውሰዳችን በፊት የአንድ ደቂቃ የሕሊና ጸሎት ለዚህ ሚስኪን ሰው እንድታደርጉ መጠየቅ መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ፈንጂ ላይ የቆመው ሰው ቀሪ ዕድሜ፤ አንድ ደቂቃ ላይሞላ ስለሚችል ቀጥታ ወደ ህይወት ታሪኩ ንባብ እንሄዳለን፡፡
ፈንጂ ላይ የቆመው ሰው አጭር የሕይወት ታሪክ፡፡ (…ይቅርታ ባለ ካሜራ፤ እንባዬ ከመውረዱ በፊት ቶሎ ቅለብልኝ) አዎ! ፈንጂ ላይ የቆመው ሰው አጭር የህይወት ታሪክ፤
‹‹እንዳትንቀሳቀስ!›› አለው ወዳጁ ድንገት የተቀበረ ፈንጂ የረገጠውን ምስኪን፡፡
‹‹እንዳትንቀሳቀስ!››
ያልታደለው በድንጋጤ ቁልቁል ተመለከተ። በእርግጥም ይሄ ገደ ቢስ እግሩ ሄዶ፣ ሄዶ፣ ሄዶ… ፈንጂ ላይ አርፏል፡፡
‹‹አይ ዕድሌ!›› አለ ፍርሃት በሰበረው ድምፅ፡፡
‹‹እንዳትንቀሳቀስ!›› አለው አሁንም ወዳጁ በስልታዊ እንቅስቃሴ ወደ ኋላ እያፈገፈገ፡፡
‹‹እሺ!›› አለ ፈንጂ ላይ የቆመው ምስኪን፤ በፍርሃት ሁለመናው እየራደ፡፡
‹‹ትሰማለህ!?››
‹‹አቤት!››
‹‹ጥቂት እንኳን ነቅነቅ እንዳትል!›› አለው ወዳጁ ከአጠገቡ በስልት እየራቀ፡፡
‹‹እሺ!›› አለ ጭቁኑ ፈንጂ ላይ የቆመው ሰው።
‹‹እሺ!››
ከስር ፈንጂው አለ፤ ከላይ ራሱን ለማዳን እየሸሸ ያለው የወዳጁ ብርቱ ማሳሰቢያ፡፡ …ተጨነቀ። ኩልልልል አለ፤ ከጭኑ መሃል ፈሳሽ ነገር፡፡ እዚህ ላይ ጣልቃ እንግባ፤ ፈንጂ ላይ ከቆመው ሰው ጭን መሃል የወጣው ፈሳሽ ቁልቁል ወርዶ፣ የሚያመጣው ጦስ አይታወቅምና በእርግጥም እዚህ ላይ ጣልቃ መግባት ግድ ይለናል፡፡
‹‹ፈንጂ ላይ የቆመው ሰው የዘመኑን እኩሌታ በትምህርት፤ እኩሌታውን ደግሞ በሰልፍ አሳለፈ። ሰልፉ የድጋፍ አይደለም፤ ሰልፉ የተቃውሞም አይደለም፡፡ ሰልፉ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ለመፈፀም፤ የዕለት ወረትን ለመግዛት የሚደረግ የወረፋ እንጂ!›› …እንዳንል መቼ ተሰለፈ፤ የትስ ተሰለፈ የሚለው፤ ብርቱ ማብራሪያ ይፈልጋልና ‹‹ዘመኑን በወረፋ አሳለፈ›› ብለን ወደ ታሪኩ ጉዟችንን እናደርጋለን፡፡
‹‹ትሰማለህ!?››
‹‹አቤት!››
‹‹ጥቂት እንኳን ነቅነቅ እንዳትል!››
‹‹እሺ!››
‹‹እንዳትንቀሳቀስ!›› የተባለው ምስኪኑ ፈንጂ ረግጦ የቆመው ሰው፤ አረፋፍዶ ራሱን ይህን ጠየቀ፤ ‹‹ቆይ ግን እስከ መቼ!?››
‹‹እንዳትንቀሳቀስ!››
‹‹እኮ እስከ መቼ!?››
እኛም የባለታሪኩን ወገናችንን የዚህን ፈንጂ ላይ የቆመ ሰው ጥያቄ እንዲህ ስንል እንጠይቃለን። ‹‹ፈንጂ ላይ ተቁሞ እስከ መቼ!? እኮ ፈንጂ ላይ ቆሞ አለመንቀሳቀስ እስከ መቼ!?››
አድማጮቻችን ፈንጂ ላይ የቆመን ሰው የሕይወት ታሪክ መተረክ እንዲሁም መስማት፣ ፈንጂ ላይ መቆም ስለሆነ በዚሁ አልፈነዋል፡፡ ባይሆን ፈንጂ ላይ የቆመውን ሰው አጭር የህይወት ታሪክ ትተን፤ ፈንጂውን ያስቀመጠውን ሰው ረዥም የሕይወት ታሪክ ከዚህ እንደሚከተለው እንተርካለን። ‹‹ፈንጂውን ያስቀመጠው ሰው ረዥም የሕይወት ታሪክ!››

Read 2468 times