Saturday, 10 September 2016 15:23

ዚካ ቫይረስ 2.5 ቢሊዮን ሰዎችን ሊያጠቃ ይችላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 - ቫይረሱ በ70 የአለማችን አገራት ተከስቷል

     ነፍሰጡር ሴቶችን በማጥቃት የራስ ቅላቸው የተዛባ ህጻናት እንዲወለዱ የሚያደርገው ዚካ ቫይረስ ወደተለያዩ የዓለም አገራት በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝና በአለማችን በድምሩ 2.5 ቢሊዮን ሰዎችን ሊያጠቃ እንደሚችል የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
ዚካ ቫይረስ አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ አለማቀፍ የጤና ችግር ሆኗል ያለው የአለም የጤና ድርጅት፤ቫይረሱ የስርጭት አድማሱን በማስፋት ከዚህ በፊት ተከስቶባቸው በማያውቁ የአለማችን አገራት መከሰት መጀመሩን በመጠቆም ስርጭቱን ለመግታት አለማቀፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት የህክምና ባለሙያዎች ቡድን በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባደረገው ስብሰባ፣ የዚካ ቫይረስን ስርጭት መግታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከረ ሲሆን በተለይም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የአለማችን አገራት በቫይረሱ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
በዚካ ቫይረስ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ነው ከተባሉ የአለማችን አገራት መካከል ህንድ፣ ኢንዶኔዢያና ናይጀሪያ በቀዳሚነት እንደሚቀመጡም የባለሙያዎች ቡድኑ አስታውቋል፡፡ ሲንጋፖር በዚካ ቫይረስ የተጠቁባት ዜጎቿ ቁጥር 242 መድረሱን ከሰሞኑ ማስታወቋን የዘገበው ዘ ዴይሊ ሜይል ፤ማሌዢያም በሳምንቱ መጀመሪያ በቫይረሱ የተጠቃ የመጀመሪያ ዜጋዋን በተመለከተ መግለጫ መስጠቷን አስረድቷል፡፡ የዚካ ቫይረስ በግንቦት ወር 2015 በብራዚል ከተቀሰቀሰ ወዲህ ባሉት ጊዚያት በዚካ ቫይረሱ የተጠቁ የአለማችን አገራት 70 ያህል መድረሳቸውን የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Read 873 times