Saturday, 10 September 2016 15:26

የትራምፕ የእርቃን ሃውልት ለጨረታ ሊቀርብ ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  - 20 ሺህ ዶላር ያህል እንደሚያወጣ ተገምቷል
    በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካንን ወክለው በመወዳደር ላይ የሚገኙትን አነጋጋሪው ዕጩ የዶናልድ ትራምፕ እርቃን ተክለ ሰውነት የሚያሳየው ሃውልት ለጨረታ ሊቀርብ ነው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ሰውዬው አነጋጋሪ የሆነውና ዘ ኢምፐረር ሃዝ ኖ ቦልስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሃውልት፣ በመጪው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ጁሊንስ በተባለ አጫራች ኩባንያ አማካይነት በሎሳንጀለስ ለጨረታ እንደሚቀርብ የጠቆመው ዘገባው፤ሃውልቱ እስከ 20 ሺህ ዶላር ሊሸጥ እንደሚችል መገመቱን አስታውቋል፡፡
ኢንዲክላይን የተባለው የስነጥበብ ኩባንያ ንብረት የሆነውና የዶናልድ ትራምፕን ያልተሟላ ተክለ-ሰውነት በማሳየት በሰውየው ወንድነት ላይ ይሳለቃል የተባለው ሃውልት ተሸጦ ከሚገኘው ገቢ የተወሰነው ለስደተኞች መብቶች ለሚሟገት አንድ ግብረ ሰናይ ተቋም እንደሚለገስ ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የሚሳለቁ ሌሎች አምስት ሃውልቶች ከዚህ ቀደምም በአሜሪካ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰርተው ለእይታ እንደበቁ ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 3376 times