Monday, 19 September 2016 00:00

ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም (የ1966 ዓ.ም መሪ መፈክር)

Written by 
Rate this item
(21 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ የድርሰት አስተማሪ ለተማሪዎቹ፤ “አንድ ታሪክ ፃፉ፡፡ ከዚያም ያ ታሪክ የሚሰጠንን ትምህርት ወይም ግብረገብነት ታስረዳላችሁ” ሲል ይገልጻል፡፡
ተማሪዎቹ ሁሉ የመሰላቸውን ድርሰት ይፅፋሉ፡፡ ሶስት ተማሪዎች ይመርጥና ታሪኮቻቸውን እንዲያነብቡ ይጠይቃል፡፡ የመጀመሪያዋ ልጅ፤ “አባቴ አንድ እርሻ አለው፡፡ የዶሮ እርባታም አለው፡፡ ዶሮዎቹ እንቁላል ሲፈለፍሉ ወደ ገበያ ወስደን እንቁላል እንሸጣለን፡፡ ጥሩ ገንዘብ እናገኛለን፡፡ አንድ ቀን ግን ከእርሻ ወደ ገበያ ስንሄድ መኪናችን ከሌላ መኪና ጋር ተጋጨና፣ ቅርጫት ውስጥ የነበሩት እንቁላሎች በሙሉ መሬት ላይ
ወድቀው ተሰባበሩ!” አለችና ጨረሰች፡፡ አስተማሪውም፤ “ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድነው?” ሲል ጠየቀ፡፡ ልጅቷም፤ “እንቁላሎቻችንን በሙሉ አንድ ቅርጫት ውስጥ አናስቀምጥ” ስትል መለሰች።
ሁለተኛው ልጅ የሚከተለውን ታሪክ አነበበ፤ “የእኔ አባት የዶሮ እርባታ አለው፡፡ በየሳምንቱ እንቁላሎቹን ማስፈልፈያ ሳጥን (ኢንኩቤተር) ውስጥ እንከታቸዋለን፡፡ ባለፈው ሳምንት ከአሥራ ሁለቱ እንቁላሎች ስምንቱ ብቻ ጫጩት ፈለፈሉ” አለ፡፡ አስተማሪው፣ “ከዚህ ታሪክ የምናገኘው ትምህርት ምንድነው?” ሲል ጠየቀ፡፡
ልጁም፤ “እንቁላሎቻችሁ ጫጩት ከመፈልፈላቸው በፊት አትቁጠሯቸው፡፡ ጫጩቶቹን ቁጠሩ”
ሶስተኛው ልጅ፤ “አባቴ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ያውቃል፡፡ አውሮፕላን አብራሪ ነው፡፡ አውሮፕላኑ ተመታ። በጠላት ወረዳ ከመውደቁ በፊት ግን አባቴ በፓራሹት ወረደ፡፡ አንድ ጠመንጃ፣ አንድ ጎራዴና አንድ ሳጥን
ቢራ ይዞ ነበር የወረደው፡፡ መንገድ ላይ ቢራውን ጠጣው፡፡ እንደ ክፉ አጋጣሚ መቶ የሚሆኑ
የጠላት ወታደሮች መጡበት፡፡ አንድ ሰባ የሚሆኑትን በጥይት ጣላቸው። ጥይት ጨረሰ፡፡ ጎራዴውን
መዞ ሃያ የሚሆኑትን አንገታቸውን ቀላ፡፡ የጎራዴው ስለት ተሰበረ፡፡ በባዶ እጁ የቀሩትን ጣላቸው”
ሲል ጨረሰ፡፡
አስተማሪው፤
“ከዚህ የምናገኘው ትምህርት (ግብረገብነት) ምንድነው?” አለው፡፡
ተማሪውም፤
“አባቴ ከጠጣ በኋላ አይቻልም! ያኔ ከሱ ጋር መቀለድ አደገኛ ነው” አለ፡፡
*          *        *
ከየአንዳንዱ የህይወት እንቅስቃሴ የምናገኘው ትምህርት መኖር አለበት፡፡ ዕንቁላሎቻችንን ሁሉ፤ በአንድ ቅርጫት ውስጥ አለማስቀመጥ አደጋ በመጣብን ጊዜ ሁሉንም በአንዴ እንዳናጣ ይበጀናልና ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ አንድም ደግሞ ገበያችን ላይ ብቻ በማተኮር ለግጭት መዳረግ የለብንም፡፡ በዕንቁላሎቻችን ቁጥር ልክ ሁሉ ጫጩት እናገኛለን ብለን መገመትም የዋህነት ነው፡፡ የተቀፈቀፈው ሁሉ አይወለድም!! የታሰበው ሁሉ ፍሬ ላያፈራ ይችላል። የኢንኩቤተር ሙቀት ስላለ ብቻ ሁሉም ጫጩቶች እንደፈለግናቸው አይፈለፈሉም፡፡ ግምቶቻችንም መሰረት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል ማለት ነው፡፡ ባለፉት ወራት እስከ አዲሱ ዓመት ድረስ ተከስተው የነበሩ የእንቅስቃሴ ሁኔታዎች አንዳንድ ትምህርትና ግብረ ገብነትን አስጨብጠውን ማለፍ አለባቸው! የህዝብ ብሶት ምሬትና ያልተመለሰ ጥያቄ ከጠባብ ንፍቀ ክበብኝነት ተነስቶ አገሩን ሊያዳርስ እንደሚችል ያመላክታል፡፡ መንግሥት ውጪያዊ ሰበብ መፈለጉን (externalization) እና በሌሎች ማላከኩን (Blame-shifting) ትቶ ራሱን ወደ ውስጥ እያየ መፈተሽ እንዳለበት መገንዘብ እንደሚገባው አይተናል፡፡ ግምገማዎቹን የለበጣ እንዳያደርጋቸው ታላቅ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን አስተውለናል፡፡
አመራሮች ራሳቸውን ባልለወጡ ጊዜ ባለስልጣናትን ካንድ ወንበር ሌላ ወንበር ማሸጋገር ቢሮክራሲያዊ ሽርሽር ብቻ ነው! ጥፋትን እንደማንሸራሸር ነው! “የኔ ክልል ካንተ ክልል ይሻላል” ማለትም የእኩልነትን መርህ የጣሰ አመለካከት እንደሆነ ልብ ብለናል፡፡ ህዝብ ባለቤቱ የሆነን ጉዳይ፣ “ባለቤት የሌለው እንቅስቃሴ ነው” ማለት እንቅስቃሴውን እንዳላቆመውም አስተውለናል! የመንግስትን ስልጣን ለግል ጥቅም ማዋል፣ የአዘቦት ቀን ወግ ሆኖ ሳለ፤ ለእንቅስቃሴም ወሳኝ ጨዋታ ነው ብለን ማሰብም የዋህነት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ለህዝብ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠት አንድም ዳተኝነት ሳይሆን ተዓብዮ (arrogance)፤ አንድም ደግሞ ጠባብ አመለካከት ከመያዝ (Narrow Nationalism) የሚመነጭ፣ “ሁለት ጥፉ ካገር ጥፉ”፤ ሂደት ነበር፡፡ የክልል
ጠባብነት፣ አንድ ልዩ አደጋ እንደሆነ አንርሳ!
(Provincialism እንዲሉ)፡፡ ከሁሉም በላይ በቅራኔ ውስጥ መሸብለቃችንን አንርሳ። ባንድ ወገን “የህዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው - አፋጣኝ መልስ ይሻል” እያልን፤ በሌላ ወገን “ህገ መንግስታዊ መብት ተጥሶ ሁከትና ብጥብጥ አያስፈልግም” ብለናል፡፡ ለምን? እንዴት? እንበል ጎበዝ! ዕውነተኛ ግምገማ መሰረቱ በህዝብ ማመን ነው! ጥልቅ ተሐድሶ መሰረታዊ ለውጥ የማምጣቱ ጉዳይ ካልሆነ ከንቱ ድካም ይሆናል!
የኢትዮጵያ መልክ እንዲለወጥ የአመራሮች አስተሳሰብ በግድ መለወጥ አለበት! ለውጥ ድንገቴ ሳይሆን ሂደት ነው! ገጠመኝም አይደለም!
እንግዲህ ለውጥ እንፈልጋለን ካልን፣ ኢትዮጵያ የ1966 ዓመተ ምህረትን ዓይነት፤ “ጉልቻ ቢለዋወጥ
ወጥ አያጣፍጥም” መሪ መፈክር አይሰራም ብላ ማመን ግዷ ነው!! ያየናቸው ጉልቻዎች በቂ
ናቸውና፡፡ ጎበዝ! ከስህተት እንማር! የተሻለ ስህተት እንሥራ - አሁንም አልረፈደም - ጉዟችን ገና
ነው - ምርጥ ስህተት እንስራ!!

Read 9929 times