Sunday, 18 September 2016 00:00

የደቡብ ሱዳን መሪዎች ከጦርነቱ የብዙ ሚሊዮን ዶላር ሃብት አካብተዋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ደቡብ ሱዳን ለአመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ፣ በርካታ ዜጎቿ ሲሞቱና ለስደት ሲዳረጉ፣የአገሪቱ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኬር እና ተቀናቃኛቸው ሬክ ማቻር ግን፣በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የህዝብ ሃብት ወደ ግል ካዝናቸው በማስገባት ቅሌት ተጠምደው እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው ዘ ሴንትሪ የተባለ ተቋም በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው የምርመራ ሪፖርት፣ ደቡብ ሱዳን በሁለቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች የእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ በቆየቺባቸው አመታት፣ ሳልቫ ኬርና ማቻር የህዝቡን ሃብት ሲዘርፉና በጎረቤት አገራት ባቋቋሟቸው የሪልእስቴትና ሌሎች ኩባንያዎች ጠቀም ያለ ትርፍ ሲያካብቱ ነበር ብሏል፡፡
“ዎር ክራይምስ ሹድንት ፔይ” የሚል ርዕስ ያለውና ለሁለት አመታት የዘለቀውን የተቋሙን ምርመራ መሰረት አድርጎ የተጠናከረው ሪፖርት እንደሚለው፤ሁለቱ የአገሪቱ ቀንደኛ የፖለቲካ መሪዎች በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎችን ለሞት በዳረገው አስከፊ ጦርነት እጅግ ከፍተኛ የህዝብ ገንዘብ ወደ ግል ካዝናቸው አስገብተዋል፡፡ ሳልቫኬር ህጋዊ አመታዊ ደመወዛቸው 60 ሺህ ዶላር ቢሆንም፣ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያገኙና በአገራቸውም ሆነ በውጭ አገራት በድብቅ ታላላቅ ኩባንያዎችን እንደሚያንቀሳቅሱ ተደርሶባቸዋል። ቤተሰቦቻቸውም በአገሪቱ የነዳጅ፣ የማዕድንና የሌሎች ዘርፍ ንግድ ጠቀም ያለ ድርሻ አላቸው ብሏል- ሪፖርቱ፡፡
የቀድሞው የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሬክ ማቻርና ቤተሰቦቻቸውም አገሪቱ በጦርነት ስትታመስ፣የግል ሃብት በማካበት ተጠምደው ነበር የኖሩት፣ህዝቡ መከራውን ሲያይ እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ግን በናይሮቢ ባስገነቡት እጅግ ዘመናዊ ቤት ውስጥ የቅንጦት ኑሮን ሲመሩ ነበር ብሏል- ሪፖርቱ፡፡ 1.2 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን በጦርነቱ ሳቢያ አገራቸውን ጥለው ሲሰደዱ፣ ሳልቫ ኬር እና ማቻር የግል ሃብት በማካበት ቅሌት ተጠምደው እንደነበር በተጨባጭ ማስረጃዎች አረጋግጫለሁ ብሏል ተቋሙ፡፡
በሺህዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን ህጻናት የሚልሱ የሚቀምሱት አጥተው በርሃብ ሲቆራመዱ፣አራቱ የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ልጆች በናይሮቢ በሚገኝ እጅግ ውድ ትምህርት ቤት ውስጥ 10 ሺህ ዶላር እየተከፈለላቸው ተንደላቀው ይማራሉ ተብሏል፡፡ የደቡብ ሱዳን መንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ሪፖርቱን ረብ የለሽ ሲሉ ያጣጣሉ ሲሆን መንግስታቸው፣ ሪፖርቱን በአዘጋጀው ተቋም ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡

Read 1476 times