Monday, 19 September 2016 07:37

የግል ት/ቤት መምህራን በስልጠናው አልተካፈሉም

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(19 votes)

የስልጠናው ዋነኛ አጀንዳ ፌደራሊዝም ነው

      በአገር አቀፍ ደረጃ ከመስከረም 4 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር ቀናት ለመምህራን ሊሰጥ የታሰበው ስልጠና ውዝግብ አስነሳ፡፡ የግል ት/ቤት መምህራን ስልጠናው ከሙያቸው ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ከመሆኑም በላይ ለመንግስት ት/ቤቶች መምህራን የሚሰጠው የአበል ክፍያ የማይታሰብላቸው በመሆኑ ስልጠናውን አንካፈልም በማለት ጥለው ወጥተዋል ተብሏል፡፡
ሰሞኑን ተዘዋውረን ባየናቸው የግል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ መምህራኑ ስልጠናውን ለመካፈል የማይፈልጉ መሆናቸውን በመግለፅ አቋርጠው ወጥተዋል፡፡ በባሸዋም አንደኛ ደረጃና የፕሪፓራቶሪ ት/ቤት ውስጥ ስልጠናውን ለመካፈል ተሰባስበው የነበሩ የአምስት የግል ት/ቤቶች መምህራን፤ ስልጠናውን ለመካፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ተበትነዋል፡፡ ለመምህራኑ ስልጠናውን ለመስጠት በሥፍው ለተገኙት የመንግስት ተጠሪ፤ ስልጠናውን የሚካፈሉት ለመንግስት መምህራን የተሰጠው የአበል ክፍያ ለእነሱም ሲታሰብ መሆኑን በመግለፅ ስልጠናውን አንሣተፍም ብለዋል፡፡
የመንግስት ተጠሪዋ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመግለፅ፤ የግል ት/ቤቶች መምህራን የአበል ክፍያውን ከየትምህርት ቤቶቻቸው ያገኛሉ ተብሎ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “ስልጠናው ባይኖርም ሥራ ላይ መሆናችሁ አይቀርም ነበር፡፡ ስለዚህም አበል ሊከፈላችሁ አይገባም” መባላቸውን የሚናገሩት መምህራኑ፤ ከሥራችን ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ስልጠና ለመውሰድ አዳራሽ ውስጥ ቁጭ ብለን ከምንውል መደበኛ ሥራችንን ብንጀምር ይሻለናል፡፡ ይህ ስልጠና ከመደበኛ ስራችን ውጪ በመሆኑ ተገቢውን የአበል ክፍያ ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡ በአንድ ህግና መንግስት በምትተዳደር አገር ላይ ሆነን አንድ አይነት ስልጠና ለመውሰድ እየተጠራን የግል ት/ቤት መምህራን በመሆናችሁ ስልጠናውን የምንሰጣችሁ ያለ አበል ክፍያ ነው መባሉ ህጋዊ ተግባር አይደለም” ሲሉም ተችተዋል፡፡
በስልጠናው ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀው ከስልጠናው አዳራሽ ከወጡት መምህራን መካከል ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ መምህር፤ “የስልጠናው ዋንኛ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው የፌደራሊዝም ጉዳይ ከመምህርነት ሙያ ጋር ፈፅሞ የማይገናኝና ለመምህራኑ አቅም ግንባታም ሆነ ክህሎት ማሣደጊያ አንዳችም ፋይዳ የሌለው ፖለቲካ ነው፡፡ ለአመታት በመምህራኑ ውስጥ ሲነሳ የቆየውን የፈቃድ አሰጣጥ ጉዳይ አጀንዳ አድርገው ያቀረቡትም ይህንኑ ፓለቲካዊ ይዘት ያለውን የፌደራሊዝም ጉዳይ ለመሸፈን እንዲረዳ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናውን ለመካፈል ከመንግስት ት/ቤት የሄዱ መምህራን በቀን ለአበል 150 ብር ለሻይ ቡና ደግሞ 20 ብር፣ በድምሩ 170 ብር እየተከፈላቸው ስልጠናውን በመውሰድ ላይ ሲሆኑ በከተማዋ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የግል ት/ቤት መምህራን ስልጠናውን ለመካፈል ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ተበትነዋል፡፡ መምህራኑ ይህንኑ ጥያቄአቸውን በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውንና በትናንትናው ዕለትም ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረቡ መምህራን ስልጠናውን ባለመካፈል ውሳኔያቸው የፀኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ት/ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች፤ የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት  ለጥያቄያችን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

Read 4871 times