Monday, 19 September 2016 07:40

የኮንሶ ቀውስ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(95 votes)

“ጥያቄያችን በኦሮሚያ ክልል እስከመጠቃለል ይዘልቃል” አቶ ገመቹ ገንፌ፤ - የኮንሶ ኮሚቴ አባል
“ጥያቄው የህዝብ ሳይሆን የጥቂቶች ነው” - የክልሉ መንግስት

    ከኮንሶ የዞንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ግጭት የበርካቶች ህይወት ጠፍቶና በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶች ተቃጥለው ዜጎች የተፈናቀሉሲሆን የኮንሶ ህዝብ ኮሚቴ፤ ጥያቄያችን ወደ ኦሮሚያ ክልል እስከመጠቃለል ይዘልቃል ብለዋል፡፡
በአካባቢው እስከ ትናንት ድረስ ግጭቶች መቀጠላቸውንና የታጠቁ የመንግስት ኃይሎች የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ እንደነበር የኮንሶ ኮሚቴ አባል አቶ ገመቹ ገንፌ ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን በሰሞኑ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና አስክሬናቸው እስከ ትናንት ድረስ ለቤተሰብ እንዳልተሰጠ ተገናግረዋል።
የደቡብ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ አይረዲን በበኩላቸው፤ ግጭቱን ያስነሱትና በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉት የኮሚቴው አባላት ናቸው ይላሉ፡፡
“የፀጥታ ኃይሉ ጥፋቱ ከደረሰ በኋላ ነው ህዝቡን ለመታደግ ወደ አካባቢው የገባው፤ በአሁን ወቅት ግን በኮንሶ ምንም ግጭት የለም፤ ሰላማዊ ነው”፤ ብለዋል ኃላፊዋ፡፡
የኮሚቴው አባል አቶ ገመቹ፤ ጥያቄያችን በፌደሬሽን ምክር ቤት ተቀባይነት ካላገኘ በሪፈረንደም ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመጠቃለል ጥያቄ እናቀርባለን ያሉ ሲሆን ወ/ሮ ሂክማን በበኩላቸው የዞንነት ጥያቄው ተቀባይነት እንደሌለው ምላሽ ተሰጥቶቷል፤ ከህዝቡ ጋር በተደረጉ ውይይቶች አሁን ባለው የወረዳ አወቃቀር ለመቀጠል ህዝቡ ፍላጎት እንዳለው ታውቋል ብለዋል፡፡
የፌደሬሽን ም/ቤት፤ የቀረበው ጥያቄ የአስተዳደር ጉዳይ ስለሆነ ሊመለከተው እንደማይችል ጠቁሞ፤ ም/ቤቱ የሚመለከተው የማንነት ጥያቄን እንደሆነ አመልክቷል፡፡ የኮንሶ ጥያቄ የማንነት አለመሆኑን በመግለፅ፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል መንግስትና የኮንሶ ኮሚቴ አባላት በበርካታ ጉዳዮች ላይ እየተወዛገቡ ይገኛሉ፡፡ አዲስ አድማስ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ያደረገችውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በገፅ 7 ላይ ያገኙታል፡፡


Read 25894 times