Monday, 19 September 2016 07:43

ኢንጂነር ግዛቸው፤ ኳሱ ያለው በኢህአዴግ እጅ ነው ይላሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

• ኢህአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲ፣በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት አጥቷል
• ለህዝብ ጥያቄ ምላሹ እስራትና ግድያ ከሆነ፣ ችግሩን የበለጠ ያወሳስበዋል
• ተቃዋሚዎችና ምሁራን በገዢው ፓርቲ ፍራቻና ተጽዕኖ ሥር ናቸው
• ኢህአዴግም በያዘው መንገድ ችግሩን ይፈታል የሚልም እምነት የለኝም

በ97 ምርጫ ማግስት የፖለቲካ ቀውሱን ተከትሎ ታስረው ከተፈቱ በኋላ “አንድነት” ፓርቲን በመመስረትና በፕሬዚዳንትነት በመምራት የሚታወቁት አንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፤ላለፉት ሁለት ዓመታት ራሳቸውን ከየትኛውም የፓርቲም ሆነ የፖለቲካ  እንቅስቃሴ አግልለው ቆይተዋል፡፡ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን ለመስጠት ግን ፈቃደኛ ሆነው፣ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

   በኦሮሚያና በአማራ ክልል ለወራት የዘለቁት የህዝብ ተቃውሞዎች መንስኤ ምንድን ነው ይላሉ?
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ባለፈው አመት የታየው ተቃውሞ በኢትዮጵያ የወደፊት የማደግ፣ የመልማትና የህልውና ሁኔታ ላይ ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ዋናው መንስኤ ባለፉት 25 ዓመታት የዲሞክራሲ፣ የፍትህና የነፃነት እጦት ስለነበረ ነው፡፡ የዲሞክራሲ እጦት ነው የምልበት አንደኛው ማሳያ፣ ኢህአዴግ ያፀደቀውን ህገ መንግስት እንኳ እያከበረ አለመሆኑ ነው፡፡ ከየትኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን በላቀ ሁኔታ ህገ መንግስቱን የተፃረረው ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ ጥቀስ ከተባልኩ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፓርቲዎች እንዲደራጁ ህገ መንግስቱ ይፈቅዳል፤ኢህአዴግ ግን በተግባር ፖለቲካውን የሚያንቀሳቅስ ፓርቲ እንዳይኖር የተለያዩ የአፈና መንገዶችን ሲጠቀም ቆይቷል። በመጀመሪያ አካባቢ በርካታ ፓርቲዎች ነበሩ፤ አሁን የሉም ማለት በሚቻልበት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ያሉትም ከቢሮ ስራና ከመግለጫ ባሻገር እንቅስቃሴ የላቸውም፡፡ ለነዚህ ፓርቲዎች መቀጨጭ አንዱ መንስኤ በእርግጠኝነት የኢህአዴግ አፈና ነው፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ በጥሩ ቋንቋ ያስቀመጠውና የፈቀደው የመደራጀት መብት በኢህአዴግ መንግስት አልተተገበረም፡፡ ሌላው የሚዲያ ሁኔታ ነው፤ ከ97 ምርጫ በፊት በርካታ ነፃ ሚዲያዎች ነበሩ፡፡ አሁን ያሉት ከ5 የሚበልጡ አይደሉም። ብዙ ጋዜጠኞች ተሰደዋል፤ ቀሪዎቹም እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡ ስለዚህ የቀሩት ጋዜጠኞች በፍርሃት ራሳቸውን ቆልፈው፣ ራሳቸውን በራሳቸው እየገደቡ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የኢህአዴግ ልሳን እስከመሆን ደርሰዋል። የኢትዮጵያን ህዝብ ድምፅ የሚያንፀባርቁ አልሆኑም። የብዙሃኑን ድምፅ አያስተጋቡም፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ህዝብ የታፈነ ብሶቱን አደባባይ ወጥቶ ቢተነፍስ የሚደንቅ አይሆንም፡፡
ሌላው በሦስተኛ ደረጃ የፍትህ ስርአቱ ድክመት ነው፡፡ ብዙ ፖለቲከኞችና የህዝብ አፍ የሆኑ ጋዜጠኞች ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡ እነ አንዷለም አራጌ፣ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ በቀለ ገርባ፣ እነ ኦላና----እስር ቤት ነው ያሉት፡፡ ይሄን ሁኔታ አብዛኛው ሰው ያውቃል፡፡ ህገ መንግስቱ የሰጣቸውን መብት ሲጠቀሙ ነው አሸባሪ ተብለው እስር ቤት የገቡት፡፡ ሌላው የሲቪል ተቋማትና የሙያ ማህበራት፣ እንደምናውቀው ያለ ኢህአዴግ ቡራኬ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ለዲሞክራሲ ወሳኝ የነበሩት የሲቪክ ተቋማት፣ አሁን በጣም ቀጭጨው ነው ያሉት፡፡ ሌላው የምርጫ አስተዳደሩ ነው። ምርጫው ሙሉ በሙሉ በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ነው ያለው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት የተካሄዱት 5ቱም ምርጫዎች ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ነፃ አልነበሩም፡፡ ትንሽ የተለየ ነገር የታየው በ1997 ምርጫ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ተዘግቷል። ኢህአዴግ መጀመሪያ በ99.6 በመቶ፣ ከዚያ መቶ በመቶ በሆነ ድምጽ አሸነፍኩ አለ፡፡ በምንም መመዘኛ በየትኛውም አለም ታይቶ የማይታወቅ ውጤት ነው የተመዘገበው፡፡ ብዝሃነት ያላት ሀገር ብትሆንም፣ የብዙሃኑ ድምፅ የሚስተጋባበት እድል አልተፈጠረም፤ በምርጫ ስርአቱ፡፡ በፓርላማው አንድ አይነት ቋንቋ ነው የሚነገረው፡፡ ህዝቡ ትክክለኛ ውክልና ኖሮት፣ ድምጹ እየተሰማ አይደለም፡፡ በጣም ዲሞክራሲያዊ የሆኑት የአውሮፓ ሀገሮች እንኳ 50 በመቶ ውጤት ማምጣት እየተሳናቸው፣ የጥምር መንግስት ነው እያቋቋሙ ያሉት፡፡ የህዝብ እምቢተኝነት የመጣው በእነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡ መስከረም 30 አዲስ መንግስት በምርጫ ተመርጧል ተብሎ ተመስርቶ፣ተቃውሞው በሁለተኛ ወሩ በህዳር ነው በኦሮሚያ የጀመረው፡፡ እንዴት በ100 ፐርሰንት የተመረጠ መንግስት፣በዚህ ቅጽበት ተቃውሞ ሊገጥመው ቻለ? ይሄ መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ በሁለቱም ክልሎች የታዩት ተቃውሞዎች የተቀባይነት ማጣት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ድርጅቶቹ እንዴት የህዝብ ተቀባይነት ማግኘት ተሳናቸው? በሁለቱ ክልሎች ህዝብ ኦህዴድና ብአዴንን አልተቀበላቸውም ማለት ነው፡፡ ይሄ የረጅም ጊዜ ብሶቶች ድምር ውጤት ነው፡፡
የህዝብ ተቀባይነት ማጣት እንዴት ተከሰተ?
ሁለቱ ድርጅቶች ኢህአዴግን ወክለው በአማራና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ናቸው፤ይሁንና ህዝቡን በሚፈልገው መጠን አላረኩትም፡፡ እምነት አልጣለባቸውም፡፡ እነኚህ ድርጅቶች ህዝቡን በነፃነት ማስተዳደር አልቻሉም፡፡ የፌደራል ስርአቱ የሚለው፣ህዝቡ በራሱ ተወካዮች ይተዳደራል ነው። አሁን ጥያቄው፤እነዚህ ድርጅቶች ህዝቡን በአግባቡ ወክለውታል ወይ? የሚለው ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የማዕከላዊ መንግስት ተፅዕኖ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይና የማንነት ጥያቄም አለ፡፡ የብአዴን አመራሮች፣ ፍላጎታችንን ማሟላት አልቻሉም ነው የሚለው ህዝቡ፡፡ ኦህዴድም የኦሮሚያን ህዝብ ሁለንተናዊ ፍላጎት እያሟላ አይደለም የሚል ነው መሰረታዊ ጥያቄው፡፡
ሁለቱ ድርጅቶች የህዝባቸውን ፍላጎት ማሟላት ያልቻሉበትን ምክንያት ዘርዘር አድርገው ሊነግሩን ይችላሉ?
ራሱ ኢህአዴግ እኮ የተወሰኑ ሰዎችና የህውሓት የበላይነት የሚታይበት ድርጅት ነው፡፡ ይሄ ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ የኦሮሚያንና የአማራን ህዝብ የሚወክሉት ፓርቲዎች ከዚህ በመነሳት የሚወክሉትን ህዝብ በእኩል ቁመና በአግባቡ ሊወክሉት አልቻሉም፡፡ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተገቢውን ተጠቃሚነት እያገኙ አለመሆኑን ራሳቸው ይናገራሉ። ኢህአዴግ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ስለሌለ፣ የበላይነት ያለው አካል አድራጊ ፈጣሪ ነው የሚሆነው። እነሱ ራሳቸው በቅርቡ ጥሩ አመራር ያገኘ ክልል ጥሩ ይለማል፤ ጥሩ ያላገኘ ይጎዳል ብለዋል፡፡ ይሄ መሸፋፈን ነው፡፡ እነዚህ ክልሎች ራሳቸውን በፈለጉት መንገድ ማስተዳደር ይችላሉ ወይ ሲባል እንደማይችሉ እያየን ነው፤ ህዝቡም ፊት ለፊት እየነገራቸው ነው፡፡ “የህውሓት የበላይነት ይቁም” የሚል ጥያቄ ታዲያ ከየት የመጣ ነው? ምክንያቱ ይሄው ነው፡፡ የበላይነት ያለው አካል፣ በክልሉ ቀርቶ ከክልሉ ውጪም ሁሉን ነገር ለመጠቅለል ፍላጎት ይኖረዋል፡፡
የህዝባዊ ተቃውሞውን ባህሪ እንዴት ገመገሙት?
የህዝቡ እምቢተኝነት አሁን ጎልቶ የወጣው በኦሮሚያና በአማራ አካባቢ ቢሆንም በሌላው አካባቢም ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ መጀመሪያ ኦሮሚያ ነበር፤ ወደ አማራ ሄደ፤ አዲስ አበባም ተሞክሮ ነበር። ይሄ ነገር ሁሉም ጋ የመነሳት አዝማሚያ ያለው ይመስላል፡፡ በደቡብ ኮንሶ አካባቢ ጥያቄዎች አሉ። በአዲስ አበባ አብዛኛው ህዝብ ዘንድ፣መንግስት በሚገባ ሀገር እያስተዳደረ አይደለም የሚል አመለካከት አለ፡፡ ይሄን በዳሰሳ ጥናት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ጎልቶ የመታየትና ያለመታየት ጉዳይ ነው እንጂ እንደኔ ችግሩ አገር አቀፍ ነው፡፡ እንደ ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት አጥቷል፡፡
ህዝባዊ ተቃውሞው የሚቀጥል ከሆነ፣ መጨረሻው ምን የሚሆን ይመስልዎታል?
እሱ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ይሄ ይሆናል የሚል ሃሳብ እንደ ማቅረብ እንዳይሆንብኝ እንጂ ችግሩ በጊዜ መፍትሄ ካላገኘ (አያድርገውና) ሀገሪቱ ወደ ግጭት ልትገባ ትችላለች የሚል ፍራቻ አለኝ፡፡ ምክንያቱም የዲሞክራሲ፣ የፍትህ እጦት፣ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ የስራ አጥነትና የብሄረሰብ ግጭት የመሳሰሉት አስጊ ናቸው፡፡ የሀገሪቱን አጠቃላይ የመንግስት አስተዳደር የሚጎዳና የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ በሚገባ ካልተስተናገደ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ነች ብዬ እገምታለሁ፡፡
መንግስት ለችግሩ መፍትሄ አበጃለሁ እያለ ነው። መንግስት ችግሩን የተረዳበትና የመፍትሄ አሰጣጡን እንዴት ያዩታል?
መንግስት በመሰረቱ ችግሩን አውቆታል፤ የመፍትሄው አቅጣጫ ግን ወቅታዊና ችግሩን ያገናዘበ አይደለም፡፡ መግለጫ አውጥቷል፣ አንጋፋዎቹ አመራሮችም በሚዲያ ተናግረዋል፡፡ ሰዎቹ ችግሩን ያውቁታል፤ ግን አካሄዳቸው ለችግሩ መፍትሄ በሚሰጥ አግባብ አይደለም፡፡ ችግሩን እያወቁ በቀጥታ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ሌላ ከችግሩ ጋር የማይገናኝ መፍትሄ ማስቀመጥ፣ የበለጠ ነገር ማወሳሰብና ማባባስ ነው፡፡ መንግስት ችግሩን በተረዳበት መንገድ ትክክለኛ መፍትሄ መስጠት አለበት፡፡ የጉልበት መፍትሄ ዘላቂ አይሆንም፡፡ በኃይል በመሳሪያ፣ በደህንነት የሚሰጥ ምላሽ የህዝብን ጥያቄ አያቆምም፡፡ በመሳሪያ የሚሰጠው ምላሽ ችግሩን ይበልጥ ያባባሰው ይመስለኛል። ለህዝብ ጥያቄ ምላሹ እስራትና ግድያ ከሆነ መፍትሄው ይወሳሰባል፡፡ አሁን የተገደሉት 1ሺ ነው ይባላል፡፡ ጉዳዩ የቁጥር ጉዳይ አይደለም። አንድም ሰው መሞት የለበትም፡፡ ህዝቡ ባዶ እጁን ሰላማዊ ሰልፍ እስከወጣ ድረስ ሰላማዊ መስተንግዶ ማግኘት ህገ መንግስታዊ መብቱ ነው፡፡ ባለፈው ዚምባቡዌ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር፤ አንድም ሰው አልሞተም፡፡ በኛ ሀገር ሰላማዊ ሰልፍ ለምንድነው አሳሳቢ የሆነው? ለምንድን ነው አስፈሪ የሚሆነው? የሚሰጡትም ምክንያቶች አንዳንዴ አሳፋሪ ናቸው። ራሳቸው ሰልፈኞቹ ታጥቀዋል ይባላል። ግን በሁለቱም አካባቢዎች፣ ኦሮሚያና ባህርዳር ላይ ያ ሁሉ ሰው ሲሞት የታጠቀ ሰልፈኛ አልነበረም፡፡ ፍቃድ ያልተሰጠው ሰልፍ የሚባል ነገር ደግሞ አለ። ይሄ ህገ መንግስቱን በግልፅ መፃረር ነው፡፡ ፍቃድ አያስፈልግም፤ ማሳወቅ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ራሱ ችግሩን በደንብ እያወቀው፣ የሚያስቀምጠው መፍትሄ ግን መስመሩን የሳተ ነው፡፡
አንጋፋ የቀድሞ የኢህአዴግ ታጋዮች (የጦር ጀነራሎች) ሀገሪቱን ከውድቀት ለመታደግ በሚል የመፍትሄ ሃሳቦች እያቀረቡ ነው፡፡ በመፍትሄ ሃሳቦቹ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ችግሩ አሳስቧቸው የመፍትሄ ሃሳብ ሲያቀርቡ እያየን ነው፡፡ እነሱም ኢህአዴግ አምባገነን ሆኗል፤ አደጋ ከመምጣቱ በፊት የምርጫ ምህዳሩን አስፍቶ ሁሉም በምርጫው ተሣታፊ መሆን አለበት ብለዋል። መልካም ነገር ነው፤ ቢያንስ ግማሽ መንገድ ሄደዋል፡፡ እነሱ የሚሉት ጠቅለል ተብሎ ሲታይ፣ ኢህአዴግ እንዳለ ሆኖ ጥገናዊ ለውጥ ያድርግ ነው። ግን ህዝቡ በኢህአዴግ ላይ ምን ያህል እምነት አለው? የሚለውን አልተገነዘቡም፡፡ ለዚህ ነው ግማሽ መንገድ ሄደዋል ያልኩት፡፡
ኢህአዴግ በተሃድሶ ከተጋረጡበት ችግሮች የመውጣት ልምድ አለው፤አሁንም ስር ነቀል ተሃድሶ አድርጎ ችግሮችን እንደሚፈታ እየተነገረ ነው፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
እርግጥ ነው በ1993 ተሃድሶ አካሂደዋል፡፡ በወቅቱ የተካሄደው ተሃድሶ ምክንያቱ፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የፈጠረውን ልዩነት ያስታከከ ነው እንጅ የህዝብ ቁጣ አልነበረም፤ የስልጣን ሽኩቻ ተሃድሶ ነው ያደረጉት። አሁን ደግሞ ህዝብ እምቢ ሲል ተሃድሶ እናደርጋለን ማለታቸው የእሣት ማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ ችግራቸውን  በሚገባ አልፈተሹም፡፡ የአመራር ችግር እንዳለባቸው ለመገንዘብ 15 አመት ሙሉ ምን አስጠበቃቸው? ተሃድሶ እኮ ችግር ሲመጣ ብቻ አይደለም፤በእቅድ በየጊዜው መደረግ አለበት፡፡  
አንዳንድ ወገኖች ከእንግዲህ ይህ መንግስት አብቅቶለታል ይላሉ፡፡ አሁን የተቀሰቀሰው ተቃውሞ መንግስት እስከመቀየር የሚያደርስ ይመስልዎታል?
በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እርግጥ ይሄ መንግስት አበቃለት የሚሉ የተለያዩ ወገኖች አሉ፡፡ ግን ይሄ ሁኔታ ከስሜታዊነት የመጣ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የመንግስት መዋቅር ደካማ ቢሆንም የመኖር ጉልበት አለው፡፡ ጉልበቱ እስኪያልቅ ሊኖር ይችላል፡፡ አሁን አበቃለት፣ አለቀለት ማለት አያስችልም፡፡ መንግስት ችግሩን ተረድቶ ትክክለኛ መፍትሄ ካልሠጠ ግን ሁኔታዎቹ ወደዚያ ነው የሚያመሩት፡፡
በእንዲህ ያለ የቀውስ ወቅት ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ምሁራን ሚናቸው ምን መሆን አለበት?
ይሄን በእውነት በአሳዛኝ መልኩ ነው የማየው። በአጠቃላይ ምሁራኑ ራሳቸውን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አግልለው ነው ያሉት፡፡ ምሁራን ለሃገር እድገትና ለውጥ መሰረት ናቸው፡፡ ይሄ ግን ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሆኗል። ከአገሪቱ አሳሳቢ ችግር ራሱን አግልሎ ነው ያለው ምሁሩ። ይህም የሆነበት ምክንያት የዲሞክራሲ እጦት ነው፡፡ የመናገር ነፃነቱን፣ የመደራጀት ነፃነቱን ለመተግበር ምሁሩ ከፍተኛ ፍራቻ አለበት፡፡ ኢህአዴግ አካባቢ ምሁራንን የማሳተፍ ችግር አለ፡፡ ይሄ ነገር ግን ከሃላፊነት ራስን ማሸሽ ነው፡፡ መማር ማለት ትክክለኛ የሆነውንና ያልሆነውን የመለየት ክህሎት መላበስ ነው፡፡ ስለዚህ ትክክል የሆነውን ትክክል፤ ትክክል ያልሆነውን አይደለም ብለው በድፍረት መናገር አለባቸው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተመለከተ በኔ በኩል በተግባር የሚንቀሣቀስ ፓርቲ አለ ብዬ አላምንም። ፓርቲ ማለት ህዝብ የሚያደራጅ፣ ችግር ሲኖር ሠላማዊ ሰልፍ የሚጠራ፣ መንግስትን የሚፎካከር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ፓርቲዎች አሁን ያሉበት ደረጃ እጅግ የቀጨጨ ነው፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ነው የተወሰኑት፡፡ ለዚህ ሁሉ መንስኤ ግን የገዥው ፓርቲ ተፅዕኖና ፍራቻ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችም ምሁራንም አሁን ካላቸው ፍርሃት ተላቀው የሚገባቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡  
ብዙዎች አሁን ያለው የሃገሪቱ ሁኔታ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ይናገራሉ፡፡ እርስዎ መፍትሄው ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
አንዳንድ ሰዎችና ድርጅቶች ከሚሰነዝሯቸው ሃሳቦች መፍትሄ መሠል ነገር አያለሁ፡፡ ግን መንግስት ያንን ተግባራዊ ያደርጋል ወይ? የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነው። የሽግግር መንግስት፣ የባለአደራ መንግስት፣ የእርቅ መንግስት የመሣሠሉትና ጀነራሎቹ የሚሰነዝሯቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ሁሉ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግን ችግሩ እንዴት ነው የሽግግር መንግስት የሚቋቋመው? እንዴት ነው ባለአደራ መንግስት የሚቋቋመው? በማን አዘጋጅነት ነው የፖለቲካ ውይይት የሚደረገው? የሚሉት ላይ የቀረቡ ማብራሪያዎች የሉም፡፡ የመፍትሄ ሃሳቦቹ የአፈፃፀም ሁኔታ እጅግ ከባድ ነው፡፡ በአብዛኛው ኳሱ ያለው በኢህአዴግ እጅ ነው፡፡ ኢህአዴግ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ፍላጎት አለው ወይ? በጭራሽ የሚያስበውም አይመስለኝም፡፡ ምህዳሩን ነፃ ያደርጋል ወይ? አይመስለኝም፡፡ አስተሳሰባቸው ይሄን ለማድረግ አይፈቅድላቸውም፡፡ መፍትሄ በእጃችን ነው የሚል አመለካከት ነው ያላቸው፡፡
እኛ ብቻ ነን የምናውቀው ነው የሚሉት፡፡ ነፃ ምርጫ ይካሄድ የሚለውን የጀነራሎቹን መፍትሄ ምናልባት ይቀበሉታል ብንል እንኳ ምርጫው ገና 4 ዓመት ይቀረዋል፡፡ የህዝቡ ጥያቄዎች እንዴት ነው 4 ዓመት የሚቆዩት? ወይም ምርጫው ወደዚህ መምጣት አለበት። ያንን ለማድረግ ቁርጠኝነት አለ ወይ? እነዚህ ከባድ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከሁሉም ወገን የሚቀርቡ መፍትሄዎች መልካም ናቸው፤ ግን አተገባበር ላይ ለአፍ እንደሚቀሉት አይሆኑም፡፡ ስለዚህ በኔ ግምት ሁኔታው እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል፡፡ ኢህአዴግም በያዘው መንገድ ለህዝብ ጥያቄ መልስ ሰጥቶ፣ ችግሩን ይፈታል የሚልም እምነት የለኝም፡፡ እኔ እንዲህ ነው የምለው መፍትሄ አላስቀምጥም፡፡ አሁን ያለው ሂደት ራሱ፣ የራሱን መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት ነው ያለኝ። መፍትሄው በሂደት ከእንቅስቃሴዎች የሚገኝ ነው የሚሆነው፡፡

Read 3253 times