Monday, 19 September 2016 07:58

የጀግኖች እንባ በጆሲ አደባባይ!!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

      የዛሬን አያድርገውና መስከረም አደይ ነስንሶ በችቦ እየሣቀ ሲመጣ በደስታ የማይፈለቀቅ ከንፈርና ልብ የለም፡፡ ጥሎብኝ እኔም ከመስከረም ጋር ለመሣቅ ነፍሴን ሞርጄ ነበር የምጠብቀው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ለአዲስ ዓመት የነበረኝ ፍቅር የትየለሌ ነው፡፡ ሀጫ በረዶ የመሠለው ጄረቴ… ጥርት ያለው ሠማይ፣ ድፍን ጨለማ ሀምሌ ውስጥ ሆኜ በዓይኔ ይመጣ ነበር፡፡… ዘንድሮ ግን ሣቄን የሚያጠፋ፤ ተስፋዬን የሚገፍ፤ ችቦዬን የሚነጥቅ ሀዘን ተፈጠረና የጭጋግ እንቁጣጣሽ አሣለፍኩ፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን በ1958 ዓ.ም ተጠይቅ መስከረም ብሎ የፃፉት ግጥም ወደ ልቤ የመጣውም ይሄኔ ነው፤… እኔም በዕለተ እንቁጣጣሽ በJTV ያየሁትን ፕሮግራም አጥቅሼ ስለ ጀግንነትና ሀገር ወዳድነት፤ ስለተስፋና አዲስ ዘመን ጥቂት አሠኘኝ፡፡
መስከረም ተጠየቅ
ተናገር! አትሳቅ
ካልጋ ተቆራኝቶ ታሞ ለሚያጥረው
ወይ አይሞት ወይ አይድን ስቃይ ለታደለው
ለወላድዋ ድሃ ባልዋ ለሞተባት….
በፍርሃት በሥጋት ሥቃይ ለሚበሉት
ለላም አመጣህ ወይ ነፃነትና ሀብት?
ግጥሙ ጠበቅ ያለ ጥያቄ እየጠየቀ ይዘልቃል፡፡ እኔ ግን ወደ ራሴ ጥያቄ እመለሳለሁ፡፡ አዲስ ዓመት ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ ብቻ አይደለም፤እኛስ አዲሱ ዓመት አዲስ ዓይንና ጆሮ እንዲኖረው ምን አደረግን? ዓይነት!... ባለፈው ሰሞን በዚሁ ጋዜጣ ላይ ፖለቲካዊ ንዝረቴን ስለፃፍኩ፣ ዛሬ ወደ ማህበራዊውና ባህላዊው ጉዳይ ዘወር ማለት እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ!... የሀገር መውደድ ትርጓሜያችንና በጐነታችንን በተመለከተ፡፡
ለመሆኑ ሀገር ጀግኖች ውስጥ መኖርዋን፣ሀገር በጀግኖች መፈጠርዋንና መቀረፅዋን እንረሣ ይሆን!... ይህንን ስሜትና ጥያቄ የፈጠረብኝ በጆሲ ኢን ዘ ሀውስ ላይ የተመለከትኩት የእንቁጣጣሽ የበዓል ዝግጅት ነው፡፡ ጆሲ ዓውደ ዓመቱን አስመልክቶ ወደ ተዘነጉ የኪነጥበብ ሰዎች ቤት በመሄድ፣ ዘሪቱ ጥላዬ ጨዋቃ፣ ግርማ አምሀ፣ኮሎኔል አብዲስ አጋ ቤተሰቦች ዘንድ ሙክት ይዞ በሥጦታ ታጅቦ፣ አበባየሁ ወይ ለምለም ከሚሉ ልጃገረዶች ጋር በር እያንኳኳ ጀግኖቻችንን ጠይቋል፡፡ በዓለም አደባባይ ያኮራንን የሴ/ኮለኔል አብዲሳ አጋን ታሪክ ፈትሾ፣ ከቤተሰቦቹ ጋር ሲያወጋ፣ በኢትዮጵያዊነቴ አፍሬያለሁ፡፡ ጀግናን ያለማክበር በሽታችን መች ይሆን የሚለቀን? ብዬ ራሴንና ትውልድን ጠይቄያለሁ፡፡
አብዲስ አጋ፤ በኢጣሊያ ሀገር ከእሥር ቤት አምልጦ ከተለያዩ ሀገር ዜጐች ጋር በመሆን የሠራው ጀብዱና ከዕብሪተኛው የሶማሊያ ሰራዊት ጋር ያደረገውን ጀግንነት የተሞላበት ጦርነት አስታውሼ፣ በአንፃሩ ደግሞ ይህንን ሁሉ ውለታ የዋለላት ሀገሩ፤ ለቤተሰቦቹ አንዲትም ጐጆ እንኳን ለመቀለስ ፍቃደኛ ያለመሆንዋ በእጅጉ ዘገነነኝ። ስንት ሕዝብ የዘረፉ ሰዎች ተንደላቅቀው በሚኖሩበት ሀገር፣ ያንን የመሠለ ጀግና ቤተሰቦች አንገታቸውን ደፍተው ሲኖሩ፣ በጊዜው የነበረው ደርግ ብቻ ሣይሆን አጠገቡ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንስ እንዴት ዝም ብለው አዩ?-- የሚለው ነገር ጠዘጠዘኝ፡፡… የአብዲሳ አጋ ሕይወት እኮ የኢትዮጵያዊነት ክብር ነው፡፡… ግን አንድ ሁላችንም የምናውቀው በሽታ አለብን፤ በአብዛኛው እርሱ ምን ስለሆነ ነው? … የምትለዋ ዛሬም የተጣባችን ምቀኝነት አለች፡፡… ከሠለጠኑት ሀገራት ሸቀጥ ከምንሰበስብ በጐነትን ብንኮርጅ እንዴት ደግ ነበር… ግና እንዲያ አይደለም፡፡ እርሱ ምን ስለሆነ ነው? ለሚለው መልሱ ቀላል ነው፡፡ ጀግና ስለሆነ መከበር አለበት!!
“ኢትዮጵያዊነት” እያልን ስናቅራራ አፋችን ገደብ የለውም፡፡ ይሁን እንጂ ጀግኖቻችንን አኝከን አኝከን፣ በየደሳሳ ጐጆ ውስጥ ጥለናቸዋል፡፡ ጆሲ ወደተጣሉትና ወደታሰሩት ሰዎች ቤት ጐራ ባለ ቁጥር ነውራችንም አብሮ እየተገለጠ ነው፡፡ አደባባይ ላይ እጃችን ጢስ እስኪያወጣ ያጨበጨብንላቸው ሰዎች፣ሲወድቁ ዘወር ብለን አናያቸውም!... ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን መልካም ነን ብለን በየመጠጥ ቤቱና በየአደባባዩ ስናቅራራ አንደኛ ነን …. ጀግናን ወርውሮ ማቅራራት ምን የሚሉት አመል ነው? ይልቁኑ ለመተቸት አንደኛ ነን፤ሰው የሠራውን ለማሽሟጠጥ ገደብ የለንም፡፡ ሰው ቢሠራ መከራ፣ ባይሠራም መከራ ነው!
ጋዜጠኞች፤ ጀግኖችን የፕሮግራም ማዋዣ ለማድረግ ሩጫችን ዳር የለውም፤… ከዚያ ባለፈ ግን ከሀብታምና ጊዜ ከሰጠው ጋር ሽር ጉድ ከማለት ያለፈ ሕልም የለንም፡፡ ጆሲ ግን ይህንን አድርጐታል፤ የአንድ ቀን እንግዶቹን ጉዳይ ለመፈፀም ስንት ቢሮ እንደደወለ፣ ስንቱን ደጅ እንደጠና እናውቀዋለን፡፡ (ከቢሮ ፀሐፊ ጀምሮ ያለውን ውጣ ውረድ መገመት አያዳግተንም፡፡)
ታዲያ የጆሲ ሥራ እነዚህን የሀገር ቅርሶች ከማገዝ ባሻገር ለቀጣይ ዘመን የሚያመጣው ውጤት አለ፡፡ ያም ዛሬ ጆሲን የሚያዩ ሕፃናትና ወጣቶች፤ ነገ ከኛ  የተሻለ ወገንን የመርዳት፣ ጀግኖችን የማክበር ዘር እንዲፀንሱ ያደርጋል፡፡ መልካም ነገር መሥራት ክብር እንደሆነ ያስተምራል፡፡ እንደ ብዙዎቻችን “ሀገሬ!” እያሉ ከንፈር ላይ ከሚተንን ወሬ የላቀ ውጤት ያመጣል!
የኛ ዘመን ከጀግና ይልቅ ሸቀጥን ያተለቀ፣ ከሀገር ይልቅ ሆድን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ለማወቅ መፃሕፍት ማገላበጥ አያስፈልግም፡፡ በየጊዜው ብብታችን ሥር የሚፈለፈሉት “ሆዳሞች” ወገናቸውን ለቅንጣት ኑሮ ብለው እንደሚሸጡ፣ በሚፈስሰው ደሙ ላይ አበባ ነስንሰው እንደሚደንሱ በዐይኖቻችን አይተናል፡፡… ይህ ለኛ ብርቅ አይደለም። … በዚህ መሀል ግን አንዳንዱ ይጮሃል… አንዳንዱ ደወል ይደውላል፡፡ ሆዳሙ ግን መስሚያ የለውም፤… ጆሮው ላይ የሚያፋጨው ሆድ ነው፡፡ መብላትም መጠጣትም ነው፤ የሕይወቱ ግብ፡… ሰውነቱም እንደ በሬ ሥጋ መሸከም ብቻ ነው!!... እዚህ ጋ የዶክተር ፈቃደ አዘዘን ግጥም ልዋስ መሠለኝ፡- “ከበዳ ወደ በዳ” ይላል (“ዳ” ላላ ተደርጋ ትነበብ)
ይጮሃል ደራሲ
ይጮሃል አዝማሪ
ይጮሃል ከያኒ
ግን ማንስ አደምጦ
ኸረ ማንስ ሰምቶ?
ሁሉም እጆሮው ላይ በሆዱ ተኝቶ
አንድ ጣሳ አረቄ አንድ በርሚል ጠላ
ጠጅ ጠጅ አንቡላ
ከአሥራ አሥር ክትፎ ጋር አሥር ኪሎ ሥጋ
ቢጐምድ ቢሰለቅጥ ቢቸልስ ቢለጋ
ይመርጣል ዘመኑ
ጥበብ ለሱ ምኑ?
እውነት ነው፤መብላት መጠጣትና ቅንጦት የሰው ልጅ የኑሮ መለኪያ ሆኗል፡፡ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ፤ ከያኔውንም እንደ ተቆርቋሪና ጉበኛ /ሀገር ተቆርቋሪ/ አድርጐ ቆጠረው እንጂ ዋና ባንዳዎቹ፣ ከያኒ ነን ባዮቹ ሆነዋል፡፡ ከስንት አንድ ነው ለሀገሩና ለወገኑ ተቆርቋሪ?... ብዙዎቹ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፡፡ … ንባብ የለ፤ እውቀት የለ … ሽቀላ ብቻ… “ሆዳም” ሰው ደግሞ ፍቅር አያውቅም!... ስለዚህ ሀገሩንና ወገኑን ለመሸጥ ቅንጣት አይሳሳም፡፡
… ጆሲ ግን ቢያንስ ጀግኖቻችንን ከየሥርቻው ፈልጐ፣ ሕሊናችንን በፀፀት ጅራፍ ይገርፈዋል፡፡ ይህ ጅራፍ ቀጣዩን ትውልድ እንዳይገርፈው፣ጀግና አክባሪ ትውልድ ያሰለጥንልናል፡፡… ለዛራና ቻንድራ ፍቅር ከንፈሩን የሚመጠውና ለሀገሩ ጉዳይ ባይተዋር የሆነውን ሰው ያነቃቃልናል፡፡ አንዳንድ ሆድ ዓምላኩዎች ይህም ሊያስቀናቸው ይችላል። “ስፖንሰር ፍለጋ ነው!” ብለው በጐ ሥራው ላይ ጥላሸት ከመቀባት አይሳሱም፡፡ እኛ ጋ ግን እንዲህ እንላለን!... አንድ ቀን እንኳን ጀግኖችን መች አስባችሁ ታውቃላችሁ? ባለ ውለታዎችን ማክበርስ መች አስተማራችሁን? …
እኛስ ራሳችን ጀግኖቻችንን የማናከብረው እስከ መቼ ነው? … ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ፣ መልሱ፡- እስክንሰለጥን የሚል እንደሆነ ጥርጥር የለኝም። ለጊዜው ግን አንዳች ጨለማ ጋርዶናል፤ አንዳች ዳፍንት ውጦናል!...
ለማንኛውም ሰዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፤ ”ሀገር” በሚለው ግጥሙ ከተቀኘው ጥቂት ስንኞችን ልዘምር፡-
አገሬ ውበት ነው
ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት
ጸሐይ የሞላበት ቀለም የሞላበት
አገሬ ቆላ ነው ደጋ ወይና ደጋ
እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ
ተስፋ አለኝ ይነጋል፡፡ ጀግኖች የሚኮሩበትን ሀገር እንፈጥራለን ብዬም አምናለሁ፡፡       

Read 4228 times