Monday, 19 September 2016 08:02

የለውጥ እድሎች እንዳያመልጡንና ከለውጥ ወረርሽኞች ለማምለጥ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(9 votes)

    ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ የአፍሪካ አገራትን፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ከፍ ዝቅ የሚያደርጉ የለውጥ ወረርሽኞችንና ሽውታዎችን በተመለከተ፤ ባለፈው ሳምንት የመነሻ ፅሁፍ አቅርቤያለሁ - ባለፉት 50 ዓመታት የአፍሪካ አገራት የሕገመንግስት ለውጦችን (የማሻሻያና የማበላሻ ለውጦችን) በመጠቃቀስ።
ከግራ ቀኝ የሚያንገራግጩን የመልካም ለውጥ ሽውታዎችንና የክፉ ለውጥ ወረርሽኞችን፣ በቅጡ መገንዘብ፣ አዳዲስ እድሎችን ጥቅም ላይ ለማዋል፣ እንዲሁም አዳዲስ አደጋዎችን ለመከላከል ይረዳል ብዬ አስባለሁ - በጭፍን ተቀምጦ ከመጠበቅና በጭፍን ሩጫ ከመደናበር ይልቅ፣ ነገሮችን ለማገናዘብ መሞከር ይሻላልና።
እስቲ ዛሬ ደግሞ፣ ከሌላ አቅጣጫ፣ የአፍሪካ አገራትን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች አገራትንም በማካተት፣ የለውጥ ሽውታዎችንና ወረርሽኞችን ከአይነት ከአይነቱ በማሳየት፣ የሳምንቱ ሃሳቤ ላይ ላክልበት።
አቤት፣ አለማችን የለውጥ ውጣውረድ፣ በየአገሩ መመሳሰሉ!
ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከአሜሪካ እስከ ኤሽያ፣... የመጠንና የፍጥነት ጉዳይ ነው እንጂ፣ ከአንዱ ጥግ የተጀመረ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የለውጥ ማዕበል፣ ሌሎችንም አገራት ሳያጥለቀልቅ፣ ወይም ሳይነካካ አያልፍም። ያው፣ ዛሬ ዛሬ በጉልህ የሚታዩ አዳዲስ እድሎችና አደጋዎች፣ የኑሮ ችግሮችና የለውጥ ማዕበሎችም፣ በየአገሩ ተመሳሳይ እንደሆኑ ማወቅ ያስፈልገናል ለማለት ነው።
የመረጃም ሆነ የእውቀት፣ የአሉባልታም ሆነ የፕሮፓጋንዳ ዘዴዎች፣ በአስደናቂ ፍጥነት ከዳር ዳር አለምን እያዳረሱ የመጡት፤ የቴክኖሎጂና የንግድ እድሎች በእጅጉ የተስፋፉት... ለአንድ ወይም ለሁለት አገራት አይደለም። ለሁሉም አገራት ነው።
በዚያው ልክ፣ የዘመኑ ፈተናዎችና አደጋዎችም፣ በአንድ ወይም በሁለት አገር ብቻ ተወስነው የሚቀሩ አይደሉም።
የአውሮፓ ኢኮኖሚ መፍዘዙና ቅሬታ መበራከቱ፣ የቻይና ግስጋሴ መቀዝቀዙ፣ የሶሪያና የኢራቅ፣ የማሊና የጋምቢያ፣ የሊቢያና የየመን ትርምሶች፤... የኢትዮጵያ፣ የቬኒዝዌላ፣ የደቡብ አፍሪካ ወዘተ ቀውሶች፤... ኦባማ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ የብልሽት ካልሆነ በቀር የመሻሻል ለውጥ ሊፈጠር ይችላል የሚል ተስፋ የለኝም ማለታቸው፤... እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት መወሰኗ፤... ዶናልድ ትራምፕ ከምር በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ ሆነው ለውድድር መቅረባቸው፤... በጀርመን፣ በጣሊያንና በበርካታ የአውሮፓ አገራትም ወደ ዘረኝነት ያዘነበሉ አዳዲስ ፓርቲዎች እዚህም እዚያም በምርጫ ማሸነፍ መጀመራቸው... እነዚህ ሁሉ ግንኙነት አላቸው።
በእርግጥ፣ ይሄ በተደጋጋሚ ተነግሯል። ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ዩኒት (EIU)፣ በአመታዊ የዲሞክራሲ ሪፖርቱ፣ “በነፃነት ላይ የተመሰረተ የዲሞክራሲ ስርዓት” በአለም ዙሪያ፣ ፈተና ላይ መውደቁና አደጋዎች እንደተጋረጡበት ገልጿል። ከቅርብ አመታት ወዲህ፣ የመሻሻል ለውጦች መዳከማቸው ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ኋላ የመንሸራተትና የመበላሸት ለውጦች መበራከታቸውን ገልጿል - ሪፖርቱ። ያለምክንያት አይደለም። ከዋነኛዎቹ ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ የሊበራሊዝም አስተሳሰብ እየተዳከመ መምጣቱ እንደሆነ ሪፖርቱ ያስረዳል። ያው፣... እውነታንና አእምሮን የሚያከብር ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ተዳክሟል፤... በግለሰብ ነፃነት፣ በነፃ ገበያና በሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ የሊበራሊዝም የፖለቲካ ሃሳቦች ቸል ተብለዋል። አስተሳሰብና ሃሳብ ደግሞ፣ ድንበር አያግዳቸውም። ሲጠናከሩም፣ በየአገሩ ይጠናከራሉ። ሲዳከሙም፣ በየአገሩ ይዳከማሉ። ለዚህም ነው፤ የለውጥ ሽውታዎችና ወረርሽኞች ብዙ አገራትን ሳያዳርሱ የማይመለሱት።
በቅርቡ “ፍሬዘር አንስቲቱት” ያቀረበው፤ አመታዊ የኢኮኖሚ ነፃነት ሪፖርት ውስጥ የተዘረዘሩ መረጃዎችንም መመልከት ይቻላል። ሪፖርቱ የበርካታ አመታት መረጃዎችን ያካተተ በመሆኑ፣ የአለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውጣውረዶችን ሰብሰብ አድርጎ ለማሳየት ያመቻል።
በ32 የአፍሪካ አገራት ዙሪያ የተጠናቀረውን፣ የ40 ዓመት የጥናት መረጃ ተመልከቱ፡፡ ከሞሪሸስ፣ ከቦትስዋናና ከሞሮኮ በመቀጠል፤... ከ1980 እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ፣ ስንቶቹ የአፍሪካ አገራት፣ ኢኮኖሚያቸውን ወደ ነፃ ገበያ አቅጣጫ ለማንቀሳቀስ ሞክረው ይሆን? ያልሞከረ አገር እንደሌለ የተቋሙ ጥናት ይገልፃል፡፡ በጦርነት የተመሳቀሉት እነ ኮንጎ እና ሩዋንዳ፣ ሴራሊዮን እና ላይቤሪያ እንኳ፣ ከቀድሞ የተሻለ ለውጥ ማስመዝገብ የቻሉበት ዘመን ነው። መልካም የለውጥ ሽውታ፣ ሁሉንም አገራት አዳርሷል - በተመሳሳይ ጊዜ።
በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ ዓ.ም፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት፣ የዜጎችን ንብረት ለመውረስ፣ የግል ቢዝነስን ለማዳከምና ኢኮኖሚያቸውን የመንግስት እስረኛ ለማድረግ ዘምተዋል - የሶሻሊዝም ወረርሽን፣ አንድ ሁለት አገራትን በመነጠል ሳይሆን፣ አፍሪካን ያጥለቀለቀበት ዘመን ነው።
ያው፤ በመንግስት የተተበተበውን ኢኮኖሚ ለቀቅ ለማድረግና የነፃ ገበያ አሰራርን ለመሞከር የወሰኑትም በተመሳሳይ ጊዜ ነው። ከ1980 እስከ 1990 ዓ.ም፣ የነፃ ገበያ ሽውታ፣ ወደ አፍሪካ ጎራ ባለበት ዘመን... በአስር አመታት ውስጥ፣ 32ቱም አገራት፣ መልካም የለውጥ ውጤት አሳይተዋል ይላል የፍሬዘር ሪፖርት። ግን ምን ዋጋ አለው? ብዙ አልቆየም።
የነፃ ገበያው ሽውታ ተቋርጧል። የዛሬው ዘመን፣ በአብዛኛው የመንገዳገድ ዘመን ሆኗል። ወደፊት እየተራመዱ ወደኋላ የመንሸራተት፣ እየወደቁ የመነሳት፣ ግራ ቀኝ የመደናበር ዘመን ነው ዛሬ።
ከሁለት አገራት በስተቀር፣ ሰላሳዎቹ የአፍሪካ አገራት፣ ከአምስት አመት በፊት ከነበራቸው ሁኔታ ቅንጣት አልተሻሻሉም። እንዲያውም፣ ብዙዎቹ ወደ ኋላ ተንሸራትተዋል። ከሚሻሻሉ አገራት ይልቅ፣ የሚበላሹ አገራት እየተበራከቱ መጥተዋል።
ይሄ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። ነገርዬው አፍሪካን ብቻ እያነሳ የሚጥል አባዜ አይደለም፡፡
በብልፅግና ደህና የተራመዱ አገራትን ማየት ይቻላል - አሜሪካ፣ ካናዳና ጃፓንን ጨምሮ፣ አብዛኞቹ የምዕራብ አውሮፓ አገራትን (“ኦኢሲዲ” የተሰኘውን ተቋም የመሰረቱና በነባር አባልነት የሚታወቁ 24ቱ አገራትን ተመልከቱ)።
የተቋሙ የኢኮኖሚ የስታትስቲክስ ክፍል በዳሬክተር ለስምንት አመታት የመሩ፣ ዴቪድ ሄንደርሰን፣ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ ዓ.ም፣ የነፃ ገበያ ስርዓት በእነዚሁ አገራት እየተሸረሸረ፣ በተቃራኒው መንግስት እየገነነ እንደመጣ ይገልፃሉ - የሶሻሊዝም ወረርሽኝ የተስፋፋበት ዘመን ነበር ይላሉ።
ወረርሽኙ እየረገበ፣ የነፃ ገበያ የለውጥ ሽውታ፣ ምድረ አሜሪካንና ምድረ አውሮፓን ማነቃቃት የጀመረው በ1970ዎቹ እንደሆነ ሄንደርሰን ሲያስታውሱ፤ በእንግሊዝ የማርጋሬት ታቸር እና በአሜሪካው የሮናልድ ሬገን ዘመንን ይጠቅሳሉ። ግን፣ የለውጡ ሽውታ፣ በሁለቱ አገራት ውስጥ የታጠረ አልነበረም።
እና፣ ከ24 አገራት መካከል፣ ምን ያህሉ ከሶሻሊዝም ወረርሽኝ አገገሙ? ምን ያህሉ በነፃ ገበያ የለውጥ ሽውታ፣ አገራቸውን አሻሻሉ?
በአምስት አመት ውስጥ፣ 19ኙ አገራት የነፃ ገበያ ስርዓትን ለማስፋፋት፣ የተለያዩ የማሻሻያ ሃሳቦች ተግባራዊ አድርገዋል - በ1970ዎቹ አጋማሽ። ከአሜሪካና ካናዳ እስከ ጃፓንና አውስትራሊያ፣ ከእንግሊዝና አየርላንድ እስከ ኖርዌይና ስዊድን፣ ጀርመንና ኦስትሪያ... በተመሳሳይ ጊዜ ነው፣ ነፃ ገበያን ለማስፋፋት የወሰኑት። ቀሪዎቹ አገራትም… ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ግሪክና ቱርክ... ወደዚሁ የለውጥ ሽውታ ተቀላቅለዋል።
በእርግጥም፣ ሲሸረሸር የቆየውን የነፃ ገበያ አሰራር፣ እንደገና ለማጠናከርና ለማሻሻል ባደረጉት ጥረት፣ ሁሉም አገራት... (24ቱም አገራት)... በ1980 ዓ.ም ከፍ ያለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደቻሉ የፍሬዘር ኢንስቲቱት፣ የኢኮኖሚ ነፃነት ሪፖርት ያረጋግጣል። ሁሉም አገራት፣ የመልካም ለውጥ ሽውታ ተቋዳሽ ሆነዋል።  
ነገር ግን፣ እንደአጀማመራቸው፣ የነፃ ገበያ ስርዓትን እያስፋፉ አልቀጠሉም። ከ1990 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት፣ የሁሉም አገራት የመሻሻል ጉዞ ተቋርጧል። እንዲያውም፣ ሁሉም አገራት ወደ ኋላ እየተንሸራተቱ ናቸው። አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ሁለት እርምጃ ወደኋላ... ያው የመደናበር ዘመን ሆኗል።
የአፍሪካ ትለያለች፡ ለመልካም ለውጥ በመዘግየት፣ ለመጥፎ ለውጥ በመሮጥ
የሶሻሊዝም ወረርሽኝ፣ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራትን በማዳረስ፣ ኢኮኖሚያቸውን  ሲሸረሽር ቆይቷል።
ወረርሽኙ፣ የአፍሪካ አገራትን ያዳረሰው ግን፣ አስር ዓመት ቆይቶ ነው - በ1960ዎቹና በ70ዎቹ ዓ.ም።
በሌላ በኩል...
በነፃ ገበያ ሽውታ አማካኝነት፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ኢኮኖሚ የተነቃቃው፣ በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ ነው።
በአፍሪካስ?
የነፃ ገበያ ሽውታ ወደ አፍሪካ የደረሰው፣ አስር አመት ዘግይቶ ነው - በ1980ዎቹና በ90ዎቹ።
ሽውታውን ተክቶ የመጣው ሌላኛው ወረርሽኝስ?
በአሜሪካና በአውሮፓ የነፃ ገበያ ማሻሻያዎች የተዳከሙትና የኋሊት መንሸራተት የጀመሩት፣ በተለይ ከ1995 ዓ.ም ወዲህ ነው።
በአፍሪካ ደግሞ፣ ከ2000 ዓ.ም ወዲህ።
ያው፣ የለውጥ ወረርሽኙም ሆነ ሽውታው፣ አለማቀፋዊ ነው። በእርግጥ፣ ሁለት ልዩነቶች አሉ። አንደኛው ልዩነት፣ የጊዜ ቅደም ተከተል ነው፡፡ ወረርሽኙ አልያም ሽውታው፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ወደ አፍሪካ ለመድረስ፣ ጥቂት አመታት ይፈጅበታል። ግን፣ የጊዜ ልዩነቱ እየጠበበ መጥቷል - ከአስር ዓመት ወደ አምስት ዓመት።
ሌላኛው ልዩነት፣ ደግሞ የለውጡ መጠን ነው።
የመሻሻል ለውጥ ሲመጣ፣ ዞሮ ዞሮ ብዙዎቹን የአፍሪካ አገራት ሳያዳርስ አያመልጥም፡፡ ነገር ግን፣ የለውጡ መጠን የአውሮፓና የአሜሪካ ያህል አይሆንም። በመልካም የለውጥ ሽውታ አማካኝነት፣ በደንብ ተጠቃሚ ለመሆን ከመፍጠን ይልቅ፣ በማንገራገርና በዳተኝነት ጊዜ ይባክናል - አፍሪካ ውስጥ።
አውሮፓና አሜሪካ ውስጥ፣ ነገሮችን የሚያበለሻሽ የለውጥ ወረርሽኝ ሲፈጠር፣ አፍሪካ አይቀርላትም። ነገር ግን፣ የአፍሪካ ብልሽት ከሌሎቹ የባሰ ይሆናል።
ያው፤ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ፣ በሶሻሊዝም ወረርስን፣ የአፍሪካ ያህል አልተጎዱም። በእርግጥ፣ በወቅቱ... የተወሰኑ የፖለቲካ ረብሻዎችና ግርግሮች ተፈጥረዋል፡፡ የተወሰኑ የቢዝነስ መስኮች በመንግስት ስር እንዲሆኑ እየተደረገ፣ የተወሰነ የኢኮኖሚ መዳከምና ምስቅልቅል ተከስቷል፡፡ ነገር ግን፣ ወረርሽኙ ከዚህ አልፎ፣ አገሬውን የሚያተራምስበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። ወረርሽኙን የሚስፋፉ ብቻ ሳይሆኑ፤... ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ለመመከትና ለመመለስ የሚጣጣሩ በርከት ያሉ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ዜጎች አሏቸው።
አፍሪካ ውስጥ ግን፣ ... የሶሻሊዝምን ወረርሽኝ የሚያስቆም አልተገኘም። ከፖለቲካ ግርግር አልፎ፣ የአንድ ፓርቲ አገዛዝና የጅምላ ግድያ፤... የዜጎችን ንብረት ጠቅልሎ መውረስና ይብሱኑጥ ማደህየት፤... ከዚያም ረሃብና እልቂት... በቃ! ወረርሽኙ እስከ ጫፍ ድረስ ነው አፍሪካን ያተራመሳት።
በመልካም የለውጥ ሽውታ አማካኝነት፣ በስፋትና በፍጥነት ተጠቃሚ ለመሆን ብዙ አንተጋም። በመጥፎ የለውጥ ወረርሽኝ፣ በስፋትና በፍጥነት ተጎጂ እንዳንሆን፣ በአስተዋይነት ጥፋትን አንከላከልም።
እና ዛሬም፣ በአዳዲስ የቴክኖሎጂና የንግድ መስኮች እየተስፋፉ ካሉት መልካም የለውጥ እድሎች፣ በአግባቡ ተጠቃሚ ለመሆን ብዙም አየተጋን አይደለንም። በሌላ በኩል ደግሞ፣ እየተዛመቱ በሚገኙት መጥፎ የለውጥ ወረርሽኞች፣ ክፉኛ ሰለባ ለመሆን እንጣደፋለን።
አዎ፤ በመጥፎዎቹ የለውጥ ወረርሽኞች ሳቢያ፣ አውሮፓና አሜሪካ መጎዳታቸው አይቀርም። እንደምናየውም ... እዚህም እዚያም፣ በተወሰኑ የሽብር ጥቃቶች እየተጎዱ ነው፤ “ሽብርን እከላከላለሁ” በሚል ሰበብ መንግስታት በዘፈቀደ በሚያስፋፉት የስልክና የኢንተርኔት ጠለፋ አማካኝነትም፣ በርካታ ዜጎች ሰለባ ይሆናሉ።
በታክስ ጫናና በመመሪያዎች ብዛት አማካኝነት፣ ቢዝነስ እየተዳከመ፣ ኢኮኖሚያቸው እየፈዘዘና እየደነዘዘ፣ ኑሮ አልሻሻል ብሏቸዋል - በእንብርክክ የመንፏቀቅ ያህል እየሆነባቸው ብዙዎች ይማረራሉ። ይናደዳሉ። እንግሊዛዊያን በቁጣ፣ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት እንደወሰኑት ሁሉ፣ በጀርመንና በጣሊያን፣ በዴንማርክና በሃንጋሪ፣ እና በአብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት፣ ብዙ ሰዎች በንዴት፣ ለ“ፀረ ስደተኛ” ፓርቲዎች፣ ድጋፍ እየሰጡ ነው - ወደ ዘረኝነት ባዘነበለ ስሜት። በአሜሪካ ደግሞ፣ ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ ተወዳዳሪ ለመሆን የቻሉበት ዘመን ላይ ነን። ወይም ደግሞ፣ “ብላክ ላይቭስ ማተር” እያሉ... ‘በዘር መቧደን’ን የሚያስፋፉ ቀስቃሾች፣ እንደ ‘ነፃነት ታጋይ’ የሚታዩበት ዘመን።
እንዲያም ሆኖ፣ የሃይማኖት አክራሪዎች ሽብር እና የመንግስታት ሰፊ የስለላ ወከባ፣ የመንግስት መግነንና የኢኮኖሚ መዳከም፣ የዘረኝነት ስሜቶችና ግርግሮች... በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ አውሮፓንና አሜሪካን ያተራምሳሉ ተብሎ አይጠበቅም። የዘመኑ የለውጥ ወረርሽኝ፣ ክፉኛ ቢያንገራግጫቸውም፣ ለጊዜው የሚያደርስባቸው ጉዳት፣ ከልኩ አያልፍም።
ጉዳቱ የሚብሰው፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ውጭ ነው። ምኑ ይነገራል? እያየነው አይደል?
እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት፣ የመንግስት መግነንና የኢኮኖሚ መዳከም ማለት፣... መዘዙ ብዙ ነው - ሙስናና ስራአጥነት፣ ስደትና ረሃብ ማለት ነው። የአክራሪዎች ሽብርና የመንግስት ፀረሽብር ሰበቦች... በአፍሪካና በአረብ አገራት ውስጥ፣... በቃ! የለየለት ጦርነትና የለየለት አምባገነንነት ማለት ነው። በአፍሪካና በአረብ አገራት፣ የዜጎች ንዴትና የመንግስት ምላሽ ማለት፣... ግድያና እስር፣ በዘር መቧደንና መተራመስ ማለት ነው።
ይህንን ማወቅ፣ ‘ለክፉም ለደጉም’ ይበጃል - ደግ የለውጥ እድሎችን በትጋት ለመጠቀም፣ ክፉ የለውጥ ወረርሽኞችን ለመከላከል።  

Read 1814 times