Monday, 19 September 2016 08:06

አዲሱ ዓመት የማን ነው?!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

     ባለፈው አዲስ ዓመት ዋዜማ ቤተሰቤን ለማየት ሄጄ ነበር፡፡ በዓልን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል፡፡ ከመቀበል ውጭ አማራጭ የላቸውም፡፡ ልክ እንደኔው በዓል ባይመጣ የሚሻላቸው ነው የሚመስሉት፤ ከመጣ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፤ለማክበር ይገደዳሉ፡፡ በአል የማክበር ግዴታ ከሌሎች አነስተኛና ጥቃቅን ግዴታዎች ድምር ተጠረቃቅሞ የሚሰራ ነው፡፡
ዶሮ ሳይገዛ በዓል ማክበር የለም፡፡ ዶሮ መግዛት ብቻ ሳይሆን ዶሮ ወጥ መስራት የግድ ነው። ወጡ ለመሰራትም ብዙ ጣጣ አለው፡፡ በዓሉን ለምን ለማክበር እንደሚገደዱ እንጂ የማያውቁት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ግን አይጠራጠሩም፡፡
የበዓል ማክበር ጥያቄ ባልታሰበ ጥምዝ የ“Existential” ፍልስፍና ጥያቄ ሆኖ ቁጭ ይላል። የህልውና ጥያቄ ይሆናል፡፡ እንዲያውም እውነቱን ተናገር ካላችሁኝ … ከበአል ማክበር ይበልጥ የልደት ቀንን ማክበር ለግለሰቡ የቀረበ ፍላጎት ነው፡፡ የግለሰቡ ከምንነት ወይንም ማንነት ትርጉም ጋር ከእንቁጣጣሽ የበለጠ ለአክባሪው ይቀርበዋል፡፡
ቤተሰቤን እንደ አንድ ተራ ቤተሰብ ሳስተውላቸው … የደከማቸው መሰለኝ፡፡ የደከማቸው የመሰለኝ እኔን ስለደከመኝ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔን ለምን ደከመኝ? … የደከመኝ ግራ ስለገባኝና  ፍላጎቴ ምን እንደሆነ ጠንቅቄ ስለማውቅ ነው፡፡ ፍላጎቶችን ከአፈላለጉ መንገድ ነጥሎ ማየት የትም እንደማያደርስ በሂደት ተረድቻለሁ፡፡ ፍላጎቴን ከአፈላለጉ መንገድ አጣምሬ ማየት ብቻ ሳይሆን የፍላጎቴንም ምንነት መረዳትም አብሮ የተሳሰረ ጉዳይ ነው፡፡
ማንም ደስታን የማይፈልግ የለም፡፡ ዓመት በዓልን በማክበር ውስጥ ደስታ በእርግጠኝነት ይገኛል ብዬ አስባለሁ … ታዲያ ግን፤ ዓመት በአልን ካከበርኩ በኋላ ለምን ይሆን ተስፋ የመቁረጥ ስሜት የሚሰማኝ? የሌላውም ሰው ስሜት ከእኔ ብዙ የሚርቅ አይመስለኝም፡፡ ለበጉ፣ ለዶሮው፣ ለመጠጥና ለአዲስ ዓመት ልብሱ ያወጡት ወጪ አናታቸው ላይ የሚወጣው የደስታው ቀን ካለፈ በኋላ ነው፡፡ ለነገሩ መጠጥም የደስታ መፍጠሪያ የፈሳሽ አይነት ነው፡፡ ሰው ለመጠጣት ሲያቅድ፣ ሲጠጣ፣ ሲሰክር፣ ሲደንስ … በዚህ ሂደት ላይ ደስተኛ ነው፡፡ ነኝ ብሎ ያስባል፡፡ ሀሳቡ በተግባሩ ላይ ይታያል፡፡ ስካሩ ካለፈ በኋላ ግን ደስታው ወደ ራስ ምታት ጥሎት ነው የሚታየው፡፡
 እውነተኛ ደስታ እንዴት ነው የሚገኘው? በእርግጠኝነት አመት በዓል ከማክበር ጥሩ መፅሀፍ በአመት በዓል ምድር ሳነብ ብውል እመርጣለሁኝ፡፡ ግን “ጥሩ መፅሐፍ ማንበብ”ም የህልም አይነት ናት። በአመት በዓል ጥሩ መፅሀፍ አንብቤ አላውቅም፡፡ ጥሩ መፅሀፍ ለአመት በዓል ገበያ ላይ አይውልም፡፡ ልክ ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው በግ ለአመት በዓል ገበያ ላይ እንደማይገኘው፡፡
ዓመት በአልን ከደስታ ጋር አጣምሮ ማሰብ … አዲስ አመትን ከተስፋ ወይንም ብልፅግና ጋር አጣምሮ ከመመኘት ምን እንደሚለየው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ 2008 እስከ ጳጉሜ አምስት በነበረበት ቦታ ላይ ቆይቶ፣ አንድ ቀን በመጨመሩ ምን የሚለወጥ ነገር ይኖራል? …. የምኞት ተመኚው እውቀት ላይ ራሱ በሰዓታት ጊዜ ጭማሪ የሚለወጥ ነገር ሳይኖር እንዴት ከአለፈው አመት የተለየ ምኞት ለመመኘት ደፈረ?
ዓመት በዓል ማክበርን … ህገ መንግስት ከማክበር ለይቼ እንዴት ልገነዘበውስ ደፈርኩኝ? ህገ መንግስቱን በአለፈው አመት ያላከበረ መንግስት … በዚህኛው ዓመት እንቁጣጣሽን በማክበሩ፣ ወደ አዲስ ዘመን ተሸጋግሬአለሁ ቢለኝ ላምነው እችላለሁ?
ነገራትን አጣምሮ ለማሰብ ከደፈርኩ … ሁሉም ነገር ግራ ያጋባል፡፡ “አዲስ አመት” የሚባል በአየር ላይ ተንጠልጥሎ … ከሌላው ነገር ጋር ሳይነካካ የተቀመጠ ዳቦ ነገር አለ እንዴ? … “ተስፋ ርቆ የተሰቀለ ዳቦ ነው” ይል ነበር አንድ የቱያትር ገፀ ባህርይ፡፡ ያለፈው ዓመት ተሰቅሎ ሳንበላው፣ሳናየው ያለፈ ዳቦ … እንዴት ሳንበላው ቀረን ብለን ሳንጠያየቅ፤ አዲስ ዳቦ ጋግሮ ለዚህ ዓመት “ተስፋ” ተብሎ በድጋሚ እንዴት ተሰቀለ? ነው ጥያቄው፡፡
“2009 ዓመተ ምህረት ገባ” ብለን ዓመት በአልን አክብረናል፡፡ አክብረነው፣ ተቀብለነው ሳያከብረን፣ ሳንጨብጠው ያለፈ ነገር ምንድነው ተብሎ የሚጠራው? … “ተስፋ” የዚህ ሁነት መግለጫ ቃል ከሆነ በጣም ያስደነግጣል፡፡ 2009 ዓመተ ምህረት ገባ ብለን ከመደምደማችን በፊት ከዚህ ቀደም ሳይገቡ “ገብተዋል” በሚል የተጫኑብንን አመታት መጀመሪያ ተሳስበን ማወራረድ አለብን። እንዲያውም ደፍረህ እቅጩን ንገረን ካላችሁኝ…. አርባ አመታት … በ“ተስፋ” እንጂ ሳይገቡ ገብተዋል በሚል የተጭበረበሩብን ናቸው፡፡ …. ይህ ማለት እኔ ራሴ ገቡ ከተባሉት አመታት ተነጥዬ በምድረ በዳ (ተስፋ) ላይ በመኖር ላይ የምገኝ ነኝ ማለት ነው፡፡ እኔ በተጨባጭ በህልውና ካለሁኝ … አመታቱ የሉም…። “አመታቱ በተጨባጭ ነበሩ” ከተባለ እኔ በእነዚህ አመታት ውስጥ ሳልፍ የተከሰተ ለውጥ በእኔ ህልውና ላይ አሻራቸው ተፅፎ መገኘት አለበት፡፡
ሰው ዘሎ ፖለቲካ ላይ ይንጠለጠላል፡፡ ወዳጆቼ! እኔ እያወራሁ ያለሁት ስለ አዲስ አመት ነው። አመታት ራሱ እንደ “ፊያት ገንዘብ” እየመሰሉኝ መጥተዋል። ገንዘብ የሚባል እሴት በተጨባጭ ካለ … አንድ አካል ሁሌ ገንዘብ የሚያበድር … ሌላው አካል ዝንተ አለም የሚበደር ሊሆን አይችልም። ተበዳሪ ለአበዳሪ መልሶ ሳይከፍል፣ መበደሩን ያለ ጊዜ ገደብ የሚገፋበት ከሆነ … ገንዘብ የሚባለው ነገር ህልውና እንደሌለው ማረጋገጫ ነው፡፡ ከዚህ የተሻለ ምክንያታዊነት ሊኖር አይችልም፡፡
አርባ አመታት ተስፋ ውስጥ የሚኖር ትውልድ … አንድ ቀን በብስጭት ነቅቶ ማስተዋል ከጀመረ .. የሚደርሰው ሶስት የአማራጭ መፍትሄ ላይ ነው። አንድም፤ አርባው አመታት ህልም ናቸው እንጂ ተጨባጭ አይደሉም፡፡ ሁለት፤ አርባ አመታቱ ውስጥ ያለፈው ትውልድ የህልም ህልውና ነው ያለው፡፡ ሦስት፤ “ተስፋ” የተባለው ነገር ውሸት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱ አይቀርም፡፡ የሚያሳዝነው ሶስቱ አማራጭ መፍትሄዎች ተነጣጥለው የማይገኙ መሆናቸው ነው፡፡ “ተስፋ” የተባለው ነገር የማይጨበጥ ህልም መሆኑን ማረጋገጥ የትውልዱንና የዓመታቱን ህልውና መካድ ነው፡፡
… ወጣም ወረደ አዲስ ዓመትን አክብረናል፡፡ እና በፍላጎታችን ባናከብረውም እሱ ራሱን አክብሮ ንቆን አልፏል፡፡ አዲስ ዓመት ተጨባጭ ህልውና ካለው ከአክባሪው ጋር እውነተኛ የሆነ ትስስር ይፈጥራል። በፖለቲካ ዲስኩር የተጀቦነ አይሆንም፡፡ ይኼኛው አመት ተጀቡኖ፣ ተከናንቦ አልፏል፡፡ አዲስ ዓመት ህልውና ካለው … ከአሮጌው ጋር ልዩነት የሌለው አይሆንም፡፡ አለመሆን ነበረበት፡፡ በአለመሆን የነበረበት ነገር ሲሆን ስናይ … ተስፋን ሳይሆን የሚያመላክተን “ተስፋ መቁረጥን” ነው፡፡ ሰውን ተስፋ አስቆርጦ ብቻውን ተስፋ ሰንቆ የሚቀጥል ዓመት የአምባገነንነት ባህርይ የተጠናወተው ነው፡፡
ለማንኛውም አዲስ ዓመት ገብቷል … ተፈጥሮ ራሷን አድሳለች፡፡ ተፈጥሮ … ሳሩ … አበባው … ሰብሉና የፀሐይዋ ብርሃን ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። አዲስ ዓመት መግባቱ ድሮ የሚለፈፈው በተፈጥሮ አንደበት በኩል ነበር፡፡ አሁን አዲስ ዓመት መግባቱን የማውቀው ለክረምቱ ወቅት ጋብ ብሎ የነበረው የቤቶች መፍረስ ዘመቻ መልሶ ሲጀመር … ወይንም መገንባት የጀመሩ ፎቆች ተጠናቀው በመስታወት ነፀብራቃቸው አይኔን በጨረር ሲፈታተኑት ነው። የመብራት መጥፋት ባይኖር ያለፈው ዓመት ከዚህኛው አመት ጋር የሚያያይዘው ጉዳይ ተበጥሶ ያስደነግጠን ነበር፡፡ አሉታዊ መደንገጥና አዎንታዊ መደንገጥ እንደተማቱብን አለን፡፡
“አዲስ ዓመት መግባቱን … እንደ መንግስት አዋጅ በሬዲዮ ልስማው?” ያለው በእውቀቱ ስዩም ነው። ግጥሙ ይኼንን መጣጥፌን አጠናቅቆ ይገልፀዋል። አጠናቆ መግለፅ … መቻልም አንድ ነገር ነው። ተጠናቀው መግለጽ የሚችሉት ለዓመቱ ውጭ የሚኖሩና ሳይለወጥ ተለውጫለሁ ከሚለው የቀን አቆጣጠር ዑደት ጋር ምንም ትስስር የሌላቸው ናቸው። መሆናቸው ነው የሚደንቀው። ቀኑ የማይገልፃቸው … አሻራ ቢስ ትውልዶች … የማይጨበጥ ተስፋን መቀባበል አቁመዋል፡፡ .. ባልታወቀ አቅጣጫ መንጎድ ቀጥለዋል፡፡ አመቱን ከመቀበል ውጭ አማራጭ የለኝም፤ ብቀበለውም - ብክደውም--- ባዳምጠውም - ባላዳምጠውም ራሱን በራሱ እየተረከ ይቀጥላል፡፡   

Read 2002 times