Monday, 19 September 2016 08:08

ከመጠምጠም መማር ይቅደም

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(6 votes)

    የዚህ ጽሑፍ መነሻ ሰበብ፤ ባለፈው ሣምንት የአዲስ አድማስ እትም  ‹‹የለውጥ ማዕበል ገፈት ቀማሽ ሳንሆን፤ ተቋዳሽ ለመሆን ….የመፍትሔው ጅምር ይሔውና›› በሚል ርዕስ አቶ ዮሐንስ ሰ. ያቀረቡት ዓይን ገላጭ ትንታኔ ነው፡፡ ፀሐፊው፤ ‹‹ጭራ እና ቀንዱ አልያዝ ያለ›› ብቻ ሳይሆን፤ ‹‹ጨርሶ መፍትሔ የሌለው መስሎ›› የታየውን ወቅታዊ የፖለቲካ ማዕበል ለመረዳትና መፍትሔ ለመፈለግ መነሻ የሚሆን ፍንጭ ሰጥተውናል፡፡ የእርሳቸውን ትንታኔ የተቀበልኩት ሌሎቹ ትንታኔዎች አላረካ ስላሉኝና ዝም ብሎ ‹‹ነገሩ ግራ አጋቢ ነው›› እያሉ ጩታ ከማከክ ይልቅ፤ ከዚህ የትንታኔ ጣቢያ የሚተላለፈውን ድምጽ ይበልጥ ለማጥራት በመሞከር ትርጉም ያለው የመረዳት ጥረት ለማድረግ ይቻላል በሚል እምነት ነው፡፡ አንድ ጥሩ የትንታኔ ፈለግ ሆኖ ጉዳዩን በደንብ ለመፈተሽ የሚያስችል ዕድል ሊሰጠን እንደሚችል በማሰብ ጭምር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ትንታኔው፤ ወቅታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ‹‹ይበልጥ እየተጋጋለ፣ እየተበላሸ እና አስፈሪ እየሆነ›› መምጣቱን ከመቀበል የሚነሳና መፍትሔ ለማስቀመጥ ጥረት ማድረግ እንዳለብን የሚያሳስብ ትንታኔ በመሆኑ ነው፡፡
ፀሐፊው እንዳሉት፤ ለችግሮች መፍትሔ የሚገኘው፤ ‹‹ዓይንን በመጨፈን ወይም እውነታን ለመካድ በመሞከር ሳይሆን›› በጉዳዩ ላይ በደንብ ተግቶ በማሰብ እና ውይይት ለማካሄድ ፈቃደኛ በመሆን ነው፡፡ ታዲያ አዲስ መንገድ ከፋች የሆነ ሐሳብ በሚያመነጭ ማንኛውም ሰው ትንታኔ ውስጥ ሊገኝ የሚችል አለመሟላት መኖሩ ወይም በቀዳሚው ሥራ ትከሻ ላይ ለቆመ ሰው በቀላሉ ሊታይ የሚችል ተራ ጉድለት ቢኖር እንኳን የትንታኔውን ማዕረግ ዝቅ አያደርገውም፡፡
ሆኖም፤ አቶ ዮሐንስ ሰ.፤ ተጨባጭ ሐቆችንና የታሪክ ማስረጃዎችን ድልዳል አድርጎ የተደራጀና  ግጥምጥምነት ያለው ትንታኔ ለማቅረብ ድንቅ ጥረት ማድረጋቸውን አይቻለሁ፡፡ ወትሮም፤ ሐሳቦች ከአንዱ ባህረ-ህሊና መንጭተው፤ በሌላ ባህረ-ህሊና ከሚገኙ የተለዩ ልምዶችና ገጠመኞች ጋር የመላፋት፣ የመካለስ፣ የመዳቀልና የመሞረድ ዕድል አግኝተው የሚያድጉ ‹‹ፍጡራን›› ናቸው፡፡ ሐሳቦች ከአንዱ አዕምሮ መንጭተው፤ ወደ ሌላ ሰው ህሊና ተሻግረው፤ ደግሞ እንደገና  ወደ ምንጫቸው በመመለስ ሂደት ይበልጥ ጎልብተውና ብቃታቸውን አዳብረው በመውጣት ‹‹ብጽዕና›› የሚቀዳጁ ናቸው። በዚህ መንገድ በመጓዝ፤ በሁሉም አውድ ጸንቶ የመቆም ፍቱን ባህርይና የድንጋጌ ማዕረግ ከማግኘት ይደርሳሉ፡፡
ፀሐፊው እንዳሉት፤ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይበልጥ እየተጋጋለ፣ እየተበላሸና አስፈሪ እየሆነ መምጣቱ›› ግልጽ ነው፡፡ ያም ሆኖ፤ በሁሉም ጎራ የተሰለፉት የፖለቲካ ኃይሎች ይህን እውነታ ላለመቀበል ዓይናቸውን መጨፈን እንደ መረጡ የጠቀሱት አቶ ዮሐንስ፤ በመንግስትም (በመንግስት ደጋፊ) ሆነ፤ በተቃውሞ ወገን ባሉት ሰዎች ዘንድ ያለውን የነገር አያያዝ ይኮንናሉ፡፡ ‹‹ከእውነታው ለመሸሽ ካልፈለግን በቀር፤ አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የፖለቲካ ማዕበል፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሲከሰት ከምናየው ወቅታዊ ማዕበል ጋር ተያያዥነት ያለው ነው›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ፤ ሆኖም መንግስት (ደጋፊዎቹ)፤ አሁን በሐገራችን የሚታየው ክስተት፤ የግብጽ፣ የየመንና የቱኒዚያ መንግስታትን አፈራርሶ ካለፈው የፖለቲካ ማዕበል ጋር ተያይዞ እንዲታይ አይፈልግም ይላሉ፡፡
መንግስት ሁከቱን ከ‹‹ጀስሚን አብዮት›› ጋር አያይዞ ለማየት ከፈቀደ፤ ከማይቀር አደጋ ጋር መጋፈጡን ስለሚሳየው እና ከሐቁ ጋር ዓይን ለዓይን መተያየት ስለማይፈልግ ዓይኑን እንደጨፈነ፤ ‹‹ተቃዋሚዎች›› በበኩላቸው፤ አሁን የሚታየው የህዝብ ንቅናቄ በሌሎች ሐገራት ከታየው የፖለቲካ ማዕበል የተለየ አለመሆኑን እና የመጨረሻው ፍጻሜውም ሐገራቱን ቀድሞም ከነበረው የባሰ ሁኔታ ውስጥ ጥሏቸው ከተጠናቀቀው የፖለቲካ ማዕበል ጋር አንድ ሆኖ እንዲታያቸው ስለማይፈልጉ፤ ይህም የህዝቡን ተሳትፎ ሊቀንስና ትግሉን ሊያዳክም ይችላል በሚል ሒሳብ እውነቱን ለመሸሽ መምረጣቸውን አንስተው ይወቅሳሉ - አቶ ዮሐንስ፡፡
‹‹ሁለቱም ወገኖች የማዕበሉን ምንነት አብጠርጥሮ አውቆ የሚያዛልቅ መፍትሔ ለማስቀመጥና በጥንቃቄ ለማሰብ አልፈለጉም›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ ሰ.፤ አንዱ በጥንቃቄ ለማሰብ ጥረት ማድረግ አመጽን እንደማባባስ፤ ሌላው ተቃውሞን እንደማዳከም ቆጥሮት፤ ሁለቱም ዓይናቸውን ጨፈነዋል ይላሉ፡፡ በሁለቱም ወገኖች የሚታየው አንድ የጋራ ነገር፤ ‹‹በአንዳች ተአምር ሁሉም ነገር ሰላም ይሆናል›› የሚል ድፍን ምኞት ይዞ ራስን የማታለል ፍላጎት ነው፡፡
በአቶ የሐንስ ሰ. ትንታኔ፤ አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ሁከት ከ‹‹ጀስሚን አብዮት›› ጋር የተያያዘ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ማዕበል ውጤት በመግለጽ፤ ይህን ሐሳባቸውን ለማስረዳት ቀልብ የሚገዛ ትንታኔ አቅርበዋል፡፡ በእርሳቸው አገላለጽ፤ በኢትዮጵያ የሚታየው ህዝባዊ ተቃውሞዎች መንስዔዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው መንስዔ፤ ‹‹ዓለም አቀፋዊ የሐሳብ የለውጥ ማዕበል›› ሲሆን፤ ሁለተኛው ‹‹የኑሮ ቅሬታን ተከትሎ የሚመጣ የተለመደ ተቃውሞና በደፈናው ለውጥ የመመኘት ስሜት ነው፡፡››
በኢትዮጵያ የሚታየው የተቃውሞ ማዕበል የሚገፋው በእነዚህ ሁለቱ ምክንያቶች መሆኑን የጠቀሱትና ‹‹በአንድ ሐገር የተነሱ ሐሳቦች በተፈጠሩበት ሐገር ድንበር ተወስነው አይቀሩም፡፡ እናም የጊዜ ጉዳይ እንጂ ወደ ሌላ ሐገር መዛመታቸው አይቀርም›› የሚሉት ፀሐፊ፤ የለውጥ ማዕበል ሲነሳ፤ ‹‹ማዕበሉን በጭፍን ተደብቆ ለማምለጥ ከመሞከር ወይም በጭፍን ከመንደርደር ይልቅ›› የእያንዳንዱን የለውጥ ማዕበል ምንነት አስቀድሞ ተገንዝቦ ዝግጅት በማድረግና የአገሬውን የኑሮ ችግር በውል በመረዳት እያንዳንዱን የለውጥ ማዕበል የመልካም ለውጥ አዋላጅ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የታሪካዊ  አጋጣሚዎችን ትክክለኛ ባህርይ በደንብ ተረድተው ለመጓዝ የሞከሩ ሐገሮች፤ አይቀሬ የታሪክ አጋጣሚዎችን የተሻለ ዕድል በሚያስገኝ የአስተዋይነት መንፈስ ለመጠቀም እንደቻሉ፤ በተቃራኒው ደግሞ ይህን በውል ተረድተው ለመንቀሳቀስ ያልቻሉ ህዝቦች በታሪክ ማዕበል ተጠልፈው ጎርፍ እንደሚገፋው የግንድ ጉማጅ ከወዲያ ወዲህ እየተላጉ በችግር ላይ ችግር እየጨመሩ የተጓዙ መሆናቸውንም አስረድተዋል። መያዣ-መጨበጫ ያጣንለትን ወይም ድፍን ቅል ሆኖ ያስቸገረን ነገር የሆነ መያዣ እንዲኖረው ለማድረግ ወይም ለመረዳት የሚያመች ቅርጽ እንዲይዝ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ በሐሳባቸው ልንስማማ ወይም ላንስማማ እንችላለን፡፡ ሆኖም ቢያንስ ‹‹ጉዳዩ ከዚህ ጋር የሚያያዝ አይደለም›› ብሎ ለመነጋገር የሚያስችል በር በመክፈታቸው ጥረታቸው ረብ የለሽ አይሆንም፡፡  
ሌሎች በሌላ መንገድ ሊሞክሩት ይችላሉ፡፡ እኔ ግን በእርሳቸው ጎዳና በመሄድ ተጨማሪ ሐሳብ ማቅረብና እና ጥያቄ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ጸሐፊው፤ የለውጥ ሐሳቦች በየጊዜው እንደሚመጡ በመጥቀስ ሳይወሰኑ፤ የለውጥ ሐሳቦች መነሻ ምን እንደሆነ ለማብራራት ቢሞክሩ፤ እንዲሁም ለትንታኔያቸው ማሄጃ ያደረጉት ‹‹ቲዮረቲካል ሞዴል›› ምን እንደሆነ በመግለጽ ቢነሱ ጥረታቸው የተሟላ ይሆን ነበር፡፡ ይህን የምለው ‹‹በአንድ ሐገር የተነሳ ሐሳብ ወደ ሌላ ሐገር የሚሻገረው ሰው የሚያስብ ፍጡር በመሆኑ ነው›› የሚለው ደካማ ቁርኝት ሆኖ ስለታየኝ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ፤ የእስካሁን አያያዛችን የኪሳራ ጎዳናን የሚከተል መሆኑን ከመጠቆምና በጥንቃቄ በማሰብ ሊመጣ ከሚችል አደጋ ለመዳን ይቻላል ከማለት አለፍ ብለው ሊያነሷቸው የሚችሏቸውን ነገሮች አልጠቆሙንም፡፡ ያቀረቡትን ሐሳብ ‹‹ጅምር መፍትሔ›› ማለት የፈለጉትም ለዚህ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሰጡንን ብቻ መሠረት አድርገን፣ በውይይት ጎዶሎውን መሙላት ይቻላል፡፡  
አቶ ዮሐንስ፤ የሐገራችን ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መንስዔዎች ሁለት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። አንደኛው፤ ዓለም አቀፍ የለውጥ ሐሳብ ማዕበል ሲሆን፤ ሁለተኛው የኑሮ ቅሬታ ወይም የተቃውሞ ስሜት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም የተለየች ሐገር አይደለችም፡፡ ስለዚህ አሁን በሐገራችን የሚታየው ሁኔታ ‹‹ከጀስሚን (የአበባ ዓይነት ነው) አብዮት›› ጋር የተያያዘ መነሻ ያለው ነው፡፡
የቱኒዚያ ህዝባዊ ቁጣ ወደ አብዮት ሲሸጋገር የተመለከቱ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች፤ በምሥራቅ አውሮፓ የጀመሩትን ዘዬ ተከትለው የቱኒዚያን አብዮት ‹‹የጀስሚን አብዮት›› አሉት፡፡ የቱኒዚያ አብዮት በሙስና የተዘፈቀውን፣ የዜጎችን ህይወት ማሻሻል አቅቶት በኑሮ ውድነት እንዲጠበሱ ያደረገውን የፕሬዚዳንት ቤን ዓሊን መንግስት፤ አጣድፎ ከመንበረ ስልጣኑ ሲፈነግለው የተመለከቱ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ህዝቦችም በአመጽ ተነሱ፡፡ ‹‹የጀስሚን አብዮት›› ሳይውል ሳያድር ወደ አረቦች ‹‹የጸደይ አብዮት›› ተሸጋገረ። አብዮቱ እንደ ሰደድ እሣት በግብጽ፣ በአልጀሪያ፣ በቱኒዚያ፣ በሶሪያ፣ በዮርዳኖስ፣ በባህሬን፣ በየመን ተዛመተ፡፡ ዓለም አቀፍ የለውጥ ሐሳብ ማዕበል ሆነ፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው፤ ‹‹አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ሁኔታ መንስዔ የዓለም አቀፍ የለውጥ ሐሳብ ማዕበል ነው›› ሲሉ፤ ‹‹የጀስሚን አብዮት›› ተጽዕኖ የፈጠረው ክስተት መሆኑን እያመለከቱ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማዕበሉ ኢትዮጵያ ለመድረስ ለምን አምስት ዓመታትን ፈጀ? የሚል ጥያቄ ማንሳትና መልስ መሻት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሜ ወደ ሁለተኛው መንስዔ አልፋለሁ፡፡ ሁለተኛውም ‹‹የኑሮ ቅሬታ ወይም የተቃውሞ ስሜት›› በሚል የተጠቀሰው ነጥብ ነው፡፡ ይህም ከመጀመሪያው ጋር ተጎዳኝቶ ሊታይ የሚችል ነጥብ ነው፡፡
የ‹‹ጀስሚን አብዮት››ን ክብሪት ሆኖ እንዲቀጣጠል ያደረግው የቱኒዚያ ህዝብ ቁጣ ነበር፡፡ የቱኒዚያ ህዝባዊ ቁጣ ቱግ ያለውም መሐመድ ቦዋዚዚ (Mohamed Bouazizi) የተባለ የ26 ዓመት ወጣት ፍራፍሬ አዟሪ፤ በማዕከላዊ ቱኒዚያ በምትገኝ ሲዲ ቦውዚድ (Sidi Bouzid ) በተባለች ከተማ ማዘጋጃ ቤት ፊት ለፊት ራሱን በእሣት አቃጥሎ በማጥፋቱ ነበር፡፡ ይህ ወጣት ፍራፍሬ እያዞረ ቤተሰቡን የሚደግፍ ነበር፡፡ የከተማዋ ፖሊስ አባል የሆኑ ሰዎች በተደጋጋሚ ጉቦ እንዲሰጣቸው ይጠይቁት ነበር፡፡ ይባስ ብለው ዕቃውን ወረሱት። በዚህ ግፍ የተፈጠረበትን ቁጣ ለመግለጽ ማዘጋጃ ቤቱ በር ፊት ለፊት ራሱን አቃጥሎ ሲሞት፤ መሐመድ ቦዋዚዝ የቱኒዚያ ዜጎች የፍትህ እጦትና የኢኮኖሚ ቀንበር ወይም የመከራ ኑሮ  ወካይ ገጸ ባህርይ ሆኖ ታየ፡፡ በሥራ አጥነት፣ በድህነትና  በፖለቲካ መብት ማጣት የተማረሩ የቱኒዚያ ዜጎች ግንፍል ብለው ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ። አመጹ በፍጥነት ወደ ዋና ከተማው ቱኒዝ ተሻገረ። ህዝባዊ ቁጣው ቦዋዚዝ የሞተ ዕለት (December, 17, 2010) ተቀሰቀሰ፡፡ አዎ፤ የቱኒዚያ ቁጣ ማንም ደፍሮ ከፊቱ ለመቆም የማይችል እሣተ ገሞራ ነበር፡፡ ይህ እሣተ ገሞራ በፈነዳ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሐገሪቱን ፕሬዚዳንት አጣድፎና አደናብሮ ከሥልጣነ - መንበራቸው መፈንቀል የቻለ መሬት አንቀጥቅጥ ህዝባዊ ቁጣ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ቤን ዓሊ ሸሽተው ሳዑዲ ገቡ። ሆኖም ዛሬ የመንግስት ሐብትን በመመዝበር ወንጀል በፍርድ ቤት ተከሰው 35 ዓመት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ቤን ዓሊ በሐገር ቤትና በውጭ በርካታ የግል ንግድ ተቋም ተመስርተው ሐገሪቱን ሲበዘብዙ የኖሩ ሰው ነበሩ። ስለዚህ የ‹‹ጀስሚን አብዮት›› መነሻ ድህነት ወይም የህዝብ የኑሮ ቅሬታ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
እንደ አውሮጳ አቆጣጠር ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ቱኒዚያን ለሩብ ምዕተ ዓመት የገዙት ፕሬዚዳንት ዚኔ ኤል አቢዲኔ ቤን ዓሊ (Zine El Abidine Ben Ali) በታህሳስ ወር በተነሳ ህዝባዊ ቁጣ ተንጠው፤ በጥር ወር (January, 14, 2011) ከሥልጣናቸው ተጣድፈው ወረዱ። ‹‹የጀስሚን አብዮት›› እሣተ ገሞራ የፖለቲካ ምህዳሩን በኃይል ሲንጠው ፕሬዚዳንት ቤን ዓሊ ተሸቀንጥረው በመነሳት ሥልጣን ቢለቁም፤ የአብዮቱ ሰደድ እሣት ጋብ ግን ሊል አልቻለም፡፡ ጋብ በማለት ፋንታ ይበልጥ እየጋመ ና እየደመቀ እየተቀጣጠለ፣ የስርዓቱን ቅምጥል ልሂቃን ጠራርጎ ሳይጨርስ የማይገታ ሆኖ ተቀጣጠለ። ‹‹የጀስሚን አብዮት›› ወላፈን ቱኒዚያን በቅጽበት መድምዶ ከበላ በኋላ፤ እንደ ሰደድ እሣት እየነደደ የመካከለኛው ምሥራቅ ሐገራትን ያግለበልባቸው ገባ፡፡ ‹‹የጀስሚን አብዮት›› እሣት በቅጽበት ወደ ግብጽ ተሻገረ፡፡ እዚያም አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ለሰላሣ ዓመታት ግብጽን አንቀጥቅጦ በገዛው በሆስኒ ሞባራክ መንግስት ዙሪያ ይንቀለቀል ጀመረ፡፡ የግብጽ ሕዝባዊ አመጽ ተቀስቅሶ  አንድ ወር እንኳን ሳይደፍን ሆስኒ ሞባራክ በየካቲት ወር (Febryray, 11, 2011)ከመንበረ ስልጣናቸው ተፈነገሉ፡፡ ‹‹የጸደይ አብዮት›› ሊቢያን፣ ሶሪያንና የመንን እንዳይሆኑ አድርጎ ጣላቸው፡፡
የሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ፤ ‹‹በጀስሚን አብዮት›› እና ‹‹በአረብ ጸደይ›› (Arab Spring)  አብዮት እየተናጡ ሳለ ወይም ሊናጡ እየተዘጋጁ ሳሉ፤ ሁለት ምሁራን በመተባበር የጻፉትን አንድ መጽሐፍ አጠናቅቀው መቅድም እየጻፉ ነበር፡፡ መቅድሙን ሲጽፉ ሳለ የሊቢያ፣ የባህሬን፣ የሶሪያና የየመን አገዛዞች ዕጣ -ፈንታ ገና አልተወሰንም ነበር፡፡ አሴሞግሉ (Daron Acemoglu) እና ሮቢንሰን (James A Robinson)  የተባሉት እነዚህ ምሁራን ‹‹Why Nations Fail›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት ድንቅ መጽሐፍ፤ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ሐገራት የህዝብ ቅሬታና ቁጣ ዋነኛ ምንጭ ድህነት መሆኑን ይገልጣሉ፡፡ የግብጽ ህዝብ ቁጣ እንዲገነፍል ያደረገው፤ ከድህነት እሣት ላይ ተጥዶ ሲንተከተክ የነበረው ዜጋ ቅሬታ አድሮበት አጋጣሚው ሲገኝ ገንፍሎ ፈሰሰ፡፡
ስለዚህ የአቶ ዮሐንስ ሰ. ትንታኔ የኑሮ ቅሬታና  የተቃውሞ ስሜት (ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ ሙስና) እና ዓለም አቀፍ የለውጥ ማዕበል የኢትዮጵያን ሁኔታ ሊገልጹት ይችላሉ፡፡ ሆኖም በዚህ ትንታኔ መካተት ያለባቸው የኢትዮጵያ ልዩ ሁኔታዎች መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ በለውጥ ማዕበል ወይም በ‹‹ጀስሚን አብዮት›› የተቀሰቀሱት ህዝባዊ አመጾች ሁሉም ህዝቦች ወይም የህብረተሰብ ክፍሎች (ነባር ቅራኔአቸውን ጭምር በመተው) በአንድ ዓላማ የመሰለፍ አዝማሚያ የታየባቸው ናቸው፡፡ ለምሣሌ፤ በግብጽ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የዘመናት ቁርሾአቸውን ትተው ለጋራ ዓላማ ለመሰለፍ ችለዋል፡፡ በዚህ መስፈርት የእኛ ሐገር ህዝባዊ ተቃውሞ የተለየ ባህርይ አለው፡፡ የእኛ ዘረኝነትን የተላበሰ የቅስቀሳ መልዕክቶች የሚሰሙበት ተቃውሞ ጭምር ነው፡፡ ከፋም - ለማም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በሚንቀሳቀሱበት የፖለቲካ ምህዳር የታየ ተቃውሞ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች እንደ ልዩ ባህርይ ሊነሱ ና በትንታኔው ሊካተቱ ይገባል፡፡ በመጨረሻም፤ የኢትዮጵያ ሁኔታ ‹‹የጀስሚን አብዮት›› ተወላጅ ነው ማለት የሚቻል ከሆነ፤ ‹‹የጀስሚን አብዮት›› በሌሎቹ ሐገራት ካስከተለው ቀውስ በተጨማሪ፤ በእኛ ዘንድ የጎሳ መስመርን የተከተለ ግጭት የመፈጠር ዕድል በመኖሩ፤ ሂደቱን ከሁሉም በላቀ ሁኔታ በጣም በጥንቃቄ መያዝ እንደሚኖርብን መረዳት ይቻላል፡፡ ሳምንት ‹‹Why Nations Fail›› በሚል መጽሐፍ የተጠቀሱ ሐሳቦችን መነሻ አድርጌ ሌላ ጨዋታ ይዤ እመጣለሁ፡፡  በተረፈ፤ በደፈናው ለውጥን መመኘት ብቻ መልካም ውጤትን እንደማያስከትልና ከእያንዳንዱ የለውጥ ማዕበል አትራፊ ለመሆን አስተዋይነት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። ማሰብና መመርመር እንጂ በጭፍን መንደርደር እንደማያዋጣ የሚናገሩት አቶ ዮሐንስ ሰ.፤ በግራ በቀኝ የተሰለፉ ወገኖች (ገዢውም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች) ችግሩን በድፍረት በመረዳት፤ ‹‹የለውጥ ማዕበል ተቋዳሽ እንጂ ገፈት ቀማሽ ላለመሆን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡››

Read 4342 times