Monday, 19 September 2016 08:15

ያገር ልጅ

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(7 votes)

    በምን አይነት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነው አብዛኛው ሕዝብ ኑሮውን የሚገፋው? የተጎሳቀሉ መኖሪያ መንደሮች ቤቶችስ እንዴት ያሉ ናቸው? ነጮች በበላይነት በሚመሩት ማህበረሰብ ውስጥ ለጥቁር ሕዝቦች የሚበጁ ምን እድሎች አሉ? ሪቻርድ ራይት ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠበት አንጀት የሚበላ ረዥም ልቦለዱ አርእስት Native Son ይሰኛል - ‹‹ያገር ልጅ››፡፡ በመጽሀፉ ታሪክ ውስጥ፤ ቢገር ቶማስ የስራ ቀጣሪውን የሜሪ ዳልተንን ሴት ልጅ ይገድላል፡፡ ግድያውን በእጮኛዋ ላይ ለማላከክ ቢሞክርም ወንጀለኛነቱ ይደረስበታል፡፡ ቺካጎ ወስጥ በሚገኝ ››ቆሼ›› ሰፈር ውስጥ ለመሸሸግ ጥረት ባደረገበት ጊዜም፤ ወንጀሉን ለመሸፋፈን በወሰደው እርምጃ፡ የአንድ ሌላ ሰው ህይወት በእጁ ይጠፋል፡፡ ጉዳዩ ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞን የፈጠረ መነጋገሪያ ሆኖ ይሰነብትና ቢገር ይያዛል፡፡ ለፍርድ ቀርቦ ‹‹ይሙት በቃ›› ሲፈረድበት፤ ጠበቃው በበኩሉ፤ ቢገርን ለዚህ መሰል ቁጣ ቀስቃሽ የወንጀል ድርጊት ያበቃው፡ የኖረበት ማህበረሰብ፡ የተጠያቂነቱን ሰፊ ድርሻ እንደሚወስድ ለማሳየት ጥረት አድርጓል፡፡
የመጽሐፉ መሪ ገጸ ባህሪ ሆኖ የተሳለው የ20 አመቱ ወጣት ቢገር፣ ያደገበትን መኖሪያ ቤት ምስል ይከስትልን ዘንድ፤ በዚህ አሳዛኝ ረዥም ልቦለድ ታሪክ የመጀመሪያ ምእራፍ ላይ የቀረበውን ትረካ እንዲህ ተርጉመነዋል፡፡ እነሆ . . .

      አአአአአአአአአአአአአምጣ!
የሰአት ደወል ፀጥታ በዋጣት ጠባቧ ጨለማ ክፍል ውስጥ አንቃጨለ፡፡ የአሮጌ አልጋ ሲጥ ሲጥታ ተከተለው፡፡ ከዚያም የመታከት ቃና ያዘለው የእናትየዋ ድምፅ አምባረቀ፡- ‹‹አንተ ቢገር፡ ይህን ቃጭልህን አጥፋ!››
በኩርፊያ ግልፍ ያለው መነጫነጭ ከወላለቁ የአልጋ ብረቶች መንገጫገጭ ጋር ተቀይጦ ተሰማ። በባዶ እግሮቹ፡ በተሰነጣጠቀው የሳንቃ ወለል ላይ ተንጠራርቶ ደወሉን ዝም አሰኘው፡፡
‹‹መብራቱን እማታበራው ቢገር?››
‹‹እ...ሺ›› እንቅልፍ ባልጠገበ አንደበቱ አጉረመረመ፡፡
መብራቱ ሲበራ፤በሁለቱ አሮጌ የብረት አልጋዎች መካከል ባለችው ስንዝር ታህል ቦታ ላይ፤ በአይበሉባው አይኖቹን እያሸ የቆመው ጥቁር ልጅ ታየ፡፡ ከበስተቀኙ ባለው አልጋ የተኛችው እናቱ ትእዛዟን ቀጠለች፡፡ ‹‹በዲ፡ እኮ አንተም ብድግ በል! ዛሬውኑ አጥቤ እማስረክበው ቅርጫት ሙሉ ልብስ ነው የተቀበልኩት፡፡ ማናችሁም ወደዚች ቤት ዝር እንድትሉ አልፈልግም!›› አለች፡፡ ሌላኛው ልጅም ከአልጋው ላይ ተንከባልሎ ወርዶ ቆመ። እናቲቱ በሌሊት ልብሷ ሆና፡- ‹‹በሉ ፊታችሁን አዙሩና ልብሴን ልቀይር!›› አለቻቸው፡፡ ሁለቱ ልጆች ፊታቸውን አዙረው ቆመው፣ ወደ ጠባቧ ቤት የግድግዳ ጥጋ ጥጎች ማየት ጀመሩ፡፡ የሌሊት ልብሷን አውልቃ ጥላ፡ ተኝታ ወደነበረችበት አልጋ ዞር ብላ ደግሞ፡- ‹‹ቬራ፡ በይ አንቺም ቶሎ ተነሽ!›› አለች፡፡
‹‹ስንት ሰአት ሆኖ ነው እማ?›› ትንሽየዋ ልጅ ከተጠቀለለችበት ድሪቶ አልጋ ልብስ ውስጥ ሆና በታፈነ ድምጽ ጠየቀች፡፡ ‹‹ተነሺ ብዬሻለሁ እንግዲህ!›› ተቆጣቻት፡፡ ‹‹እ...ሺ እማ›› ጠይሟ ሴት ልጅ ስቶኪንግዋን ለመልበስ ጎትታ አወጣች፡፡ ዘወትር፡ ወንዶቹ ልጆች እናትና ታናሽ እህታቸውን ከእፍረት ለመንከባከብ ሲሉ፤ አሁን ፊታቸውን አዙረው እንደሚቆሙት፤ እነርሱም ልብሳቸውን ሲለብሱ፤ እናቲቱና እህታቸው በተራቸው ፊታቸውን ያዞሩላቸዋል፡፡
ድንገት የተለጣጠፈውን ግድግዳ ሰንጥቆ በገባ የፀሀይ ጨረር የተነሳ፡ ጠባቧ ክፍል ባንድ ጊዜ ቀውጢ ሆነች፡፡ ከዚያ ደግሞ ፍጹም ፀጥ እረጭ አለች!! የሁሉም ትኩረት በግድግዳው በኩል አልፎ በገባው ነገር ላይ ሆነ፡፡ እናትየውና ትንሷ ልጅ ልብሳቸውን እንደታቀፉ በፍርሀት ተውጠው፡ ሁለቱ ወንዶች ልጆችም ትንፋሻቸውን ውጠው፡ የመተፋፈሩም ጉዳይ ላፍታ ተዘንግቶ፤ ቤተሰቡ ሁሉ ቀጥሎ የሚሆነውን ነገር በመጠባበቅ  አይኖቻቸውን በወለሉ ዙሪያ ማንከራተት ያዙ፡፡
‹‹ደሞ ዛሬም መጣ!›› እናቲቱ በፍርሀት በሚንቀጠቀጡ እጆቿ እየጠቆመች ጮኸች! ‹‹ወዴት ሄደ?›› ቢገር ጠየቀ፡፡ ‹‹እኔጃ እኔ አላየሁትም!›› በዲ መለሰ፡፡ ‹‹ከበርሜሉ ስር ነው የተደበቀው መሰለኝ!›› ቬራ በቤቱ አንድ ጥግ ግድግዳውን የሙጢኝ ብላ በፍርሀት ተንዘፈዘፈች፡፡ ‹‹ነይ አንቺ እዚህ አልጋው ላይ ውጪ! ምን እዛ ወስዶ ወተፈሽ!›› እናትየዋ አፈጠጠችባት፡፡ መልበስ የጀመረችውን ስቶኪንግ ጫፍ በሁለት እጆቿ እንቅ አድርጋ ይዛ፣ በጭንቀት ወደ ጉልበቶቿ የምትጎትተው ቬራ፤ እግሬ አውጪኝ ብላ ዘልላ አልጋው ላይ ስትወጣ፤አይኖቿ በፍርሀት ተጎልጉለው የወጡ የሚመስሉት እናቷ በእቅፏ ሙሉ ተቀበለቻትና፤ አንዳቸው በሌላቸው አንገት ዙሪያ ክንዶቻቸውን አጣምረው ጥብቅብቅ ብለው ተቃቀፉ፡፡
ቢገር፡ ቁርጥ ቁርጥ ከሚሉ ትንፋሾች በቀር ምንም በማይሰማበት፤ ውጥረት በነገሰበት የቤቱ ዙሪያ አይኖቹን ወዲህ ወዲያ እያዟዟረ ሲፈልግ ቆይቶ፤ ከምድጃው በላይ ሁለት የብረት መጥበሻ ሰሀኖች አውርዶ አንዱን ለታናሽ ወንድሙ ሰጠውና አንሾካሾከለት፡- ‹‹በዲ፤ አንተ ያንን ሳጥን ውሰድና የጎሬውን መውጫ ድፈነው፡ማምለጫ ስለማይኖረው እንይዘዋለን›› አለው፡፡ በዲ፡ ከራሱ ክንድ የሚበልጥ ርዝመት ያለውን የመጥበሻ እጀታ አጥብቆ እንደያዘ፤ የጉድጓዱን አፍ በሳጥኑ ዘጋው፡፡ ያን ጊዜ ቢገር በጣቶቹ ጫፍ በቀስታ እየተራመደ ሄዶ፣ በርሜሉን በእግሩ ገፋ ሲያደርገው፤ ትልቅ ጥቁር አይጥ ከተደበቀበት ቱር ብሎ ወጥቶ ለማምለጥ ሲሞክር ጉድጓዱ ዝግ ሆነበት፡፡ በግድግዳው ላይ ተጠማዝዞ ሲታከክ፤ ቢገር ባለ በሌለ ሃይሉ በመጥበሻው ጀርባ መታው። አይጡ አቅም አንሶት ሲቃትት፡ ወንድማማቾቹ ደጋግመው ቀጠቀጡትና፤ አንዳች ሰቅጣጭ ድምጽ አሰምቶ፡ የቤቱ መሀል ወለል ላይ ወርዶ ተዘረረ፡፡እናቲቱ ራሷን ድሪቶው ብርድ ልብስ ውስጥ ቀብራ እያለቀሰች፤‹‹አምላኬ ሆይ ይቅር በለን!›› አለች፡፡ ሴቷ ልጅ፡- ‹‹አታልቅሺ እማ፤ በቃ ሞቷልኮ!›› ብላ አጽናናቻት፡፡ ወንዶቹ ልጆች፡በጣሉት የአይጥ ሬሳ ግዳይ ስር ቆመው እንደማቅራራት ሲከጅላቸው፤ ቬራ የምትገባበት ጠፍቷት ‹‹ቢገር፡ እባክህን ወደ ውጪ አውጥተህ ጣለው!›› ብላ ተማፀነች፡፡ እናቲቱም ወስደው እንዲጥሉ አዘዘቻቸውና፤ምግብ ለማብሰል ተሰናዳች፡፡
ቢገር፡ የገደለውን አይጥ ጅራቱን ይዞ እያወዛወዘ፤ ቬራን በማስፈራራት ለመሳቅ ሲከጅል፤ ቬራ በከፍተኛ ድንጋጤ ጩኸቷን አቅልጣው ስትዘል፤ የአጭሩ ጣራ ማገር አናቷን መትቷት ተዝለፍልፋ ወደቀችና ራሷን ሳተች፡፡ ከእናቱ ጋ ሊፋጁ ደረሱ። በንዴት ጦፋ የቁጣዋን መአት አወረደችበት። ‹‹አንዳንድ ጊዜ ትልቅዬ ጅል ትሆንብኛለህ!›› አለችው፡፡ ‹‹ስለሞተ አትፈራም ብዬኮ ነው እማ›› አለ ቢገር፡፡ ‹‹ደሞ ይህን አጉል ጠባይ የምትቀስመው ከነዚያ አብረኻቸው ከምትውላቸው ሥራ ፈት ጓደኞችህ ነው! ምናለች በለኝ ደሞ፡ ይኸ ጋጠ ወጥ ባህሪህ አንድ ቀን መቼም ከማትወጣው መቀመቅ ውስጥ ይዘፍቅሀል!›› አለችው፡፡ ‹‹ ተይ’ንጂ እማ፡ በነገ ህይወቴ ላይማ አታሟርቺብኝ!›› አላት ቅር እያለው። ‹‹ስጋቴ ካጥወለወለህ ተነስቶ ጥርግ ማለት ነዋ! በዚህ እድሜህ ገቢ አምጥተህ፣ እኛን እንደመደገፍ ይኸው የሸማቾች የቀለብ እዳ እላያችን ላይ ሲያናጥር ተጎልተህ ታየናለህ! መኖርህ ምን ጠቀመን...አንተም ባትኖር ይህንኑ በመከራ የምንገፋውን ህይወት እንኖረዋለን! ሥራ አጥ! ገልቱ!›› ብላ ስታበቃ በሀዘን ኩርምትምት ብላ አንገቷን ደፍታ፣ ‹‹አምላኬ ሆይ፤ እስከ መቼ ነው በእንዲህ ያለ ጣርና አሳር መከራ መኖርን የምቀጥለው? እባክህን ሞቴን አፍጥንልኝ!›› እያለች በምሬት ተንሰቅስቃ አነባች፡፡
ይህን መሰሉን የቤተሰቡን ሲቃ ሰቆቃ ማሰብ ሲጀምር ብቻውን ሆኖ አምርሮ ያለቅሳል፡፡ በእነርሱ ፊት ግን ልፍስፍስነቱን ማሳየት አይፈልግም፡፡ ለብቻው ሲሆን ነው የሚኖሩትን በስቃይ ጽልመት የታነቀ የተዋረደ የህይወት ገመናቸውን በማብሰልሰል የሚጠመደው፡፡ታዲያ ግን ሀሳቡን ከፈቀደለት ሄዶ ሄዶ የሚደርስበትን ድምዳሜ ያውቀዋል፡፡ አንድ ቀን ራሱን አጥፍቶ ስለመገላገል! ወይም ደግሞ አንድ ቀን አንድ የሆነ ሰውን ስለ መግደል! ሹክ ይለዋል አእምሮው፡፡
ቬራም ስትነቃ፡- ‹‹ስማ፡ ልንገርህ፡ አንተ የኔ ወንድም ሆነህ መፈጠርህን ሳስብ ቅጥል! እርር! ድብን! ነው እምለው እሺ!›› ስትል ጨመረችለት፡፡ ቢገር ግን ዝም አለ፡፡
የአይጡ ሬሳ በጋዜጣ ተጠቅልሎ ወደ ውጪ ተወስዶ ከተጣለና ነገሮች ከተረጋጉ በኋላም፤ እናትየው ምግብ እያበሰለች በምታንጎራጉረው ዜማም ደስተኛ አልነበረም፤ ቢገር፡፡ ሁልጊዜም ሲሰማው ምቾት እሚነሳና እሚያስተክዝ፡እሚጎረብጠው ነገር አለው...
‹‹ህይወት እንደ የተራራ ላይ ሀዲድ ነው
ብርቱው ጠይብ እንደሰራው በተአምር፤
ሳንሰለች እየቧጠጥን እምንወጣው
ተግተን ከልደት እስከ መቃብር...››
የሚል ነው የዘፈኑ ግጥም፡፡ እንደ ምንም ታግሶ ተቀመጠ፡፡ ከምግብ ማብሰሉ መጠናቀቅ ጋር  እንጉርጉሮዋም አብሮ ቆመለትና እረፍት አገኘ፡፡ ቤተሰቡም በማእዱ ዙሪያ ተሰባሰቡ፡፡
‹‹ጌታ ሆይ፡ በፊታችን ስላዘጋጀህልን ገበታ እናመሰግንሀለን፤ ለሰውነታችን በረከት ይሆንልን ዘንድ ያንተ ፈቃድ ይሁን፤ አሜን፡፡›› በዚያው ጸሎት ባደረሰችበት የድምጽ ለዛ፡ አይኗን ከብለል አድርጋ፡- ‹‹ስለዚህ ከዚህም በተሻለ ማልደህ መነሳትን መለማመድ እንደሚኖርብህ ታውቃለህ፤ ሥራ ያለው ሰው ሆነህ ለመኖር፡፡›› አለች እናቲቱ፡፡ ቢገር ምንም ምላሽ አልሰጠም፤ ፊቱንም አላዞረም፡፡
‹‹ትንሽ ቡና ላፍላልሽ እማ?›› ቬራ ጠየቀች፡፡
‹‹ጥሩ፡፡ እ...ሥራ ልጀምር ነው ያልከኝ መስሎኝ ነበር ልበል ቢገር?›› አለች እናቲቱ፡፡
‹‹ትናንት ማታ’ኮ ሁሉንም ነገር ዘርዝሬ ነግሬሻለሁ እማ፤ ስንት ጊዜ ነው እምትጠይቂኝ?››
‹‹እና በትእቢት መልስ አትስጣታ! አንድ ጥያቄ ነው የጠየቀችህ በቃ!›› አለች ቬራ፡፡
‹‹ማቃጥርሽን ተዪና ዳቦውን አቀብያት!››
‹‹ሚስተር ዳልተን ዛሬ በአስራ አንድ ሰአት ተኩል መጥተህ አግኘኝ እንዳለህ ታውቃለህ?!›› አለችው እናቲቱ ፡፡
‹‹ይሄንንም ቢሆን’ኮ ዛሬ ከነጋ እንኳ አስር ጊዜ ያህል ጠይቀሽኝ፡ አዎን ብዬሻለሁ እማ፡፡››
‹‹እንዳትዘነጋው ብዬ ነዋ ልጄ!››
‹‹እናም አውቀህ ለመርሳት ከፈለግክ ልትረሳው ስለምትችልም ጭምር!››  አለችው ቬራ፡፡
‹‹አቦ በቃ ተፋቱታ!›› በዲ ተቆረቆረለት ‹‹ስራ ሊጀምር እንደሆነ ነግሯችኋል’ኮ በቃ!››
‹‹ተዋቸው በዲ፡ ዝም በላቸው፡፡›› አለው ቢገር።
‹‹አንተ አፍህን ዝጋ በዲ! አለያ ተነስ ውጣ!›› አለች እናቲቱ ‹‹ደሞ አንተን እንደሱ የማንቆለባብሽበት ጎን የለኝም! ያለው አንድ ጅላጅል ልጅ ይበቃል ለቤቱ!››
‹‹አረ እንደዛ አትበዪ እማ!›› በዲ ቅር እያለው በድፍረት መለሰላት፡፡
‹‹እና አታየውም’ንዴ ወንድምህ’ኮ ተረጋግቶ ተወዝፏል! ከቶም የሚሄድበት ያለውም ሆነ ስራ ለመጀመር የተነሳ አይመስልም’ኮ ሁናቴው ሁሉ!››
‹‹እና ምን ማድረግ ነበረብኝ? መጮህ?›› ቢገር  ጠየቀ፡፡
‹‹እንዴ! አንተ ቢገር!›› አለች እህቱ፡፡
‹‹አንቺ ይሄን አቧሬ አፍሽን አትክፈቺ ብዬሻለሁ ዋ!›› ጮኸባት፡፡
‹‹እውነት ተሳክቶልህ ስራውን ከጀመርክ...›› እናቲቱ ዳቦውን በቢላ እየገመሰች ቅስስ ባለ አሳዛኝ ድምጽ ተናገረች፡- ‹‹ከዚህ ሻል ያለ የመኖሪያ ቤት ይኖረን ይሆናል ልጆቼ፡፡ እናንተም ዧ ብላችሁ ሳትሳቀቁ እምትንከላወሱበት ስርፋ ታገኙ ይሆናል። እንዲህ እንደ እርያ መንጋ ከመታጎር ትገላገሉም ይሆናል፡፡››
‹‹ምን ዋጋ አለው፤ቢገር እንዲህ ያለውን ሀሳብ አልፈጠረበትማ!›› ሹክ አለች ቬራ፡፡
‹‹ኦ! አምላኬ ሆይ! ቢቻል ሁላችሁም ሥጋዬን  ብትበሉትም እንኳ ቅር አይለኝም!›› አለ ቢገር፡፡
እናትየው የእሱን ንግግር እንዳልሰማች ሆና ልትቀጥል ስትል፤ ቬራ አሁንም ወቀሰችው፡- ‹‹እማ እያወራች ያለችው ላንተ ጥሩ በማሰብ መሰለኝ’ኮ ቢገር!››
‹‹እና ምን ይጠበስ?!››
‹‹ተው እንዲህ መረን አትውጣ ቢገር!›› እናቲቱ መሀላቸው ገባች፡፡
‹‹ እያየሽው፤‹ መስሚያዬ ጥጥ ነው› እያለ’ኮ ነው  እማ!››
ቢገር፡ በዱልዱም መዳፉ የጠረጴዛውን ጫፍ ተደግፎ፡ የወንድሙን ሰሀን ገልብጦ ቢላ ሲያነሳ፤ ቬራ በፍርሀት ራደች፡፡ ‹‹ነገርኳችሁኮ! ከቻላችሁ እንኩ ይኸው ስጋዬን ቆራርጡና ብሉት!›› አላቸው።
ማንም መልስ አልሰጠውም፡፡
ቤተሰቡ ሁሉ፡ ዛሬ ከሰአት በኋላ ስራ ለመጀመር በተያዘለት ቀጠሮ መሳካት ጉዳይ በስጋት መጠመዳቸውን አጤነ፡፡ እናም በዚህ ሁኔታ አብሯቸው ተቀምጦ ሊመገብ እንደማይችል ታወቀው፡፡ እናቱ:- ‹‹ይኸው ዛሬ በቤቱ ያለን ቁርስ ለየፋንታችን የሚደርሰን ይኸው ብቻ ነው!›› ብላ አራት ቦታ ከተካፈለው ቁርስ የእርሱን ድርሻ በሰሀን ስትሰጠው፤ ተቀበላትና ሱሪ ኪሱ ውስጥ ከትቶ፤ ኩባያውን አንስቶ በአንድ ትንፋሽ ዥው አርጎ ጨለጠና፤ ጃኬቱን እየደረበ፡ የጠባቧን መኖሪያ ቤታቸውን በር ከፈተ፡፡
‹‹ሰማህ ልጄ ቢገር፡ ስራውን ካልጀመርክ ምን እንደሚጠብቀን ታውቃለህ አይደል? የሸማቾች የቀለብ እዳ ስለተቆለለብን፡ ያለብንን ውዝፍ ሂሳብ ካልከፈልን በቀር ዳግመኛ ድምቡሎ ዱቤ የሚባል አይሰጡንም! በቤታችን ደግሞ ይኸው እንትፍታህል ምግብ የለንም! እየቆጠብን የከረምንባት አስቤዛም ተሟጥጣ አልቃለች! እና እንግዲህ ምናምኒት የሚቀመስ ...! ››
‹‹ኡ...! ነገርኩሽ’ኮ እማ!
ስራ ለመጀመር ሁልጊዜም ዝግጁ ነኝ--እእእ!
ብቻ ዋናው ነገር ስራው መገኘቱ ነው እንጂ!!!››
 በንዴት ጮኾ ተናግሮ ወጣና፣ በሩን በሀይል ጠረቀመው፡፡

ምንጭ - Modern Black Stories
From - Native Son
by - Richard Wright

Read 1061 times