Monday, 19 September 2016 08:17

ባሕልና የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ

Written by  በሚፍታ ዘለቀ (የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
Rate this item
(6 votes)

 “---ምነው ዩኒቨርስቲዎች በየክልሉ እንደ አሸን ሲፈሉ፣ አንድ ሁለት ሥነ-ጥበብን የሚያስተምር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ብርቅ ሆነብን? የሥነ-ጥበብ ምርምር የሚያደርግ ተቋም ይነሰን? ኧረ እንደው ቢያንስ ሁለት ሶስት ክልሎች የሥነ-ጥበብ ሙዚየም መገንባት ተስኗቸው ነው በጭርታ የተኮራመቱት?----”

     የዚህ ዓምድ ትኩረት ሥነ-ጥበብ፡ በዋነኝነትም የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ነው። በተለይም ዘመንኛው(Contemporary) የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ላይ አጽንኦት በመስጠት ወቅታዊና በመታየት ላይ ያሉ ትርዒቶችን ይዳስሳል፡ ገለጻ ያቀርባል፡ ያትታል፡ ይመረምራል፡ ሂስ ያቀርባል። ግለሰቡን ሳይሆን ስራውን በመተቸት የሂስ ባሕልን ለማዳበር ይጥራል፡፡ የዓምደኛውን እይታ መሬት በያዙና ሚዛን በሚደፉ አመክንዮች በማስደገፍ ግለሰብ አንባቢ ስለ ሥነ-ጥበብና ስለ ኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ግንዛቤ እንዲጨብጥ፡ የዕይታ ባሕሉ(Visual Culture) እንዲዳብር፡ የሥነ-ጥበብ አድናቆቱ ከፍ እንዲል፡ ሥነ-ጥበብን የሕይወት ዘዬው(Life Style) አድርጎ እንዲወስደው መንገድ ለመክፈት ይጥራል። በማኅበረሰብና በሃገር ደረጃም ልክ እንደ ኤኮኖሚያዊ፡ ፖለቲካዊ፡ ማኅበራዊ፡ ባሕላዊና ትውፊታዊ እንዲሁም ታሪካዊ  እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሥነ-ጥበብን የሰፊው የሕይወት መር (Mainstream) አካል እንዲሆን ይተጋል።
                       

         (ክፍል ሁለት)
የዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል የባህል ትርጓሜዎችንና ተግባራት፣ የባህል ምርት ምንነትና የኢፌዲሪ የባህል ፖሊስ ከኪነ-ጥበብና በተለይም ከኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ አንፃር ሲታይ ምን አይነት ገፅታዎችና ድክመቶች እንዳሉት ለመዳሰስ ሞክሯል። በዚህ በሁለተኛው ክፍል የባህል ፖሊሲያችን የባህል ምርትን ከመከሰት አንፃር እንዲሁም የመንግስታችን የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ለኪነ-ጥበብና ለሥነ-ጥበብ ያለውን ቦታ በመፈተሽ እንቀጥላለን፡፡ መንደርደሪያችንም ባህልና ልማት ይሆናል፡፡
‘መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር እውን ማድረግ፣ በምግብ ራስን መቻል፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ ማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ መሰረት ልማቶችን መዘርጋት፣ ስራ አጥነትን መቀነስ፣ ባለ ሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገብ…’ የመሳሰሉት ከሀገራችን የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች የሚመዘዙና ለኢኮኖሚያዊ ልማት የሰጠነውን ትኩረት የሚያሳዩ እሳቤዎች ናቸው፡፡ እርግጥ ነው የኢኮኖሚ እድገት በተለይ እንደኛ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ቁልፍ የልማት አቅጣጫ መሆን ይገባዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ እድገት ሌሎች እድገቶችን ማሳካት ይችላል? ለምሳሌ፤ ኢኮኖሚያዊ እድገት ፖለቲካዊና ማህበራዊ፣ ማህበረሰባዊና የዜጎችን ግላዊ እንዲሁም አዕምሮአዊና መንፈሳዊ ብልፅግናን መከሰት ይችላል? ኢኮኖሚያዊ እድገትን ብቻ ሳይሆን ባህልንም የሚያካትት ልማት ግን የተሟላ ብልፅግናን መከሰት ያስችላል፡፡ ምክንያቱም የቁሳዊ ብልፅግና አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የባህል ልማት ደግሞ ከምንም በላይ መልማት ያለበት የዜጎች አዕምሮአዊና መንፈሳዊ ሀብት ልማት በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን መሰረት ያላደረገ ልማትና ዕድገት አስፈላጊነቱም በእጅጉ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በምሁራኖች ዘንድ ባህልና ልማትን ነጣጥሎ አልያም በቅንጅት የመመልከቻ አያሌ መከራከሪያዎችና አቀራረቦች አሉ፡፡ ይህንን ለመተንተንና ለመከራከር ጊዜውም ቦታውም ባለመሆኑ ወደ ዋናው ጉዳያችን እናልፋለን፡፡
ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማሳካት ሂደት ውስጥ ባህልና የባህል ምርት ያለው ሚናስ በልማት ፖሊሲዎቻችንና ስትራቴጂዎቻችን ለምንስና እንዴት ነው መካተት የሚገባቸው? ይህን ጥያቄ በተለይ በኢትዮጵያ ዓውድ ለመመለስ የሞከርን እንደሆን የባህል ፖሊሲያችንና የልማት ፖሊሲያችን ዘይትና ውሃ ሆነው ነው የምናገኛቸው፡፡ የባህል ፖሊሲው ተረቅቆ ወጥቷል፤ መልማት ያለባቸውን የባህል መገለጫዎችንና እሴቶችንም ለይቶ አስቀምጧል። ነገር ግን ይህንን ታሳቢ ያላደረገ የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው እየተተገበረ ያለው። ኢኮኖሚያዊ እድገት ሁለቱ ፖሊሲዎች (ማለትም የልማትና የባህል ፖሊሲዎቻችን) የግድ መናበብ ሳይኖርባቸው ለየቅል ተግባራዊ ሆነው ውጤት ማምጣት ይቻላል ቢባል እንኳን ቢያንስ የባህል ፖሊሲያችን ያስቀመጣቸውን የተግባራዊነት ስትራቴጂዎች እውን ለማድረግ የሚያስችሉና ባህልን ከልማት ሊያስተሳስሩ የሚችሉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት ግድ ይላል። ባህል በልማት ሂደት ውስጥ ቦታ እንዲኖረው ካስፈለገ የባህልን አቅም መገንባት የሚያስችሉ የተቋምና የሰው ሃይል የአቅም ግንባታዎች ወሳኝ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ አንፃርም የኢፌድሪ የባህል ፖሊሲ ስለ አቅም ግንባታ ባይጠቅስም አቅምን ለመገንባት የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፏል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ፖሊሲው በተጨባጭ የገነባው የባህል አቅምም ሆነ የልማት አቅጣጫችን ተግባራዊ የባህል ፈለግ እንዲኖረው ያደረገው አስተዋፅኦ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ይህም በሃገራችን አውድ የባህልና የባህል ምርት ልማት አስፈላጊነት ታምኖበት የተደረገ የማይመስል በመሆኑም ፖሊሲው ጠንካራ መሰረት ኖሮት የተሳካ ውጤት ማምጣት አለመቻሉ በግልጽ ይታያል፡፡ በሂደቱም ለውጥ ለማምጣት  የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ያለመፍጠሩ እንዲሁም የባህል ልማትና ምርት እንዳይከሰት የሚያግዱ ማነቆዎችን አለመለየቱና ችግሮቹን መቅረፍ አለመቻሉ የባህላችንና የኢኮኖሚያዊ ልማታችንን ለየቅል እንዲሆኑ ካደረጉ ምክንያቶች መሃል ዋንኞቹ ናቸው። ስለዚህ አሁንም ጉዳያችን የባህል ፖሊሲያችን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን እንዴት ማጣጣም ይችላል የሚለው ይሆናል፡፡
የባህል ፖሊሲያችን በተለይ ሥነ-ጥበብን ተግባራዊ በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እንዲሰሩ ባለማስቻሉ፣ ሥነ-ጥበባችን በባለሙያዎች ትከሻ ላይ ብቻ የወደቀ ዘርፍ እንዲሆን አስገድዶታል። የሥነ-ጥበብ ልማትም ሆነ እድገታችን በመንግስት ከመደገፍ ይልቅ በሠዓልያን ብቻ የሚወጣ ኃላፊነት ሆኖ ቆይቷል፡፡ የመንግስትና የባለ ድርሻ አካላት ጥረት እስካልታከለበት ድረስም ይኸው አያያዛችን የሚቀጥል ነው የሚመስለው። መንግስታችን ለባህልና ለሥነ-ጥበብ ድጋፍ ለማድረግ እንዲችል ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነጥቦች መሃከል ተያይዥነት፣ ቀጣይነትና ተናባቢ የሆኑ የልማት፣ የኢኮኖሚና የማህበረሰብ ድንበሮችን በግልፅ ማስቀመጥ ዋንኛው ነው፡፡ ፖሊሲዎቹን ለመተግበር የሚያስችል መልካም አስተዳደር ማስፈንም የወጣውን ፖሊሲ የሚያስፈፅሙ ህጎችን ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የባህል ፖሊሲ ሥነ-ጥበብን ለማልማትና ሥነ-ጥበባዊ የባህል ምርት መከሰት የሚያስችል ህግ ማውጣት ባለመቻሉ በዚህ ጉዳይ ምንም መነጋገር አያስችልም። የባህል ፖሊሲያችን ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ካንቀላፈበት ባንኖ /ምናልባት ነው/ ለባህልና ለሥነ-ጥበብ አቅም መገንባት ቢያስብ /ይሄም ‘እዬዬ ሲዳላ ነው!’/ የትኞቹ ነጥቦች ላይ ነው በተለይ የሥነ-ጥበባችንን ድክመት ማሻሻል የሚችለው?
ቀዳሚው በአቅም ግንባታው ማመን ነው። በአቅም ግንባታው ሲታመን አቅም መገንባትን የስትራቴጂው አካል ያደርጋል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የባህል ፖሊሲ ግን አቅም ግንባታ የሚባል ነገር አንዳችም ቦታ አያነሳም፡፡ በአቅም ግንባታው ታምኖበት ሲሰራ ደግሞ ተቀዳሚው የባለሙያዎችን አቅም መገንባት ነው፣ ፖሊሲውንም ሆነ ፖሊሲውን ለማህበረሰቡ ተግባራዊ የሚያደርጉ የባለሙያዎችን አቅም መገንባት፡፡ ይህ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ማለትም በሥነ-ጥበቡ ውስጥ ሚና የሚጫወቱ ሠዓሊያንን አቅም መገንባትንም ያካትታል። የሌሎች ዘርፎች ምሁራን የሥነ-ጥበብ አቅም መገንባትም ይከተላል፡፡ ጉዳያችን በተለይ ሥነ-ጥበብ በመሆኑ የሥነ-ጥበብን አቅም ለመገንባት በሚደረግ ሂደት ውስጥ ‘የሌሎች ዘርፎች ምሁራንን የሥነ-ጥበብ አቅም መገንባት ለምን ያሻል?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። አመክንዮው እንዲህ ነው፤ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ፣ የልማት፣የፖለቲካና … ወዘተ ፖሊሲዎች ሲቀረፁ የየዘርፉ ምሁራን የባህልና የሥነ ጥበብ አቅም ያልተገነባ ከሆነ፣ እንዴት ብለው ነው ተያያዥነት ያላቸው ፖሊሲዎችን የሚቀርፁት? ፖሊሲዎቻችን ውስጥ ባህልና ሥነ-ጥበብን ማካተት የሚችሉት እውቀቱ ሲኖራቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የሌሎች ዘርፎች ምሁራንን አቅም መገንባት የሚያሻው፡፡ ይህንን እውን ማድረግ ለሀገራችን እጅግ አስቸጋሪ፣ ፈታኝና ሩቅ ይመስላል። ግን ደግሞ ይህንን ማድረግ የግዴታ ግዴታ ነው፡፡ አለዚያ የባህልና የሥነ-ጥበብ አቅማቸውን የገነቡ የሌሎች ሀገራት ምሁራን መጥተው ፖሊሲ እንዲያወጡልና ህግ እንዲቀርፁልን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ የዚህ ጉዳት ደግሞ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ላይ በግልፅ እያየነው ነው፡፡ የባህልና የሥነ-ጥበብ አቅም በመገንባት ሂደት ውስጥ ከመንግስት የሚጠበቀው ሌላኛው ሀላፊነት በቂ ገንዘብ መመደብና የድጋፍ ምንጭ ማበጀት ነው፡፡ በአቅም ግንባታው የመጨረሻ ምዕራፍ መሆን የሚገባው ደግሞ የባህልና የሥነ-ጥበብ ዘርፍ በተፈጠረለት አቅም አማካኝነት ያመረተውን የባህልና የሥነ-ጥበብ ምርት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ማስቻል ነው፡፡ ይህ በበኩሉ ለማህበረሰቡ እንዲደርስና እንዲሰርፅ ማድረግን ይጨምራል፡፡ የባህል ፖሊሲያችን በሁለት አስርት ዓመታት ገደማ እድሜው ይህንን ለማድረግ ጥረት አድርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ዜጎች ከሥነ-ጥበብ ትሩፋቶች መጠቀም ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ልማትና ኢኮኖሚም በማይናቅ ሁኔታ ከሥነ-ጥበብ መጠቀም ማደግና መበልፀግ ይቻለው ነበር፡፡
ሥነ-ጥበብን በተለይ ለማልማት በሚደረግ የአቅም ግንባታ ሂደቶች ህግ ማውጣት ፖሊሲውን ለመተግበርም ሆነ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ከማስቻሉም በላይ የልማትና የባህል ፖሊሲውን ማጣጣም የሚያስችሉ ነጥቦችን ለማንሳትም ምቹ ሁኔታን ፈጣሪ ነው፡፡ በሀገራችን የልማት አቅጣጫ የኮንስትራክሽን ግንባታና መሰረተ ልማቶችን ለመዘርጋትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለመገንባት ከፍተኛ ርብርብ እየተካሄደ ነው - ፎቅ እንደ ሙጃ ሳር አይደል እየበቀለ ያለው? አደባባዮች በመንገድ ግንባታ አማካኝነት በዝተው የለ? ታዲያ ይህንን አይነት ልማቶች እንዴት ነው ሥነ-ጥበብን ለማልማት መዋል የሚችሉት? መልሱ ቀላል ነው። ህግ ማውጣት፡፡ ምን አይነት ህግ? ለምሳሌ ባለሀብቶች በሚገነቧቸውም ሆነ መንግስት በሚሰራቸው ህንፃዎች ውስጥ የሥነ-ጥበብ ውጤቶችን እንዲያካትቱ የሚያስገድድ ቀጭን ህግ ማውጣት ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡ ማህበረሰቡ ወደ ተቋማትም ሆነ ወደ አገልግሎት መስጫ ህንፃዎች በሚሄዱበት ጊዜ የሥነ-ጥበብ ውጤቶችን የማየትና ቀስ በቀስ የማድነቅ ባህል ያዳብራል፡፡ የሙያተኞች አቅምም ይዳብራል፡፡ ገቢያቸው ይጨምራል። መንግስት ከሥነ-ጥበብ የሚያገኘው ታክስ ከፍ ይላል፡፡ ይህ በግርድፍ የተቀመጠ ሀሳብ ነው፡፡ ብዙ ጥያቄዎችም ያስፈልጉታል። የባህል ፖሊሲያችን እንዲህ አይነት ሀሳቦችን ጥቅም ላይ ለማዋል ልቦና ያገኘ ጊዜ ሰፊ ክርክሮች ይጠብቁናል- ይህ እውን ሊሆን እንደሚችልም ተስፋ እናደርጋለን፡፡
የሥነ-ጥበብ አቅም ግንባታው ሌላኛው ገፅ፣ ጠንካራ ተቋማትን መመስረት ነው፡፡ የትምህርትና የምርምር እንዲሁም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መፍጠርና አቅም መገንባት ያሻል፡፡ በኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ‘አንድ ለእናቱ’ ሆኖ ሥነ-ጥበባችንን እዚህ ያደረሰው ከስምንት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር የተካተተው የአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ነው፡፡
ምነው ዩኒቨርስቲዎች በየክልሉ እንደ አሸን ሲፈሉ፣ አንድ ሁለት ሥነ-ጥበብን የሚያስተምር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ብርቅ ሆነብን? የሥነ-ጥበብ ምርምር የሚያደርግ ተቋም ይነሰን? ኧረ እንደው ቢያንስ ሁለት ሶስት ክልሎች የሥነ-ጥበብ ሙዚየም መገንባት ተስኗቸው ነው በጭርታ የተኮራመቱት? የኢትዮጵያ ሠዓሊ የሚኖረውም የሚሰራውም እዚችው አዲስ አበባችን ነው፡፡ የየክልሎቻችን ህዝቦች ሙዚየም ተከፍቶላቸው፣ የሥነ-ጥበብ ሥራዎችን የማየትና የማድነቅ እድሉ ቢፈጠርላቸው ምን አለበት? ሳምንት ይቀጥላል፡፡ ቸር እንሰንብት!

Read 1809 times