Monday, 19 September 2016 08:31

በ3 ሊትር ውሃ አንድ መኪና የሚያጥብ ቴክኖሎጂ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(7 votes)

    አንድ አካባቢ ክረምት ከበጋ በቆሻሻ የውሃ ፍሳሽ ጨቅይቶ ሲያዩ፣ ስፍራው የመኪና ማጠቢያ መሆኑን ይገምታሉ፡፡ ግምትዎ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ዓይንዎን በየአቅጣጫው ወርወር ቢያደርጉ፣ የታጠቡ መኪኖች ወይም ለመታጠብ ወረፋ የያዙ መኪኖች ያያሉ፡፡ በየመንገዱ መኪና ሲያጥቡ የምናያቸው ወጣቶች አንድ መኪና ለማጠብ ከ2 እስከ 3 ጀሪካን ውሃ ይጠቀማሉ፡፡ በዚህም አካባቢውን በቆሻሻ ውሃ እንደሚበክሉና እንደሚያጨቀዩ ይታወቃል፡፡ ላባጆ የሚባሉት ደግሞ ለአንድ መኪና ከ70-100 ሊትር ውሃ ይጠቀማሉ፡፡   
አሁን ግን ይህን ተለምዷዊ አሰራር በመለወጥ፣ መቶ በመቶ ለአካባቢ ደህንነት ተስማሚ የሆነ ከኤሌክትሪክና ከውሃ መስመሮች ጋር የማይገናኝ፣ ተደራሽና ጊዜ ቆጣቢ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ አዲስና ዘመናዊ “ኤ.ቢ ተንቀሳቃሽ የመኪና እጥበት አገልግሎት” የዛሬ ሳምንት ቦሌ መድኃኒዓለም ጀርባ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
ኤቢ ተንቀሳቃሽ የመኪና እጥበት፣ አንድ መኪና አጥቦ ለመጨረስ የሚወስድበት ጊዜ እንደ መኪናው ይወሰናል፡፡ ትንሽ የቤት መኪና ከሆነ 20 ደቂቃ፣ ትልቅ መኪና ከሆነ ደግሞ 30 ደቂቃ ይፈጅበታል። እዚህ ላይ አስገራሚና ለአካባቢ ተስማሚ የሚያደርገው የውሃ አጠቃቀሙ (ፍጆታው) ነው። አንድ መኪና ለማጠብ የሚፈጀው 3 ሊትር ብቻ ነው፡፡ ተንቀሳቃሹ ማጠቢያ ከ60-70 ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም ሲኖረው፣ በቀን ከ15-23 መኪና ለማጠብ እንደሚያስችለው የተንቀሳቃሽ ማጠቢያው መስራች፣ ባለቤትና ዋና ኃላፊ አቶ አብርሃም ግርማይ ተናግሯል፡፡
በትግራይ ክልል በሃውዜን ወረዳ፣ ተወልዶ አስመራ ከተማ ያደገው የ35 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ አብርሃም፤ ወደ ዱባይ ሄዶ ለ8 ዓመት የተለያዩ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ይናገራል፡፡ የፊኒሺንግ ፅዳት ስራም ነበረው፡፡ ይህን ስራ ያወቀው እዚያ ነው፡፡ ስራውን ለመጀመር አስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሀሳቡን አልገፋበትም፣ ፈቃድ ቢያወጣበትም ተወው፡፡ ይህንን ዓለም እየተጠቀመበት ያለውን ቴክኖሎጂ አገሬ ወስጄ ባስተዋውቀው ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በማለት አሰበ፡፡
አገር ቤት መጥቶ ስራ ከመጀመሩ በፊት እዚህ ስላለው የመኪና እጥበት መጠነኛ ጥናት አደረገ። መኪና አጣቢዎቹ አንድ መኪና ለማፅዳት ከ60 እና 70 ሊትር በላይ ውሃ ይጠቀማሉ፡፡ በዚህም አካባቢው በቆሻሻ ውሃ ይበከላል፣ ይጨቀያል፡፡ የአጣቢዎቹን ጉልበት ይበላል፡፡ የደንበኛውን ጊዜም ይባክናል፡፡ ይህ አዲሱ የእጥበት ዘዴ፣ በብዙ የዓለም አገሮች፡- በሆቴሎች፣ በግልና በመንግሥት መ/ቤቶች፣ በገበያ ማዕከላት፣ መኪና ማቆሚያ ባላቸው ስፍራዎች፣ … በብዛት ይጠቀሙበታል፡፡ የውሃ ፍጆታው ትንሽ ነው፤ ለአንድ መኪና 3 ሊትር ብቻ ነው የሚፈጀው፣ የምንጠቀምባቸው ነገሮች የመኪና ሻምፖና የየራሳቸው ደረጃ ያላቸው ማይክሮ ፋይበር ፎጣዎች ብቻ ናቸው፡፡
አንድ መኪና ለመታጠብ ወደ እኛ ሲመጣ አቧራው ይነሳል፡፡ 3 ዓይነት ፎጣዎች አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ የመጀመሪያው ቆሻሻውን ያነሳል፣ ሁለተኛው ማድረቂያና ሶስተኛው የዳሽ ቦርድ መጥረጊያ ናቸው፡፡ ሌላ ምንም መጥፎ ዓይነት ኬሚካል ስለማንጠቀም የመኪናውን ቀለም አይጎዳም፡፡ ሌላውና ዋነኛው ጥቅም ለብዙ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡ አሁን እንኳን በ10 ማጠቢያዎች ለ10 ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥረናል። ወደፊትም በሁሉም ክፍለ ከተሞችና አስፈላጊ ናቸው በምንላቸው ቦታዎች ሁሉ ለመጀመር ዕቅድ ስላለን በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ በማለት አቶ አብርሃም አስረድቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ሞተርና ሻንሲ የማናጥብ ስለሆነ ምንም ዓይነት የአካባቢ ብክለት የለውም፡፡ እኛ የምናፀዳው ቦዲውን (የውጪ አካሉን) ብቻ ነው፡፡ ይህ ጥቅም እንጂ ምንም ጉዳት የሌለውን ቴክኖሎጂ ወደዚህ ባመጣ፣ አገሬን ጠቅሜ እኔም እጠቀማለሁ በማለት አሰብኩ ሲል ገልጿል፡፡ ለአቶ አብርሃም ቴክኖሎጂ እውን መሆን ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ሰው አሉ፤ አቶ ፀጋዬ ደበበ ይባላሉ፡፡ የ“ደብል ፒ ፋይበር” ፋብሪካ ባለቤት ናቸው፡፡
እንዲህ ዓይነት ነገር ለመስራት አስቤያለሁና ምን ትመክረኛለህ? ምን ትረዳኛለህ? በማለት ሀሳቡን አጫወታቸው፡፡ አቶ ፀጋዬም ሀሳብህ በጣም ጠቃሚ ስለሆነ፣ አንተ ለመጀመር ያብቃህ እንጂ እኔ በምችለው መንገድ ሁሉ እረዳሃለሁ በማለት አበረታቱት፡፡ በመጀመሪያ የመሳሪያውን ፎቶግራፍ አሳያቸው፤ በመቀጠልም ከዱባይ ማሽኑን ገዝቶ አምጥቶ ሰጣቸው፡፡ አቶ ፀጋዬም አስመስለው ሰርተው 10 ማጠቢያ ማሽኖች አስረከቡት፡፡ በእነዚህ ነው እንግዲህ ባለፈው ቅዳሜ ሥራ የጀመረው፡፡
አቶ አብርሃም ማሽኖቹን የተሰሩበትን ትክክለኛ ዋጋ አያውቅም፡፡ አቶ ፀጋዬ በእገዛ መልክ ነው የሰራልኝ ፤ወደ 75 በመቶ ረድተውኛል፡፡ በግምት ፋይበሩ ብቻ ያለአክሰሰሪው ከ25 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር ሊደርስ ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አሁን ያሉን ማጠቢያዎች 10 ናቸው፡፡ ይህን ያዩ ሰዎች፤ “ስራችሁ ጥሩ ነው፡፡ እዚህ ብቻ ነው? ወይስ በሌሎችም ቦታ ትጀምራላችሁ?” እያሉ እያብረታቱን ነው፡፡ መንገድ ላይ አናጥብም፡፡ በየመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችና በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንጀምራለን፡፡ በቅርቡ 100 መኪና ማጠቢያዎች ይኖሩናል፡፡ በአሁኑ ወቅት እኛ ለቤት መኪናዎች 50 ብር፣ ላንድክሩዘርና ፒክ አፕ 60 ብር እያስከፈልን ነው፡፡ ኅብረተሰቡም የሚሰጠን አስተያየትም ተገቢና ተመጣጣኝ እንደሆነ ነው፡፡ እዚህ ላይ እኔ መበርታት ያለብኝ፤ ታማኝ ሰራተኞች ማግኘትና ማሰልጠን ላይ ነው፡፡ ደንበኛው በመኪናው ውስጥ ብዙ ውድና በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ ንብረቶች ይዞ ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡ መኪናው እንዲታጠብለት ሲሰጥ ለእነዚህ ንብረቶቹ ዋስትና ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ታማኝ ሰራተኛ ማቅረብ ግዴታ ነው ይላል፡፡
ይህን ስራ ከጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነው የጠቀሰው አብርሃም፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ400-500 ሺህ ብር መፍጀቱን ገልጿል፡፡ ላሰበው ዕቅድ ደግሞ ብዙ ገንዘብ ስለሚያስፈልገው መንግስትና ባንኮች እንዲደግፉት ይፈልጋል፡፡ አቶ ዳዊት ዓለሙ፤ የቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 3 ምክትል ስራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ልጁ ያቀረበው ጥያቄ በክፍለ ከተማም ደረጃ ታይቶ ምርጥ ተሞክሮ ስለሆነ ተቀብለነዋል፡፡ ከውሃ ብክነት አንፃር ስናየው፤ ጥቂት ውሃ ነው የሚጠቀመው፡፡ አስፋልት ሳይጎዳና ሌሎችም ብክለቶች ሳያጋጥሙ አገልግሎት ይሰጣል። የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ በአንድ ማዕከል ውስጥ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል በማለት ስለ ኤ.ቢ ተንቀሳቃሽ የመኪና እጥበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ወ/ሮ ሸምሲያ ነጋሽ የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 የጥቃቅንና አነስተኛ ጽ/ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ “በከተማችን ላይ ያልተለመደ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው። ሌላው ጥቅም ደግም ወጣቱን ወደ ስራ ከማስገባት አኳያ ሰፊ ጥቅም እንዳለው አይተናል፡፡ ያደረግንለት ድጋፍ ቦታ በነፃ እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ እስካሁን የተንቀሳቀሰው በራሱ ገንዘብ ነው፡፡ ወደፊት የገንዘብ ድጋፍ የሚፈልግ ከሆነ አዲስ ብድርና ቁጠባ የእኛ አባል ስለሆነ በውስጠ ደንባቸው መሰረት በዚያ በኩል ድጋፍ እንዲደረግለት እናደርጋለን” ሲሉ ገልጸዋል፤ ወ/ሮ ሸምሲያ፡፡  

Read 3984 times