Monday, 26 September 2016 00:00

‹‹መከፋፈል አያዋጣንም፤ አንድ መሆን አለብን››

Written by  አቶ አበባው መሃሪ (የመኢአድ የቀድሞ ፕሬዚዳንት
Rate this item
(4 votes)

- የወልቃይት ችግር ታሪክን መሰረት ያደረገ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል
- በየሰው ደጅ ወታደር በማሰማራት መፍትሄ ማምጣት አይቻልም
- መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ሌላ ችግር የሚወልድ ነው
- የሃይማኖት አባቶች ይሄ ሁሉ ሲሆን የት ነው ያሉት?

አቶ አበባው መሃሪ
(የመኢአድ የቀድሞ ፕሬዚዳንት

በእርስዎ ግምገማ የህዝብ ተቃውሞዎች መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
መንግስት ችግሮቹን የመልካም አስተዳደር እጦት ነው ብሎ ይደመድማል፡፡ መልካም አስተዳደር አንዱ ችግር ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን ሌሎች ያልተፈቱና መፈታት የነበረባቸው ነገሮች ተዳፍነው መሠንበታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል የተነሣውን ብንመለከት፣ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ፤ የሁለት ክልሎች አመራሮች ያልፈቱት ችግር ነው ብለዋል፡፡ ይሄ ዋናው ችግር ይመስለኛል፡፡ ሌላው መንግስትና ህዝብ ሣይገናኙ እስከ ዛሬ መቆየታቸው ነው፡፡ የሚሾሙ ባለስልጣናት ራሳቸውን ለመጥቀም ነው የሚኖሩት፡፡ ከዚያ በመለስ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት በሃገሪቱ ላይ አለመኖሩ ተጠቃሽ ነው፡፡ እኩል ተጠቃሚነት ከሌለ ‹‹የሃገሪቱን ሃብቶች እንዳልጠቀም ተገፍቻለሁ›› የሚለው አካል ተቃውሞ ማቅረቡ የማይቀር ነው፡፡  እነዚህ ይመስሉኛል ዋና ምክንያቶቹ፡፡
ተቃውሞዎቹ በዚሁ ከቀጠሉ ወዴት የሚያምሩ ይመስልዎታል?
እኔ እንደማየው አቅጣጫው ለአገሪቱ መልካም አይደለም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያስብበትና ጸሎት ሊያደርግበት፣ ሊመካከርበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ የሊቢያ፣ የየመንና የሶርያን ሁኔታ ብናይ፣ መነሻቸው የዚህ አይነት ተቃውሞዎች ናቸው፤ ስለዚህ ተመሳሳይ ችግር እነዳከሰት ህዝቡ መመካከር አለበት፤ ፀሎት መደረግ አለበት። ሁሉም ሰፊ ልብ እንዲኖረው ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለእነዚህ  ችግሮች መንግስት መፍትሄ የማያበጅላቸው ከሆነ ወደ መጥፎ ሁኔታ ይወስደናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ የእርስ በእርስ ግጭትና መተላለቅ እንዳይመጣ እሠጋለሁ፡፡
መንግስት ለተቃውሞዎቹ የሚሰጣቸው ምላሾች፤ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣሉ ብለው ይገምታሉ?
የመንግስት አካሄድ ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡  መንግስት ማለት አባት ነው፡፡ አባት፤ ልጆቹ ሲቆጡ እንዲህ አይደለም የሚመልሰው ቋሚ መፍትሄ እንጂ ለጊዜው በኃይል ማዳፈን ለውጥ አያመጣም። ስንት ሰው አስሮና ገድሎ ይዘልቀዋል? እንደውም ነገሩን ያባባሰው የሃይል እርምጃ ነው፡፡ በአጠቃላይ መንግስት እየተከተለ ያለው አካሄድ ቁስሉን የሚያሽርና መፍትሄ የሚሰጥ መስሎ አይታየኝም። ላይ ላዩን ነው እየሄደ ያለው፤ እውነተኛው ቁስል ጋ አልደረሠም፡፡  እየወሠደ ያለው እርምጃ ከችግሩ በእጅጉ የራቀ፣  ሌላ ችግር የሚወልድ በመሆኑ፣ ምን ማድረግ እንዳለበት ቆም ብሎ ማሠብ አለበት፡፡
እርስዎ አባል የሆኑበትና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በፕሬዚዳንትነት የመሩት ፓርቲ በአንዲት ኢትዮጵያ (ሪፐብሊክ) የሚያምን ከመሆኑ አንፃር የሚነሱ የብሄር ማንነት ጥያቄዎችን እንዴት ይመለከቷቸዋል?
በመጀመሪያ ደረጃ እኛ አሁን ያለው ቋንቋና ብሄርን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ሊሰራ አይችልም ስንል ከርመናል፡፡ የትም ሃገር አልሰራም፡፡ ሩሲያን አፍርሷል፡፡ ዛሬ የቤልጅየም ህዝብ ወዝግብ ውስጥ የገባው በእንዲህ ያለው የፌደራሊዝም አወቃቀር የተነሣ ነው፡፡ በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን የተለየ ባህሪ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ በአንድ ላይ በልተን
ጠጥተን የምንኖር ስለሆነ ይሄ ፌደራሊዝም ሊሰራ አይችልም፡፡ አሁን ለተፈጠረው ቁስለትም መነሻው ይኸው ስንለው የነበረው ጉዳይ ቸል የመባሉ ውጤት ነው፡፡ መንግስት በዚህ ላይ አሁንም ደጋግሞ ማሠብ አለበት፡፡  ጉዳዩ እንደገና ሊፈትሽና መፍትሄ ሊፈልግለት ይገባል፡፡ ሌላው ህዝቡ ላለፉት 25 ዓመታት ልቡ የቆሠለና ያመረቀዘ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ፍትሃዊነትና ተጠቃሚነት ማጣትን የመሣሠሉት ጉዳዮች ህዝቡን አቁስለውታል፡፡ መንግስት ያንን የቆሠለ ልብ ለማዳን ነው መጣር ያለበት እንጂ ከዋናው ችግር ሸሽቶ፣ ዳር ዳሩን መሄድ የትም አያደርስም፡፡ እንደ ወልቃይት፣ ኮንሶ የመሣሠሉትን  ጥያቄዎች ያነሡ በአግባቡ መስተናገድ አለባቸው። ሰው መብቱን በመጠየቁ መሞት የለበትም፡፡ አንድም ዜጋ መሞት የለበትም፡፡ መንግስት ለእያንዳንዱ ችግር ቋሚ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠት አለበት እንጂ በእያንዳንዱ ሰው ደጅ፣ ወታደር በማሠማራት መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም።
የወልቃይት ችግር በምን አግባብ ሊፈታ ይችላል ብለው ያስባሉ?
ድሮ ልጅ ሆኜ ጎንደር ስማር፣ ታዋቂው ድምፃዊ ይርጋ ዱባለ፤ ‹‹ለምለሚቷ ጎንደር እንኳን ደስ አለሽ የሠሊጧን መሬት ሁመራን ይዘሽ››፡፡ እያለ ይዘፍን ነበር፡፡ ይሄ የራሱ ታሪክ አለው፡፡ የትግራይና የአማራ ልሂቃን በእርጋታ ተቀምጠው ታሪክ መመርመር አለባቸው፡፡ ህዝብ እንዲመክር ተደርጎ ታሪክን መሰረት ያደረገ መፍትሄ ሊሠጠው ይገባል፡፡ የፌደሬሽን ም/ቤት ይሄን ተግባር ሊወጣ ያስፈልጋል። ይሄን ካልሰራ ምንድን ነው ስራው? የኮንሶ ህዝብ ያነሣውም ተመሣሣይ መፍትሄ የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡ ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ መፍትሄ ይፈልጋል፡፡ መስተዳደሩን አፍርሶ፣ ሰው አስሮና ገድሎ የሚመጣ መፍትሄ ወይም የሚዳፈን የህዝብ ፍላጎት አይኖርም፡፡
ኢህአዴግ በሚያደርገው ተሃድሶ ለተነሱ የህዝብ ተቃውሞዎች ምላሽ መስጠት የሚችል ይመስልዎታል? በዚህ ተሃድሶ ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል ብለው ያምናሉ?
ይሄ  አሁንም ኢህአዴግ እየሠራ ያለው ሌላኛው ስህተት ነው፡፡ ባለስልጣናት ተለዋውጠው ብቻ ለውጥ አይመጣም፡፡ ህዝቡ መለወጥ አለበት፡፡ መለወጥ ሲባል የቆሠለ ልቡ መዳን መቻል አለበት። ላለፉት 25 አመታት አንዱ ታግዶ ሌላው ሲነግድ፣ አንዱ ቀረጥ ከፍሎ ሌላው ሳይከፍል፣ አንዱ  ፎቅ ከመሬት ሲያበቅል እያደረ፣ ሌላው መጠለያ አጥቶ መንገድ ላይ እያደረ ነው የተኖረው፡፡ ይሄ የህዝቡን ልብ አድምቶታል፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ካልተለወጠ የእነሱ መታደስ ብቻ ውጤት አያመጣም። ‹‹ተሳስቻለሁ፤ ይቅርታ አድርግልኝ›› ቢሉት የኢትዮጵያ ህዝብ በቀናነት ይቅር የሚል ህዝብ ነው። የነሱ ችግር ግን ወደዚህ ቀናነት መምጣቱ ላይ ነው። የሚታደሱት የሚለወጡት ወደ እውነቱ ሲቀርቡ ብቻ ነው፡፡ በሬድዮና በቴሌቪዥን ስለተወራ ለውጥ አይመጣም። ለውጥ ለብቻ ሳይሆን ከህዝቡ ጋር ከልብ ተማክሮ ሲሆን ነው ውጤት የሚያመጣው። ከዚህ ቀደም ያጠፉት ጥፋት የት ሊሄድ ነው? ብቻቸውን እንለወጣለን የሚሉት፡፡
አንድ ነገር  ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ የሃይማኖት አባቶች ይሄ ሁሉ ሲደረግ የት ነው ያሉት? ሃገር ከጠፋ በኋላ ሃይማኖት ይኖራል እንዴ? ስለዚህ የሃይማኖት አባቶች ወደ አንድ ጎን ከማድላት ይልቅ ቢሆንላቸው ገብተው ማስታረቅ ነበረባቸው፡፡ ዛሬ ዝም ብለው  የሚመለከቱት ነገር ነገ ጠዋት የአባትነታቸውን ክብር የሚያሳጣቸው ነው የሚሆነው፡፡ እኛ እንደ መኢአድ እርቅ እንዲወርድ፣ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ለመገናኘት ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ በእውነቱ ከሆነ ላመሰግናቸው  የምችለው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ክርስቲያን ጳጳስን ብቻ ነው፡፡ እሳቸው እጅግ በጣም ጥሩ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ሌሎቹ ግን ‹‹እንዲህ እንባላለን…. እንዲያ እንባላለን›› እያሉ ከእውነቱ ሲሸሹ ታዝበናቸዋል። የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ አባቶች፣ የክርስቶስን ስራ ለመስራት የማሉ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ ካመኑ ሚሳኤል ቢመጣ መፍራትና መደንገጥ የለባቸውም፡፡ ክርስቶስ በምድር ሳለ የሚሰራውን ስራ እንሰራለን ካሉ፣ እርሱ ስለ እውነት ተሠቅሏል፡፡ ለምን እነሱስ ስለ እውነት ዋጋ ለመክፈል አይቆርጡም? ለምን እውነተኛ አባትነታቸውን አያሣዩንም? እኔ በእነሱ ሁኔታ በእጅጉ አዝኛለሁ፡፡
በዚህ የህዝብ ተቃውሞ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሚና እንዴት ይገመግሙታል?
በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከራሳቸው ጋር መታረቅ አለባቸው፡፡ ከቅራኔያቸው ተላቀው ወደ አንድነት መምጣት አለባቸው፡፡ የዚያን ጊዜ ነው የኢትዮጵያን ህዝብ ሊመሩ የሚችሉት። አለበለዚያ ለዚህ ህዝብ አይመጥኑትም፡፡ አንዱ ለአንዱ ብሄር፣ ሌላው ለአንዲት ወረዳ እያሠበ የሚንቀሣቀስ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ለሃገሪቱ ችግር መፍትሄ ይፈልጋል ማለት ዘበት ነው፡፡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ምን አይነት ናቸው ተብሎ ቢጠና፣ በዜሮ፣ የምንቀር ይመስለኛል። ‹‹አብረን እንስራ›› ሲባሉ፤ ‹‹የአይንህ ቀለም አላማረኝም፤ አብሬህ አልሰራም›› የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ለሃገሪቱ ችግሮች መፍትሄ ያመጣሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
አሁን ያሉት ችግሮች በምን አግባብ ሊፈቱ ይችላሉ ይላሉ?
የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ የማይነጣጠል ወንድማማች ህዝብ ነው፡፡ የአማራና የኦሮሞ ህዝብ የማይነጣጠል ወንድማማች ህዝብ ነው፡፡ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የህዝቡን የወንድማማችነት ታሪክ ይፋ አውጥቶታል፡፡ በካድሬዎች እየተገፋፋ እርስ በእርሱ በብሄር ሲቃረን የኖረው ህዝብ ከአንድ የዘር ምንጭ የተገኘ መሆኑ ሲረጋገጥ ትልቅ ነገር ነው፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ… የሚለው መከፋፈል  አያዋጣንም፡፡ አንድ መሆን አለብን፡፡  አንድ ሆነን፤ ጠንካራ የታመነ የመንግስት ስርአት መፍጠር አለብን፡፡ የብሄር ተቃርኖ ማቆም አለበት፡፡
መንግስት ህዝቡ ልቡ የቆሠለ መሆኑን ተረድቶ፣ ያንን ቁስል ለማዳን ጥረት ማድረግ አለበት እንጂ የውሸት መፍትሄ ማቅረብ የትም አያደርስም። ከህዝቡ ጋር ወርዶ በሰፊው መነጋገር አለበት፡፡ ይሄን ሲያደርግ ከሚደግፉት ጋር ሳይሆን እውነተኛ ችግሩን ሊነግሩት ከሚችሉት  ተቃዋሚዎች ጋር ነው መነጋገር ያለበት። እነሱ ናቸው ጉድፉን የሚያሣዩት፤ የሚደግፉትማ ‹‹አንተ ያልከው ይሁን፤ ልክ ነው›› እያሉ እንጀራቸውን የሚጋግሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱ ስህተቱን ሊነግሩት አይችሉም፤ ስህተቱን የሚነግሩት የሚቃወሙት ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ካልተደረገ የችግሩ መፍትሄ ይበልጥ ይወሳሰባል፡፡

Read 6238 times