Monday, 26 September 2016 00:00

የፖለቲካ ፔንዱለም (ሐገራት ለምን ይወድቃሉ?)

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(6 votes)

    ባለፈው ሣምንት ‹‹Why Nations Fail›› በተሰኘ መጽሐፍ የታተቱ ሐሳቦችን መነሻ በማድረግ ጨዋታ ይዤ ልመጣ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ይኸው ቃሌን አክብሬ መጥቻለሁ፡፡ ይህን ቃል የገባሁበት ያለፈው ሳምንት ጽሑፌ መነሻ ሰበቡም የአቶ ዮሐንስ ሰ. ጽሑፍ ነበር። አቶ ዮሐንስ በወዲያኛው ሣምንት ያቀረቡት  (እኔ መነሻ ያደረግኩት) ጽሑፍ ተከታይ የሚሆን ሌላ ጽሑፍ አስከትለዋል፡፡ ታዲያ በዚህ ተከታይ ጽሑፋቸው፤ ዛሬ ለማቀርበው ጨዋታ ጥሩ መንደርደሪያ የሚሆን ሐሳብ አምጥተዋል፡፡ እንዲያውም በዚህ መጣጥፍ ማንሳት ለፈለግኩት ነገር ማሄጃ ታስቦ በጥንቃቄ የተዘጋጀ የመቅድም ትንታኔ የሰጡኝ መስሎ ታይቶኛል፡፡
እኔም የአቶ ዮሐንስን ሐሳብ የሚያጠናክር፣ የሚያጠራና የሚሞግት ተከታይ ሐሳብ ነበረኝ፡፡ ሆኖም ያለኝ ሐሳብ ብቻውን ቦታ የሚይዝ እንጂ ደባል ሆኖ ለመቅረብ የሚያስቸግር ስለሆነብኝ፤ የእርሳቸውን ትንታኔ መነሻ አድርጌ፤ ቃሌን በማክበር ‹‹ሐገራት ለምን ይወድቃሉ?›› (Why Nations Fail) በሚል አጀንዳ ዙሪያ ማንሳት በፈለግኩት ጉዳይ መወሰንን መርጫለሁ፡፡
አቶ ዮሐንስ፤ በቀደመው ሥራቸው እንዳደረጉት፤ በተከታዩ ጽሑፋቸውም፤ እንደ ፔንዱለም ከወዲያ - ወዲህ እየተመላለሰ የሰዎችን ህይወት የሚያተራምስ፤ የገዛ ራሱን ‹‹የተፈጥሮ›› ህግ በመከተል ህብረተሰብን አፍርሶ እንደገና በመስራት የሚዝናና አንዳች ስውር ኃይል ያለ መስሎ እንዲሰማኝ የሚያደርግ ትንታኔ አስነብበውናል፡፡ አንዴ ወደ ቀኝ፤ ሌላ ጊዜ ወደ ግራ እየዘመተ የሰዎችን ህይወት እንዳሻው የሚያደርገውን የታሪክ ፔንዱለም ፍንትው አድርገው አሳይተውናል። ይህ ፔንዱለም፤ በሆነ ምክንያት ተነስቶ ዥዋዥዌ ሲጫወት፤ በቀደመው ዘመን የተሰራን ወይም የቀደመው ዘመን ዋና መገለጫ የሆነን ነገር (ተቋማትን) ሁሉ እየለየ በማጥፋት፤ በዚያ ምትክ አዲስ ነገር በመገንባት የሚዝናና ይመስላል፡፡
አቶ ዮሐንስ ሰ.፤ ጊዜ እየጠበቀ ከወዲያ - ወዲህ በኃይል ሲምዘገዘግ ያሳዩን ፔንዱለም በጣም አስገራሚ ባህርይ አለው፡፡ ምህረትን የማያውቅ ጨካኝ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ፔንዱለም ነው፡፡ ይህ ፔንዱለም የተለያየ ቅርጽ ወይም መልክ ይዞ ሊገለጥ ይችላል፡፡ ከአምባገነን ወደ አምባገነን እየተመላለሰ (መልክ ብቻ እየቀያየረ) ሲያጠፋ ብዙ ጊዜ ሊያጠፋ ይችላል፡፡ የአቶ ዮሐንስ ሰ.ን የትንታኔ ፈለግ ከተከተልን ደግሞ፤ አንዴ ግለሰባዊ፣ በሌላ ጊዜ ህብረተሰባዊ ቅርጽ እየያዘ ሲገለጥ ሊታይ ይችላል፡፡ ፔንዱለሙ፤ አንዴ የግለሰብ ነጻነትን፣ ነጻ ገበያን፣ ዴሞክራሲን ….. በሚያጠናክር አቅጣጫ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ ሶሻሊዝምን፣ የመንግስት ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ገብነትን፣ አምባገነንነትን……. በሚያበረታታ መስመር አሳይተውናል፡፡
በነገራችን ላይ፤ ‹‹ግለሰባዊነት›› የተባለው በዚሁ ክበብ የሚገቡትንና በተለያየ ስያሜ ሊጠሩ የሚችሉትን አመለካከቶች እንዲወክል ታስቦ ነው፡፡ ‹‹ህብረተሰባዊ›› የተባለው ደግሞ ዋና መገለጫ መልኩ ሶሻሊዝም ወይም ኮምዩኒዝም ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ የጸሐፊው ትንታኔ ፔንዱለሙ በሁለቱ ተቃራኒ አቅጣጫዎች ሲወነጨፍ ለማየት የሞከረ ትንታኔ ነው፡፡ አንዴ ጠቅልለን ለሶሻሊዝም (በተለያየ ቀለሙ) እጅ ስንሰጥ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለካፒታሊዝም (በተለያየ ቀለሙ) ስንማረክ የሚያሳይ የታሪክ ዥዋዥዌ ነው፡፡
የታሪክ ዘይቤ  
አቶ ዮሐንስ ሰ. የታሪክ ‹‹ማስ ስፖርት›› ትርዒት አሳይተውናል፡፡ በስቴዲየም ‹‹የማስ ስፖርት›› ትርዒት የሚፈጠረውን ውበትና መልዕክት፤ የትርዒቱ ተመልካች እንጂ ተሳታፊው የማየት ዕድል የለውም፡፡ የአቶ ዮሐንስን ጽሑፍ የሚያነብብ ሰው ከተሳታፊነት ወጥቶ፤ በክቡር ትሪቡን የማዕረግ ወንበር ተመልካች ሆኖ ተቀምጦ፤ የታሪክን ‹‹የማስ ስፖርት›› ትርዒት የማየት ዕድል ያገኛል፡፡ የትርዒቱን መልዕክትና ውበት፤ ከፍ - ራቅ ብሎ ለማየት ይችላል፡፡ እኔ በዚህ ጽሑፍ ሌላ ዕድል ለመፍጠር ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ ጥረቴ ከሸፈ እንጂ ከክብር ትሪቡን ወርዳችሁ ‹‹የታሪክን ወርክሾፕ›› እንድትጎበኙ ለማድረግ አስቤ ነበር፡፡ ከ‹‹ታሪክ ወርክሾፕ›› ገብተን፤ የተለያዩ የታሪክ ዕቃዎች የምርት ሂደት ምን እንደሚመስል የማየት ዕድል እንድታገኙ አስቤ ነበር፡፡ አልተቻለም፡፡
ለጊዜው በአቶ ዮሐንስ ሰ. ትንታኔ መቆዘም እንችላለን፡፡ በ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› የምናውቃት የዲማው ጊዮርጊስ ፊታውራሪ መሸሻ አንድያ ልጅ የሆነችው ሰብለወንጌል፤ በሰፊው የአባቷ ግቢ ቁጭ ብላ አረንጓዴ ስጋጃ ምንጣፍ የተነጠፈበት መስሎ የሚታየውንና ልዩ ልዩ ቀለማት ባላቸው አበቦች የተዋበውን ምድረ ግቢ እየተመለከተች፣ በአበቦቹ ዙሪያ እየበረሩ የሚዳሩትን ቢራቢሮዎች ባስተዋለች ጊዜ፤ ክስተቱን ከራሷ በጌትነት የተሸፈነ የባርነት ህይወትና ከአገልጋይዎቿ ከካብትሽ ይመርና ከባለ አንዲሩ ገብሬ ባርነት የመሰለ የነጻነት ህይወት ጋር በማነጻጸር የተፈጠረባትን ስሜት እንዳስታውስ አድርጎኝ ነበር። ሰብለ ወንጌል በክረምቱ እንዲያ አምሮ የሚታየው የአባቷ ምድረ ግቢ፤ በበጋ አመድ እንደሚመስል በማስታወስ ክስተቱን ከራሷ (ከሰው) ህይወት ጋር አዛምዳ በማየት ትልቅ ሐዘን እንደተሰማት፤ እኔም የአቶ ዮሐንስን ጽሑፍ ሳነብብ፤ በሰፊው የታሪክ ምድረ ግቢ ተቀምጬ፤ አንዴ በውብ አበቦች የሚያጌጠውን - ሌላ ጊዜ ደግሞ አመድ ተነዝቶበት የሚታየውን የሰውን ልጅ የማህበራዊ ህይወት በመመልከት፤ ከሰብለወንጌል ተመሳሳይ የሆነ የሐዘን ስሜት አደረብኝ፡፡
የአቶ ዮሐንስን የትንታኔ ፈለግ ተከትዬ ከታሪክ ምድረ ግቢ ስገባ፤ ማህበራዊ ስርዓት በታሪክ ምድረ ግቢ የበቀለ ሣር መስሎ ታየኝ፡፡ ማህበራዊ ስርዓት፤ በክረምት እንደ ሣር ለምልሞ ይቆይና፤ በጋ ሲመጣ ደርቆ - ተረጋግጦ ይጠፋል፡፡ የሄግልን መነጽር አድርጌ የህብረተሰብን ታሪክ ስመለከት፤ ስርዓት እንደ ሰው ሲወለድ፤ ሲያረጅና ሲሞት አየሁ፡፡ ነባራዊና ህሊናዊ ነገሮች ሲሟሉ የአሮጌ ስርዓት ሞትና የአዲስ ስርዓት ልደት ይበሰራል፡፡ በአሮጌው ስርዓት ማህጸን ሁሌም አዲስ ስርዓት ይረገዛል፡፡ አሮጌው ስርዓት ገድሎ የሚያስወግደውን አዲስ ስርዓት አርግዞ ይወለዳል፡፡ የሟቹን ስርዓት ተዝካር በልቶ፤ አዲሱ ስርዓት ይቆማል። ሁሉም ስርዓት፤ የዕድሜ ዘመኑ ምዕራፍ ሲቃረብ፤ እንደ ሽማግሌው ሶቅራጥስ ‹‹ትውልድን ታበላሻለህ›› የሚል ክስ ይቀርብበታል፡፡ የታሪክ ባለሟሎች ወህኒ ያወርዱታል፡፡ ይታሰራል፡፡ በደቀ መዛሙርቱ ምልጃና ልመና ከወህኒ ወጥቶ ከሞት መሸሽ አይችልም፡፡ ጽዋው ሲሞላ ጠብቆ፤ እንደ ሶቅራጥስ የ‹‹ኮንዮን›› ጭማቂ ዥው አድርጎ ጠጥቶ፤ ለመልዐከ ሞት እጁን ይሰጣል። ከምድረ ገጽ ይሰናበታል፡፡
ይህን ጉዳይ አንድ የሥነ ሰብእ ምሑር በፔንዱለም መስሎ ሲተርከው አውቃለሁ፡፡ የሰዎች ስግብግብነት ፔንዱለሙን ወዲያ - ወዲህ ያደርገዋል ይላል። በስግብግብነት የሚራኮቱ የማህበረሰብ አባላት የሐብት ወይም የስልጣን ሽሚያ ውስጥ ሲገቡ፤ አሸናፊው ወገን ፔንዱለሙን አለመጠን ወደ አንድ ጫፍ ስቦ ይወስደዋል። ሆኖም ወዲያ ተስቦ ብዙ ሊቆይ አይችልም፡፡ በስበቱ የሚጎዳ ህብረተሰብ በቁጣ ይነሳል። በቁጣ ገመዱን ወደ እሱ ለመጎተት ይሞክራል። ያኔ ፔንዱለሙ በኃይል ተወንጭፎ እንደገና ወደ ሌላው ጫፍ ይወረወራል። ይሄዳል - ይመለሳል፡፡ ሲሄድ - ሲመለስ ግን ዝም ብሎ አይደለም፡፡ የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀነጠሰ ነው፡፡ ጎዳናውን በደም እያጨማለቀ ነው፡፡ ‹‹እስኪ ወዲያ ሄደሽ፤ ወዲህ ተመለሺ፤ እኔም ደስ ይበለኝ፤ ሰዎቹም ይዩሽ›› እያለ ይዘፍናል፡፡ ታዲያ ይህ ፔንዱለም በእርጋታና በሰላም ተንጠልጥሎ የሚረጋው ፍትሕ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ፤ አቶ ዮሐንስ እንዳሳዩን፤ አንዴ ‹‹በመንግስት መግነን›› ወዲህ ይወነጨፋል፤ ሌላ ጊዜ ‹‹በግለሰቦች ነጻነትና በህግ የበላይነት›› ወዲያ ይምዘገዘጋል፡፡ ስለዚህ ፔንዱለሙ በነገር አያያዛችን ኃይል ወዲያ - ወዲህ መወዛወዙን ይቀጥላል፡፡
የታሪክ ወንጌል  
አሁን ህዝባዊ ቁጣ አለ፡፡ ህዝባዊ ቁጣ ከድህነት ጋር ይያያዛል፡፡ ድህነት ደግሞ ከፖለቲካ መዋቅር ችግር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመሆኑም ከድህነት ለመላቀቅ ፖለቲካዊ መዋቅር እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል። ፖለቲካዊ መዋቅርን ለማሻሻል ደግሞ ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ አስፈላጊ ነው፡፡ ግን ሁሉም ህዝባዊ ንቅናቄዎች የህዝብን ህይወት የማሻሻል ውጤት ፈጥረው አይጠናቀቁም፡፡ በመጀመሪያ፤ የአንድ ህብረተሰብን አደረጃጀት የሚቀይር የለውጥ እንቅስቃሴ ሲደረግ፤ ለውጥ ፈላጊዎችና ነባሩ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣኑን የያዙትና የስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑት ወገኖች ለውጡን በመቃወም ይነሳሉ፡፡
የሁሉንም የህብረተሰብ የለውጥ ሒደት የመመልከት ዕድል ያለው ታሪክ፤ እንደ ክርስቶስ በአጭር ቁመት - በጠባብ ደረት ተወስኖ በመካከላችን እየተመላለሰ ‹‹ህብረተሰባዊ ወንጌል›› (Social Gospel-ይህ ቃል ሌላ ፍቺ እንዳለው አውቃለሁ) ሊሰብክና ሊያስተምረን ቢመጣ፤ ‹‹ከኦሪት ዘፍጥረት›› እየጠቀሰ የሚነግረን፤ ህብረተሰብ ለውጥ ፈሪ መሆኑን ነው፡፡ በለውጥ ፈላጊው ሰፊ ህዝብና የፖለቲካ-ኢኮኖሚውን መዋቅር በፍላጎታቸው አምሳል ቀርጸው፤ ከመንበረ-ሥልጣን ተቀምጠው፤ በትረ-ሙሴን ጨብጠው፤ የሆነ ስርዓት አስፍነው ህዝብ በሚገዙ ወይም በሚያስተዳድሩ ልሂቃን በኩልም ሆነ በለውጥ ፈላጊ ህብረተሰብ ወገን በተደጋጋሚ የሚፈጸም የጅል ስህተት መኖሩን ይነግረን ነበር፡፡
ህብረተሰባዊ ለውጥ ማምጣት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አሁን እንደ ቀላል ነገር ሊታዩ የሚችሉ፤ እንኳን በዕድሜ የበሰለ፤ በቀለም የተጠመቀ ሙሉ ሰው ቀርቶ፤ አፍ የፈቱ ህጻናት ጭምር የሚያውቁትን ነገር (ለምሣሌ መንግስት በህዝብ ምርጫ ሊቋቋም እንደሚችል ማሰብ) ለመረዳትና ለመቀበል የማይቻልበት ዘመን አሳልፈናል፡፡ ንጉሡ ከወረዱ ፀሐይ ትጠልቃለች ሲሉ አምነን ተቀብለናል፡፡
የአሁኑን ህገ መንግስታዊ ስርዓት ከማግኘታችን በፊት እንደ ሐገር ተደጋጋሚ ስህተት ሰርተናል። ታሪክ በወንጌል ከሚነግረን እውነቶች መካከል ‹‹ህዝብ እና ገዢዎች ደጋግመው ካልተሳሳቱ በቀር የታሪክን ትምህርት አይረዱትም›› የሚል ቃል አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሌም በለውጥ ፈላጊ ኃይል (ኃይሎች) እና ነባሩ ስርዓት እንዲቀጥል በሚፈልጉ ወገኖች መካከል ፖለቲካዊ ግጭት ይኖራል፡፡ ለውጡ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፤ ከለውጡ ቅኝት ጋር ተስማሚ የሚሆን አቋም በመያዝ፤ ለለውጥ ፈላጊው ህብረተሰብ ጥያቄ ምላሽ በሚሰጥ አኳኋን ራሳቸውን አስተካክለው በመሄድ፤ በፖለቲካዊ ግጭት ምክንያት ሊፈጠር የሚችልን አደጋ በማስቀረት፤ ለህዝብ ጥያቄ ትኩረት ሰጥተው፤ አጽንተው ያቆሙትን የህብረተሰብ አደረጃጀት አፈራርሰው፤ በአዲስ አደረጃጀት በመቀየር ለመጓዝ የሚችሉ ገዢዎች ብዙ ጊዜ አይገኙም፡፡ ብዙዎቹ ነባሩን ነገር አጥብቀው በመያዝ ድርቅ ብለው ይቆሙና በለውጡ ማዕበል ተጠራርገው ከፖለቲካው መድረክ ተወግደው፤ ቅርሳቸውን በታሪክ ግምጃ ቤት አኑረው ይጠፋሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ ለውጥ ፈላጊዎቹም የለውጥ ባለሟል የሆኑት ‹‹ህሊናዊ እና ነባራዊ›› ቀስ በቀስ አድገው፤ ለአቅመ-ለውጥ እስኪደርሱ ድረስ፤ የታሪክ ስር - ሚዜዎች  ከየቦታው ተሰባስበው፤ ተኳኩለው - አምረው ለአጀብ እስኪገኙ ድረስ፤ ብቅ ጥልቅ የሚሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ተመልክተው የሚጎዱ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ የለውጥ ንቅናቄ በአንድ ጀምበር ተጠንስሶ፣ ተሸሞ፣ ተብላልቶ፣ ፈልቶ፣ ጉሹ ጠርቶና ጠልሎ ለመጠጥ አይደርስም፡፡ በእርግጥ ጉሽ የለውጥ ጠላ ጠጥተው የሚሰክሩ ይኖራሉ፡፡ ሰክረውም ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ የህዝብ የለውጥ ንቅናቄ እንደ ውቂያኖስ ለመምቴ ማዕበል እየሰገረና እየፎገላ መጥቶ፤ በግብታዊ ኃይል የስርዓቱን ዳር ዳር በእሣት ምላሱ እየላሰ ለወዲያው አስደንግጦ ይመለሳል፡፡ እንደገና የወትሮውን ባህርይውን የያዘ መስሎ ተደላድሎ ይተኛል፡፡ የለውጥ ንቅናቄዎች ሁሉ ተፈላጊውን ለውጥ ወይም የብልጽግና ጎዳናን በመክፈት አይጠናቀቁም፡፡ የለውጥ ንቅናቄዎች የለውጥ ኃይል ተሞልተው ይመጣሉ እንጂ፤ በፍጻሜው ግባቸውን ሊያሳኩ አለያም ሊመክኑ ይችላሉ፡፡ በውድቀት ወይም በስኬት የመጠናቀቅ ዕድል ይዘው የሚጓዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለውጥ ፈላጊዎች በታሪክ ፊት ደጋግመው ሲሳሳቱ የተመለከተ የታሪክ ‹‹ሊቀ ካህን›› በለውጥ ንቅናቄ የተነሳ ህዝብ አስተውሎ ሊሄድ እንደሚገባ ምክር መለገሱ አይቀርም፡፡
አቶ ዮሐንስ ሰ. እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በ1966 ዓ.ም ያገኘውን ዕድል በሚያተርፍ ጎዳና ለመምራት አልቻለም፡፡ በ1966 ያገኘነውን የለውጥ ዕድል በጁንታዎች ተነጥቀን የመከራ ዘመን ጎትተናል። የግብጽ ህዝብም በቅርቡ ያገኘውን ዕድል የብዙዎችን ህይወት ሊቀይር በሚችል አግባብ ከዳር ሊያደርሰው አልቻለም፡፡ የግብጽ አብዮት አንድን ጨቋኝ የልሂቃን ቡድን፤ በሌላ ቡድን ከመተካት በቀር የሚሊዮኖችን ህዝብ ለመቀየር የሚያስችል ዕድል ይዞለት አልመጣም። አሁን ያለው ሁኔታ የእኛም ነገር ተመሳሳይ ዕድል የሚገጥመው እንዳይሆን አስጊ ነገሮች ይታያሉ፡፡
የተቋማት ምስጢር  
ጸሐፊው ‹‹እኛ [አፍሪካውያን-ኢትየጵያውያን] በመልካም የለውጥ ሽታ አማካኝነት፣ በስፋትና በፍጥነት ተጠቃሚ ለመሆን ብዙ አንተጋም፡፡ በመጥፎ የለውጥ ወረርሽኝ፣ በስፋትና በፍጥነት ተጎጂ እንዳንሆን በአስተዋይነት ጥፋትን አንከላከልም›› ብለዋል፡፡ ትክክል ነው፡፡ ስለዚህ ፔንዱለሙ በአደገኛ ሁኔታ እንዲወናጨፍ እናደርገዋለን፡፡ በእርግጥ አቶ ዮሐንስ እንዳሉት፤ ‹‹በመጥፎዎቹ የለውጥ ወረርሽኞች ሳቢያ፣ አውሮፓና አሜሪካ መጎዳታቸው አይቀርም፡፡…..›› በዚህም ጊዜ ፔንዱለሙ በመጠኑ ይወናጨፋል። መንግስታት በየጊዜው በሚለዋወጥ ‹‹ታክስና በመመሪያዎች ብዛት አማካኝነት›› ፔንዱለሙን ያናውጡታል፡፡ አውሮፓና አሜሪካ መንግስታት፤ የመንግስት ሥልጣንን በመጠቀም የረጋውን ፔንዱለም ሊያስቆጡት ይችላሉ፡፡ አለያም በዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከል የሚሰሩ ባለሟሎች ወይም ለነዚህ ተቋማት የተቀጠሩ ምሁራን የለውጥ ሐሳብ ቀስቅሰው ፔንዱለሙን ሊያወዛውዙት ይችላሉ፡፡
አቶ ዮሐንስ፤ በየጊዜው የሚነሳው ወረርሽኝ፤ በአውሮፓና በአሜሪካ በእኛ ሁኔታ እንደሚታየው ‹‹….አገሬውን የሚያተራምስበት ደረጃ ላይ አይደርስም። [ምክንያቱም በዚያ] ወረርሽኙን የሚያስፋፉ ብቻ ሳይሆኑ፤…ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ለመመከትና ለመመለስ የሚጣጣሩ በርከት ያሉ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ዜጎች አሏቸው›› ብለዋል፡፡ ትክክል ነው። ግን አንድ ነገር ሊጨመር ይገባል፡፡ እነዚህ ‹‹ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ዜጎች›› ወደ እኛ ሐገር ቢመጡ ብዙ ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ይልቅስ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነው ይቆማሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በእኛ ሐገር ለውጥ ባያመጡም፤ በሐገራቸው ለውጥ ለማምጣት ይችላሉ። በሐገራቸው ‹‹ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ለመመከትና ለመመለስ›› ሲችሉ፤ ወደ እኛ ሐገር መጥተው ቢሰሩ ያን ያህል ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
እነዚህ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ዜጎች ለውጥ ለማምጣት፤ ችግር ሆኖ የታያቸውን ነገር ያለ አንዳች ሰቀቀን ለመናገር የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ በሚናገሩት ነገር የተከፋ ሰው ወይም ቡድን ጥቃት ሊያደርስባቸው እንደማይችል ተማምነው የመናገር ድፍረት ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት ለማጥቃት የፈለገ ሰው ቢነሳም፤ ከጥቃት ለመከላከል የሚችሉ የታመኑ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል፡፡ ስለዚህ ዋናው ጉዳይ የተቋማት ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ጠንካራ ተቋማት (የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ…..) በሌሉበት ሐገር ቢሄዱ ብዙ ለውጥ አያመጡም፡፡ የባህል፣ የእምነትና ታሪክ ጉዳዮችም መሰናክል ሆነው ቀፍድደው ሊይዟቸው ይችላሉ፡፡
‹‹በአፍሪካና በአረብ አገራት የዜጎች ንዴትና የመንግስት ምላሽ ማለት፣…ግድያና እስር፣ በዘር መቧደንና መተራመስ›› የሚሆነው እኛ አንድ ነገር ስለጎደለን ነው፡፡ ‹‹ደግ የለውጥ ዕድሎች በትጋት ለመጠቀም፤ ክፉ የለውጥ ወረርሽኞችን ለመከላከል›› የምንችለው አንድ ነገር ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ይህም ነገር ተቋም ነው፡፡ ይህ ነገር ተቋም የሚሉት ድንቅ ነገር ነው።
‹‹Why Nations Fail›› የተሰኘ  መጽሐፍ የጻፉት ምሁራን፤ ‹‹ሐገራትን ድሃ ወይም ሐብታም የሚያደርጋቸው፤ የልዩነታቸው ምስጢርና የመለያየታቸው መንስዔ፤ በነዚህ ሐገራት የሚገኙ ተቋማት ናቸው›› ይላሉ፡፡ ትንታኔአቸውን በዚህ ሐልዮት ላይ አቁመው  ሐሳባቸውን ያስነበቡን እነዚህ ምሁራን፤ ባለጸጋዎቹ ሐገራት የብልጽግና ጉዞን ሲጀምሩ የስራቸው መነሻ ፖለቲካዊ ተቋማትን ማሻሻል መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ የዓለምን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ እየፈተሹ ዋቢ እየጠቀሱ ሐሳባቸውን ለማብራራት ይሞክራሉ፡፡
በዚህ ትንታኔአቸው ወደ ኋላ አራት መቶ ዓመታት በመሄድ ይነሳሉ፡፡ ከቅርቡም ‹‹የአረብ ጸደይ››ን ጠቅሰው፤ ሆስኒ ሞባራክን ከስልጣን ያስወገደውን የግብፅ ህዝባዊ አመጽ ያጣቅሳሉ፡፡ በሚያቀርቡት ትንታኔ፤ የዓለም ህዝቦችን ህይወት እንዲሻሻል ያደረገ የፖለቲካዊ ተቋማት ለውጥ የተፈጠረው ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ባለው ህዝባዊ ንቅናቄ መሆኑን ያመለክታሉ። ህዝቦችን ለብልጽግና ህይወት የሚያበቃ እንዲህ ያለ ሥር ነቀል የፖለቲካ ተቋማት (transformations) ለውጥ የሚያስከትል የህዝብ ንቅናቄ መቼ እና ለምን እንደሚፈጠር ለማወቅ ከቻልን፤ ህዝባዊ ንቅናቄዎቹ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደታዩት ንቅናቄዎች ስኬት አልባ ጥረት እንደሚሆኑ ለመረዳት ወይም የሚሊዮኖችን ህይወት የሚያሻሻል ስኬታማ ጥረት መሆን-አለመሆናቸውን ለመመዘን ጥሩ አቋም ያስይዘናል፡፡
የፖለቲካ ተቋማት ጉዳይ የተጻፈ ህገ መንግስትንና የዴሞክራሲ ጎዳና የሚከተል ህብረተሰብ የመኖር - አለመኖር ጉዳይን ያካትታል እንጂ በእነሱ ብቻ ተወስኖ የሚያበቃ ጉዳይ አይደለም፡፡ Political institutions include but are not limited to written constitutions and to whether the society is a democracy.  የፖለቲካ ተቋማት ጉዳይ፤ የመንግስት በስልጣን የመጠቀም አቅምና ህብረተሰብን የማስተዳደር ብቃት የመያዝ ጉዳይ ነው። እንዲሁም፤ መንግስት ሁሉም ሰው ህግ አክባሪ ሆኖ ህይወቱን እንዲመራ ለመቆጣጠር የሚያስችል ብቃት የመገንባቱን ጉዳይ ይመለከታል፡፡ ይኸ ብቻ አይደለም። ነገሩን ሰፋ አድርጎ በማየት፤ በህብረተሰቡ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን የሚከፋፈልበትን አግባብ የሚወስኑ ጉዳዮችን፤ በተለይም የተለያዩ ቡድኖች ዓላማቸውን ለማሳካት ያላቸውን ችሎታ ወይም ከእነርሱ ዓላማ ተጻራሪ የሆነ ግብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉትን አፍራሽ እንቅስቃሴ ለመግታት ያላቸውን ችሎታም ይመለከታል፡፡ የፖለቲካ ተቋማት ጉዳይ እነዚህን ነገሮች እንደሚያካትት መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡
የተቋማት ጉዳይ፤ በህብረተሰብ ተጨባጭ ህይወት ውስጥ ሰዎች የሚኖራቸውን ባህርይና የስራ ተነሳሽነታቸውንም የሚወስኑ በመሆናቸው፤ የሐገራትን ውድቀት ወይም ስኬት የመወሰን ችሎታ ያላቸው ናቸው፡፡ በየትኛውም የህብረተሰብ እርከን የግለሰቦች የፈጻሚነት ችሎታ ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም፤ ይህ የፈጻሚነት ችሎታ አወንታዊ ኃይል ወደ መሆን መሸጋገር የሚችለው ጥሩ ተቋማዊ ማዕቀፍ ሲኖር ነው፡፡ ለምሣሌ፤ የማይክሮ ሶፍት ባለቤት ቢል ጌትስ፤ በመረጃ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንደ ተሰማሩ ሌሎች ሥመ ጥር ቱጃሮች (ፖል አለን፣ ስቲቭ ቦልመር፣ ስቲቭ ጆብስ፣ ላሪ ፔጅ፣ ስርጂ ብሪን እና ጄፍ ቤዞስ) እጅግ ከፍተኛ የፈጻሚነት ችሎታና ሥራ የመስራት ታላቅ መሻት ያላቸው ሰው ነበሩ፡፡ አሁንም ናቸው፡፡ ይህ እውነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ዞሮ ዞሮ የቢል ጌትስ የፈጻሚነት ችሎታ እውን መሆን የቻለው፤ በአካባቢያቸው አበረታች ሁኔታ በመኖሩና ያን ምቹ ሁኔታ እንደ መስፈንጠሪያ ተጠቅመው መሥራት በመቻላቸው ነው። የቢል ጌትስና የሌሎች መሰሎቹ እምቅ የፈጻሚነት ችሎታቸውን እውን ለማድረግ የሚያስችል ልዩ ልዩ እና ድንቅ ክህሎቶችን ማግኘት ያስቻላቸው የአሜሪካ የትምህርት ዘይቤ ነው፡፡ የአሜሪካ የኢኮኖሚ ተቋማት እነዚህ ሰዎች ከባድ እንቅፋት ሳይገጥማቸው በቀላሉ ኩባንያ መስርተው ሥራ መጀመር የሚችሉበትን ቀና የሆነ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡
እነዚህ የኢኮኖሚ ተቋማት፤ እነ ቢል ጌትስ ያረቀቁት ፕሮጀክት በፋይናንስ እጦት ከንቱ ህልም ሆኖ ነው እንዳይቀር ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው። የአሜሪካ የጉልበት ገበያም ቢል ጌትስ የሰለጠነ የሰው ኃይል በቀላሉ መቅጠር፣ እንዲሁም በአንጻራዊ ሚዛን ውድድር በሰፈነበት የገበያ ስርዓት ውስጥ ኩባንያቸውን በየጊዜው በማስፋፋትና ምርታቸውን ለመሸጥ የሚያስችል ሁኔታን አመቻችቶላቸዋል። እነዚህ ሥራ ፈጣሪ ሰዎች ገና ከመነሻው ያለሙት ፕሮጀክት እውን እንደሚሆን መተማመን አሳድረው የተነሱ ናቸው፡፡ በተቋማቱ ላይ እምነት አላቸው፡፡ ተቋማቱን መሠረት አድርጎ የቆመው የህግ የበላይነት መርህ አለኝታ ሆኖ ይታያቸዋል፡፡ ስለ ንብረት መብቶቻቸው መከበር ጭንቀት አያድርባቸውም፡፡ በመጨረሻም፤ የፖለቲካ ተቋማቱ ሰላም፣ መረጋጋትና ቀጣይነትን ያረጋግጡላቸዋል፡፡
አንድ አምባገነን ተነስቶ ሥልጣን መያዝ የሚችልበት ዕድል እንዳይኖርና የጨዋታ ህጉን እንዳያፈራርሰው፣ ሐብታቸውን እንዳይወርሰው፣ እነሱንም ወህኒ እንዳይረውራቸው፣ ህይወታቸውንና የኑሮ መሠረታቸውን እንዳይንደው፤ እንዲህ ያለ ሰው ሥልጣን ለመያዝ የሚችልበት ዕድል ዝግ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የተለየ ጥቅም ለማራመድ የተደራጁ ቡድኖች ኢኮኖሚውን ገደል ውስጥ በሚከት ጎዳና እንዲጓዝ ለማድረግ ተጽዕኖ በመንግስት ላይ ለማሳረፍ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም፤ የፖለቲካ ስልጣን በህግ የተገደበና ሁነኛ በሆነ መጠን ለተለያዩ አካላት እንዲከፋፈል በመደረጉ፤ ለብልጽግና ለመሥራት ተነሳሽነት መፍጠር የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ተቋማት እንዳያብቡ አንቆ የሚይዝ ችግር አይገጥማቸውም፡፡

Read 3127 times