Monday, 26 September 2016 00:00

ዓሣ ለማጥመድ ዛፍ ላይ አይወጣም ሞጋችና መብቱን ጠያቂ ህዝብ የፈጠረው…እውን ኢህአዴግ ነው??

Written by  አልአዛር.ኬ
Rate this item
(16 votes)

     የረዥሙን ዘመን የታሪክ ድርሳናቸውን ማገላበጥ የቻለ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው የደረሰባቸውን የመብት ረገጣ፣ አፈናና፣ ብሄራዊ ጭቆና አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን ሲቃወሙ መኖራቸውን በቀላሉ መረዳት ይችላል።
የዛሬ አርባ ሶስት አመት ኢትዮጵያዊያን ያካሄዱት ህዝባዊ ተቃውሞ አይደፈሬ ነው ሲባል የነበረውን ዘውዳዊ አገዛዝ እስከ ወዲያኛው ገርስሶታል፡፡ የኢትዮጵያውያን የፀረ-ጭቆናና የነፃነት ትግል የቅርብ ጊዜው ታሪክ ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያውያን በኢህአዴግ መሪነት ለአስራ ሰባት አመታት ባካሄዱት መራራ የትጥቅ ትግል፣ ለመቸውም የሚወድቅ የማይመስል የነበረውን የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ የዛሬ ሀያ አምስት አመት ማስወገድ ችለዋል፡፡
ብሔራዊ ስልጣን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ፤ ላለፉት ሀያ አመታት በሱ ግንባር ቀደምና ወሳኝ አመራር፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ስርአት በመገንባቱ፣ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ህገመንግስታዊ እውቅናና ዋስትና አግኝተው መከበራቸውን፤ እንዲሁም መንግስትና ሀይማኖት መነጣጣላቸውንና የሃይማኖት እኩልነት መረጋገጡን ባገኘው ጊዜና አጋጣሚ ሁሉ በከፍተኛ ስሜት ሳያስገነዝበን ያለፈበት ወቅት የለም፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፤ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አይነት ፌዴራላዊ የእኩልነት ስርአት ገንብቶ፤ የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት እኩልነት በሚገባ ማስከበር እንደቻለ ያልማለበትና ያልተገዘተበት ጊዜ የለም፡፡
በተለይ ደግሞ ኢህአዴግ ባቋቋመው ልማታዊ መንግስትና በሚከተለው ‹‹ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር››፤ የሀገራችን ኢኮኖሚ ላለፉት አስራ ሶስት አመታት ባለ ሁለት አሃዝ ተከታታይ እድገት በማስመዝገብ፣ የህዝቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደቻለ ጧትና ማታ በከፍተኛ ኩራት ሳይሸልልብን፣ በምስራቅ የወጣችው ጀምበር፣ በምዕራብ እንደማትጠልቅበት ቋሚ ምስክር ነን። በአንፃሩ ደግሞ በርናርድ ሾው፤ ‹‹ራስን ማሞካሽት መቸም ቢሆን የመልካም ስራ ማስረጃ ሊሆን አይችልም›› ብሎ እንደተናገረው፤ ምንም እንኳ ኢህአዴግ የአመራር ገድሉን እየዘረዘረ ራሱን ቢያሞካሽም ኢትዮጵያውያን ግን ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብታቸው እንዲከበር፣ ማንነታቸውና ነፃነታቸው እንዲረጋገጥ፣ በሀይማኖት ጉዳያቸው ላይ የሚደረግ ማናቸውም አይነት ጣልቃ ገብነት እንዲቆምና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ጥያቄ ከማቅረብና ከመሟገት ቦዝነው አያውቁም፡፡
‹‹የማያለቅስን ህፃን እናቱ አታጠባውም›› እንደሚባለው፣ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያቀረቡት የመብትና የማንነት ጥያቄ፤ አገሪቱን በሚመራው በኢህአዴግ ዘንድ በወጉ መደመጥና መስተናገድ አለመቻሉ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳስቆጣውና ለታላቅ አመጽና ተቃውሞ እንደ ገፋፋቸው ግልጽ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያውያን ላፉት ጥቂት ወራት ካካሄዱት አመጽና ተቃውሞ ይልቅ ወገብ የሚሰብረውን የመብት ረገጣና ጭቆና ለረዥም አመታት በከፍተኛ ትዕግስት ተሸክመው መቆየት መቻላቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡
ኢህአዴግ በህዝቡ ቁጣ ቆሽቱ እርር ድብን በማለቱ አመዱን እንደ ‹‹ቅብጠት ወይም ‹‹ጥጋብ›› እንደቆጠረው ያወጣው መግለጫ  ቢያሳብቅበትም ለወዳጅም ሆነ ለጠላት ደስ አይበለው በሚል ስሜት ደንግጦና ፈርቶ መታየትን አልፈለገም፡፡
ይልቁንስ የመረጠው ዘዴ፣ የህዝቡ ቁጣና አመጽ የእሱ የአመራርና የስራ ውጤት እንደሆነ በማስረዳት፤ ከዚህ ሊገኝ የሚችል አንዳች አይነት ፖለቲካዊ ጥቅም ካለ ለመውሰድ መሞከር ነው፡፡
እናም ኢህአዴግ በአሮሚያና በአማራ ክልል አመጽ ሊቀሰቀስ የቻለው ፀረ ሰላም በሆኑ የውስጥና የውጭ ሀይሎች ገፋፊነት ነው ብሎ በተደጋጋሚ የሰጠውን መግለጫ ጨርሶ እንዳልተሰጠ በመቁጠር፣ አንጋፋ መሪዎቹ በኢቢሲ የቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው፤ ‹‹አመጽ የተቀሰቀሰው ኢህአዴግ ሞጋችና መብቱን ጠያቂ ህዝብ መፍጠር በመቻሉ ነው፡፡›› ብለው እንዲያስረዱ አድርጓል፡፡
በዚህ መርካት ያልቻለው ኢህአዴግ፤ መብቱን የማይጠብቅና የማይሞግት ይልቁንም ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋልን፣ ፀረ-ዲሞክራሲ፣ አስተዳደራዊ በደልንና ወገንተኛ አሰራርን ተሸክሞ የሚጓዝ ህዝብ፤ የልማት አቅም መሆን እንደማይችል ተጨማሪ ማብራሪያውን በማህበራዊ ድረ-ገጹ አሰራጭቷል፡፡
እንግዲህ ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ህዝብ የፀረ-ጭቆና ትግል ታሪክ ተቃራኒ በሆነ መልኩ፤ ‹‹ሞጋችና መብቱን ጠያቂ ህዝብ የፈጠርኩ እኔ ነኝ።›› በሚል የነገረንን ሁሉ ‹‹ግዴለም ይሁንልህ›› ብለን ለጊዜው እንቀበለው። እዚህ ላይ  ይሁንልህ ብለን የማናልፈውን አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ግን እናቅርብ፡- ኢህአዴግ ወገብ በሚያጎብጥ ርብርብ ፈጠርኩት ያለውና ‹‹ለልማታዊው መስመር ጥራት እንዲሁም ለህዳሴ ጉዞ መሳካት ወሳኝ ነው›› በሚል የመሰከረለት ‹‹ሞጋችና መብቱን ጠያቂ ህዝብ›› መብቱ እንዲከበርለት የጀመረውን እንቅስቃሴ ያስተናገደው ወይም ምላሽ የሰጠው እንዴት ባለ አኳኋን ነው? ወሳኙና ቁልፉ ጥያቄ ይህ ነው፡፡
በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ በመንግስትና መንግስቱን በሚመራው በኢህአዴግ ላይ ያመፁትና አደባባይ በመውጣት ተቃውሞአቸውን በግልፅ ያሰሙት፣ ለመዝናናት ሳይሆን ለአመታት የደረሰባቸው የመብት ረገጣና ብሄራዊ ጭቆና በእጅጉ እንዳስመረራቸው በማሳወቅ፣ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን ጭቆናና አፈና ተሸክመው መኖር እንደማይፈልጉ ሳይሆን ጨርሶ እንደማይችሉ በግልጽ ለማሳየት ነው። ኢህአዴግም ቀደም ብሎ እንደተገለፀው፤ የተቀዛቀዘ ህዝባዊ ተሳትፎ ወይም ህዝቡ ሞጋችና መብቱን ጠያቂ ካልሆነ፣ የመንግስትን ረጃጅም እጆች በመጠቀም ኪሱን የሚያደልብ የአመራር አካል እንዲፈጠርና ዋናውን ‹‹የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር፣ መሪዎች›› በማበስበስ የመደብ ሽግግር እንዲያደርጉና አብዮታዊነታቸውን በመሸርሸር ባለህበት ርገጥ ወደሆነው የአፍሪካ መንግስታት ባህርይ እንዲቀየር ያደርገዋል በማለት፣ ስለ ህዝቡ አመጽ ትክክለኛነት ቃሉን በግልጽ ሰጥቷል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ አሁን ያሉበትን ችግሮችን ህዝቡ ለሚቀጥሉት አመታት ተሸክሞ ቢቆይ ኖሮ የስርአቱ አደጋ ይሆን ነበር በማለት፣ የህዝቡ አመጽና የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተገቢ መሆኑን አምኖ መቀበሉን በይፋ አሳውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የህዝቡ አመጽና ተቃውሞ ትክክለኛና ተገቢ ነው ብሎ የእምነት ቃሉን የሰጠው ኢህአዴግ፤ ይህን የህዝብ አመጽና የተቃውሞ እንቅስቃሴ ያስተናገደው  ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ፤ ሳይሆን ከፍተኛ ወታደራዊ ሀይል በማሰማራትና በጉልበት ለማፈን በመሞከር ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን አፈናን፣ ጭቆናን በመቃወም ለመብታቸው መከበር ላደረጉት ለዚህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ፣ ‹‹ሞጋችና መብታቸውን ጠያቂ›› እንዲሆኑ አደርጌአቸዋለሁ ብሎ በከፍተኛ የኩራት ስሜት ከሸለለው ኢህአዴግ ከሚመራው መንግስት ያገኙት ምላሽ፤ ግንባራቸውን በጥይት መፈርከስና ደማቸው ለጎዳና አፈር ሲሳይ መሆን ብቻ ነው፡፡
መቼም ማንም በቀላሉ መረዳት እንደሚችለው፤ በአገር ጤና አሳ ለማጥመድ ዛፍ ላይ አይወጣም። ኢህአዴግ ያደረገው ግን ልክ እንደዚህ ነው፡፡ ጣሊያኖች ይህን አይነቱን የኢህአዴግ በእብሪትና፣ በማናለብኝነት የተሞላ ድርጊት በሚገባ የሚገልጽ አንድ አሪፍ አባባል አላቸው፡፡ ‹‹የማይረባ አናጢ ከመጋዙ ጋር ይጣላል። ይላሉ፡፡ ኢህአዴግም በመቶ አመትም እንኳ ቢሆን ማሸነፍ የማይችለውን አምባጓሮ የጫረው የሁሉም ነገር ዋነኛ ባለቤትና ባህር ከሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ተቃውሟቸውን በመግለጽ ላይ እንዳሉ ከመንግስት ወታደራዊ ሀይል በተተኮሰባቸው የጥይት አረር ደረትና ግንባራቸውን ተመትተው በየአውራ መንገዱ ደፋ ክንብል ያሉትን ወገኖቹን ዲካ በማይገኝለት ከፍተኛ የሀዘን ስሜት ደረቱን እየደቃ ‹‹ወዮ›› ብሎ አልቅሶ ቀብሯቸዋል። የቆሰሉትንም ከወደቁበት አንስቶና ቁስላቸውን አጥቦ በማስታመም ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ወደር በሌለው ከፍተኛ የሀዘንና የሰቀቀን አለንጋ ክፉኛ እየተገረፈ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቹን ህይወት አለአግባብ የቀጠፉና አካላቸውን ያጎደሉ ባለ ጠመንጃ የመንግስት አካላት፤ አግባብ ባለው የዲሞክራሲ ተቋም ህግ በሚፈቅደው መጠን ተመርምሮና ተጣርቶ፤ አጥፊዎች በህግ ፊት የእጃቸውን ያገኛሉ ብሎ እንዳይተማመንም ሆነ ተስፋ እንዳያደርግ የከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ተሞክሮዎቹ አስገንዝበውታል፡፡
ይሁን እንጂ የአመፁን ትክክለኛነትና ተገቢነት በተመለከተ ከሠጠው መግለጫና ያለ ገደብና ከመጠን በላይ በወሰደው የሀይል እርምጃ ባጠፋው ጥፋት የተነሳ ኢህአዴግም ሆነ የሚመራው መንግስት፤ እንዲያው ሌላው ቢቀር ህዝቡን በይፋ ይቅርታ ይጠይቃሉ ተብሎ ተገምቶም ተጠብቆም ነበር፡፡ ከኢህአዴግም ሆነ ከሚመራው መንግስት የተገኘው ምላሽ ግን የህዝቡን በሀዘንና በሰቀቀን የተኮማተረ ልብ ይበልጥ ያኮራመተ ነበር። ኢህአዴግም ሆነ የሚመራው መንግስት፤ ህዝቡን እንኳን በይፋ ይቅርታ ሊጠይቁ ቀርቶ፣ ለተገደሉና ለቆሰሉት ሰዎች የተሰማቸው ሀዘን ከልባቸው ሳይሆን የለበጣ እንደሆነ በአመፁ ወቅት ለወደሙና ጉዳት ለደረሰባቸው ንብረቶች ይበልጥ እንደተቆረቆሩና እንዳዘኑ ባወጡት ዘገባና ማብራሪያ አቋማቸውን በይፋ ገለፁ፡፡
ለምሳሌ ባለፈው ነሀሴ ወር መጨረሻ አካባቢ በባህርዳርና አካባቢዋ ህዝቡ ባካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በርካታ ሰዎች እንደተገደሉና ለአካል ጉዳት እንደተዳረጉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን መንግስት ካጠፋው የሰው ህይወትና ካጎደለው የሰው አካል ይልቅ ጉዳት የደረሰበት ንብረት ይበልጥ እንዳሳዘነውና እንደቆረቆረው ‹‹በባህርዳርና በአካባቢው ሰሞኑን በተከሰተ ሁከት በስምንት የአበባና በአንድ የአትክልት እርሻ ልማት ፐሮጀክቶች ላይ ጉዳት ደረሰ›› በማለት ነሀሴ 27 ቀን 2008 ዓ.ም በመንግስት የዜና አገልግሎት አማካኝነት ባሰራጨው ዜና ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤትም በፌስቡክ ገጹ ላይ ነሀሴ 27 ቀን 2008 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ዘገባ፤ ህይወታቸውን ላጡና አካላቸውን ለተጎዳ ኢትዮጵያውያን ቁብ እንደሌለው፤ የገለፀው ‹‹በዚህ ሰሞን ከተከሰተው አስደንጋጭ ድርጊት አንዱ፣ በባህር ዳር ከተማ  ለህዝቡ የንፁህ ውሀ የሚያቀርበው ተቋም ላይ ጥቃት መድረሱ ነው፡፡›› በማለት ነው፡፡ አሁን ሁለተኛውን መሰረታዊ ጥያቄ እናንሳ፡፡ ለመሆኑ ይህን የመሰለው የኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ነገረ ስራ ምንን ያሳያል? ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡

Read 5346 times