Monday, 26 September 2016 00:00

“ታሪኩን ያጣ ትውልድ ምንጩን የማያውቅ ትውልድ ነው”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

- አፄ ምኒልክ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ጋብቻቸውን የፈፀሙበት ቤት ለግለሰብ መኖሪያነት ተሰጥቷል

   የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በአገራችን ለ29ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሰሞኑን የጉብኝት ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም ላይ በጋዜጠኞች እንዲጎበኝ የተደረገው በ1872 ዓ.ም በአፄ ምኒልክ የተሰራው የእንጦጦው ደብረኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወ ኤልያስ ቤተክርስቲያንና በዙሪያው የሚገኙት ታሪካዊ ቅርሶች ነበሩ፡፡
 ከመናገሻ ሱባ ተራራ በሰው ጫንቃ እንጨት እየተመላለሰ፣ በኖራ፣ በአሸዋና በእንቁላል አስኳል የተገነባው ይህ ቤተ ክርስቲያን፤በውስጡ ከ137 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የቅዱሳን ስዕሎችንና ሌሎች ቅርሶችን የያዘ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ቅፅር ግቢ ውስጥ የሚገኘውና ከ700 ዓመታት በፊት በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግስት ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራው ዋሻ ከታሪካዊነቱም ባሻገር እጅግ አስገራሚ ጥበብ የታየበትና የወቅቱን የስልጣኔ ደረጃ የሚያሳይ ድንቅ ሥራ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ቅፅር ግቢ ውስጥ የነበረንን ጉብኝት አጠናቀን ከመውጣታችን በፊት የአፄ ምኒልክ የቅርብ ረዳትና የመጀመሪያው የፅህፈት ሚኒስትር የነበሩት የፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ወልደአረጋይ የመቃብር ስፍራን ተመልክተናል፡፡
 ቀጣይ ጉብኝታችን የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግስት መሆኑ ተነግሮን፣ ወደዚያው ለማምራት  ጉዞ ጀመርን። የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ኃላፊዎችና አባቶች፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም የሥራ ኃላፊዎችና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ አጃቢነት ወደ ስፍራው አመራን። እየፈረሰ ያለውን የቤተ መንግስቱን የግንብ አጥር አልፈን እንደገባን የፎቶ ጋዜጠኞች በካሜራዎቻቸው ምስል ቀርፀው ለማስቀረት እንቅስቃሴ በጀመሩበት ደቂቃ የሬዲዮ መገናኛ የያዘና የፌደራል ፖሊስ አባል እንደሆነ በተነገረን ቀጭን ወጣት፤ ያነሳናቸውን ምስሎች ሁሉ ባስቸኳይ አጥፍተን ከስፍራው መጥፋት እንዳለብን ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠን። ሁኔታው በጣም ቅፅበታዊ በመሆኑ ሁላችንም ደነገጥን፡፡- ‹‹አጥፋና ከዚህ ጥፋ›› የሚለው ቀጭን ትዕዛዝ ያስደነገጠን ቢሆንም፣ የመጣነው የአለም የቱሪዝም ቀንን ለማክበር እንደሆነና ህጋዊ የሆነውን አሠራር ተከትለን ለጉብኝት በሥፍራው መገኘታችንን ለትዕዛዝ ሰጪው ወጣት ተናገርን፡፡ ምናልባትም አለቆቹ ስለ ጉዳዩ ሊያውቁ ስለሚችሉ በሬዲዮ መገናኛው እንዲጠይቅልንም ጠየቅነው፡፡ ቀድሞውንም ከእኛ ጋር መነጋገርም ሆነ የምንለውን መስማት ያልፈለገው ወጣት፤ በጉብኝቱ ላይ የነበሩትን ታላላቅ የሃይማኖት አባቶችና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል በማየቱ #ቆዩ ካላችሁበት ነቅነቅ ማለት አትችሉም” ብሎ መነጋገሪያውን በማንሳት ከሆነ ሰው ጋር ተናጋገረና “አልተፈቀደላችሁም፤ በአስቸኳይ ሥፍራውን ለቃችሁ ሂዱ” ሲል አዘዘን፡፡
ሁኔታው ግራ ቢገባኝ አስጎብኚያችን የነበረውን የደብሩን ዲያቆን ጠጋ ብዬ፤#እዚህ ሥፍራ ምን አለ?” ስል ጠየኩት፡፡ የሬድዮ መገናኛ ዋና ጣቢያ መሆኑንና በዚህ መልኩ ግን እንግዶች ወደ ስፍራው መጠጋት አንዳይችሉ ሲደረግ አይቶ እንደማያውቅ ነገረኝ፡፡ ሥፍራው ከደርግ ዘመን ጀምሮ የሬድዮ መገናኛ ዋና ጣቢያ ሆኖ ይሰራበት የነበረ ቢሆንም እነሱ ግን እንደ ልባቸው እንግዶቻቸውን ሲያስጎበኙ እንደኖሩ፣ ቤተመንግስቱና ጣቢያው የሚገኝበት ሥፍራም የተራራቀ እንደሆነ ዲያቆኑ ጨምሮ ነገረኝ። የምኒልክን ጥንታዊ ቤተመንግስት ፍራሽ የማየት ፅኑ ጉጉቴ መሰናከሉ እየቆጨኝ ሌሎች ታሪካዊ ሥፍራዎችን ለማየት ጉብኝቴን ቀጠልኩ፡፡
የንጉሱ የፈረስ ቤት እየተባለ የሚጠራው ቤት ከተቀረጹ ድንጋዮች የተገነባና በቤተመንግስቱ ለሚካሄዱ የግብር ግብዣዎች የሚቀርቡ የእርድ ከብቶችና የመኳንንት ፈረሶች ማደሪያ የነበረ ሲሆን አሁን ቀድሞ የአፄ ሚኒልክ አገልጋይ በነበሩና በፈረስ ቤቱ ውስጥ ረዥም ጊዜያቸውን ባሳለፉ ሰው ቤተሰቦች ተይዞ፣የበግና የፍየሎች ጉርኖና የምግብ ማብሰያ ቤት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ የሥፍራውን ታሪካዊነት የሚገልፅ ምንም አይነት ነገር የሌለ ሲሆን ለቤቱ የሚደረግ ጥበቃና እንክብካቤም አነስተኛ መሆኑ በእጅጉ ያስቆጫል፡፡
አፄ ሚኒልክ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ጋብቻቸውን የፈፀሙበትና በሰርጋቸው ላይ የታደሙትን እንግዶች ግብር ያበሉበት ቤት ከሁለት ወራት በፊት ቀበሌ ለግለሰቦች በመኖሪያ ቤትነት መስጠቱንም ለማየት የቻልነው በዚሁ የጉብኝት ወቅት ነበር፡፡ በአስብኚያችን ርዕሰ ደብር ህሊና ግርማ እንደተነገረን፤ ቤቱ ንጉሱ ከእቴጌይቱ ጋር ጋብቻቸውን የፈፀሙበት፣ እንግዶቻቸውን ግብር ያበሉበት ሲሆን በቤቱ ግድግዳና ጣሪያ ላይ የንጉሱና የንግስቲቱ ስምና ምስሎች ተቀርፀው የተቀመጡበት እንደሆነ ነግረውናል፡፡
ሥፍራው ተገቢው እንክብካቤና ጥበቃ ተነፍጎት የቆየ መሆኑን የገለጹት የደብሩ አስጎብኚ፤ ከወራት በፊት የአካባቢው ቀበሌ የሥራ ኃላፊዎች፤ ቤቱን ለሁለት የተለያዩ ሰዎች በመኖሪያነት እንዲጠቀሙበት መስጠታቸውን ነግረውናል፡፡ ከሁለቱ ነዋሪዎች አንደኛው የቤቱን መስኮት አፍርሰው በር ያደረጉት ሲሆን ወ/ሮ ብዙአየሁ ደገፋው የተባሉት ሌላኛዋ ነዋሪ የቤቱን ግድግዳ እበት በመለቅለቅና ጋዜጣ በመለጠፍ፣ በጣሪያው ላይ ደግሞ ማዳበሪያ በመወጠር የቤቱን ታሪካዊነትና ግርማ ሞገስ ሊያጠፋ በሚችል መልኩ በአጥር ከልለውታል፡፡  
ለመሆኑ ስለዚህ ቤት ታሪካዊነትና በቅርስ የተመዘገበ ስለመሆኑ የሚያውቁት ነገር የለም ስል የቤቱን ‹‹ባለቤት›› ጠየኳቸው፤ “እረ እኔ እቴ፤ ቀበሌ ሰጠኝ፤ ከልጆቼ ጋር አስተካክዬና አድሼ ገባሁበት፡፡” ምላሻቸው ቀጥተኛ ነበር፡፡
አስጎብኚያችንም ሆነ በሥፍራው የነበሩ የደብሩ አባቶች በሁኔታው እጅግ ማዘናቸውን፣ በተደጋጋሚ ቢናገሩም የሚሰማቸው አካል አለማግኘታቸውን የገለጹልን ሲሆን ሥፍራው ታሪካዊ ቅርሶቹንና ቤቶቹን እያጣ መሆኑን አክለው ነግረውናል፡፡ እስቲ እናንተ የሚሰማችሁ ካለ ንገሩልን” ሲሉም ልከውናል። አንድ በሥፍራው ያገኘናቸው አባት ደግሞ፡- ‹‹ታሪክ ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩን ያጣ ትውልድ ደግሞ የተበላሸ፣ ምንጩን የማያውቅና መድረሻ ቢስ ትውልድ ነው›› አሉን፤በእልህና በቁጭት ስሜት፡፡  
የዕለቱ ጉብኝት ማጠናቀቂያ በጌትፋም ሆቴል፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድና በአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገ/ፃዲቅ ሃጎስ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነበር፡፡ ከመግለጫው በኋላ በእንጦጦ እየጠፋ ስላለው ታሪክና ቅርስ በማንሳት ሚኒስትሯ ለግለሰቦች ስለተሰጠው ታሪካዊ ቤት ያውቁ እንደሆነ ጠየቅኋቸው፡፡ ሥፍራው ለግለሰቦች በመኖሪያ ቤትነት መሰጠቱን እንደማያውቁ የተናገሩት ሚኒስትሯ፤በቅርቡ በተያዘው የእንጦጦ አካባቢዎች ታሪካዊ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ፕሮጀክት፣ ችግሩ መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል ገለጹልኝ፡፡ በዚህ ዓይነት የንጉሱ ቤተመንግስትም ለግለሰቦች መኖሪያ ቤትነት ሊሰጥ እንደማይችል እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

Read 6253 times