Monday, 26 September 2016 00:00

የእይታ አንፃር ፍፁም አይደለም!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

(መጣጥፍ)
                                

       የከረመ፣ የኖረና ምናልባትም የሰለቸ ክርክር ነው። በፈጣሪ አንደ ተፈጥረናል (አንሻሻልም) ይላል አንዱ ጎራ፡፡ በፈጣሪ ሳይሆን በተፈጥሮ ሂደት ነው የተገኘነው --- በሂደት እንደተገኘነው በሂደት እየተለወጥን መጥተናል … መለወጥም እንቀጥላለን ይላል ሌላኛው። ምናልባትም እውነት ሊሆን ይችላል የመለወጣችን ጉዳይ፡፡ ግን ስንለወጥ ጥያቄዎችና ጥያቄዎቹን በሁለት አንፃር ብቻ የሚመልሱ ጎራዎችስ ይለወጡ ይሆን? ያጠራጥራል፡፡
*          *         *
ዝግመተ ለውጥ ለምን እንደማይሰራ ወይንም እውነት እንዳልሆነ ለማስረዳት አንድ የካቶሊክ ቄስ የሚከተለውን ምክኒያት ሰጡ፡፡ ምክኒያቱ ከተለመደው “በፈጣሪ ተፈጥረናል” ከሚሉት  (creationist) አመለካከት የተለየ ስለመሰለኝ ልጠቅሰው ፈለግሁ፡፡
- ኦርኪድ የሚባለው ወንዴው አበባ የዘር ፍሬውን ወደ ሴቴዋ ለማድረግ የሚጠቀመውን ዘዴ በተመለከተ በአንድ ጽሁፍ ካሰፈሩት ላይ ነው የሚከተለውን ያስነበቡት፡፡
ወንዴው አበባ ሲታይ የሚመስለው ሴቴዋን ተርብ ነው፡፡ የመምሰሉ ደረጃ እንከን የለሽ ከመሆኑ የተነሳ ወንዱ ተርብ አበባው ላይ አርፎ የዘር ፍሬውን ያራግፋል፡፡ ግን የዘር ፍሬውን ሲያራግፍ በዛው ቅፅበት የአበባውን የዘር ዱቄት በአካሉ ይዞ ነው ለመብረር የሚነሳው፡፡ ተነስቶ ሄዶ ሌላ አበባ ላይ ያርፋል። ሲያርፍ ይዞ የመጣውን የአበባ ዱቄት በማራገፍ አበቦቹ እንዲራቡ ያደርጋል፡፡
የካቶሊክ ቄሱ ይሄንን አስተውለው፣የኤቨሉሽን ሐሊዮ ስህተት ነው አሉ፡፡ እንደ ቄሱ እይታ፤ አበባው በዝግመተ ለውጥ ሂደት ይህንን ተርብ የመምሰልን ጥበብ ሊማረው አይችልም፡፡ ተርብን እንዲመስል ተደርጎ መጀመሪያውኑ ከተፈጠረ ብቻ ነው ተርቡ ሙሉ ለሙሉ ሊታለልና ሊያርፍበት የሚችለው። ተርቡ ሙሉ ለሙሉ መጭበርበር ካልቻለ፣ በአበባው ላይ አርፎ የራሱን የዘር ዱቄት ተርቡ ይዞ ወደ ሌላ አበባ እንዲያደርሰው ማድረግ አይችልም፡፡ ስለዚህ አበባው ዘሩን ማራባት ባለመቻሉ ይሞታል፡፡
“በዝግመተ ለውጥ የሙከራና የስህተት ሂደት ሳይሆን በአንድ ሙከራ ትክክል መምጣት ያለበት ሆኖ መፈጠር የግዴታ ያስፈልገዋል …” ይላሉ የካቶሊክ ቄሱ፡፡ ስለዚህ የማይሻሻል፣ መጀመሪያውንም ግን የማይሳሳት ተፈጥሮ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት የማይሰራ ንድፍ ሰሪ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ፈጣሪ አለ … ብለው ቄሱ ሀሳባቸውን ፅፈው አስነበቡ፡፡
ሀሳቡ አሳማኝ ይመስላል፡፡ በአንድ ጎን ለተመለከተው፡፡ ግን ሁሉም እይታ ሌላ አንፃር አለው። ለቄሱ ምልከታ ተቃራኒውን አንፃር ያሳየው የኒዮ ዳርዊኒዝም አራማጁ ሪቻርድ ዳውኪንስ ነበር። እርግጥ ዳውኪንስም ለመጣለት የመረጠው ጭፍን አማኙን ሳይሆን መሰረታዊ ምክኒያታዊነት ተጠቅሞ የፈጣሪን መኖር ለመግለፅ የሞከረውን የአማኝ አይነት መርጦ ነበር፡፡ እናም በቄሱ እይታ ላይ ጥያቄዎቹን መሰንዘር ይጀምራል፡፡
…በመጀመሪያ ደረጃ የጠየቀው የሰውየውን የእውቀት መጠን ነው፡፡ ቄሱ አበባውን ሲያዩት በቅርፁና በቀለሙ ሴቴ ተርብን መምሰሉ ሁሉን አቀፍ እውነት ነው ወይ? ሲል ይጠይቃል፡፡ ቄሱ አበባዋን ሲያዩና ተርቡ አበባዋን ሲያይ የሚታየው ምስል አንድ ነው ወይ? ብሎ ይጠይቃል፡፡ ተርቡ አበባዋን ሲያይ ሴቴ ተርብ መስላው እንደተጭበረበረው ቄሱስ ተጭበርብረው ቢሆን? ለተርቡ እይታ አበባዋ ለቄሱ እንደታየችው “ተርብን” ባትመስልስ? የተርብ አይን እንደ ሰው አይን ነው እንዴ ነገራትን የሚመለከተው? ብሎ “ከስህተት አስተሳሰብ የመጣ ክርክር ነው” በማለት የቄሱን ክርክር ዳውኪንስ ያጣጥለዋል፡፡  
እንዲያውም እንዲህ አይነቱን የክርክር መጣረዝ (Kind of fallacy) “the argument from personal incredulity” ብሎ ይሰይመዋል፡፡ ቀጥሎም የተለያዩ ምሳሌዎች ይጠቅሳል፡፡ ከምሳሌዎቹ በፊት ወይንም በኋላ የሚገባን ነገር ቢኖር መጭበርበር የተፈጥሮ ቋንቋ መሆኑንና “ማየት ማመን አለመሆኑን” ነው። ለምሳሌ ይላል ዳውኪንስ፡- ሰዎች በመንገድ ላይ አንድ የሚያውቁትን ሰው ያገኙ መስሏቸው መሳሳት የተለመደ ነገር ነው፡፡ ሰዎች በሁለት አውታር ሸራ ላይ የተሳለ ስዕል ወይንም ተንቀሳቃሽ ፊልም አይተው የወሲብ ስሜታቸው ይቀሰቀሳል፡፡ የወሲብ ፊልም አይተው የወሲብ እርካታ የሚያገኙ ሰዎች ፊልሙ ተራ ሸራ ወይንም ሰሌዳ መሆኑን ሳያውቁ ቀርተው አይደለም፡፡ የወሲብ ስሜት በሚሰማቸው ሰዓት ግን ሰሌዳው ሰሌዳ መሆኑን ለግዜውም ቢሆን መርሳት ይኖርባቸዋል፡፡ የዚህን አይነቱን መጭበርበር በተለያየ አንፃር እየመሰለ ለማሳየት ይሞክራል፡፡
ለምሳሌ “Turkey” ተብሎ የሚጠራው ዶሮ መሰል  እንስሳ- እንቁላሎቹ ከተፈለፈሉ በኋላ ጫጩቶቹን ለመግደል የመጣውን ማንኛውንም ጠላት የሚከላከለው ድምፅን እንደ ዋና መለያ እየተጠቀመ መሆኑ የተደረሰበት በቅርቡ ነው ይለናል። ጫጩቶቹ ከሚያወጡት ድምፅ ውጭ የሆነ ሌላ ባዕድ ድምፅን ሁሉ ታጠቃለች እናትየዋ። ቀደም ሲል “ተርኪዋ” ጠላቷን የምትለየው በአይኗ ተጠቅማ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ በአንድ አጋጣሚ እዚህ አዲስ ግኝት ላይ የደረሰው ሳይንቲስት… ከሚያረባቸው ተርኪ (Turkery) አንዲቷ ልጆቿን በሙሉ ገድላቸው ተገኘች፡፡ የራሷ የእናትየዋ ጆሮ የማይሰማ በመሆኑ ምክኒያት አደጋ የመጣ በመሰላት ቅፅበት የጫጩቶቿን ድምፅ ማድመጥ ባለመቻሏ ለጥቃት ከመጣው ጠላት ጋር ደባልቃ እንደፈጀቻቸው ይገነዘባል፡፡ ሳይንቲስቱ በአይኑ ጠላትን እንደሚለየው፣ ዶሮዋ ትለያለች ብሎ ቢያስብ ለድርጊቱ የሚፈልገው መንስኤ ወይንም የምክኒያት አመለካከት አቅጣጫው ሌላ ነበር የሚሆነው፡፡
ቀጥሎ ስለ ንብ ይገልፃል- ዳውኪንስ፡፡ ንቦች በአይናቸው ተጠቅመው አይደለም ከመሀከላቸው የሞተና በመበስበስ ላይ ያለውን መሰላቸውን የሚለዩት፡፡ የሞተ ንብ በመበስበስ ሂደት ላይ የሚያመነጨው Oleic acid የሚባል ንጥረ ነገር አለ። የንቦች የመጠቆሚያ አንቴና የሚለየው አንድን አሲድ ብቻ ነው… ሌላው የሰውነታቸው ህዋሶች ሌላ ኬሚካል የሚለውጠው ሊሆን ይችላል። የመጠቆሚያ አንቴናቸው ግን የሚያነፈንፈው ‹‹ኦሊክ አሲድን›› ነው።
ሳይንቲቶቹ ይህንን አሲድ በህይወት ባሉ ንቦች ላይ ጠብ ባደረጉ ጊዜ .. አሲዱ የተንጠባጠበባቸው ንቦች እየተፈራገጡና እየተወራጩ በሌሎቹ ንቦች ተይዘው ወደ ሬሳ ማስወገጃ ስፍራ ሲጣሉ መመልከት ችለዋል .. ይላል ዳውኪንስ፡፡
…ሌላም ብዙ ተመሳሳይ ምሳሌዎችን በመጥቀስ  ነጥቡን ለማፅናት ይጥራል… ነጥቡ የሰዎች እይታ ከተርብ እይታ የተለየ መሆኑ ነው፡፡ ምናልባት የአይን የዝግመት ለውጥ ደረጃቸው ተቀራራቢ በሆነ ተፈጥሮ የዝግመት ሂደት ላይ የሚገኙ ፍጡራን ከሆኑ፣ ለማነፃፀር ይቻል ይሆናል፡፡ የተርብን እይታ ግን ሰው… የሰውን የአይን እይታ ደግሞ ወደ ተርብ ሊተረጎም አይችልም ባይ ነው፡፡  
የሰው አይን የአልትራ ቫዮሌት ጨረርን ማየት እንደማይችለው ሁሉ ነፍሳት ደግሞ የአልትራ ቫዮሌትን ጨረርን ተጠቅመው ቅርፅን ማየት ወይንም መለየት ይችላሉ፡፡ የእይታ ተፈጥሯቸው ነው፡፡ ግን ይህ ተፈጥሯቸው ስህተት የለሽ ነው ማለት አይደለም። ብዙ ነፍሳት ከዛፍ ወድቆ እየተውለበለበ የሚወድቅ ቅጠልን የፆታ አጋር እየመሰላቸው ሲያሽኮረምሙ በአጥኚዎች ታይቷል፡፡
ሰዎችም ይጭበረበራሉ፡፡ ግን አንድ አይነት አይን ስለሌለን ----- ከነፍሳት ጋር አንድ አይነት መጭበርበር ውስጥ አንገኝም፡፡ ተርቡ ወደ አበባዋ የተሳበው በዝግምታ ለውጥ ሂደት በማይደገም የአበባዋ ተርብን መስሎ የመገኘት ተፈጥሮ ሳይሆን በሌላ አይነት ሚስጢር ሊሆን ይችላል፡፡ አበባዋም ሆነ ተርቡ ዝግመተ ለውጥ ይቀጥላል፡፡ ምክኒያቱም ‹‹Perfect›› መሆን የሚባለው ነገር አንፃራዊ እንጂ ተጨባጭ ነገር አይደለም… እንደ ዳውኪንስና ኤቮሉሽን ሀሊዮ፡፡
የሰው ልጅ አይን በራስ ወዳድ እይታው ራሱን ሙሉ ቢያደርግም በአንፃራዊ ጉድለት ያለው ነው፡፡ የሰው አይን ከሆነ ርቀት በላይም ሆነ በታች አያይም። … እና በዚህ መልክ ክርክራቸውን አድርገዋል፡፡ ክርክሮቹም ግን ምናልባት የሰው እይታ አንፃር ሊሆን ይችላል፡፡ ለሌላው እውነታ የጥያቄውና የክርክሩ አስፈላጊነት ራሱ ትርጉም አልባ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠርም አስፈላጊ ሳይሆን አይቀርም ባይ ነኝ፡፡

Read 1159 times