Monday, 26 September 2016 00:00

የወሲብ ስንፈት... ምክንያቶች እና መፍትሔአቸው

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(21 votes)

      ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ትኩረትን ከሚያደርጉላቸው ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ወሲብን በብቃት መወጣት መቻል ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በታወቀም ይሁን ባልታ ወቀ ምክንያት የወሲብ ስንፈት ያጋጥማል። በተቃራኒው ደግሞ በጣም ትንሽ ቁጥር ቢሆንም ጤናማ ያልሆነ የወሲብ ፍላጎት የሚያጋጥማቸው ሰዎችም እንደአሉ አንዳንድ እማኝነቶች ያስረዳሉ። እነዚህ ወቅትን ያልጠበቀ ማለትም ቶሎ ቶሎ ወሲብ መፈጸም የሚፈልጉ ሰዎች ምናልባትም ይወስዱአቸው ከነበሩ አንዳንድ ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮች አሊያም መድሀኒቶች መቋረጥ ጋር ሊያያዝ ይችል ይሆናል የሚል እሳቤን ይዞ በቀጥታ ወደሕክምናው ሲኬድ ግን የስነልቡና ወይንም የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎችን ማግኘት ጠቃሚ ነው። ወሲብ የመፈጸም ችግርን በሚመለከት ግን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና ረዳት ፕሮፌሰር እንዲሁም የስነተዋልዶና፣ የቤተሰብ ምጣኔ እንዲሁም የመካንነት ሕክምና ባለሙያ የሆኑትን ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽን ለዚህ እትም ምላሽ እንዲሰጡ አነጋግረናቸዋል።
ጥ/ የወሲብ ችግር ማለት በምን ምክንያት የሚከሰት ነው?
መ/ ውስብስብ የሆነው የሰውነታችን ክፍል አእምሮንና የሰውነት አካልን ግልጽ ባልሆነ መልኩ አጠቃሎ የያዘ እና የተቆራኙበት ሁኔታ ነው ያለው። እነዚህ የተቆራኙ የሰውነት አካላት አንዳቸው ሲጎዱ ወይንም አንዳቸው ስራ ሳይሰሩ ሲቀሩ የወሲብ ችግር ሊከሰት ይችላል። ስለዚህም የወሲብ ግንኙነት ሲባል የስነልቡናንና የአካልን ጤንነት እንዲሁም ኃይልን የሚፈልግ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ነው። ስለሆነም በተገለጹት ተፈጥሮአዊ አካላት ላይ ምንም አይነት ችግር ቢፈጠር በሴትም ሆነ በወንድ ላይ የወሲብ ስንፈት ሊከሰት ይችላል። ይህ ሲባል ግን እንደየህብረተሰቡ የሀይማኖት ፣የእድሜ ፣የዘመን ሁኔታ የወሲብ ድርጊት አይመራም ማለት አይደለም። በዚህም ሳቢያ እንደየህብረተሰቡ ማንነት ከፍና ዝቅ እንዲሁም እንደየትርጉም አሰጣጡ ሊለያይ ይችላል እንጂ ወሲብ ሲባል አንድ አይነት ተፈጥሮአዊ ክስተት ነው።
ጥ/ ወሲባዊ ድርጊት ተፈጥሮአዊ እንደመሆኑ በምን መልክ በባህል በሀይማኖት...ወዘተ ይመራል?
መ/ በእርግጥ ተፈጥሮአዊ መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን መቼና እንዴት ይፈጸማል የሚለውን ስንመለከት ግን አንዳንድ ባህላዊ ፣ልማዳዊ እና ሀይማኖታዊ ፍላጎቶች የሚታዩበት አጋጣሚ ይስተዋላል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ በአንዳንድ ባህል ከትዳር በፊት በፍጹም ወሲብ እንዲፈጸም አይፈቀድም። በአንዳንድ ሀይማኖቶች ደግሞ ህጋዊ የሆነ የሀይማኖቱን ስነስርአት ሳያሟሉ ወሲብ መፈጸም አይቻልም።እነዚህ ነገሮች ከሚፈጥሩት የስነልቡና ጫና የተነሳ ስር ይሰዱና ለወሲብ መነሳሳት ፍላጎትን ሊቀይሩት ይችላሉ። የወሲብ ድርጊቱ የሚፈጸመው የሀይማኖቱና የባህሉ ሂደት ከሚፈቅድበት ደረጃ ሲደረስ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ተቃራኒ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። ለምሳሌም ትዳር ቢፈጸምም ባይፈጸምም ወሲብ መፈጸም እንደነውር የማይቆጠርባቸው እንዲያውም የመወደድ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድባቸው አካባቢዎችም አሉ። ለምሳሌም እንደ ኦሞ ባሉ አካባቢዎች ሴት ልጅ ከትዳር አስቀድማ ወሲብ መፈጸምዋ የበለጠ እንድትወደድ እንደሚያደርጋት ይገለጻል። ስለዚህም ባህልና ሀይማኖት እንዲሁም ዘመን ሁኔታዎችን የሚጫኑበት መንገድ አለ። ለምሳሌም ዘመን ሲባል በኢትዮጵያ እንኩዋን ያለውን ብናነጻጽር ቀደም ባለው ዘመን ሴትና ወንድ በመንገድ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ወይንም ተቃቅፈው መሄድ የማይፈቀድበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን አሁን ግን እንደነውር ከማይቆ ጠርበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ስለዚህ ለወሲብ የመነሳሳት ሁኔታን ማህበራዊና ባህላዊ እንዲሁም ልማዳዊ እና ሀይማኖታዊ ነገሮች ቅርጽ የሚያስይዙበት ሁኔታ አለ።
ጥ/ መደሰትና መከፋት ከወሲብ ግንኙት ጋር ግንኙነት አለው?
መ/ በትክክል። መደሰትና መከፋት ለወሲብ ተግባር ከሚያነሳሱና ከሚያቅቡ መንገዶች መካከል ናቸው። ለምሳሌ መከፋትን ስንመለከት...ከስራ ጫና ሊሆን ይችላል... ከአኑዋ ኑዋር ባህርይ ሊፈጠር ይችላል...የስነልቡና ችግር ሊሆን ይችላል...የጉዋደኛ በወሲብ ጠንካራ አለመሆን...ሀዘን የመሳሰሉት ነገሮች በሚያደርሱት የስነልቡና ጫና የወሲብ ፍላጎት ላይኖር ይችላል። በሌላ ጎኑ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የደስታ ስሜት የሚሰማን ከሆነ የወሲብ ፍላጎት ሊኖር ይችላል። ከዚህ ውጪ በእድሜ ምክንያት የሆርሞኖች እጥረት ሲከሰት የወሲብ ፍላጎትም ሊዳከም ይችላል። እንዲሁም በተለየ የስራ ባህርይ ላይ በማተኮር ወሲብ የመፈጸም ተግባርን መርሳት ወይንም በተለያዩ ምክንያቶች ወሲብ ሳይፈጽሙ መቆየት እየዋለ እያደረ የወሲብ ስንፈትን ሊያስከትል ይችላል። ባጠቃላይም ወሲብ የስነልቡናን ጥንካሬ በእጅጉ ይፈልጋል።
ጥ/ ከአካልና ስነልቡና ጥንካሬ በተጨማሪ አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮች ምንድናቸው?
መ/ ሰዎች በተለያዩ ሕክምናዎች ምክንያት የሚወስዱአቸው መድሀኒቶች ከወሲብ ፍላጎት ጋር የሚገናኙበት ሁኔታ ይከሰታል። ለምሳሌም ለካንሰር ፣ለደም ግፊት ፣ለስኩዋር ሕመም፣ ለአእምሮ ችግር፣ ለድብርት ለመሳሰሉት የሚወሰዱት መድሀኒቶች ወሲብ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖራቸዋል። ሌላው የሆርሞኖች አለመሟላት ነው። እስትሮጂን ለሴት እጅግ አስፈላጊ ነው። የዚህም አገልግሎት አንደኛው የሴትየዋን ወሲባዊ ፍላጎት በማምጣት እና የወሲብ አንልን ዝግጁ ለማድረግ ይረዳል። ወንድ ላይ ደግሞ ስስ ትሮን የተባለው እጢ እጥረት ካለ ችግሩን ያስከትላሉ። ከዚህ ውጭ ሆርሞኖቹ በጨረር ወይንም በኬሞራፒ የካንሰር ሕክምና በመሳሰሉት ሆርሞንን የሚያመነጩ አካላትን የሚጎዱ ሕክምናዎች ሲያጋጥሙ የወሲብ ችግር ሊኖር ይችላል። የነርቭ መጎዳት ከዚህ በተጨማሪ የደም ዝውውር እጥረት በስነተዋልዶ አካላት ላይ መከሰት የወሲብ ችግርን ሊያስከትል ይችላል። ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች በወንዱም በሴቶችም ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን የወንዱንና የሴትዋን ችግር በተለይ ሲታይ ደግሞ...
የወንዶች፣
የፍላጎት ማጣት ነው። ይህ በተለይም እድሜ እየገፋ ሲሄድ የሚታይ ነው።
የወሲብ አካል ላይ የደም መዘዋወርን የሚቀንስ ነገር ሲከሰት፣
 ወይንም ደግሞ ፈሳሽ ያለመኖር ...የፕሮስት እጢ ችግር፣
የሴቶች ፣
የፍላጎት ማጣት፣
 የመነቃቃት ችግር፣
 የመርካት፣
 ከወንድ ጋር ሲገናኙ ሕመም መኖር፣
ባልታሰበና ባልታወቀ ምክንያት የብልት መኮማተር እና ለግንኙነት አለመዘጋጀት ናቸው።
ጥ/ የወሲብ ችግር ሕክምና አለው?
መ/ ሕክምና በሚገባ አለው። በመጀመሪያ ይህንን ችግር ያመጣው ምንድነው? የሚለውን ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይገባል። በእርግጥ ችግሩ የረጅም ጊዜ ወይንም የአጭር ጊዜ መሆኑ መታወቅ አለበት። ህክምናው በጣም ትእግስት ይፈልጋል። ችግሩ ከልጅነት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ከሆነ ሕክምናው ከበድ ይላል። ነገር ግን የአጭር ጊዜ ችግር ከሆነ ከስነ ልቡና ጋር ተያይዞ መታከም ይችላል። በእርግጥ ሐኪሙ አስቀድሞ ችግሩ ይሄ ነው ወይንም ጉዳዩ እንደዚህ ያለ ነው በሚል እርምጃ መውሰድ ሳይሆን ታካሚውን ባማከለ መንገድ በእርጋታ የሚሰራ ስራ ነው። መታከም የሚችል ከሆነ ይታከማል። ካልቻለ ደግሞ ወደስነልቡና ወይንም ስነአእምሮ ሕክምናው ሪፈር ይባላል።
ጥ/ የወሲብ ስንፈት ያለባቸው ሰዎች በግልጽ ወደሕክምናው ይቀርባሉ?
መ/ ይህ ችግር ብዙ ጊዜ በግልጽ በጠረጴዛ ዙሪያ አይመጣም። በአብዛኛው የሚመጣው ከማህጸንና ጸንስ ሕክምና ጋር ተያይዞ ነው። ችግሩ ግን የስነ አእምሮና የስነልቡና ሕክምናንም የሚያካትት ነው። ነገር ግን ወደጽንስና ማህጸን ሕክምናው ክፍል ጉዳዩ ሲቀርብ ቀለል ያሉትን ነገሮች በማከም ከፍ ያለውን ነገር ወደሚመለከታቸው የህክምና ባለሙያዎች እናስተላልፋለን። በእርግጥ ለሕክምናው እንዲረዳ ማንኛዋም የማህጸን ታካሚ ስትመጣ የሚቀርቡ ጥያቄዎች አሉ።
ወሲብ መፈጸም አለመፈጸምዋን፣
ወሲብ ግንኙነት ላይ የሚያሳስባት ነገር ካለ፣
ሕመም የሚሰማት የማይሰማት መሆኑ ጥያቄ ይቀርብላታል።
ከእነዚህ ጥያቄዎች በሁዋላ የሚደረግላት ሕክምና የስነልቡና እንዲሁም የተለያዩ አግባብ የሆኑ መድሀኒቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ግን በሁለት ተጉዋዳኞች መካከል አለመቀራረብ ሊኖር ስለሚችል ሁለቱን ጉዋደኛሞች በማቅረብም ማነጋገር እና የምክር አገልግሎት መስጠት አንዱ የህክምና ዘዴ ሊሆን ይችላል።በኢትዮጵያ የለም እንጂ በውጭው አገር የጉዋደኛ አማካሪ የሚባሉ ያሉ ሲሆን እነርሱም ሊረዱ ይችላሉ። ከዚህ ካለፈም ከፍ ወዳለ ሕክምና እንዲተላለፉ ይደረጋል። ማንኛውም ሰው ሙሉ የአካልና የስነልቡና ጤንነት ካለው የወሲብ ፍላጎቱም የተ ሟላ ይሆናል። ይህ የተሟላለት ሰው ደግሞ በመንፈሱ ሙሉ የመሆን በስራውም ሆነ በቤተሰቡ ዘንድ ተወዳጅ የሚያደርገውን ተግባር የመፈጸም ብቃት ይኖረዋል።

Read 16893 times