Monday, 26 September 2016 00:00

ኢትዮጵያ የሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮናን ማስተናገድ አለባት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     ባለፉት 2 ሳምንታት በኡጋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የ2016 የሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮና የፍፃሜ ጨዋታ ታንዛኒያ  2ለ1 ኬንያን በመርታት የዋንጫው አሸናፊ ሆናለች፡፡ በሻምፒዮናው በአፍሪካ ዋንጫ ሴካፋን በመወከል የምትሳተፈው ኬንያ በ2ኛ ደረጃ ስታጠናቅቅ፤ ኢትዮጵያ 3ኛ ደረጃ እንዲሁም አዘጋጇ ኡጋንዳ 4ኛ ደረጃዎችን አግኝተዋል፡፡ የኪሊማንጃሮ ንግስቶች የሚባሉት የታንዛኒያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋንጫውን ለማሸነፍ የበቁት በሚያስደንቅ የቡድን ጥንካሬ እና ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ነው፡፡ በሻምፒዮናው የኡጋንዳዋ  ሃሳኒ ናሳና በ6 ጎሎች ኮከብ ግብ አግቢ ሆና ስትጨርስ የሉሲዎቹ አጥቂ ሎዛ አበራ በ5 ጎሎች ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድንን በዋና አምበልነት የመራችው ብርቱካን ገብረክርስቶስ ኮከብ ተጨዋች እንደነበረች ታውቋል። ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው ኬንያ  ዞኑን በመወከል ከ2 ወራት በኋላ ካሜሮን ላይ በሚካሄደው የ2016 የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ የምትሳተፍ ሲሆን፤ በሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮና የነበራት ተሳትፎ ለአፍሪካ ዋንጫው ጠቃሚ ዝግጅት እንደሚሆንላት ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በቀጣይ የሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮናን ቢያስተናግድ በአገሪቱ ለሚካሄደው የሴቶች እግር ኳስ ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥር አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
በሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮናው ሉሲዎቹ በምድብ 2 ከሩዋንዳ እና ከታንዛኒያ ጋር ተደልድለው ነበር፡፡ በመጀመርያ ጨዋታቸው በሎዛ አበራ ሁለት ጎሎች እና በመስከረም ኮንካ አንድ ተጨማሪ ግብ ሩዋንዳን 3ለ2 አሸነፉ፡፡ በሁለተኛ ጨዋታቸው ደግሞ ከታንዛኒያ ጋር 0ለ0 አቻ በመለያየት በምድባቸው  4 ነጥብ እና አንድ  የግብ ክፍያ ካስመዘገቡ በኋላ በእጣ ሁለተኛ ደረጃ አግኝተው ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፈዋል፡፡ በግማሽ ፍፃሜው  የተገናኙት  ከኬንያ አቻቸው ጋር የነበረ ሲሆን 3ለ2 ተሸንፈው ለዋንጫ ፍልሚያው ሳይደርሱ ቀርተዋል፡፡ በዚህ ጨዋታ ሁለቱንም ጎሎች ያገባችው ሎዛ አበራ ነበረች፡፡ ለደረጃ ጨዋታ የተገናኙት ደግሞ ከአዘጋጇ አገር ኡጋንዳ ጋር  ሲሆን 4ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ የሴካፋ ሻምፒዮና ተሳትፏቸውን በ3ኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ በዚህ ጨዋታ  ረሂማ ዘርጋው 3 ጎሎች በማስቆጠር ሃትሪክ ስትሰራ 1ኛውን ጎል ያገባችው ደግሞ ሎዛ አበራ ነበረች፡፡ ሉሲዎቹ ለዋንጫ ቅድሚያ ግምት ቢሰጣቸው በግማሽ ፍፃሜ በኬንያ አቻቸው በገጠማቸው መራር ሽንፈት ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡  በአጠቃላይ በሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮናው ከምድብ አንስቶ እስከ ደረጃ ጨዋታው  4 ጨዋታዎች አድርገው ሁለቱን ሲያሸንፉ በአንድ አቻ ወጥተው በአንድ ጨዋታ ደግሞ ተሸንፈዋል፡፡ በተጋጣሚዎቻቸው ላይ  9 ጎሎች አስመዝግበው 6 ጎሎች ደግሞ አስተናግደዋል፡፡
ኡጋንዳ ስፖንሰር የሌለውን ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕ ሻምፒዮና ማስተናገዷን ያደነቁት የሴካፋ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙንሶኜ ናቸው፡፡ ሻምፒዮናው በሴቶች እግር ኳስ  አብዛኛዎቹ የዞኑ አባል አገራት የሚገኙበትን ደካማ  ደረጃ  እንደሚቀይር ሲገልፁም፤ ለአፍሪካ ዋንጫና ሌሎች ኢንተርናሽናል ውድድሮች የሚደረጉ ዝግጅቶችን የሚያግዝ መሆኑን  አመልክተዋል። በሌላ በኩል ሻምፒዮናው በሴቶች እግር ኳስ ላይ የሊግ ውድድሮች ለሚያካሂዱት እና በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች በመስራት ላይ ለሚገኙት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥርም የሴካፋ ዋና ፀሃፊ አስገንዝበው ፤ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የዞኑ አገራት ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት ሲናገሩ የሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮናው ይህን የዞኑን ብሄራዊ ቡድኖች ተሳትፎ ለማጠናከር ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ በሴካፋ የሴቶች ሻምፒዮናው ለዋንጫ ከተፋለሙት ታንዛኒያ እና ኬንያ ባሻገር ሁሉም ተሳታፊዎች በተለይ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ታዝበናል የሚሉት ዋና ፀሃፊው በሚቀጥሉት የአፍሪካ ዋንጫዎች ከዞኑ ሁለት እና ሶስት አገራት መሳተፍ የሚችሉ ከሆነ  እድገት መኖሩን ያመለክታል ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ትልቁ የተሳትፎና የውጤት ክብረወሰኖች የተመዘገቡት  ሶስት ጊዜ በ2002፤2006 እና 2012 እኤአ ላይ መሳተፍ በቻለችው ኢትዮጵያ ሲሆን ሉሲዎቹ በ2006 እኤአ ላይ በአፍሪካ ዋንጫው ባገኙት አራተኛ ደረጃ የዞኑን ከፍተኛ ውጤት ነበራቸው፡፡ ታንዛኒያ በ2010 እኤአ ላይ ሴካፋን በመወከል በአፍሪካ ዋንጫው የተሳተፈች ሲሆን ለኬንያ የ2016 የአፍሪካ ሴቶችዋንጫ የመጀመርያው ይሆናል። ካሜሮን ለምታስተናግደው የ2016 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫው የምድብ ድልድሉ ሰሞኑን የታወቀ ሲሆን ኬንያ በምድብ ሁለት ከናይጄርያ፤ ጋና እና ማሊ ጋር ስትደለደል በሌላ በኩል በምድብ 1 ካሜሮን፤ ግብፅ፤ ደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ ከ2014 ጀምሮ እስከ 2018  እኤአ በመላው ዓለም በሴቶች እግር ኳስ ተግባራዊ የሚሆን የእድገት ፕሮግራም በመንደፍ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡  ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር አባል አገራቱ  የሴቶች እግር ኳስን በማሳደግ እንዲሰሩ የባለሙያ ክትትል ማድረግ፤ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት፤ የገንዘብ ድጋፍ በማበርከትንና የፕሮሞሽን ተግባራትን በማከናወን እያገዛቸው ይገኛል፡፡  ፊፋ በዚህ የሴቶች እግር ኳስ የእድገት ፕሮግራሙ  በሁሉም የእድሜ ደረጃዎች አገር አቀፍ፤ ክፍለ አህጉራዊ እና አህጉራዊ ውድድሮች እንዲካሄዱ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በስሩ ያሉ 209 አባል አገራት ለተግባራዊነቱ የስራ እቅዶችና ስትራቴጂዎች ነድፈው እንዲያቀርቡ በመጠየቅ የሚሰራበትን ሁኔታ እስከ 2018 እኤአ የሚቀጥልበት ይሆናል፡፡  ከዚህ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር የሴቶች እግር ኳስ የእድገት ፕሮግራሙን በ2014 እኤአ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ከመጀመሩ በፊት የሰራው ጥናት ነበር፡፡ ከአባል አገራቱ መካከል  177 የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች በጥናቱ ላይ የተካተቱ ነበሩ፡፡ በዚህ የዓለም ሴቶች እግር ኳስ አጠቃላይ ጥናት ላይ የተሳተፉት 177 ፌደሬሽኖች በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በሴቶች እግር ኳስ ላይ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ዙርያ ላቀረበላቸው ጥያቄዎች 85 በመቶ ምላሽ ሰጥተዋል። በየአባል አገራቱ የሴቶች እግር ኳስ እድገትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች ተብለው በጥናቱ ከተጠቀሱት መካከል የሊግ ውድድሮች አለመሻሻል፤ አስተዳደራዊ ድክመቶች፤ የባለድርሻ አካላት በቅንጅት አለመስራት፤ በስፖርቱ የሴቶች ተሳትፎ ማነስ፤ ደካማ ኢንቨስትመንት፤ በአጠቃላይ የግንዛቤ ማነስ እና የሚዲያ ትኩረት ቀዝቃዛ መሆን ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ይፋ ባደረገው ይህ ጥናት በመላው ዓለም በእግር ኳስ ስፖርት ከ30 ሚሊዮን በላይ ሴቶች በተጨዋችነት እና በሌሎች ሙያዎች የሚሳተፉ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በፊፋ የተመዘገቡት ሴት እግር ኳስ ተጨዋቾች ብዛት ከ4.8 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም  በታዳጊ ፕሮጀክቶች የታቀፉት ደግሞ  እስከ 1.2 ሚሊዮን እንደሚገመቱ አመልክቷል። በጥናቱ የተሳተፉት 177 የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች በአጠቃላይ በሴቶች እግር ኳስ እንቅስቃሴያቸው በዓመት እስከ 157 ሚሊዮን ዶላር በጀት ያወጣሉ፡፡ በየፌደሬሽኖቹ በእግር ኳስ አስተዳደርና ልዩ ልዩ ሃላፊነቶች የሴቶች ተሳትፎ 23 በመቶ፤  የሴቶች ዋና ብሄራዊ ቡድን ያላቸው 80 በመቶ፤ የወጣቶች ቡድን ያላቸው 50 በመቶ፤ የሊግ ውድድሮችን የሚያካሂዱ 78 በመቶ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በሌላ በኩል በእግር ኳስ ፌደሬሽኖቻቸው ስራ አስኪያጅ ኮሚቴዎች የሴቶች ተሳትፎ 8 በመቶ ፤ የሴት አሰልጣኞች 7 በመቶ እንዲሁም የሴት ዳኞች ተሳትፎ 10 በመቶ ብቻ እንደሆነም ጥናቱ አመልክቷል፡፡
የሴካፋ ምክር ቤት በዞኑ የወጣቶች እና የሴቶች እግር ኳስ ላይ ለመስራት የአምስት ዓመታት ስትራቴጂ በመቀየስ መንቀሳቀስ የጀመረው በ2014 እኤአ ፊፋ ባካሄደው 64ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በተወሰነው ፕሮግራም መነሻነት  ነው፡፡ በመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ ያሉ 12 አገራትን በአባልነት ያቀፈው የሴካፋ ምክር ቤት ፊፋ በነደፈው ፕሮግራም እና አቅጣጫ ለመስራት ስትራቴጂውን ነድፎ ቢንቀሳቀስም ውድድሮችን ለማዘጋጀት የአባል አገራቱ ፍላጎት ማነስ እና የስፖንሰሮች እጥረት እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ በ2015 እኤአ የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ በኢትዮጵያ መስተናገዱ የሚታወስ ቢሆንም በቀጣይ ውድድሩን የሚያዘጋጅ አገር ጠፍቶ 2016 ላይ ላይካሄድ እንደሚችል ስጋት ተፈጥሮ ነበር።  ከዋናው የሴካፋ ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕ ባሻገር የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ካጋሜ ካፕ ፤ የሀ17 የሀ20 የእግር ኳስ  ሻምፒዮናዎችን ለማካሄድ በነበሩት እቅዶችም ሲቸገር ቆይቷል።  ይህ ሁኔታም በዞኑ የእግር ኳስ አስተዳደር ላይ ንትርኮችን እየፈጠረ ሲሆን፤ ዋንኛው ማስረጃም ምክርቤቱን በዋና ፀሃፊነት እና በተለያዩ የስራ ድርሻዎች ለ15 ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት ኬንያዊው ኒኮላስ ሙንሶኜ ተጠያቂ ተደርገው ከሃላፊነታቸው ለማንሳት ዘመቻ በሩዋንዳ ፊት አውራሪነት መጀመሩ ይጠቀሳል። የሴካፋ ምክር ቤት አንዳንድ አባል አገራት ውድድሮችን ማካሄድ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ እና ስፖንሰሮችን ማቆየት አለመቻሉን  እንደ አስተዳደራዊ ድክመት በመቁጠር ዋና ፀሃፊውን  ኒኮላስ ሙንሶኜ እንዲባረሩ እየጠየቁም ነበር፡፡  ኒኮላስ ሙንሶኜ ከሴካፋ ምክር ቤት ከተሰናበቱ በኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትነት ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው በአፀፋዊ ምላሻቸው ያስታወቁ ሲሆን ምናልባትም በኡጋንዳ አስተናጋጅነት የሴካፋ ሴቶች ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱ ህልውናቸውን እንደሚወስን እየተገለፀ ነበር፡፡ በኡጋንዳ አስተናጋጅነት ከሰላሳ ዓመታት በኋላ የሴቶች ሻምፒዮናው በስኬት መከናወኑን ተከትሎ  ግን የሴካፋ     ምክር ቤት አንዳንድ ውድድሮችን እነማን እንደሚያስተናግዱ  በይፋ አስታውቋል፡፡ዋና ፀሃፊው ኒኮላስ ሙንሶኜ ሰሞኑን በኡጋንዳዋ ከተማ ጂንጃ በሰጡት መግለጫ ኬንያ የ ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ እና የክለቦች ሻምፒዮና የሆነው ካጋሜ ካፕ በማከታተል እንድታስተናግድ መመረጧን እንዲሁም ኡጋንዳ የሀ17 ኻምፒዮናውን እንደምታዘጋጅ አስታውቀዋል፡፡ ኬንያ ሁለቱን ውድድሮች ለማዘጋጀት በምታደርገው ጥረት የሴካፋ ምክር ቤት ሙሉ ድጋፍ እንደሚኖርቃል የገቡት ዋና ፀሃፊው የውድድሮቹ መካሄጃ ሳምንታት በቅርብ ጊዜ ይወሰናሉ ብለዋል፡፡ የሁለቱ የሴካፋ ውድድሮች መቀራረብ በተለይ በብሄራዊ ቡድን እና በክለብ አሰልጣኞች በተጨዋቾች አስፈላጊነት ዙርያ ቅራኔዎችን እንደሚፈጥር የተሰጋም ሲሆን በተለይ ከአፍሪካ ሌሎች ውድድሮች ጋር የጨዋታ መደራረብ መኖሩ እያከራከረ ነው፡፡  የሴካፋ ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕ ሱዳን እንዲሁም የሴካፋ ክለቦች ሻምፒዮና ካጋሜ ካፕን ሱዳን ለማስተናገድ ተመርጠው እድሉን ሰርዘዋል፡፡ በ2016 የሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮና ስኬታማ መስተንግዶ የነራት ኡጋንዳ በ2017 ደግሞ የዞኑን የሀ17 ውድድር እንደምታስተናግድም ይጠበቃል፡፡ ቀጣዩ የሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮናን ማን እንደሚያዘጋጅ የተገለፀ ባይሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ይህን እድል ለመጠቀም መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡

Read 2419 times