Monday, 03 October 2016 00:00

‹‹ዮ ማስቃላ ዮ ጃናው ዳና!››

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

    መስቀል፣ መከበር ብቻ ሳይሆን ይሸኛልም በጋሞ ጎፋ ሕዝቦች፡፡ መስቀል የሚሸኘው በገበያ መኻል በማቋረጥ ነው፡፡ ይህ ሥነ-ሥርዓት የሚከናወነው ደግሞ ደመራው ከተከናወነ ከአንድ ሳምንት በኋላ በሚውለው የመጀመሪያው ገበያ ቀን ነው፡፡
በጋሞ ጎፋ የዛላ ወረዳ አስተዳደር ዋና ከተማ ከሆነችው ጋልማ ከተማ 8 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ባለፈው ሳምንት የዛላ ካዎ (የነገሥታት ማዕከል) በሆነችው ደቦጭ በና የተከናወነውን ሥነ-ሥርዓት ላስቃኛችሁ፡፡
በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ከሁሉም የወረዳዋ ቀበሌዎች ተሳትፈዋል፡፡ ከሁሉም ቀበሌዎች ሰዎች ተሰልፈው ቢወጡም ቅድሚያ የሚሰጠው አንድ ቀበሌ አለ- የዛላ ካዎ (የነገሥታት ማዕከል) ቀበሌ ነዋሪዎች፡፡ ይህ ቀበሌ  ገበያውን ካልዞረ ሌሎች ቀበሌዎች ቀድመው ቢመጡም ገበያውን አይዞሩም-ይጠብቃሉ፡፡ የንጉሡን ቀበሌ ማስቀደም ግዴታ ነው፡፡ ገበያ አዟዟሩም ሥነ-ሥርዓት አለው፡፡ በበቅሎ የመጡ ምዕመናን ይቀድማሉ፡፡ ከዚያም ወንዶችና ሽማግሌዎች ይከተላሉ፡፡ ከዚያም ሴቶች፣ ወጣት ወንዶች ሴቶች ልጆች እየዘፈኑና እየጨፈሩ ገበያውን ሦስቴ ከዞሩ በኋላ ወደ ዳር ይወጣሉ። ከዚያም ሌሎች ቀበሌዎች በመጡበት ቅድመ ተከተል እየገቡ ገበያውን ሦስቴ ዞረው ይወጣሉ። ሁሉም ከዞሩ በኋላ በቅሎዎቻቸውን አስረው ይጨፍራሉ፡፡ ጭፈራው ካበቃ በኋላ ‹‹ዮ ጃናው ዳና›› (ለሚመጣው ዓመት በሰላም ያድርሰን) በማለት ተመራርቀው ይበታተናሉ፡፡ ሽኝቱ የገበያ ቀን የሆነው ለገበያ የሚመጣው ሰው እግረመንገዱን በጣም በሚወደው ባህላዊ ጨዋታ እንዲሳተፍ ነው፡፡ ሽማግሌና አሮጊቶች ሴቶችና ወንዶች፣ ጎልማሶች፣ ወጣቶች ልጃገረዶችና ልጆች መኻል ገብቶ ለመጨፈር ያላቸው ፍላጎት በጣም የሚገርም ነው፡፡ ከፖሊሶችና ሥነ-ሥርዓት አስከባሪዎች ጋር የሚያደርጉት ድብብቆሽ የሚገርም ነው፡፡ ወደ መኻል እየሮጠች የምትሄደውን ሴት ይዘው ሲመለሱ፣ ‹‹ልቀቁኝ እጨፍራለሁ›› ‹‹አንለቅሽም አትገቢም›› የሚለው ውዝግብ ራሱን የቻለ ትርዒት ነበር፡፡ ፖሊሶቹ በዚህ በኩል አንዱን ይዘው ሲመልሱ በዚያ በኩል ደግሞ ሌላው አምልጦ ይገባል፡፡ ለጭፈራ ያላቸው ስሜት ከፍተኛ ነው፡፡ የተከለከሉት እንባ ቀረሽ ኅዘን ያዝናሉ፣ ይበሳጫሉ፣ ይናደዳሉ፡፡ እንደተከለከሉ አይቀሩም፤ አዘናግተው እንደገና ይሞክራሉ፡፡
ጎፋዎች  ለመስቀል በዓል ያላቸው ፍቅርና ከበሬታ ልዩ ነው፡፡ ባለሥልጣናትና የበዓሉ አስተባባሪዎች ደማቁን የባህላቸውን ልብስ ሱሪና ኮት ለብሰዋል። ሽማግሌዎች ነጠላና ቡልኮ ደርበዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ የክቱን ፅዱ ልብሳቸውን ለብሰው፤ ፀጉቸውን ተሠርተውና አማምረው መጨፈር ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ያልጣመኝ ነገር አስተውያለሁ፡፡ እሱም ‹‹ዘመናዊነት›› ነው፡፡ በኪነት የተደራጁ ወጣቶች የተለያዩ ሙዚቃዎችን በኦርጋን እየተጫወቱ 4 ወንዶችና 4 ሴቶች ወጥተው ባህላዊውን ጨዋታ ያስነኩታል፡፡ ቱባውን ባህል ለመጫወት ከሩቅ ስፍራ የመጣውን ሰው ሁሉ ጨዋታውን ነጥቀውት ተሳታፊ ሳይሆን የእነሱ ተመልካች ያደርጉታል። ይኸ መታረም አለበት እላለሁ፡፡ ከዚህ በተረፈ የጎፋ ሕዝብ ‹‹ዮ ማስቃላ›› እያለ ሳምንቱን ሙሉ ይጨፍራል፡፡
ዮ ማስቃላ!- ‹‹መስቀል እንኳን መጣህ! እንኳን አደረሰን›› ማለት ነው በጋሞጎፋ ሕዝበች ቋንቋ። መስቀል በአብዛኛው ኢትዮጵያ በታላቅ ክብርና ድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ ማኅበራዊና ባህላዊ በዓላት አንዱ ነው፡፡ ይህ በዓል በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ቢከበርም አንደ ደቡብ ክልል በከፍተኛ ክብር፣ ፍቅርና ድምቀት የሚከበርበት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለአብነትም ልዩ በሆነ ከፍተኛ ድምቀት የሚከበርበትን የጉራጌ ዞን የጋሞ ጎፋን ዞንን መጥቀስ ይቻላል፡፡
አቶ በድሉ ቁጮ የዛላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ በጎፋ የመስቀል በዓል አከባበሩ፣ አለባበሱ፣ አመጋገቡና አጨፋፈሩ ከሌላው ብሔረሰብ ይለያል ይላሉ፡፡ መስቀል ሲደርስ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ ወንድም፣ ልጅ፣ የልጅ ልጅ በአንድ ላይ ተሰባስበው ያከበራሉ፡፡ ቅርብም ሆነ ሩቅ ያሉ ዘመዶችም ተሰባስበው የመስቀል በዓልን በጋራ ስለሚያከብሩ በህዝቡ ውስጥ ትልቅ ማኅበራዊ ትስስር፣ ትልቅ ፍቅር ይፈጥራል ይላሉ፡፡
መስቀል ኃዘንን መርሻ ነው፡፡ በጎፋ ባህል መሠረት በመስቀል በዓል ወቅት ሰው ቢሞት ኀዘን አይፈቀድም፡፡ የአካባቢ ሕዝብ ተሰብስቦ ወደ ለቅሶ ቤቱ ሄዶ ያለቅሳል፡፡ ከዚያ በኋላ የሞት አደጋ ያጋጠመው ሰው ኀዘን እንዳይሰማውና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኀዘኑን እንዲረሳ ከእነሱ ጋር ይዘውት ወጥተው ‹‹ዮ መስቃላ›› ‹‹መስቀል እንኳን መጣህ! እንኳን አደረሰን›› እያሉ ያጫውቱታል፡፡ ይህም በሕዝቡ መካከል እርስ በርስ የመከባበርና ኀዘን የማስቀረት ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
በመስቀል ወቅት የሕዝቡ አለባበስ ለየት ያለ ነው። አዲስ ባህላዊ ልብሶች ገዝቶ፣ መግዛት ያልቻለም ያለውን አጥቦና አሳምሮ ያለብሳል፡፡ የመስቀል ወቅት ጨዋታም ከሌላው ጊዜ ይለያል፤ ከበዓሉ ውጭ የመስቀል ጨዋታን መጫወት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሆሴ›› በመስቀል ጊዜ ብቻ የሚዘፈን ነው፡፡ በመስቀል ወቅት የተጣላ ወይም የተኳረፈ ሰው ካለ ይታረቃል፡፡ በቤተሰብ ውስጥ እንኳ ሕፃናት መጣላት አይችሉም፡፡ ሕፃናት ችቦ ሲለቅሙ ‹‹ዮ ማስቃላ ሆሴ›› እያሉ ይዘፍናሉ፤ ልብስ እንዲገዛላቸው ይጠይቃሉ እንጂ እርስ በራስም ሆነ ከቤተሰብ ጋር አይጣሉም፡፡ የተጣላ ሰው ካለ ካልታረቁ በስተቀር አብሮ መብላት አይቻልም በማለት አስረድተዋል፡፡
የመስቀል በዓል ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ዓመታዊ የደስታና የምስጋና በዓል እንደሆነ የጠቀሱት የዛላ ወረዳ ም/ቤት አስተዳደርና የገቢዎች ኃላፊ አቶ ዮናስ ከበደ፣ ሽማግሌዎች ዓመቱን ሙሉ ያጋጠሙ ለቅሰዎች ካሉ በየቤቱ እየሄዱ ኅዘኑ እንዲረሳ ያደርጋሉ፡፡ በመስቀል ዕለት ወይም ሁለት ቀን ሲቀረው ሰው ቢሞት ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ይለቀስና ‹‹የመስቀል ደመራ በልቷል እንጂ አልሞተም›› በማለት ወዲያው ኅዘኑ እንዲቀርና ለማረሳሳት ወዲያውኑ ይዘፈናል፣ ይጨፈራል፡፡


Read 1533 times