Monday, 03 October 2016 00:00

ምላሽ “ደብዳቤዬ የብዙዎችን ትኩስ እንባ ያዘለ የከበረ መልዕክት ነበር”

Written by  ያሬድ ጥላሁን
Rate this item
(9 votes)

     በቅዳሜ መስከረም 7 ቀን 2009 ዓ.ም በ“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ባሕል ዐምድ ላይ አቶ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ “የወንጌላዊው ደብዳቤ ለአቶ ኃይለማርያም ወይስ ለአቶ ኦባማ” በሚል ርዕስ የሰፈረውን ጽሁፍ በጥሞና አንብቤዋለሁ። ጽሁፉ በአመዛኙ በግምትና በመላምት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በዝምታ ለማለፍ መርጬ ነበር፤ ነገር ግን ጽሁፉ የተስተናገደበትን ተወዳጁን አዲስ አድማስና የተከበሩ አንባብያኑን ሳስብ ይህን መልስ ለመጻፍ ተነሳሳሁ። መልሴ ለጸሐፊው ብቻ ሳይሆን ለአንዳንድ የፌስ ቡክ ጓደኞቼም እንደሚያገለግል አስባለሁ።
አሁን ያለንበት ወቅት ማለትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤውን እንድጽፍ የተነሳሳሁበት አገራችን በከፍተኛ ውጥረት ላይ ስለሆነች፣ሕዝብ በጭንቀት የተሰነገበት፣ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት የዕለት ተለት ትዕይንት የሆነበት ፈታኝ ወቅት ስለሆነ ነው። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከሸክምና ከልብ ጭንቀት የተጻፈ ደብዳቤ መመዘን ያለበት፣ በመጀመሪያ ደረጃ በይዘቱ ነው ወይንስ ጸሐፊው ጽሁፉን ሲጽፍ በቆመበት ቦታ? በቅድምያ እኔ ኢትዮጵያ ሆኜ ልጻፈው፣ አሜሪካ፣መመዘን ያለበት በጊዜው ሁኔታና በመልዕክቱ ይዘት እንጂ ባጋጣሚ በተገኘሁበት ቦታ ሊሆን የሚገባው አይመስለኝም።
በሰው ላይ መፍረድ ከፍተኛ ተጠያቂነት ያለበት ትልቅ ኃላፊነት ነው። በወቅቱ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታና የተገለጠውን የደብዳቤዬን ይዘት ወደ ጎን ጥሎ፣ “ይህን የጻፈው ጥገኝነት ለማግኘት አስቦ ነው” የሚለው ምንም ማስረጃ የሌለው ሃሳብ ድኩም አመክንዮ ከመሆኑም በላይ ትዝብት ላይ የሚጥል ነው። እውን ስህተትን መንቀስ ካስፈለገ የተገለጡ የስህተት ክምሮች አሁንም በዙሪያችን የሉምን? ወይስ “አህያውን ፈርቶ፣ ዳውላውን” ነው?
ከጸሐፊው ውጪ ሌሎች ሰዎች ሲሰጡ እንደ ሰማሁት አስተያየት፤ግጭቶች ከተነሱባቸው አካባቢዎች በአንዱም አልተወለድኩም፣ ከእነዚህ በየትኛውም ሥፍራ የሥጋ ዘመድ የለኝም። እና ፍትህ ተጓድሏል ብዬ ሳስብ፣ ድምጼን ለማሰማት የግድ ዘር መቁጠር አለብኝ? በእርግጥ ሁሉን ነገር በዘር የማሰብ ዝንባሌ እየተጠናወተን ስለመጣ በዚህ ጉዳይ በማንም ልፈርድ አልችልም። ለእኔ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኩል ክቡር ነው። በተለይ ስለ ትግራይ ሕዝብ ለመናገር በጥቂቱም ቢሆን የሞራል ብቃት ያለኝ ይመስለኛል። በአስተዳደጌ እንደ እናቴና እንደ አባቴ በማያቸውና በምወዳቸው የትግራይ ተወላጆች መሃል አድጌአለሁ። በክርስትና ሕይወቴም ሆነ በአገልግሎቴ መቼም፣ በምንም የማልለውጣቸው የልብ ወዳጆች አፍርቻለሁ። በ1986 እና በ1987 ዓመታት በመቐሌ በመቀመጥ፣ በመላው ትግራይ ተዘዋውሬ የክርስቶስን ፍቅር አካፍያለሁ፣ ተካፍያለሁ። እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ ባለኝ ፍቅር ማንም ሊያማኝ አይችልም። መንግሥት ይመጣል ይሄዳል፤ ሕዝብ ግን ጸንቶ ይኖራልና መንግሥትና ሕዝብ ተለይተው መታየት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ።
ሚዲያን በተመለከተ የሰጠሁት ሃሳብ በተዛባ መልኩ የቀረበ ስለመሰለኝ አስተያየቱን ማረም እንዳለብኝ ተሰምቶኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ የኢንፎርሜሽን ምንጭ የለም የሚል ሃሳብ አላስተጋባሁም፡፡ ነገር ግን እንደ ወንጌል አገልጋይነቴ፣ የፖለቲካ ሃሳቦችን ጠልቄ የመመርመር ዝንባሌ ስለሌለኝ ከሰዎች ከምሰማው፣ በማህበራዊ ሚዲያ ከማነብበው ውጭ ዋናው የዜና ምንጬ ኢቢሲ መሆኑ ሊያስገርምም ሆነ ሊያስጠይቀኝ የሚገባ አይደለም፡፡ ከአገር ውጭ ለአገልግሎት በወጣሁበት ወቅት ግን አገራችን ያለችበት ሁኔታ ስለተባባሰና ጉዳዩን የመከታተል የዜግነት ሃላፊነቴ ወደተለያዩ ሚዲያ ምንጮች እንድሄድ ስላደረገኝ፣ኢቢሲን ብቻ መከታተሌ ጉዳዩን በተጨባጭ እንዳይ አላደረገኝም የሚል ሃሳብን ገልጫለሁ፡፡ ስለሆነም አነጋገሬ ተዛብቶ ለሌላ ትርጓሜ መዋሉ ትክክል አይደለም፡፡
በኦሮሚያ እንዲሁም በጎንደርና በአካባቢው በተከሰተው ግጭት በሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ እንደደረሰው ሁሉ ንብረታቸው የወደመባቸውና በተለይም በጎንደር በሥጋት አካባቢውን ለቀው ወደ መቐሌ የተሰደዱ ወገኖች እንዳሉ ሰምቻለሁ፤ አዝኛለሁም። ወንጀል የሠራ ሰው ካለ በሕግ ይጠየቃል እንጂ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በዘር ማንነቱ አንዳች ሲደርስበት ማየት አልሻም። ሆኖም እየሞተ ላለውና ንብረት ለወደመበት እኩል ልጮኽ አልችልም። ጦር ለዘመተበትና ፈጥኖ ዕርዳታ ለደረሰለት እኩል ልጮኽ አልችልም። ስለዚህ በአክብሮት ያቀረብኩት የተማጽኖ ድምጽ፣ ከዘርና ከማናቸውም ፖለቲካዊ ፍላጎት በጠራ መልኩ በአርአያ ሥላሴ ለተፈጠረ ሰው ሁሉ እኩል የሚያገለግል ይመስለኛል። አቶ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይም ደብዳቤዬን በቅን ልብ ቢረዱት ኖሮ፣ ነገ እሳቸውም ላይ አላግባብ አደጋ ቢያንዣብብ የምጮኽበት የፍቅር ድምጽ እንደሆነ ይገነዘቡ ነበር። ጸሐፊው እሥራትና ሞት ፈርተሃል ብለዋል። ይህን ጨዋነት የተላበሰ ጥያቄ ስላቀረብኩ እስርና ሞት የምፈራበት ምክንያት የለም! በተጨማሪም መንግሥት አገር የማስተዳደር ግዙፍ ሥራውን ትቶ፣ለምን ደብዳቤ ጻፍክ ብሎ ይጠይቀኛል ብዬ አላስብም። ደግሞስ በተለያዩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች በርዕቱ አንደበት፣ በተለያዩ የግል ጋዜጣዎች በሰላ ብዕር ቀን ተሌት መንግሥትን የሚተቹ ወገኖች በአገር ውስጥ እየኖሩ፣እኔ ደብዳቤ ስለጻፍሁ የምፈራበት ምክንያት ፈጽሞ አይታየኝም።
አሜሪካ መሄድና በዚያም መኖር ምናልባት ለአንዳንዶች የሕልም እንጀራ ተደርጎ ይቆጠር ይሆናል። እኔም በዚህ ስሜት ወደ አሜሪካ ለመሄድ የዛሬ 30 ዓመት በስደት ከአገር ወጥቼ ነበር። ለሁለት አመት ጎረቤት አገር ኖሬ ሸሽቼው የሄድኩት የደርግ ሥርዓት ሳይለወጥ፣የእኔ ሕይወት በወንጌል ተለውጦ፣ ለሕዝቤ የቀመስኩትን ጣፋጭ ሕይወት ለማካፈል፣የምዕራብ አገራት ሕልሜን ጥዬ ተመልሻለሁ። ላለፉትም 27 ዓመታት ቀን ተሌት፣ ክረምት በጋ፣ ሰርክ አዘቦት ሳልል፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ሕዝቤን አገልግያለሁ። አሁንም ትኩረቴ ሙሉ በሙሉ የወንጌል አገልግሎት ላይ ብቻ ነው። አገልግሎቴም ሰዎችን ለዘላለም ሕይወትና ለሰማያዊ መንግሥት የሚያዘጋጅ ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚጠቅሙ ጤናማ ዜጎች በማፍራት ላይ ያተኮረ ነው። እናም ለእኔ ውጪ መሄድ አገልግሎትን ያማከለ እንጂ የመኖርን ምኞት ማመቻቻ አይደለም። ቢያንስ ከመቶ ጊዜ በላይ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ወጥቼበታለሁ፤ ገብቼበታለሁ። ኢትዮጵያ የምኖረው መርጬ እንጂ መንገድ ጠፍቶኝ አይደለም።
አቶ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ደብዳቤዬን ለኦባማ የቀረበ የጥገኝነት ጥያቄ እንደ ሆነ አድርገው ለመሳለቅ ሞክረዋል። ሆኖም ከፖለቲካ ፍላጎትና ከሥጋ ማንነት አለፍ ብለው ቢያስቡት፣ የብዙዎችን ትኩስ እንባ ያዘለ የከበረ መልዕክት ነበር። በነገራችን ላይ ሰው በአሜሪካ የፖለቲካ ጥገኝነት የሚያገኝበት መስፈርት በትውልድ ወይም በመኖሪያ አገሩ በሰላም የመኖር ዋስትና ማጣቱ እንጂ ለአገሩ ጠ/ሚ ደብዳቤ ስለጻፈ አይደለም። ይህንን የማያሟላ ሰው ካልዋሸና የፈጠራ ምክንያቶችን ካልደረደረ በቀር በማኀበራዊ ድረ-ገጽ ላይ ለመንግሥት ባለስልጣን ደብዳቤ ስለጻፈ የፖለቲካ ጥገኝነት ሊያገኝ አይችልም። እኔ ደግሞ ባለፉት 25 ዓመታት በአገሬ ተከብሬ፣ እንደ ልቤ ወጥቼ ገብቼ፣ በነጻነት እምነቴን ገልጬና አስፋፍቼ የኖርኩ ዜጋ ነኝና ኀሊናዬን ካልሸጥኩ በቀር መንግሥት በደለኝ ብዬ ጥገኝነት የምጠይቅበት አንዳች ምክንያት የለኝም። መቼም ቢሆን አላደርገውም። አሁን አሜሪካ ያለሁት በአገልግሎት ምክንያት ነውና ስመለስ ጊዜውና ፈቃዱ ካለዎት አብረን ቡና እንደምንጠጣ ቃል እገባልዎታለሁ።
የዶ/ር ደብረጽዮንን የፌስ ቡክ መልዕክት በተመለከተ የአንድን የመንግሥት ባለሥልጣን ጉዳይ በዚህ ጽሁፌ ባላነሳ ምርጫዬ ቢሆንም አቶ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ከንክኗቸው ስላነሱት ጥቂት ልበል። ለሰው ንግግሩና ጽሁፉ አሻራው ነው። ስለዚህ ከዚህ ቀደም ከማውቀው ንግግራቸውና ጽሁፋቸው በመነሳት መልዕክቱ የእሳቸው ለመሆኑ ጥርጥር አልገባኝም። በዚያ መጠን የእሳቸውን አሻራ የያዘ አስመሳይ ብዕርተኛ (pseudonym) ካለ እጅግ ሊደነቅ ይገባዋል።
እስቲ ከጽሁፉ መሃል አንዱን አንጓ እንውሰድና የተደረገውን ለውጥ በማስረጃነት እንመልከት፡-“መከላከያችን አመጾች በሚነሱበት ጊዜ ጉዳዩን በትዕግሥት የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ነው እንጂ እንኳንስ ለ30 ሚሊዮን ሕዝብ አይደለም መላው አፍሪካን ለመደምሰሰ አቅም እንዳለው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያረጋገጡት ጉዳይ ነው . . . ድል ለመከላከያ ሠራዊታችን” ይላል። ታዲያ የሳቸው ጽሁፍ ካልሆነ በሳምንቱ “መደምሰስ” የሚለው ተለውጦ “ማረጋጋት” በሚል ስለ ምን ተተካ? የትኛው አስመሳይ ብዕርተኛ ነው ግድ ብሎት ይህን የአስተዋይ ዕርምት የሚያደርግ? በእርግጥ ዶ/ሩ የኃይለ ቃሉን ጽኑዕነትና በእንደዚህ አይነት የውጥረት ጊዜ ከአንድ አገር ከሚመራ ሰው የማይጠበቅ መሆኑን ተረድተው ወይም በወዳጅ ዘመድ ተመክረው ለውጠውት ከሆነ የሚያስመሰግናቸው ነው። ሆኖም እሳቸው ቢለውጡትም ከመለወጡ በፊት በስክሪን ሾት ያነሳው ሰው ከሥር አስተያየት በመስጪያው ውስጥ ያልተስተካከለውን የቀድሞ ጽሁፍ ለጥፎ “ምነዋ?” ሲል ይሞግታቸዋል። ደግሞስ የፌስ ቡክ አካውንቱ የሳቸው ካልሆነ ስለ ምን ይህ ወሬ ከተናፈሰ በኋላ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዘጋ? ደግሞስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለቀረቡላቸው ቃለ መጠይቆች ለሰዓታት መልስ ሲሰጡ፣ ለአፍታ “የእኔ ፌስ ቡክ አልነበረም!” ብለው በገዛ አንደበታቸው ምላሽ ለመስጠት እንዴት ተሳናቸው? እንደ እኔ ትልቁ ቁምነገር፣ በደሎችን እያነሱ ቅሬታ ማስፋት ሳይሆን ለተፈጠሩ ስህተቶች ተገቢ ይቅርታ ጠይቆ ማለፉ ይመስለኛል።
ሌላው አቶ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ እኔን ለመንቀፍ ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንደሌለ የሚያሳብቅባቸው ከወራት በፊት በየአብያተ ክርስቲያናቱ ያቀረብኳቸውን የቃለ እግዚአብሔር መልዕክቶች ማሰሳቸው ነው። መልዕክቴን ከዐውዱ አፋተው፣ቃላቱን ለውጠው “ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አትውጡ” ብሏል በማለት ይከሱኛል። አዎን በአመጽ አላምንም! መቼም ቢሆን አመጽን አልደግፍም! ሕዝብ ሕግ እንዲያከብርና ለመንግሥት ሥርዓት እንዲገዛ እሰብካለሁ፣ አስተምራለሁ። ሆኖም በዚያው መጠን መንግሥት መስመር ሲስት፣ ፈር ሲለቅ፣ ፍትሕ ሲዛባ፣ መድልዎ ሲሰፍን፣ ኃይል ሲበዛ ከሕዝብ ውጪ ተስተካከል ሊለው የሚችል እንደ ሌለ አምናለሁ። ሕዝብ ጥያቄው እስኪመለስለት ድረስ በሰላማዊ መንገድ እምቢተኝነቱን በመግለጽ ድምጹን ቢያሰማ አግባብ እንደ ሆነ አምናለሁ። ስለዚህ “በስብከቱ እንዲህ ብሏል” እንዳሉት፣ በእርግጥ ብዬ ከሆነ (በትክክል ለማስታወስ ስላልቻልኩ ነው) ይህን አቋሜን የሚያንጸባርቅ ነው።
በመጨረሻም ለአገራችንና ለሕዝባችን፣ ለዛሬም ሆነ ለመጻኢ ዘመን እጅግ አስፈላጊ የሆነው ሰላምና ፍቅር፣ ፍትሕና ምሕረት መሆኑን ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈልግም። በእርግጥ ሰላም ስለ ጠሯትና ስለ ፈለጓት ብቻ አትመጣም። በሁሉም አቅጣጫ መስዋዕትነት ትጠይቃለች። ሰላም የምትጠይቀውን መስዋዕትነት ከፍለን፣ የሚቀጥለውን ትውልድ ከጥላቻና ከመዘዙ የምናሳርፍ እንድንሆን ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን። የሰላም አምላክ ለምድራችን ሰላምን ይስጥ።


Read 6479 times