Monday, 03 October 2016 00:00

ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(26 votes)

አዋላጇ ጠፍታ ልጁም በእግሩ መጥቶ
እናቲቱ ሞተች ልጅዬውም ሞቶ
የሚል የልቅሶ ግጥም አለ። ነፍሰ ጡር እናት ስትወልድ ልጁ በእግሩ ከመጣ አደጋ ነው ይባላል። ጎበዝ አዋላጅ አግኝታ ልጁ በአናቱ እንዲመጣ ልታግዛት ይገባል። ያ ካልሆነ ግን ባልተስተካከለ መንገድ የመጣውን ልጅ ለመውለድ የምታምጠው እናት፣ ለረዥም ጊዜ በማማጧ የተነሣ ደክማ ለሞት ትዳረጋለች። ልጇም የመሞት ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል። መውለድ ደስታ የሚሆነው ልጁ በሰላም ተወልዶ፣ ለእናቱ ጤናና ደስታ ካመጣ ነው። መውለድ ካልተስተካከለ ማርገዝ ብቻውን ድካም ነው። ለዚህ ነው ነፍሰ ጡሮች በሕክምና እርዳታ ሲታገዙ ቆይተው፣ በሕክምና እርዳታ እንዲወልዱ የሚመከረው።
ሀገር ለውጥን ልትወልድ የምትችለው የለውጥን ጽንስ በጤናማ መልኩ አርግዛ በጤናማ መልኩ እንድትወልድ የሚረዷትን ሐኪሞች ካገኘች ነው። ጽንሱ ጤናማ መሆኑን በየጊዜው የሚከታተሉ፤ ችግር ሲፈጠር ወዲያው መፍትሔ የሚሰጡ። ስትወልድም ልጁም እናቲቱም ጤንነታቸው በተጠበቀበት መንገድ እንድትወልድ የሚረዱ አዋላጅ ሐኪሞች ያስፈልጓታል። ይህ ሲጠፋ ልጁም እናቲቱም ለሞት ይዳረጋሉ።
ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ለውጥን ፀንሳ ታውቃለች። ብዙ ጊዜ የማታገኘው ጎበዝ አዋላጅ ሐኪም ነው። በዚህ ምክንያትም ብዙ ጊዜ ልጇ ሞቶባታል። ያውም በእርሷም ላይ ከባድ አደጋ አድርሶ። ማኅፀኗን ጎድቷት ስለሚሄድ፣ ሌላ ልጅ ለመጸነስ ዘመናትን እንዲፈጅባት አድርጎ።
የቅርቡ ታሪካችንን እንኳን ብንመለከተው፣የልጅ ኢያሱን ዘመን ፀንሳ ነበር። ነገር ግን ካለፉት ዘመናት በተለየ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ሂደት ባለቤት እንዲሆን ከዘመኑ በቀደመ ሐሳብ የተነሣውን ወጣቱ ንጉሥ ሐሳቡን የሚያዋልድለትና ፅንሱ በእግሩ መጥቶ እናቱንም ራሱንም እንዳይገድል የሚያደርግ ሐኪም አጥቶ፣ ሀገሪቱ ያንን ዕድል አመከነችው። የተገኙት አዋላጆች ሳይሆኑ አምካኞች ነበሩ። ልክ ፈርዖን በግብጽ፣እሥራኤላውያን ላይ አሠማርቷቸው እንደነበሩት የአዋላጅ አምካኞች።
በ1953 ዓ.ም ኢትዮጵያ እንደገና ሌላ የለውጥ ልጅ ፀንሳ ነበር። ነባሩ ንጉሣዊ ሥርዓት ከመሠረቱ ሳይናጋ ነገር ግን ዘመኑ የሚጠይቀውን ሥርዓታዊ ለውጥ ለመውለድ ፀንሳ ነበር። አዋላጅ ግን አላገኘችም። ያንን ሐሳብ በሚገባ ፀንሳ በሚገባ እንድትወልድ የሚያደርጉ አዋላጆች ብታገኝ ኖሮ፣የጥንቱን ከዘመኑ ያጣጣመ ሥርዓት ገንብታ ለመጓዝ ትችል ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው፤ ጨነገፈ።
 በ1966 ዓ.ም ሌላ የለውጥ ልጅ ፀነሰች። ሀገሪቱን ወደተሻለ ሥርዓት ሊወስድ የሚችል ተስፋ የሰነቀ ልጅ። ምን ዋጋ አለው። አዋላጆች አላገኘችም። ልጁን ጤናማ ሆኖ እንዲወለድ ከማገዝ ይልቅ አዋላጆቹ እርስ በርሳቸው ሲጨፋጨፉና ሲቧቀሱ፣ ልጁ ‹ታሪክ የጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት› ብለው በተነሡ የወታደር አጨናጋፊዎች እጅ ወደቀ። አንዲት የገጠር ሴት ለመውለድ ደርሳ አዋላጅ ጠራች። የቀን ጎደሎ ሆኖባት የማይችል ሰው እጅ ወደቀችና እርሷም ልጇም ሞቱ። አልቃሽ፡-
እንዲህ ያል ክፉ ቀን ክፉ ሰው ላይ ጥሏት
እንኳን ልጅ ልታገኝ እርሷንም ገደሏት፤
ብላ ገጠመች ይባላል። ኢትዮጵያም በ66 እንዲህ ነው የሆነቺው። ሐኪሞች ልጆቿ፤ የራስዋን ልጅ ማዋለድና ማሳደግ ሲገባቸው፣ የማደጎ ልጅ ከሶቪየት አምጥተው ልጅሽ ይሄ ነው አሏት። በማኅፀንዋ የተፀነሰውን የራስዋን ልጅ ገድለው የሰው ልጅ አሳቀፏት። የአዋላጆቹ ጠብም ልጇን እንዴት እናዋልዳት? መሆኑ ቀርቶ፣የትኛውን ልጅ ትታቀፍ? የሚለው ላይ ሆነ። እንኳን አዲስ ልጅ ልትወልድ እርሷም በወሊድ ምክንያት በተከሠተ ሕመም ለዘመናት ትሰቃይ ጀመር።
ያ ዘመን አልፎ 1983 ዓ.ም መጣ። ሁሉንም ያሳተፈ፤ የኅብረተሰብም የሐሳብም ብዝኃነትን የተቀበለ፤ ሀገሪቱ ስትመኘው የኖረቺውን ልጅ ልትወልድ የምትችልበት ዕድል ገጠማት። አሁንም ግን አዋላጆች ጠፉ። ያንን ለውጥ በፖለቲካ ብስለት፣ በዕውቀትና በትዕግሥት፣ በአመራርና በጥበብ አዋልደው፣ሀገሬ ዴሞክራሲና ዕድገትን ከነ ቃጭሉ ዱብ እንድታደርግ የሚያስችሉ አዋላጆች ጠፉ። ሁሉም የራሱን ብቻ ሲሰማና ‹ልጁ እንዲፀነስ የታገልኩት እኔ ነኝና እኔ ብቻ ልወስን› ሲል ሀገሬ ልጇን አጣችው። እርሷ ለመፅነስ እንጂ ለመውለድ ሳትታደል ቀረች።
ከሕዝቡ አብራክ ተከፍሎ በኢትዮጵያ ማኅፀን የተፀነሰውን ያንኑ ልጇን ተባብሮ ከማዋለድና እርሱኑ ተከባክቦ ከማሳደግ ይልቅ አሁንም ኮሚኒዝሙን፣ ማኦኢዝሙን፣ ዴሞክራሲውን፣ ቀያይጠንን እንደ አሻንጉሊት ሰፍተን፣ ‹ልጅሽ ይሄ ነው› አልናት። የብሔረሰቦችን ጥያቄ ልንግባባበትና ሀገር ልንመሠርትበት በምንችለው መንገድ መፍትሔውን መውለድ ሲገባን፣ ዘወትር የሚያጣላንንና የሚያበጣብጠንን የማደጎ ልጅ አመጣን። ከራሳችን አብራክ በራሳችን ማኅፀን ለኛ የሚሆን የፌዴራሊዝም ልጅ ልንወልድ ሲገባን የማደጎ ልጅ አመጣን። ይኼው አሁን በሂደት ልጁ የኛ ልጅ አለመሆኑን፤ ኢትዮጵያ የወለደችው ልጅ አለመሆኑን እየነገረን ነው። ከኛ ፍላጎት፣ ባህል፣ አስተሳሰብና ታሪክ ጋር መኖር አቅቶታል። የገዛ ልጃችን ዕዳ ነው የሆነብን። ሀገሬ ልጅ አልወጣላትም።
በ1997 ዓ.ም ሀገሬ ሌላ ልጅ ፀንሳ ነበር። ዴሞክራሲን። የአስተሳሰብ ብዙኅነትን ልትወልድ ነበር። እኛም ትወልዳለች ብለን የገንፎውንና የአጥሚቱን እህል አዘጋጅተን ነበር። ግን ምን ያደርጋል፤ ሐኪም አላገኘችም። ‹እኔ ብቻ› የሚል ሐኪም ገጥሟት፤ የዛሬውን እንጂ የነገውን የማያይ ስግብግብ አዋላጅ ገጥሟት፤ ምንጊዜም በሆስፒታሉ ውስጥ ‹ብቸኛው ስፔሻሊስት ሐኪም› እየተባለ መኖር የሚወድ ራስ ወዳድ ሐኪም ገጥሟት፤ ጊዜያዊ ችግሮችን ለዘላቂው ጥቅም ሲል መታገሥ የማይችል ሐኪም ገጥሟት፤ ወይ ‹ሁሉን ማግኘት አለያም ሁሉን ማጣት› የሚባል የማዋለጃ መሣሪያ የያዘ ሐኪም ገጥሟት ሀገሬ ልጇ ሞተባት።
እርሷም ትፀንሳለች እኛም እንፈጫለን
ለልቅሶ ነው እንጂ ለእልልታ አልታደልን፤
አለ አሉ፤ ኀዘን የጎዳው ባል። ሚስቱ በፀነሰች ቁጥር ለአራሷ የሚሆን እህል በቤቱ ይፈጫል። ነገር ግን ወለደች ተብሎ እልል ሳይባል፣ ሞተባት ተብሎ ይለቀሳል። ይሄ ነበር ባልን እንዲህ እንዲያንጎራጉር ያደረገው። ሀገሬም እንዲህ ነው የሆነቺው።
አሁንም ሀገሬ ፀንሳለች። እኛም ሊያግባባንና ሊያስማማን የሚችል ሥርዓተ መንግሥት፤ የብዙኃኑን ውክልና የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሂደት፤ የትብብር መነሻ የሚሆን፣ ከአጥር ይልቅ ድልድይ የሚገነባ ፌዴራሊዝም፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብርና የሚጠብቅ የፖለቲካ ምኅዳር ትወልዳለች ብለን ተስፋ እያደረግን ነው። ይህ እንዲሆን ግን ማዋለድ ያስፈልጋል። ኃይልና ጉልበትን፣ ዘረኝነትና ጽንፈኝነትን፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀልና እኔ ብቻ ዐውቅላችኋለሁን፣ እኔን ምን አገባኝና እኔ የለሁበትምን፣ አግላይነትንና ጠቅላይነትን፣ ጥገናዊነትንና ጊዜያዊነትን ትተን ሀገሬ ለሁላችንም የሚሆን፣ ሁላችንም እልል ብለን የምንቀበለው፤ ሁላችንም የአራስ ጥሪ የምናመጣለት፣ ሁላችንም በመወለዱ ገንፎ የምንበላበት፣ ሁላችንም ልደቱን የምናከብርለት፣ ከሩቅ ያሉት እንደ ሰብአ ሰገል ገሥግሠው፣ ከቅርብ ያሉት እንደ እረኞቹ ነቅተው ሄደው የሚያመሰግኑት ልጅ እንዲወለድልን ማዋለድ አለብን። ምሁራኑ፣ የፖለቲካው ልሂቃን፣ ደጋፊዎች፣ ተቃዋሚዎች፣ የእምነት መሪዎች፣ የሚዲያ ተዋንያን፣ ነጋድያን፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወታደራዊ አለቆች፤ ሀገራችን የፀነሰቺውን ልጅ በሰላም እንድትገላገል እንርዳት። አንዱ እግሩን፣ አንዱ እጁን፣ አንዱ ጆሮውን፣ አንዱ ጭንቅላቱን እየሳበ፣ ለራሱ ብቻ የሚጠቅመውን የየራሱን ልጅ ለማዋለድ ቢጥር ልጁ ይሞታል እንጂ ልጅ አይሆንም። ሀገሬም ፀንሳ በወለደች ቁጥር እየተጎዳች፣ እየደከመች ትሄዳለች።
እናት በተደጋጋሚ ልጆች ሞተውባት በስተመጨረሻ ተወልዶ የሚያድግላትን ልጅ ‹ማስረሻ› ትለዋለች። ያለፈውን መከራና ስቃይ ሁሉ የሚያስረሳ ማለቷ ነው። ሀገሬ ማስረሻ የሆነ ልጅ ትፈልጋለች። እልህና ኃይለኝነት አልጠቀመንም። ዘረኝነትና መከፋፈል አልፈየደልንም፣ ጥላቻና ሽኩቻ አላሳደገንም፤ ግዴለሽነትና ራስ ወዳድነት አላራመደንም። አሁን ሰከን ብሎ፤ ከስሜታዊነትም ወጥቶ፣ሀገሬ የፀነሰቺውን ልጅ እንዴት በሰላም ልትገላገል እንደምትችል መነጋገር፣ መመካከርና መተባበር ያስፈልጋል። ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት፤ ኑ፡፡ እስከ መቼ ልጅ ይሙትባት?

Read 29139 times