Monday, 03 October 2016 00:00

ለፖለቲካዊ ችግሮች - ፖለቲካዊ ውይይት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   በአገሪቱ ለተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ዕውቅ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች የመፍትሄ ሃሳብ የሚሉትን መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል። ሃሳባቸው ጆሮ አግኝቷል ወይ ለሚለው እርግጠኛ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ውጤቱን በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የመፍትሄ ሃሳቦቹ አሁንም መቀጠል አለባቸው፡፡ መንግስት በአዲሱ ዓመት አገርን ወደ ሰላምና መረጋጋት የሚያመጣ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ይደርሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ወጣት ፖለቲከኞችንና ጦማሪያንን በወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮችና መፍትሄ ዙሪያ አስተያየታቸውን አጠናቅሯል፡፡ የዚህ ውይይት ዓላማ፣ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሸራሸር መፍትሄ ማፈላለግና መጠቆም ነው፡፡ በአገራችን ለተከሰተው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ወይም አስተያየት አለን ለምትሉ ወገኖች መድረኩ ሁሌም ክፍት ነው፡፡

“አልተደመጠም እንጂ ህዝቡ ውስጥ መፍትሄ አለ”

አናኒያ ሶሪ (ጋዜጠኛና ጦማሪ)

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ተከስቷል፡፡ መንግስትና ህዝብ መሀል ያለው ግንኙነት መዛባትና የከረረ ቅራኔ ውስጥ መግባት፣ አልፎ አልፎም ማህበረሰባዊ ውጥረቶች እየናሩ መምጣታቸውን ምን እንዳስከተላቸው ስናስብ፣ ባለፉት 25 ዓመታት የህዝብና የመንግስትን ግንኙነት ለመወሰንና የሰመረ ለማድረግ የተሄደበት መንገድ ምን እንደሚመስል መገምገም ይጠበቅብናል፡፡ በ1983 የመንግስት ለውጥ ከመጣ ወዲህ ዋነኛው ቅራኔ የብሄር መብቶች ታፍነዋልና ነፃ ይውጡ የሚል ነበር፡፡ እንደ መፍትሄም አሃዳዊ  አደረጃጀቱን ወደ ፌደራላዊ ቀይሮ ብዝሃነትን ለማስተናገድ ተዘየደ፡፡ ነገር ግን ብዝሃነትን ለማስተናገድ ሲሞከር፣ በዚያው ልክ አንድነታችንንና አብሮነታችንን የሰመረ ለማድረግ ምንም አልተሰራም፡፡ ልዩነት ተኮር ሆኖ የተቀመረው ፌደራላዊ ስርአት፤ አንድነታችንን እንድንዘነጋ አድርጎናል፡፡ አንደኛው ችግር፣ የአንድነትና ልዩነት ሚዛን መሳት ያመጣው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌላው የኢኮኖሚ ችግር ነው፡፡ በስም ልማት ይባላል እንጂ በተጨባጭ የሚታየው የተወሰኑ ግለሰቦችና ዘርፎች እድገት ብቻ ነው፡፡ በጥቂት ሰዎች የተያዘ ልማት ነው፡፡ በሌላ በኩል በድህነት ውስጥ ሆኖ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚዳክረው ቁጥሩ የትየለሌ ነው፡፡ በድርቅ ተጠቅቶ በሴፍቲ ኔት እገዛ የሚዳክር ብዙ ሚሊዮን ህዝብ አለ፡፡ ከየኮሌጆቹ ተመርቆ ስራ የማያገኝ ተሰዳጅ ወጣት በብዛት ነው ያለው፡፡ መለስ ብለን የ25 ዓመቱን ጉዞ ስንገመግመው፣ በዚህች ሀገር ላይ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማትን ለማረጋገጥ የተሄደበት መንገድ እንደሚለፈፈው ሳይሆን በተግባር የተዛባና ጥቂቶችን ብቻ የጠቀመ ነው፡፡ አንድነትና ሀገራዊ ብሄራዊ ስሜትን የሚንከባከብ ባለመሆኑም ለዛሬው ችግር ዳርጎናል ብዬ አምናለሁ፡፡
አንድ ቡድን ወይም አካል በሀሳብ አሸናፊ መሆን ሲያቅተው ወደ ኃይል እርምጃ ያመዝናል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት፣ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የሃሳብ ንጥፈት የሚታይበት የአባላት ስብስብ ሆኗል፡፡ ችግሮችን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መነፅር እያየና እየተነተነ መፍትሄ የሚተልም አዲስ ብርሃን የሚሆን ኃይል ወይም ግለሰብ አለመፍጠራቸው ለዝቅጠት ዳርጓቸዋል፡፡ ኢህአዴግ ርዕዮተ አለማዊ ጉዞውን ትቶ ወደ ኃይል እርምጃ ያዘነበለው ለዚህ ነው፡፡ ወደ ወታደራዊ መንገድ ጭልጥ ብሎ እንደገባም የኃይል እርምጃው አመላካች ነው፡፡ የኃይል እርምጃ ደግሞ መቼውንም ቢሆን መፍትሄ ሆኖ አያውቅም፡፡
በቻይና ኮሚኒስታዊ ስርአት ያለውን ልምድ ብንመለከት፣ ጊዜው ለሚጠይቀው ነባራዊ ሁኔታ የፖሊሲ ማሻሻያ ይዘው የሚመጡ አዳዲስ ኃይሎች በውስጡ አሉት፡፡ በአንድ ፓርቲ ውስጥ አሻሻዮች ወይም ለውጥ አምጭዎች ይኖራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኮንሰርቫቲቭ (ወግ አጥባቂዎች) አሉ፡፡ ይህ በኢህአዴግ የለም፡፡ አቶ መለስ በዚህ ረገድ ከሳቸው ድምፅ ውጪ ያሉት እንዲደፈቁ ነው ያደረጉት፡፡ አሁን ያሉትም ያንን የአቶ መለስን ይዘው ነው ተቸክለው የቀሩት፡፡ በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ደግሞ አቶ መለስ የቸከሉትን ፖሊሲና ርዕዮተ አለም ይዞ መንገታተግ የትም አያደርስም፡፡ ሁሉም እርስ በእርስ ተፈራርተው ነው ያሉት፤አቶ መለስ ያስቀመጡትን ቀኖና ለመንካት አንዳቸውም አይደፍሩም፤ምክንያቱም ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አሸናፊ ሃሳብ ይዞ ሊመጣ የሚችል ቡድን በውስጣቸው የለም፡፡ ይህ እስከሌለ ድረስ ደግሞ በጥልቅ መታደስ የሚለው ዘበት ነው የሚሆነው፡፡ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ራሱን እያደሰ የመጣው ከውስጥ በሚፈጠሩ ቡድኖች የለውጥ ንቅናቄዎች ነው፡፡ ሀገርን መምራት ሳይንሳዊና ርዕዮተ አለማዊ ነው፡፡ ዝም ብሎ በካድሬ ማነብነብ ሀገር ከችግር አትወጣም፡፡ ስለዚህ ወቅታዊ፣ በሳይንስ የዳበሩ የመፍትሄ ሀሳቦች መምጣት አለባቸው፡፡ ኢህአዴግ ለሀሳብ መዳበርና መፋፋት ውስጡን ዝግ ስላደረገና አዲስ ሀሳብን ስለሚፈራ፣ ቃላት ከማንኳኳት ባለፈ መፍትሄ አያመጣም፡፡
እንደኔ ከዚህ በኋላ መፍትሄ ሊሆን የሚገባው፣ በመጀመሪያ ደረጃ የተገነባ የአፈና ስርአት አለ፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ ፍርሃትን በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ ኢህአዴግ በእጅጉ ተግቷል፡፡  አፋኝ አዋጆች ወጥተዋል፡፡ የሲቪል ተቋማት እንዲጠፉ ተደርገዋል፡፡ ስለዚህ  ለእነዚህ አካላት ሙሉ ነፃነት ሰጥቶ፣ የሃሳብ መንሸራሸርን መፍቀድ ያስፈልጋል። ከአፈና ስርአት ወደ ነጻ ማህበረሰብ ልንሸጋገር ይገባል፡፡ ችግሮቻችን ማህበረሰባዊ እንደመሆናቸው መፍትሄዎቻችንም ማህበረሰባዊ መሆን አለባቸው። ከእያንዳንዳችን ውስጥ ሃሳብ ፈንጥቆ በተግባር እየተሞከረ መሄድ አለበት፡፡
ህዝቡ ውስጥ መፍትሄ አለ፤ አልተሰማም አልተደመጠም እንጂ፡፡ እኔ ብቻ አውቃለሁ ሲባል ነው የቆየው፡፡ ህዝብ አሁን ያንን በቃኝ ብሏል። ኢህአዴግ ለራሱም ሆነ ለሀገሪቱ የሚበጀው ነፃ ውይይት መክፈት ነው፡፡
ይሄ በህገ መንግስቱ የተቀመጠ መብት መሆኑ ይታወቃል፤ነገር ግን በተግባር ሰዎች ዋስትና አግኝተው መናገር አለባቸው፡፡
ደቡብ ኮሪያውያንም በአንድ ወቅት እንዲህ ያለ ማህበረሰባዊ ቅርቃር ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ የማሻሻያ ሃሳቦችን አውጥተዋል።
ከእነሱም ውስጥ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን መፍታት፣ አፋኝ አዋጆችን መሰረዝና የውይይት መድረኮችን ከፍቶ ሃሳቦች እንዲንሸራሽሩ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ከብዙ ሃሳቦች ውስጥ መፍትሄ ይገኛል ብሎ ማመን ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለንበት ችግር የሁሉንም ተሳትፎ የሚፈልግ ነው። በዚህ መንገድ ብቻ ነው ችግሮችን መፍታት የምንችለው፡፡


=================================

‹‹ኢህአዴግን አግልሎ የሚመጣ መረጋጋት የለም››
ናትናኤል ፈለቀ (ጦማሪ)


አሁን አገሪቷን እያስተዳደረ ያለው መንግስት በአሳታፊነት የማያምን አግላይ መሆኑ ነው ዋናው ችግር፡፡ ጉልበትን ለመፍትሄነት መጠቀም በየጊዜው እየተጠራቀመ ሄዶ፣ አሁን ያለውን ችግር ወልዷል፡፡ ድንገት የመጣ ሳይሆን ከስርአቱ ባህሪ የተነሳ ሲጠራቀም ቆይቶ፣ ፈንቅሎ የወጣ ችግር ነው፡፡ ስርአቱ አሳታፊ አለመሆኑና ተቃርኖዎች የሚፈቱበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑ አሁን የተከሰተውን ችግር ፈጥሯል፡፡
አሁን መንግስት ችግሩን ለመፍታት የመረጠው መንገድ፣ ነገሩን አሳንሶ ከማየት የሚመነጭ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እንደሚደረገው በጉልበት ነገሮችን እናበርዳለን የሚል ሃሳብ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፖለቲካዊ መሸፈኛ አድርገው የያዙት በጥልቅ መታደስና ከህዝቡ ጋር እየተነጋገርን ነው የሚለውን ነው፡፡ እንደኔ ከምራቸው መፍትሄ ያበጃሉ ብዬ አላስብም፡፡
መፍትሄ እንስጥ ቢሉም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም አሳታፊ አይደሉም፡፡ ከመፍትሄው በእጅጉ ርቀዋል፡፡ ጥገናዊ ለውጥ ደግሞ ውጤት አያመጣም፡፡ ህዝቡም በመፈክሮቹ ይሄንኑ ነው ያንፀባረቀው፡፡ ለእንዲህ ያለው ችግር መፍትሄው፣ተቀራርቦ መነጋገር የሚቻልባቸው መድረኮች መፍጠር ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የህብረተሠቡ አካላት መወያየት አለባቸው፡፡ ችግሩን ግን ስርአቱ ይሄንን እንኳ መፍጠር የሚችል አይደለም፡፡ መድረክ ሊመቻች ቢችልም ልሂቃን አምነውበት፣ ያለ ስጋት የሚናገሩበት አይሆንም፡፡ መንግስት ለመስማት የሚፈልገውን ብቻ ለመድገም የተዘጋጁ ልሂቃን የሚሰባሰቡበት መድረክ ስለሚሆን፣ እውነተኛ  መፍትሄ አይመጣም፡፡   
አሁን ያለው ስርአት ዝም ብሎ ተንኖ የሚሄድ አይደለም፡፡ የመፍትሄው አካል መሆን አለበት። የመፍትሄው አካል ሲሆን ግን እንደከዚህ ቀደሙ ብቻውን ሆኖ አይደለም፡፡
ወዶም ሆነ ተገዶ ከሌሎች ጋር ለመፍትሄ አብሮ መቀመጥ አለበት፡፡ ኢህአዴግን አግልሎ የሚመጣ መረጋጋት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ራሳቸውን የሚያሳትፍ ለውጥ መፍቀድ አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ሃገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት አለኝ፡፡

=================================

“መፍትሄው የሽግግር መንግስት ማቋቋም ብቻ ነው”

ወይንሸት ሞላ (የሰማያዊ ፓርቲ አባል)


ችግሮች የተፈጠሩት በኔ እምነት ፍትሃዊ የሆነ አስተዳደር ባለመስፈኑ ነው፡፡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፍትሃዊ መሰረት ያላቸው ጥያቄዎች ናቸው ከህዝቡ እየተነሱ ያሉት፡፡ ገዥው ፓርቲ ደግሞ 25 ዓመት ያህል በስልጣን ላይ ቆይቶም፣ለህዝቡ የረባ ነገር ያልሰራ መሆኑን እነዚህ የህዝቡ ጥያቄዎች ምስክር ናቸው፡፡ የተፈጠረው ችግር የእነዚህ ውጤት ነው፡፡ አሁን መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት እየሄደበት ያለው አግባብ፣ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡
ኢህአዴግ እንደ ስርአት ብዙ መጓዝ የማይችል፣ፖሊሲዎቹም ኋላ ቀር በመሆናቸው የመጣ ችግር እንደመሆኑ፣ አመራሮችን በመቀያየር የሚመጣ ለውጥ አይኖርም፡፡
እንደኔ ህዝቡም ከዚህ ብዙ የሚጠብቅ አይመስለኝም፡፡ ኢህአዴግ የህዝቡን ጥያቄ አክብሮ ለሽግግር መንግስት እድሉን መስጠት አለበት፡፡ መፍትሄው የሽግግር መንግስት ማቋቋም ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ገዥው ፓርቲ በተለያዩ ሀገራት የተፈጠሩ የህዝብ ቁጣዎች ያስከተሉትን መመርመርና ችግሩም ወደዚህ እንዳይመጣ መጠንቀቅ አለበት፡፡
ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች፤ የሽግግር መንግስት አቋቁመው፣ከዚያ በኋላ ምርጫ መደረግ አለበት፡፡


==============================

“የህዝቡን ብሶት የሚያስተጋባ ሚዲያ የለም”

ሣምሶን ማሞ (ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ)


ትልቁና መሰረታዊው ጉዳይ የህዝብን በደልና ችግር ለማዳመጥ የተዘጋጀ መንግስት ያስፈልጋል፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሚዲያዎች በመንግስት ተፅዕኖ ስር የወደቁ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የህዝቡን ብሶት ማዳመጥ የሚችል ሚዲያ አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ህዝቡ የተሰማውን ቅሬታ አዳምጦ የሚያስተጋባ ሚዲያ ቢኖር፣ መንግስት የህዝቡን ብሶት ማዳመጥ የሚችልበትን እድል ያገኝ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ነው ለአመታት የታመቁ የህዝብ ብሶቶች የፈነዱት፡፡ ችግሮቹ በፊትም የነበሩ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ በስብሰባዎች ላይ የተገለጹ  የመልካም አስተዳደር ችግሮች ነበሩ፡፡ ሚዲያዎች እነዚህን ችግሮች ሊያነሱ የሚችሉበት ሁኔታ የለም፡፡ የህዝብን ችግር ማዳመጥ የሚችሉበት ሁነኛ አሰራር የላቸውም፡፡ ትልቁ መሰረታዊ ችግር ደግሞ ይሄ ነው፡፡ በአብዛኛው የባለስልጣን እግር እየተከተሉ ስብሰባ፣ ሲምፖዚየምና ሴሚናር በማሳደድ የተጠመዱ ሚዲያዎች ናቸው ያሉት፡፡ ለምሳሌ እኔ በቡራዩ ግጭት መቀስቀሱን የሰማሁት በአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው፡፡ ይሄ ለምን ይሆናል? የአገሬን ጉዳይ ለምን በአገሬ ሚዲያ መስማት አልችልም? ግጭቱን ለምን የኢትዮጵያ ሚዲያ አይናገርም? በጎንደርና በባህርዳር ስለተቀሰቀሰው ግጭት ከአማራ ማስሚዲያ መረጃ አገኛለሁ ብዬ ስከፍት፣ ስለ አተትና ተቅማጥ በሽታ ነበር የሚያወራው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ይፋ የሚያደርግ ሚዲያ ቢኖር ኖሮ፣ መንግስት አላየሁም አልሰማሁም የሚልበት አጋጣሚ አይኖርም ነበር፡፡ ሚዲያዎች ህዝብና መንግስትን የሚያገናኙ ድልድይ ናቸው፡፡
ሌላው በዚህ 25 ዓመት ውስጥ የተዘረጉት የመንግስት መዋቅሮች፣ ለሌባና ለአጭበርባሪ በጣም የተጋለጡ ናቸው፡፡ በአብዛኛው በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ጉዳይ የሚፈፀመው በእጅ መንሻ ነው፡፡ በግለሰቦች መልካም ፍቃድ ነው አገልግሎት ማግኘት የሚቻለው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ከንቲባዎችና አስተዳዳሪዎች፣ ከመንግስትም በላይ ሆነው ራሳቸውን የቻሉ አምባገነን የጎበዝ አለቃዎች ሆነዋል፡፡ መንግስት እነዚህን ማየት እንዲችል፣ ሚዲያው ሚናውን መወጣት ነበረበት፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ስለተፈጠሩ ችግሮች፣ መንገድ ላይ ያሉ ሰዎችን በማነጋገር ማስተባበያ የሚሰጥበት መንገድ ደግሞ እጅግ አስገራሚና አሳፋሪ ነው። ተቃዋሚዎች፣ ፀረ ሰላም ሃይሎች፣ አሸባሪዎች የሚባሉት፣ በእሳቱ ላይ የተጨመሩ ቤንዚኖች እንጂ ችግሩን የፈጠሩ አይደሉም፡፡ የታፈነውን የህዝብ ብሶት መንግስት ማዳመጥ የሚችልባቸው ሚዲያዎች አለመኖር የፈጠረው ቀውስ ነው፡፡
እነዚህን ቀውሶች መንግስት ለመፍታት እያደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ችግሮችና ስህተቶችን አምኖ መቀበሉ መልካም ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ውጤት ለማምጣት መንግስት ያለበት የቤት ስራ ደግሞ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡
መፍትሄው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ከስልጣን በመቀየር የሚመጣ አይደለም። በአጠቃላይ መንግስት መዋቅሩን እንደገና መፈተሽ አለበት። የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የፓርቲ አባልነትን መሠረት አድርጎ በሚሾሙ ሰዎች የማይመራበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የትኛውም የመንግስት ተቋም ለቦታው የሚመጥን ባለሙያ መመደብ አለበት እንጂ በፓርቲ አባልነት መስፈርት ሊሆን አይገባውም፡፡ የመንግስት ተቋማት አሰራራቸውን የሚፈትሹ ከሆነ ደግሞ ስር ነቀልና እውነተኛ መሆን አለበት፡፡
እያንዳንዱ ቤት እያንኳኳ ምረጡኝ ብሎ ለምኖ የተመረጠ ፖለቲከኛ፤ኋላ ዞር ብሎ አገልግሎት ፈላጊን፣ “በሣምንት አንድ ቀን ብቻ ነው የማነጋግረው” የሚልበት ሃገር ላይ እኮ ነው ያለነው፡፡ እንዲህ ያሉ ብልሹ አመራሮች፣ በመንግስት ቁርጠኝነት መወገድ አለባቸው፡፡ ህዝቡ ሳይፈራ ሳይሸማቀቅ በሙሉ ነፃነት የሚናገርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በሙሉ ፈራርሰው፣እንደገና መዋቀር ነው ያለባቸው።  
ከላይ ከጠቀስኳቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ባሻገር፣ መንግስት መዋቅሩን ፈትሾ፣ ህዝብ አወያይቶ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ የህዝቡን ችግር አድምጦ፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ማመንጨት ያስፈልጋል እንጂ እሳት ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት የትም አያደርስም፡፡
ሚዲያዎች ባለፉት 50 እና 60 ዓመታት ከገቡበት የመንግስት ብቻ አገልጋይነት ወጥተው፣ ለህዝቡም ማገልገል አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ሃገሪቱ አደጋ ላይ ትወድቃለች፡፡ እነ ሶርያ ባለቤት አልባ ሆነው፣ ለዜጎቻቸው የሲኦል ምድር የሆኑት በእንዲህ ያሉ ችግሮች ነው፡፡ መንግስት ረጅም ርቀት ተጉዞ፣ፅንፈኛ የሚባሉ ተቃዋሚዎችን ሳይቀር ወደ ሰላማዊ ትግል መመለስ አለበት፡፡ አለበለዚያ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ስኬታማ ሊሆን አይችልም፡፡  

Read 3310 times