Saturday, 01 October 2016 00:00

ኹለቱ ታራሚዎች

Written by  ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

    በአንድ አገር የተዘረጋን ሥርዓት በምናይበት ጊዜ፣ በውስጡ የተሸከማቸውን ግድፈቶች ለመሻገር የሥርዓቱ ስያሜ በራሱ መፍትሔዎችን ሊጠቁም ይችላል፡፡ ለአብነት ያኽል፣ ‹‹ፍጹማዊ የዘውድ አገዛዝ›› ስንል፣ በአንፃሩ እንደ መፍትሔ፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ የዘውድ አገዛዝ›› የሚለው ስያሜ በአእምሯችን ውስጥ ይከሠታል፡፡ ‹‹ዓምባገነናዊ ሥርዓት›› በምንልበትም ጊዜ፣ በአንፃሩ የዴሞክራቲክ ሥርዓትን በመፍትሔትነት ይጠቁመናል፡፡ የብሔር ቅራኔን በበላይነት ይዞ ልዩነትን እያፋፋመ ለሚንቀሳቀስ ሥርዓት፣ በአንፃሩ የሀገራዊ አንድነትን አስፈላጊነት እንደ መፍትሔ መንገድ ያሳየናል፡፡
‹‹ኹለቱ ታራሚዎች›› በሚል ርእስ የማቀርበው መጣጥፍ፣ ኹለት ዓላማዎች አሉት፡፡ አንደኛው ዓላማ፣ የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝብ ለሩብ ምእተ ዓመት ያኽል ክፍፍል፣ ግጭትና ጥላቻ በመካከላቸው እንዲኖር ኢሕአዴግ እንደ ሥርዓት የተከተለውን አሠራር በጥቂቱ ለማሳየት ነው፡፡ ኹለተኛው ዓላማ፤ ኹለቱ ብሔሮች ቀድሞውንም የአንድነት መንፈስ እንደነበራቸውና ወደፊትም እርስ በርስ በመገናዘብ ኅብረታቸውን ማጠናከር ያለባቸው መኾኑን ለማሳሰብ ነው፡፡
የኢሕአዴግ የመከፋፈል ዘይቤ
በኦሮሞ እና በአማራ ሕዝብ መካከል የመከፋፈል ዘይቤ ገቢራዊ ለማድረግ ሥርዓቱ በቀዳሚነት ሦስት ዐበይት መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ እነኚኽም፡- ‹ታሪክ›ን፣ ‹ስያሜ›ንና ‹ቅራኔ›ን ማስተጋባት ናቸው፡፡
ሀ/ ታሪክ
የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ተቀዳሚ ዓላማ ታሪክን አስታውሶ መዘገብ ነው፡፡ ኾኖም ግን፣ ታሪክ በይዘቱም ኾነ በባሕርይው እጅግ ሰፊ ስለኾነ፣ ዘጋቢው የሚጽፈውን ታሪካዊ ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ አጠቃሎ በማኅደሩ ሊያሰፍር አይችልም፡፡ በመኾኑም ከታሪክ ጸሐፊው አቀራረብ ልብ ሳይባል ሾልኮ አልያም ተዘንግቶ የሚቀር ይኖራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በየጊዜው የሚመጡ ሥርዓቶች፣ ታሪክን እንደ መሣርያ ለአገዛዝ ይገለገሉበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይኸውም ይኹነኝ ተብሎ ሰዎች ታሪካቸውን እንዳያውቁ፣ እንዳያስታውሱና እንዳያነሡ፣ ኢ-ታሪካዊ የኾነ የአእምሮ ድባብ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ሕዝብ በእንዲህ ዓይነት ታሪክን የመርሳት መዳፍ ሥር በሚወድቅበት ጊዜ፣ ሥርዓቱ ለፖለቲካው የሚበጀውን ነገር እየጻፈ፣ ያልተደረገን እንደተደረገ፣ የኾነውን ነገርም በጣም እያጋነነና የታሪክን ሒደት እያፋለሰ ሕዝብ እንዲቀበለው ለማድረግ ይሞክራል። በተጨማሪም፣ ለሥርዓቱ ይበጃል በሚል ወደ ኋላ ተመልሶ ታሪክን በቁንጽል በመምዘዝና በማጣመም በበጎ እንዳይተያዩ በሚፈለጉ ብሔሮች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ለዚኽም ዓላማው፣ ከየወገኑ መርዶ ነጋሪ አለቆችን በማሠልጠን፣ ‹‹በዚያን ጊዜ እንዲኽ ተደርጋችኋል››፤ ‹‹በዚኽን ጊዜ እንዲኽ ተደራርጋችኋል›› በሚል የሚፈልገውን የቅራኔ ታሪክ በሕዝቡ ዘንድ ለማሥረጽ በብዙ ይታትራል፤ ታሪክን ለሚፈለገው የፖለቲካ ዓላማና ግብ ማሳኪያም ያውለዋል፡፡
የኢሕአዴግ ሥርዓት፣ ሕዝቡ ቢያስታውስ የሚበጀውንና የሚፈልገውን ታሪክ ከመንገር ይልቅ ራሱ ሥርዓቱ የመረጠውንና የፈለገውን ታሪክ ብቻ እንድናስታውስ ብዙ ጥሯል፡፡ ይህ ጥረቱ በኹሉም የአገራችን ብሔሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ቢኾንም፣ በተለይም በኦሮሞው እና በአማራው መካከል የመለያያ ታሪክ ፍለጋ ጉልበቱን እንደ ጨረሰ እንረዳለን፡፡ ታሪክን ለፖለቲካ መሣርያ የመጠቀም ሒደት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለታሰበለት አሉታዊ ግብ እንደዋለ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በአኹኑ ወቅት፣ የአገራችን ሕዝብ የሚያደርገው ትግል የተለያየ መልክና ይዞታ እንዳለው ይታወቃል። ከእነዚህ ትግሎች አንዱ፣ የኢሕአዴግ ሥርዓት በብሔሮች መካከል ታሪክን ሽፋን በማድረግ የፈጠረውን የጥላቻ ፖለቲካ መታገልና ማሸነፍ ነው፤ ትግሉም ውጤታማ እንዲኾን የሚረዳው አንደኛው መንገድ፣ ‹‹ታሪክን ማስታወስ›› ነው፡፡
ሚላን ኩንዱራ የተባለው የቼክ ጸሐፊ፣ ”Book of Laughter and Forgetting” በሚል ርእስ በጻፈው መጽሐፍ፣ ‹‹ማስታወስ››፣ ለሰው ልጅ ነፃነት ዋና መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑን ሲገልጽ፣ ‹‹የሰው ልጅ ከገዢዎች ኃይል ጋር የሚያደርገው ተጋድሎ፣ በማስታወስና በመርሳት መካከል የሚደረግ ትንቅንቅ ነው፤›› ብሏል፡፡ በመኾኑም፣ ዜጎች በመጀመሪያ ደረጃ የማስታወስ ልዕልናቸውን ማስከበር ይኖርባቸዋል። ይህም ሲባል፣ የማስታወስ ልዕልናቸውን በመጠቀም፣ ገዢዎች ለፖለቲካ ፍጆታቸው ሲሉ ሕዝብ እንዲያስታውስ የሚፈልጉትን ታሪክ ብቻ ከማስታወስ አልፈው፣ ሕዝቡ በራሱ ፍላጎት ይበጀኛል የሚለውን ታሪክ በነፃነት ማስታወስና ለትውልድ ማስተላለፍ ሲችል ነው፡፡
ለ/ ስያሜ
በብዙ አገሮች ታሪክ እንደታየው፣ አሸናፊ የኾነ ቡድን ለተሸናፊው የተለያየ ዓይነት የስያሜ ‹በረከት› ያቀርባል፡፡ የኢሕአዴግ ሥርዓት፣ አማራ እና ኦሮሞ አለባቸው ብሎ የሚያምነውን የአመለካከትና የጠባይ ሕጸጽ ያሳይልኛል በሚል በሚከተሉት ስያሜዎች ይገልጻቸዋል፡፡ አንደኛውን፡- ‹‹ትምክህተኛ›› ሲለው፤ ኹለተኛውን፡- ‹‹ጠባብ›› ይለዋል፡፡ እኒኽን የገዥውን ግንባር ስያሜዎች፣ በሚከተሉት ኹለት ነጥቦች ሥር የበለጠ ለማብራራት እንሞክራለን፡፡
ጠባይ ማረሚያ
አማራ፣ እንደ ኢሕአዴግ አተያይ፣ ከባድ ጠባዕያዊ ጉድለት ያለበት ነው፡፡ አማራው፣ ራሱን ከኹሉም የበላይ ነኝ በሚል ትምክህተኝነት ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ ስለኾነ፣ ለራሱም ኾነ ለሌሎች ብሔሮች የሚበጀው፣ በተወሰነ የጠባይዕ ማረሚያ ተቋም ውስጥ ገብቶ ከትምክህት ጠባዕዩ ሲታረም ነው፡፡
ለመኾኑ ትምክሕት ሲባል ምን ማለት ነው? እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ስዋስው ትርጓሜ፣ ትምክሕት የሚለውን ቃል፣ ‹‹መመኪያ፤ ክብር፤ ተመካሒነት፤ ትዕቢት፤ ኩራት›› ሲል ይፈታዋል፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ በ1993 ዓ.ም. ባሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ትምክሕት የሚለው ቃል፣ ‹‹ከመጠን በላይ በራስ መመካት፤ መተማመን፤ ራስን ከፍ አድርጎ የማየት ስሜት›› እንደኾነ ይገልጻል፡፡
ያመሳከርናቸው መዝገበ ቃላት እንደሚያስረዱን፣ ትምክሕት የሚለው ቃል አዎንታዊም አሉታዊም ፍቺዎች እንዳሉት እንገነዘባለን፡፡ ከቃሉ አዎንታዊ ትርጓሜ መካከል፡- ‹‹መመኪያ፣ ክብር፣ ተመካሒነት፣ በራስ መተማመን›› የሚሉትን እናገኛለን፡፡ በአንፃሩ አሉታዊ ፍቺውን ስንመለከት ደግሞ፤ ‹‹ትዕቢት፣ ኩራት፣ ከመጠን በላይ በራስ መመካት፣ ራስን ከፍ አድርጎ ማየት፣ ማንኣኽሎኝነት›› የሚሉትን እናገኛለን፡፡ ቃሉ በዚኽ መልክ፣ ኹለት ተፃራሪ እሳቤዎችን ይዞ ሳለ፣ ኢሕአዴግ ቃሉን በአሉታዊ ፍቺ ብቻ በመጠቀምና በማጉላት ለአማራው መገለጫ ቅፅል እንዲኾን ይጠቀምበታል፡፡ በመኾኑም የአማራው ሕዝብ በራሱ መተማመን እንዳይኖረውና በታሪኩ እንዳይኮራ ኢሕአዴግ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡      
የኢሕአዴግን አተያይ ስንፈትሽ፣ ስያሜያዊ ፍረጃው የቆመባቸውን ሦስት ስሑት መሠረቶች እናገኛለን፡፡ አንደኛው፡- የአንድን ሕዝብ አእምሮና ለብዎ በጅምላ ሰይሞ፣ እንዲኽና እንዲያ ነው ማለት፣ የሥነ ልቡና ዲሲፕሊን አኹን የደረሰበት የጥናት ዕድገት ደረጃ አይፈቅድም፡፡ ኹለተኛው፡- ‹‹ለብሔሮች መብት መከበር ዘብ የቆምኩ ነኝ›› የሚለው ኢሕአዴግ፤ አማራው በራሱ ታሪክ፣ ባህልና ማንነት እንዲኮራ ከማስቻል ይልቅ በራሱ እንዳይተማመንና አንገቱን ቀና አድርጎ እንዳይራመድ ለማድረግ የታሰበ ነው፡፡ ሦስተኛው፡- ትምክሕተኛ ተብሎ የተፈረጀ ሕዝብ፣ ከአገራዊ ጥቅም ተነሥቶ አንዳንድ የመንግሥት ፖሊሲዎችን ለአገር አይበጁም ብሎ ጥያቄና አስተያየት ባቀረበ ቁጥር፣ ‹‹ያለፈ ሥርዓት ናፋቂ›› በሚል ማሸማቀቂያ አፉ እንዲሸበብ ይደረጋል፡፡
በአጠቃላይ ከገዢው ፓርቲ አንፃር፣ ከአማራው ወገን የሚመነጭ ሐሳብና ጥያቄ፣ ከፖለቲካዊ የሐሳብ ልዩነት የፈለቀ ብቻ ሳይኾን፣ ከትምክሕት የሚነሣ ጠባዕያዊ ግድፈት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በመኾኑም ሕዝቡ ጠባይዕ ማረሚያ ውስጥ ገብቶ፣ አለበት የተባለውን ‹ግድፈት› እንዲሽርና እንዲታረም ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ፡፡
ምኞት ማረሚያ
እንደ ኢሕአዴግ አተያይ፣ አማራው የጠባዕይ ጉድለት አለበት ተብሎ እንደታሰበው ኹሉ፤ ወደ ኦሮሞ ሕዝብ ስንመጣ በመሠረቱ የአመለካከት ግድፈት አለው ብሎ ያምናል፡፡ እንደ ሥርዓቱ እይታ፣ የዚኽም የአመለካከት ግድፈት መንሥኤ፣ ከጠባብ ብሔረተኝነት የመነጨ እንደኾነ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡
የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ባዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ‹‹ጠባብ ብሔረተኛ›› የሚለውን ቃል፣ ‹‹ለጎሳው ብቻ የሚያስብና የሚያደላ፤ በሌላው ላይ ጥላቻ የሚያሳይ›› በሚል ይተረጉመዋል፡፡ ጠባብ ብሔርተኛ ሙሉ ለሙሉ አሉታዊ ትርጉም እንዳለው ከመዝገበ ቃላቱ መረዳት እንችላለን፡፡ እዚኽ ላይ ጠባብ ብሔረተኛ የሚለው ቃል ‹‹ለጎሳው ብቻ የሚያስብ›› እና ‹‹ለሌላው ጥላቻ ያለው›› የሚሉትን ኹለት እሳቤዎች መያዙን እንረዳለን፡፡
ኦሮሞ፣ በአገሪቷ ከሚገኙ ብሔሮች መካከል በሕዝብ ቁጥር ቀዳሚ ነኝ፤ ሰፊ መሬትም አለኝ፤ ኾኖም የሚገባኝን ሥልጣን አላገኘኹም ብሎ የሚያስብ ሲኾን፤ በኢሕአዴግ ቸርነት የተሰጠውን የሥልጣን ድርሻ ብቻ ይዞ ለመቆየት የማይፈልግና ከፍተኛ ሥልጣን የሚመኝ ጠባብ ብሔረተኛ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ስለኾነም፣ የኦሮሞ ሕዝብ፣ ‹ጠባብነት ከወለደው ምኞት› እንዲነፃ የምኞት ማረሚያ ተቋም መግባት አለበት፤ ብሎ ያምናል፡፡
ገዥው ግንባር ኢሕአዴግ፣ ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ የፈረጀበት የጠባብነት ስያሜ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉበት እንረዳለን፡፡ አንደኛው፡- የሰውን አእምሮ እንደ ማሰሮ ወስዶ፣ ጠባብ ወይም ሰፊ ብሎ መግለጽ፣ ከመቶ ዓመት በፊት በፍልስፍናም ኾነ በሥነ ልቡና መስኮች ውድቅ የተደረገ አተያይ ነው። በመኾኑም ይህ ‹‹የጠባብና የሰፊ ተምሳሌት››፣ ስለ ሰው ልጅ አእምሯዊ ምንነት እንድንረዳ የሚፈይደው ምንም ነገር የለም፡፡ በተጨማሪም፣ ብዙኃኑን ሕዝብ በአንድ ስያሜ የሚጨፈልቅ የኢሕአዴግ አካሔድ፣ እንገልጸዋለን የሚሉትን ሕዝብ ሳይኾን በአንፃሩ ሥርዓቱ ያለበትን የአመለካከት ግድፈት የሚያሳይ ነው፡፡
ኹለተኛው፡- የኦሮሞ ሕዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር በተሰጠው ክልል ውስጥ፣ ኦሮሞ ያልኾኑ በርካታ ሕዝቦችም በሰላም የሚኖሩበት ነው። ይህም ክልሉ ከሌሎች ክልሎች በላይ ከብሔሩ ተወላጅ ውጪ በውስጡ አቅፎ እንደያዘ በግልጽ የሚታይ እውነታ ኾኖ ሳለ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ያለውን ሀብት ለሌላው የማያካፍልና የእኔ ብቻ ባይ- ጠባብ እንደኾነ መገለጹ በጣም የሚያስገርም ነው። ይህም ከክልሉ ጥቅም የሚፈልጉ አካላት፣ ‹‹የእኛ ሀብት የእኛ ብቻ ነው፤ ያንተ ሀብት ግን የአንተ ብቻ ሳይኾን የእኛም ጭምር ነው›› ከሚል የብልጣብልጥ አመለካከት የሚመነጭ እሳቤ ነው፡፡
ሦስተኛ፡- የኦሮሞ ብሔር ባለው የሕዝብ ቁጥር፣ የመሬት ስፋት፣ የሰው ኃይል ወዘተ… ኢሕአዴግ እመራበታለኹ በሚለው ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት መሠረት፣ የሚገባውን የፖለቲካ ሥልጣንና ብሔራዊ ድርሻ ይገባኛል ብሎ ሲጠይቅ ሕልመኛና ተስፈኛ ተደርጎ ይታያል፡፡ ውብሸት ሙላት የተባሉ የሕግ ምሁር፣ ስለዚኽ ጉዳይ፣ መስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ እንደጻፉት፣ ‹‹እነዚኽ ፍረጃዎች፣ ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ መኾናቸው የሚያወላዳ አይደለም፡፡… ስለኾነም ጥላቻን የሚሳድግና የሚያበረታታ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ፣ የኦሮሞ ሕዝብ አኹን አገራችን በምትመራበት ሕገ መንግሥት መሠረት የሚገባውን መብት ሲጠይቅና ለአገር ይበጃል የሚለውን የፖለቲካ አቅጣጫ ሲጠቁም፣ ይህ አመለካከት ከጠባብ ብሔረተኝነት የሚነሣ ያልተገደበ የምኞት አባዜ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በመኾኑም ከላይ እንደጠቀስኹት፣ ኢሕአዴግ፤ ሕዝቡ ምኞት ማረሚያ ውስጥ ገብቶ ከተባለው አባዜ መፈወስ ይኖርበታል ብሎ ያምናል፡፡
ሐ/ ቅራኔን ማስተጋባት     
የተፋፋመው የሕዝብ ዐመፅ፣ ወደ አገር ማፍረስ ደረጃ ይደርሳል ብለው የሰጉ ግለሰቦች በጠሩት ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ በስብሰባው ላይ የነበሩ አንድ የቀድሞ የኢሕአዴግ ባለሥልጣን፣ በአማራው እና በኦሮሞው መካከል እየታየ ያለው ትብብር ጠንካራ መሠረት እንደሌለው ተናገሩ፡፡ ይህን ሲያስረዱም፡-‹‹ጎንደር ላይ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ሕዝቡ ይዞት የወጣው የቀድሞው የአንድነት ባንዴራ ሲኾን፣ በተቃራኒው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በተካሔዱ ሰልፎች ላይ በአብዛኛው የታየው የ‹ቢሊሱማ›(የነፃነት) ተምሳሌት የኾነው ባንዴራ ነው፡፡ በመኾኑም በሰላማዊ ሰልፍ የታየው የኹለቱ ብሔሮች ትብብር፣ በአመለካከት ደረጃ የተቃረነ ነው፤›› በማለት በመተባበሩ ላይ አለኝ ያሉትን ጥርጣሬ አቀረቡ፡፡
የእኚህ ሰው አመለካከት የተመሠረተው በአንድ አገር ውስጥ የተለያዩ ዕሴቶች ተቻችለው ሊኖሩ እንደሚችሉ ካለመረዳት ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ፥ አንድነት፣ ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት ወዘተ… የተለያዩ ዕሴቶች ተደጋግፈው እንዲኖሩ መደረጋቸው የሕዝቡን የወል ጥቅም ያስከብራሉ፡፡ ባይኾን ችግር የሚመጣው፣ አንደኛውን ዕሴት ብቻ መርጦ በበላይነት በማስቀመጥ፣ ሌሎቹን የበታች በማድረግ ለመድፈቅ ሲሞከር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አንድነት በራሱ በጎ ነገር ነው፤ ነጻነትም በራሱ በጎ ነገር ነው። እነኚኽ ዕሴቶች እርስ በርስ የሚቃረኑ ሳይኾኑ፣ ኹለቱም በዕሴቶች ብዝኃነት ተጣጥመው ቢሔዱ ለአገር ህልውናና በጎነት ይጠቅማሉ፤ የአንድነትም ኾነ የነፃነት ኃይሎች በመደጋገፍ ሲኖሩና አንድ ዕሴት ብቻውን ውጤት እንደማያመጣ ስንቀበል ብቻ ነው።
የኹለቱ ብሔሮች የኅብረት ዘይቤ
በአኹኑ ወቅት በየክልሉ የተነሣው ተቃውሞና ዐመፅ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል እየተካሔደ ያለ ትግል ነው፡፡ ትግሉን በድል የሚወጣው በተለያየ መልኩ የተንቀሳቀሰው የሕዝብ ኃይል፣ አቅሙን አስተሳስሮ በመቀጠል ጠንካራ የጋራ ትብብር ሲኖረው ነው፡፡ የኹሉም ኢትዮጵያዊ ሕዝብ የጋራ ትብብር ለአገራችን ቀጣይ ህልውና አስፈላጊና ወሳኝ ነው ብዬ አምናለኹ፡፡ በዚኽ መጣጥፍ የማተኩረው፣ በአማራው እና በኦሮሞው ሕዝብ መካከል መኖር ስለሚገባው የኅብረት ዘይቤ ነው፡፡  
የኻያኛው ክፍለ ዘመን ዕውቁ ፈላስፋ ዣን-ፖል ሳርትረ፣ በፈረንሳይ ዐብዮት ወቅት የሰው ልጅ የጭቆና እና የግፍ ቀንበር ተምሳሌት የነበረው፣ ትልቁ የባስቲል እስር ቤት እንዴት በሕዝብ ትብብርና ዐመፅ እንደ ፈረሰ ሲገልጽ፤ ኹኔታው ከተራ የሰዎች ስብስብ ተጀምሮ ወደ ቡድኖች በማደግ፣ በመጨረሻም ከፍ ያለ ኅብረት ፈጥሮ ዐብዮቱ በድል እንዲጠናቀቅ ማድረጉን ያሳያል፡፡ ይህን የሕዝብ መሰባሰብና መተባበር፣ ሳርትረ በሦስት ዕርከን ይከፍለዋል፡፡ እነርሱም፡- ያልተቀናጀና ያልተናበበ የሰው ድምር(Seriality)፤ ቡድን(Group) እና የቡድን ጥምረት(Group-en-Fusion) ናቸው፡፡ እነዚኽን ሦስት ነጥቦች በማብራራትና ከነጥቦቹም አንፃር የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝብ ኅብረትን ቀጥለን እንመልከት፡፡
ሀ/ ያልተቀናጀና ያልተናበበ የሰው ድምር(Seriality)
ለሳርትረ፣ ያልተቀናጀና ያልተናበበ የሰው ድምር(Seriality) የሚለው ቃል የሰዎች ተቀዳሚ የስብስብ ዕርከንና የማኅበረሰብ ቅርፅ ነው፡፡ ይህ ስብስብ ቋሚና ዘለቄታዊነት የለውም፡፡ ለነገሩ ማንኛችንም በተለያየ ጊዜ የዚኽ ስብስብ አካል መኾናችን አይቀርም፡፡ በተጨማሪም ስብስቡ በአብዛኛው ጊዜያዊ ሲኾን፣ አልፍ አልፎ ግን የቋሚነት ጠባይ ይኖረዋል፡፡
በስብስቡ ሥር የሚገኙ ሰዎች በአንድ ቦታ ላይ ቢኾኑም፣ በመካከላቸው የአብሮነት ስሜትም ኾነ የጋራ ዕቅድ የላቸውም፡፡ በአንፃሩ ስብስቡ፣ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን የፈጠረው በመኾኑ በራስ ወዳድነት እንዲተያዩ ያደርጋቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እንዲኽ ዓይነት ስብስብ የሚከሠተው፣ እንደ መዲናችን የታክሲና የአውቶቡስ መናኸርያ ወይም የባቡር ጣቢያ አልያም ወደ ስታዲዮም፣ ካፍቴሪያ… ወዘተ. ለመግባት በምንሰለፍበት ተራ ነው፡፡
ለ/ ቡድን      
ለሳርትረ፣ ቡድን የሚለው ቃል የሰዎች ኹለተኛ የስብስብ ዕርከንና የማኅበረሰብ ቅርፅ ነው፡፡ የቡድኑ አፈጣጠር የሚመነጨው ከውስጣዊ ኑባሬ ሳይኾን በውጫዊ ኹነቶች ነው፡፡ እነዚኽ ውጫዊ ኹነቶችም በኹለት ይመደባሉ፡፡ አንደኛው፡- ፍላጎት እና እጥረት ሲኾን፤ ኹለተኛው ደግሞ፣ የጋራ ጥቅምንና ህልውናን የሚፈታተን የውጭ አደጋን ለመቋቋም ነው፡፡
የፈረንሳዩን የባስቲል እስር ቤት ኹኔታ ስንመለከት፥ ሕዝቡ፡- ተርበናል፣ ሥራ ዐጥ ኾነናል፤ ፍትሕ አጥተናል፤ መብትና ነፃነት ተነፍገናል… ወዘተ ብሎ በተናጠል ሲጮኽ ነበር፡፡ ይህ በተናጠል ይጮኽ የነበረ ሕዝብ፣ ከንጉሡ ታማኝ ወታደሮች የጥይት ሩምታ ሲዘንብበት፣ የተለያዩና ተናጠላዊ ጥያቄዎቹን በጋራ በማስተጋባትና መብቶቹንና ጥቅሞቹን ያፈነውንና የረገጠውን ዘውዳዊ ኃይል በጋራ በመጋፈጥ ግንባር መፍጠር ጀመረ፡፡ ለዚኽ የጋራ ግንባር መፈጠር ምክንያት የኾነው የንጉሡ ወታደሮች የኃይል ርምጃ ነው፡፡ በመኾኑም ሕዝቡ ራሱን ለመከላከል ሲል፣ ያልተቀናጀና ያልተናበበ ከነበረው ተራ ስብስብ (series) ወደ ቡድን ተለወጠ።
ሐ/ የቡድን ጥምረት     
ለሳርትረ፣ የቡድን ጥምረት(Group-en-Fusion) የሚለው ቃል፣ የሰዎች የመጨረሻው የስብስብ ዕርከንና ለተቀናጀ ትግል ወሳኝ የኾነ ኅብረተሰባዊ ቅርፅ ነው፡፡ ጥምረቱ የሚፈጠረው፣ ከውጭ በመጣ ኃይል ግፊት አይደለም፡፡ ጥምረቱ የሚፈጠረው በጋራና በራሳቸው ውስጣዊ ፍላጎት፣ በራሳቸው ገቢራዊ ነፃነት፣ ባላቸው የባህል፣ የሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የጋብቻ፣ የኢኮኖሚ፣ የአኗኗር… ወዘተ. የዕሴት ትስስር ነው፡፡ በእነዚኽ የጋራ ዕሴቶች የሚፈጠረው ቡድን፣ የራሱን ውስጣዊ ፍላጎትና ያለውን የማንነት ዳራ መሠረት ያደረገ በመኾኑ፤ ከብጥብጥ፣ ከክፍፍል፣ ከአድሏዊነትና ከመናናቅ የጸዳ ነው፡፡ የጥምረቱ መርሖም፣ ‹‹የአንተ ጉዳይ፣ የእኔም ጉዳይ ነው፤ የእኔ ጉዳይ፣ የአንተም ጉዳይ ነው›› የሚል ነው፡፡
ከእነዚኽ ሦስት የማኅበረሰብ የአደረጃጀት ዕርከኖች በመነሣት፣ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብን የኅብረት ዘይቤ እንፈትሻለን፡፡ ዘይቤአዊ ፍተሻው፣ በኹለት መንገድ የቀረበ ነው፡፡ በመጀመሪያ፣ ኢሕአዴግ የአማራውንና የኦሮሞውን የኅብረት ግንኙነት፣ በየትኛው ኅብረተሰባዊ ዕርከኖች ላይ ይገኛል ብሎ ያምናል? በኹለተኛ ደረጃ፣ ኹለቱ ሕዝብ ያላቸው ተጨባጭ የግንኙነት ኹኔታ ምን ይመስላል?
ከላይ ከቀረቡት የሳርትረ ምደባዎች፣ ኢሕአዴግ፣ የኹለቱ ብሔሮች ግንኙነት፣ በትንሹ፣ በተራ ስብስብና የሰው ድምር(series) ቢበዛም፣ ከቡድን ዕርከኖች እንደማያልፍ የሚያይ ይመስላል። ኢሕአዴግ በአብዛኛው እንደሚገልጸው፣ አማራ እና ኦሮሞ ከቁርሾና ቅራኔ በቀር አንድ የሚያደርግ የኅብረት ዘይቤ እንደሌላቸው አድርጎ ያስባል፡፡ ከሹመኞቹ ደጋግመን የምንሰማውን ‹‹የእሳት እና ጭድ›› ተምሳሌት ለመጥቀስ ይቻላል፡፡ ምናልባትም አብረው ይሔዳሉ ቢልም፣ ትውውቃቸው ከታክሲና ከአውቶቡስ መናኸርያ ስብስብና ሰልፍ ያለፈ አድርጎ የሚያየው አይመስልም፡፡
እንደኔ ግንዛቤ፣ የኹለቱ ሕዝብ ግንኙነት፣ ጊዜአዊና የጋራ ጠላትን ለመመከት የተፈጠረ ሳይኾን፣ በረዥም ታሪክና የጋራ ዕሴት ላይ የተመሠረተ ትስስርና መዋሐድ ነው፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ ግንኙነቱ ግጭቶችንና ጦርነቶችንም ያስተናገደ ነው። ታሪክ በባሕርይው ሒደት በመኾኑ፣ ግጭቶቹ፣ ለሕዝቦች ግንኙነት መነሻ እንጂ ኢሕአዴግ እንደሚለው የግንኙነታቸው መበየኛና የመጨረሻ ምዕራፍ ተደርገው መወሰድ የለባቸውም፡፡ በታሪክ ሒደት የነበረው ግጭት፣ የኹለቱን ብሔሮች ግንኙነት ለዘለዓለም የሚወስን አድርጎ ማሰብ ስሕተት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን፣ ግጭትን ብቻ ከታሪክ ማኅደር እያሠሠ፣ የኅብረተሰባዊ ግንኙነት መድረሻና ለቀጣይ ዕጣ ፈንታቸውም በወሳኝነት ያቀርበዋል፡፡
በመጨረሻም፣ ኢሕአዴግ በዚኽ የአመለካከት ማጥ ውስጥ የገባው፣ ከሕዝብ ግጭት በኋላ አብሮነት በፍጹም ሊኖር አይችልም በሚል እሳቤ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ ኹለቱ ሕዝብ በጋራ የሠሩት አኩሪ ታሪክ፣ ያላቸው የጋራ ዕሴት እንዲኹም የባህልና የማንነት ትስስር በማንነት ልዩነት ላይ ለተመሠረተው ፖሊቲካው አይበጅም ብሎ ስላመነበት ነው፡፡ ከኹሉም በላይ የሚገርመው፣ ራሱ ማስታወስ የሚፈልገውን ብቻ ከታሪክ ማኅደር ውስጥ በመምዘዝ፣ እኛም እርሱ መርጦ ያስታወሰንን ብቻ እንድናስብና ሌላውን የጋራ ታሪክ እንድንረሳ ጥረት ማድረጉ ነው፡፡
ማጠቃለያ     
የአባቴ ጓደኛ የኾኑ አንድ አዛውንት፣ ከምርጫ ዘጠና ሰባት በፊት አግኝቻቸው፣ ‹‹ወደየትኛው ፓርቲ ገቡ?›› ብዬ ስጠይቃቸው፣ ‹‹የትኛውም ፓርቲ ውስጥ አልገባኹም፤ ምክንያቱም ገና አቅጣጫው አልተገኘም›› ሲሉ መለሱልኝ፡፡ ምርጫው በሚካሔድበት ሰሞን አግኝቻቸው፣ ‹‹እንዴት ነው አኹንስ?›› ስላቸው፣ ‹‹አኹንማ አንድ ፓርቲ ተቀላቅያለኹ፤ አቅጣጫውም ተገኝቷል›› አሉኝ። በወቅቱ እርሳቸው እንደ አቅጣጫ የወሰዱት፣ የተለያዩ ፓርቲዎች የፈጠሩትን ቅንጅትና ኅብረት ነበር፡፡ በእኔ በኩል፣ በአኹኑ ወቅት፣ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብ፣ ኢሕአዴግ የጣለባቸውን ‹‹የማረሚያ ሰንሰለት›› ሠብረው በመውጣታቸውና የጋራ ትብብር በመጀመራቸው፣ በቅርቡ ለተቀሰቀሰው ትግል አዲስ አቅጣጫ ሰጪ ነው፣ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይኼንኑ አቅጣጫ ሳንለቅ አጥብቀን ይዘን መጓዝ እንዳለብን አምናለኹ፡፡
በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝብ የተጀመረው የኅብረት ዘይቤ፣ ለጋራ ትግሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው፡፡ የኹለቱ ሕዝብ ትብብር፣ ይበልጥ እየዳበረ ሲሔድ ሌላውም ሕዝብ በጋራ የሚሳተፍበትና የሚተባበርበት ምዕራፍ ላይ ይደርሳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለአገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታና ቀጣይ ህልውና ኹሉም ኢትዮጵያዊ ወገን ወሳኝና እኩል ሚና አለው፡፡
መጣጥፌን የማሳርገው፣ የዛሬ ኃምሳ አንድ ዓመት፣ መሐመድ እንድሪስ በጻፈውና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካሳተመው ‹‹የኮሌጅ ቀን ግጥሞች›› መድበል ባገኘኹት የግጥም ስንኝ ነው፤
ይህን ጨለማ ወንዝ ብጓዘው ብጓዘው፣
አድማሱ እየሰፋ ልቤን አፈሰሰው፤
….
ተናግቷል መሰለኝ ያ ዐውደ ሥርዓቱ፣
ታዲያ ለምን ይኾን መርዘሙ ሌሊቱ፤
ትንቢት ተናጋሮች እነኤርሚያስ እነሚክያስ፣
ዳንኤል፣ ሕዝቅኤል እነሚልክያስ ወዘካርያስ፣
ትንቢተ አብድዩ ትንቢተ ዮናስ፣
ያወራም እንደኾን ፍካሬ ኢየሱስ፣ መርምሩልኝ
እስቲ
ተናግቶም እንደኾን ሥርዓቱ በመልቲ፤
እስቲ መርምሩልኝ ምሕዋረ ልብን፣
እስቲ መርምሩልኝ ምሕዋረ ምድርን፣
እስቲ መርምሩልኝ ምሕዋረ ጨረቃን፣
ምሕዋረ ደመናን ትክክል ነወይ፣
አልተዛነፈም ወይ ዐውዱ ከፀሐይ፤
ታዲያ ለምን ይኾን ሌሊቱ መርዘሙ፣
እግዜር ታሞ እንደኾን በወዳጁ ስቅለት ባፈሰሰው
ደሙ፣
ዲያብሎስና እግዜር ፉክክር ይዘው፣
እንደኾን ነገሩ ቀን የጨለመው፣
በመሀል ተጎዳ የእግዜር እንስሳው፡፡


Read 5263 times