Saturday, 01 October 2016 00:00

በጨለማ የሁሉም አይጦች መልክ ግራጫ ነው!

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(1 Vote)

    ዓሳ ማጥመድ የፈለገ ሰው መቸም ምንም ቢሆን ዛፍ ላይ ይወጣል ተብሎ አይገመትም፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዲሞክራሲ ስርአት በመገንባት፣ ሞጋችና መብቱን ጠያቂ ህዝብ መፍጠር ችያለሁ ብሎ ከፍ ባለ የኩራት ስሜት፣ የጀብዱ ስራውን ጠዋት ማታ የሚዘረዝር ገዢ ፓርቲና መንግስት፣ ህዝብ ላቀረበለት የመብት ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ ጥይት ይሆናል ተብሎ ጨርሶ አይገመትም፡፡
ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ግን ያደረጉት እንደዚህ ነው፡፡ ዓሳ ለማጥመድ ዛፍ ላይ ወጣ። ለህዝብ የመብት ጥያቄ መልሱን በጥይት ሰጠ። የዲሞክራሲ ስርአት ተገብንቶ፣ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረዋል እየተባለ ዘወትር በሚነገርባት ሀገር፣ የመብት ጥያቄአቸውን አደባባይ በመውጣት ያቀረቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ የዲሞክራሲ ስርአት ገንብቻለሁ፤ ህዝቡም ሞጋችና መብቱን ጠያቂ እንዲሆን አድርጌዋለሁ በሚል ገዢ ፓርቲና መንግስት እጅ በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡
ነገሩ በዚህ ብቻ ቢቆም ኖሮ ራሳችንን እድለኞች አድርገን መቁጠር በቻልን ነበር፡፡ የህዝቦችን ኑሮ ለማሻሻል ድህነትን ታሪክ ለማድረግና ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ፣ ሌት ተቀን የምሰራ ልማታዊ መንግስት ነኝ እያለ፣ ነጋ ጠባ ለአመታት የሚወተውተን ኢህአዴግና መንግስቱ፣ አለአግባብ ከፈጀው በመቶዎች የሚቆጠር የሰው ህይወት ይልቅ ወደመብኝ ላለው ንብረት አብልጦና አብዝቶ መጨነቁ፣ የህዝቡን ሀዘን ይበልጥ አመረረው፡፡  
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ አንድም እንደ ሀገር መሪነታቸው፣ አንድም ደግሞ የጽድቅን መንገድ ሲሻ እንደኖረ መልካም አባት፣ የወላጅን ሀዘን በሚገባ ስለሚረዱ የተገደሉ ልጆቻቸውን ቀብረው ሀዘን የተቀመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩትን ወላጆች ለቅሶአቸውን ደርሰው “እግዜር ያጥናችሁ” ባይሉ እንኳ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ድርጅት ኢህአዴግና በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመሩት ‹‹ልማታዊው›› መንግስታቸው፣ ያሳዩትን ክብር ለሆነው የሰው ልጅ ህይወት ደንታ ቢስነት፣ ከልብ የሆነ የይቅርታና የእርቀ ሰላም ንግግር በማድረግ፣ ያዘነውንና የተቆጣውን ህዝብ ለጊዜውም ቢሆን አጽናንተው ቁጣውን ያበርዱታል፤ብለው ብዙዎች ገምተው ነበር፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተጨማሪ ሰዎች ተገድለው ተጨማሪ እናቶች የሀዘን ከል እንዳይለብሱ፣‹‹አምላክ በኢህአዴግ ተመስሎ ለመሪነት ሲቀባቸው” ባጎናፀፋቸው ስልጣን፣ ያሰማሩትን የጦር ሀይል ወደ ካምፑ በመመለስ፣ የጠፋው ሰላምና መረጋጋት በቸር እንዲመለስ አብዝተው ይጥራሉ ተብለው ተጠብቀው ነበር፡፡ ጣሊያናውያን፤ ‹‹መብረቅ አንድን ቦታ ሁለት ጊዜ አይመታም›› የሚል ጥሩ አባባል አላቸው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያገኙት ምላሽ፣የብራ መብረቅ በሀዘን የተኮማተረ ልባቸውን ሁለት ጊዜ እንደመታቸው አድርገው እንዲቆጥሩ ያስገደደ ነበር።
መንግስታቸው ያሳማረው የጦር ሀይል በተኮሰው ጥይት፣በየአውራ ጎዳናው ተደፍተው ለቀሩት ለእነኛ ምስኪን ወገኖቻቸው ሀዘናቸውን ገልፀው፣የሟች ቤተሰቦችን ያጽናናሉ ተብለው የተገመቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመግለጫቸው እንደ ታላቅ ትንግርት የተረኩልን፣ በጥፊ የመታውን ወጣት ጎረምሳ፣ በታጠቀው ክላሽ እንደ ባልደረቦቹ መግደል ሲችል፣ ጥፊውን ታግሶ ስላሳለፈው አንድ የመንግስት የፀጥታ አባል ገድል ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ ከህዝቡ ጋር በመነጋገር ላቀረባቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ህዝባቸውን ከተጨማሪ ግድያ ከመታደግ ይልቅ ሁሉም የፀጥታ ሀይሎቻቸው የህዝቡን የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዲቆጣጠሩና ህግና ስርአትን እንዲያስከብሩ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ በዚህም ለህዝብ ፍላጎት ከመገዛት ይልቅ ያላቸውን ሀይል ለማሳየት መምረጣቸውን በይፋ አሳወቁ፡፡ ይህ ትዕዛዝ ከተላለፈ በሁዋላ በተፈጠሩ ግጭቶች በአማራም ሆነ በኦሮምያ ክልል በርካታ ዜጎች በጥይት እየተመቱ በየአደባባዩ ወደቁ፡፡ ህዝቡም የጥይት አረር የበላቸውን ልጆቹንና ወዳጅ ዘመዶቹን ከወደቁበት እያነሳ፤ እንደተለመደው ‹‹ወዮ›› ብሎ አልቅሶ በመቅበር እርሙን እያወጣ ተቀመጠ፡፡
ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በቀጥታ በመወያየት ለችግሩ ተገቢውን እልባት ከመስጠት ይልቅ ባለው ሀይል መተማመንና የጡንቻውን ጥንካሬ ለማሳየት የመረጠበት ምክንያት ደካማ መስሎ መታየት ጨርሶ ባለመፈለጉ ነበር፡፡ ይሄንንም በማህበራዊ ድረ-ገጽ ባሰራጨው መረጃ ሲገል
ፅ ‹‹አንዳንድ ወገኖች የስርአቱን ባህርይ በሚገባ ካለመገንዘብ፣ ህዝቡ ጥያቄ ማንሳቱንና ለመብቱ መታገሉን ከስርአቱ መዳከም ጋር አያይዘው ሲረዱት አይተናል፡፡ ይሄ እጅግ የተሳሳተ ግምገማ ውጤት ነው፡፡›› ብሏል፡፡
ይህ ሁሉ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታም ኢህአዴግ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርአት በመገንባት፣ የህዝቡን ሰብአዊና ዲሞክራሲያ መብቶች ማስጠበቅ መቻሉን ከመናገር ለአፍታም እንኳ አልቦዘነም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ አንጋፋው የኢህአዴግ አመራር አባል አቶ በረከት ስምኦን፤ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ከሀያ አምስት አመታት የዲሞክራሲ ትግበራ በኋላ ያለውን ህብረተሰብ በምንወስድበት ጊዜ በጣም የሚያኮራ አስተሳሰብ ያለው ህብረተሰብ ለመፍጠር ተችሏል። የዲሞክራሲ ልምዱና ባህሉ ጨምሯል፡፡ ፍላጎቱን በደንብ የሚያውቅ፣ ሃሳቡን ማራመድና መግለጽ የሚችል ህብረተሰብ ተፈጥሯል፡፡ እንዲህ አይነት ህብረተሰብ በብዙ አገሮች አይገኝም›› በማለት ተናግረዋል፡፡
እዚህ ላይ እጅግ አስገራሚው ነገር ከሀያ አምስት አመታት በኋላም ኢህአዴግ ለዚህ ህዝብ የሚመጥን ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት አለመቻሉ ነው። ባለፉት ሀያ አምስት አመታት ስለ ኢህአዴግ ብጥር፣ ጥርጥር አድርገን ያወቅነው አንድ መሠረታዊ እውነት፡- ኢህአዴግ ለዲሞክራሲና፣ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ባዕድ ወይም ባይተዋር መሆኑን ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግና ዲሞክራሲ ዘይትና ውሀ ናቸው፡፡ እናም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲሞክራሲያዊ ስርአት በመገንባት፣ የዜጎችን መብት ማስከበር ችያለሁ፤ ዲሞክራሲን ተግባራዊ ማድረግና ማስፋት ችያለሁ፤ ሞጋችና መብቱን ጠያቂ ህዝብም ፈጥሬአለሁ የሚለው የኢህአዴግ መከራከሪያ፤ ላመል ታህል እንኳ ውሀ መቋጠር የማይችል፣ ከገሀዱ እውነታ ጋር የሚጣረስ፣ የባዶ ገረወይና ጩኸት ብቻ ነው፡፡
አንድ የመንግስት ስልጣን የተቆጣጠረ ፓርቲ፤ ጨርሶ የማያውቀውንና የማይፈልገውን የፖለቲካ ስርአት መገንባት አይችልም፡፡ (የቀድሞው አንጋፋ የህውሃት ታጋይ ሜጄር ጄነራል አበበ ተክለአረጋይ በአንድ ፅሁፋቸው እንደገለፁት፤ የ60ዎቹ ትውልድ የአመፃ እንጂ የዲሞክራሲ ትውልድ አይደሉም) የኢህአዴግም ነገር ልክ እንደዚህ ነው። እናም ኢህአዴግ የማያውቀውንና የማይፈልገውን ዲሞክራሲን ተግባራዊ ማድረግና ማስፋት ችያለሁ እያለ ቀንና ማታ የሚወተውተን፣ እንዲያው ክፉ የአፍ አመል ሆኖበት ነው እንጂ ነገርየው ባዶም ሀሰትም እንደሆነ ራሱም አሳምሮ ያውቀዋል፡፡
ይህ የኢህአዴግ ውትወታ ለሞት መድሀኒት ታህል ጥቂት እውነት ኖሮት ቢሆን፣ የሺ ወገኖቻችን ግንባርና ደረት የፀጥታ ኃይሎች ጥይት ሲሳይ መች ይሆን ነበር? እንደ ጎርፍ የፈሰሰው ደማቸውንስ መቸ አፈር ልሶት ይቀር ነበር፡፡
ኢህአዴግ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ፌደራላዊ አስተዳደር ተገንብቶ፣ የብሄር ብሄረሰቦች ማንነት እንዲታወቅና እኩልነታቸው እንዲረጋገጥ ተደርጓል ብሎ ላለፉት ሀያ አመታት ቢለፍፍም፤ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ማንነታቸው እንዲታወቅና እኩልነታቸው በተግባር እንዲረጋገጥላቸው ላለፉት ሀያ አመታት በመሟገት ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢህአዴግ ግጭቶችን ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በመከተል እየፈታሁ በመሆኑ ውጫዊና ውስጣዊ ሰላም ተከብሯል እያለ ቢከራከርም፣ ‹‹ሀገሪቱን የብሄር ብሄረሰቦች እስር ቤት አድርገዋት ነበር›› በሚል ዘወትር በሚያወግዛቸው ንጉሱና በደርግ ስርአት ዘመን እንኳ ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ፣ የህዝቦች መፈናቀልና የብሄር ብሄረሰቦች ግጭት ባለፉት ሀያ አምስት አመታት እንደተከሰቱ እማኝ መቁጠርም ሆነ  ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡
ኢህአዴግ መንግስትና ሀይማኖት ተለያይተዋል፤ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነትም ተከብሯል ቢልም ምዕመናን፤ መንግስት በሀይማኖታቸው ጉዳይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም ጥያቄአቸውን ዛሬም ድረስ ከማቅረብ አልቦዘኑም። እነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች የኢህአዴግ የፌደራሊዝም ፕሮጀክት በይዘቱም ሆነ በአተገባበሩ ቀላል የማይባሉ ችግሮች እንዳሉበት ያሳያል፡፡
 አሁን ኢህአዴግ ያለው ብቸኛ አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይኼውም  ከእውነታ ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ!! ራሱን ማወደሱንና ማሞገሱን ለጊዜው ወዲያ ብሎ ከተጨባጭ እውነታው ጋር መታረቅ ይኖርበታል፡፡
ራሱን ሳይሆን ህዝብን ማዳመጥና መልስ መስጠት መጀመርም አለበት፡፡ አለበለዚያ መጨረሻው አያምርምር፡፡


Read 4376 times