Saturday, 01 October 2016 00:00

መፍትሄው፤ ከየትም አይመጣም - እዚሁ እኛው ካልፈጠርን!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(10 votes)

     ከአሜሪካና ከአውሮፓ ግድም፣ ለአገራችን ችግር የሚበጅ አንዳች መፍትሄ ወይም ድጋፍ ለማግኘት መመኘት፣ በጭራሽ ነውር አይደለም። በእውቀትም ሆነ በሃብት ቀድመው የደረጁ፣ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ስርዓታቸው የተሻሉ... በአጠቃላይ፣ በስልጣኔ ደህና የተራመዱ አገራት ናቸው - እነ አሜሪካ እነ እንግሊዝ። ከአርአያነታቸው በተጨማሪ፣ በተግባር የአገራችንን ችግሮች ለመፍታት ሊያግዙን ይችላሉ ብለን ብንመኝ፣ ተገቢ ነው። ደግሞም፣ ካሁን በፊት፣ አግዘውናል። ሳንጠይቃቸውም ጭምር፣ በራሳቸው ፍላጎት ሊያግዙን የሞከሩበት ጊዜ አለ።
የስንዴና የዘይት እርዳታ በመስጠት ብቻ አይደለም። ለዘለቄታው የሚጠቅም.... በግለሰብ መብት፣ በነፃ ገበያና በሕግ የበላይነት ቁልፍ ሃሳቦች ላይ የተመሰረተ፤ “ስልጡን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የኑሮ ሥርዓት” እንድናዳብር በተደጋጋሚ ግፊት አድርገዋል። በእነዚህ ቁልፍ ሃሳቦች ላይ በመተማመን፣ ተቀናቃኝ ድርጅቶች ሳይቀሩ በሰላም እንዲወያዩና እንዲደራደሩ በማበረታታት፤ የበርካታ አገራትን ችግር ለመፍታትም ድጋፍ ሰጥተዋል።
አዎ፣ አልፎ አልፎ ስህተት ሰርተዋል። አንዳንድ ተቺዎች ግን፣ “የአሜሪካና የአውሮፓ ጣልቃ ገብነት”ን፣ በደፈናውና በጭፍን ለማንቋሸሽ ይሽቀዳደማሉ። እንዲያውም፣ ግጭትና ቀውስ በየአገሩ በተፈጠረ ቁጥር፣ በተለይ አሜሪካን ተጠያቂ በማድረግ ውግዘት ማዥጎድጎድ፣... የአዋቂነት ምልክት ይመስላቸዋል። ይኸውና ምኞታቸው እየደረሰ ነው፤ ደስ ይበላቸው። ከቅርብ አመታት ወዲህ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፣ የዳር ተመልካችነትን መምረጥ ጀምረዋል። “ጣልቃ ገብነትን እርም” ወደ ማለት እያዘነበሉ ነው። ቢቢሲ፣ “An Obituary for the age of Intervention?” በሚል ርዕስ ሰፊ ዘገባ አቅርቦ የለ! የምስራች አዋጅ ነው? ወይስ የመርዶ አዋጅ? ምንም ሆነ ምን፣ ከሕልፈት ጋር የሚመጣው፣ ቀብር ነው -- “የጣልቃ ገብነት ቀብር”!
እንደ ቢቢሲ ዘገባ፣ “የጣልቃ ገብነት ዘመን” በተለያዩ ህመሞች ከተዳከመ በኋላ፣ በሊቢያ ሰበብ ሞቷል። የቀብር ቦታውም፣ የእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥ እንደሆነ ተጠቁሟል። ለምን? መልሱን የምናገኘው፣ የእንግሊዝ ፓርላማ ካሰራጨው አስገራሚ ሪፖርት ነው። በፈረንሳይ ፊታውራሪነት፣ በእንግሊዝ አይዞህ ባይነት፣ በአሜሪካ ይሁንታ፣ በዩኤን አስተናባሪነት... “ሊቢያን ለማዳን” የተካሄደው የጣልቃ ገብነት ዘመቻ፣... አገሪቱን ለትርምስ የዳረገ የስካር ድግስ እንደሆነ ያብራራል - የፓርላማው ሪፖርት።  
እንግዲህ፤ ወደ እንግሊዝና ወደ ሊቢያ ጎራ በማለት በምንጀምረው የዛሬ ቅኝታችን፤ የተባበሩት መንግስታት (ዩኤን)፣ በአፍሪካና በሌሎች አገራት የሚከሰቱ ቀውሶችን ከማብረድ ይልቅ የሚያባብስ እየሆነ መምጣቱን እንመለከታለን። ከዚያ...ወደ አሜሪካ በማቅናትም፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ እንደ ሊቢያ በመሳሰሉ የአፍሪካና የአረብ አገራት ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ ከራሳቸው አንደበት እንሰማለን። የአፍሪካና የአረብ አገራትን፣ ተራ በተራ ለቀውስና ለትርምስ እየዳረጉ የሚገኙ ሦስት ዋና ዋና ችግሮች ምን ምን እንደሆኑ በመዘርዘር ትንታኔ የሚያቀርቡልን ባራክ ኦባማ፤ ሦስቱን ችግሮች የሚፈውስ መድሃኒት እንደሌላቸው ቁርጡን ይነግሩናል።
ከትርምስ ለመዳንና ከቀውስ ለመውጣት፤ እንዲሁም በትክክለኛ የስልጣኔና የብልፅግና ጎዳና ለመጓዝ፤ ከእነ እንግሊዝ ወይም ከእነ አሜሪካ ሁነኛ መፍትሄ አናገኝም ማለት ነው። ለምን? ዘመኑ፣ የመደናበር ዘመን ሆነና፤ አውሮፓና አሜሪካም፣ በየራሳቸው አገር ችግር፣ ግራ እየተጋቡ መሆናቸውን ምስክርነት ሰምተን፣ የቅኝት ጉዟችንን ለማጠናቀቅ ወደ አገራችን እናመራለን - የአገራችንን ችግር ለመፍታት፣ ከኛ ሌላ ማንም እንደሌለ በመገንዘብ፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመፈተሽ።      
የእንግሊዝ ፓርላማ ሪፖርት - ምናባዊ ሊቢያና እውነተኛ ሊቢያ
የፓርላማ አባላት የዛሬ ሁለት ሳምንት ሪፖርታቸውን ይፋ ያደረጉት፤ ከአንድ አመት በላይ የፈጀ የምርመራ ስራ በማጠናቀቅ ነው። የሊቢያን ችግር ለመፍታት፣ በእነ እንግሊዝ የተወሰዱ እርምጃዎችን፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ መርምረዋል - የሪፖርቱ አዘጋጆች።
የነገሩ መነሻ፣ 2003 ዓ.ም ነው። ከቱኒዚያና ከግብፅ በመቀጠል፣ በሊቢያ የዜጎች ቅሬታ ገንፍሎ፤ ተቃውሞና አመፅ የተቀጣጠለበት፤ ከዚሁ ጎን ለጎን አገሪቱን ለ40 ዓመታት የገዙ ዝነኛው አምባገነን ሙዐመር ጋዳፊ፣ “እነዚህ አይጦች”... እያሉ የሚፎክሩበት ጊዜ ነው። ጋዳፊ፣ ተቃዋሚዎችን ለማስፈራራትና ለማስበርገግ በማሰብ ነበር፣ የዛቻ መዓት ያዥጎደጎዱት። ግን መዘዝ አመጣ። ለጣልቃ ገብነት መነሻ ሆነ።
“ጋዳፊ ህዝቡን ሊጨርሱት ነው” በሚል ስጋት፣ ሲቪሎችን ከእልቂት ለማዳን ነበር እነ እንግሊዝ ጣልቃ ለመግባት የወሰኑት። ለካ አላወቁም። ተቃውሞው፣ ወደ አመፅና ወደ ጦርነት ሲለወጥ፣ በጎሳ የተቧደኑ ታጣቂዎችና የሃይማኖት አክራሪዎች እየተበራከቱ አገሪቱን ለማጥለቅለቅ አሰፍስፈዋል። የእንግሊዝ መንግስት ግን ይህንን አያውቅም ነበር ይላል የፓርላማው ሪፖርት። መዘዙ ቀላል አይደለም። አምባገነኑ የጋዳፊ መንግስት ሲፈርስ፣ አገሪቱ የታጣቂ ቡድኖች መነሃሪያ ሆነች። በእርግጥ፣ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት፣ “ደረጃቸውን የጠበቁ” ሁለት የፖለቲካ ምርጫዎች ተካሂደዋል - አንድ የሽግግር ምርጫ፣ አንድ ደግሞ መደበኛ ምርጫ። ምርጫዎቹ ግን ጥቅም አላስገኙም። ስድብና ዘለፋ፣ ዛቻና የታጣቂ ቡድኖች ዘመቻ በተጧጧፈበት ምርጫ ውስጥ፣ አሸናፊ ለመሆን የሚችሉት ጤናማዎቹ ፖለቲከኞች አይደሉም። እናም የእንግሊዝ የፓርላማ ሪፖርት እንደሚገልፀው፤ በብስለት የሚታወቁ የሊቢያ ፖለቲከኞች፣ ከጨዋታ ውጭ የሆኑት በምርጫ ነው።
ለነገሩ፤ በምርጫ ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ፣ ትርጉም ያጣው ወዲያውኑ ነው። በመጀመሪያው ምርጫ ስልጣን የያዙ ቡድኖች፣ ስልጣን አልለቀቁም። በሁለተኛው ምርጫ ላይ፣ አሸናፊ የሆኑ ፖለቲከኞች፣ ያው... ከጎን ሌላ ሁለተኛ መንግስት መሰረቱ። ሊቢያ፣ የእልፍ ታጣቂ ቡድኖች መነሃሪያ መሆኗ ሳያንስ፣ የሁለት መንግስት አገር ሆነች - በምስራቅና በምዕራብ። በየፊናቸው ሁለት የነዳጅ ሚኒስትር፣ ሁለት የመከላከያ ሚኒስትር ወዘተ ሾመዋል። ነገር ግን፣... የራሳቸው የጦር ሃይል የላቸውም። የነዳጅ ማመንጫ ጣቢያዎችም በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች እጅ ስር ናቸው።
አገሪቱ እንዲህ በስርዓት አልበኝነት ብትተራመስም፤ ... እንግሊዝንና ዩኤንን ጨምሮ ሊቢያን ለማገዝ ከየአቅጣጫው የጎረፉ መንግስታትና ተቋማት፣ ያን ያህልም ግድ አልሰጣቸውም። በቃ... በእልፍ አዕላፍ የትምህርት፣ የንፁህ ውሃ፣ የጤና ፕሮጀክቶች አገሪቱን ለማጥለቅለቅ ይዋከባሉ። ሁሉም፣ ስለ ውይይትና ስለ ድርድር ያወራል፤ ስብሰባና ጉባኤ ያዘጋጃል።
ወይ ጉድ!... ‘ሊቢያ’ የተሰኘች ሌላ ምናባዊ አገር ፈጥረው በምኞት ዓለም ውስጥ የሚንሳፈፉ ይመስላሉ። እውነተኛዋ ሊቢያ ግን፣ ምስቅልቅሏ ወጥቷል።
በበርካታ ወራት ውይይት፣ በአታካች ሽምግልናና ድርድር አማካኝነት የተፈረመ ስምምነት፣ ለአንድ ቀን እንኳ ተግባራዊ ሳይደረግ ይፈርሳል። በዚህ በዚህ፣ ግራ መጋባት የጀመሩ ለጋሾች፣ ከጭንቀት የተነሳ፣ ያላውጠነጠኑት የዘዴ አይነት የለም ማለት ይቻላል። የዲሞክራሲ ህልም፣ የምርጫ ናፍቆት፣ የነፃነት ምኞት፣... ተራ በተራ እየደበዘዙና እየራቁ፣ ጨርሶ የማይታሰቡ ሆነዋል። ትርምሱ ረግቦ ትንሽ ሰላም እንዲፈጠርና ሊቢያ በወጉ ‘አገር’ እንድትሆን ማድረግ እንኳ አልተቻለም። በቃ መፍትሄ አልተገኘም። ምናልባት...  “ከ40 ዓመት በፊት የፈረሰው የሊቢያ ንጉሣዊ ስርዓት፣ እንደገና ነፍስ ቢዘራ፣ አገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት ይረዳ ይሆን?” ... እንዲህ እስከ ማሰብም ተደርሷል ይላል - የእንግሊዝ ፓርላማ ሪፖርት። እንደ ብዙ ሃሳቦች፣ ይሄኛውም ሃሳብ፣ ቅንጣት የተስፋ ፍንጭ አልተገኘበትም።
በአጭሩ፣ እነ እንግሊዝ ሊቢያን ለመርዳት የወሰዱት እርምጃና ውጤቱ ሲታይ... “Shit Show” የሚለው ስያሜ ይመጥነዋል ይላሉ - የሪፖርቱ አዘጋጆች። (ይህንን ስያሜ ያገኙት፣ ከባራክ ኦባማ እንደሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም)።
በዚሁ ሪፖርት ውስጥ፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አራቴ በቀጥታ ተጠቅሰዋል። ታዲያ፣ የኦባማ ሃሳቦችን ለማሳየት ሲባል በሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱት አባባሎች፣ ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ናቸው - “The Obama Doctrine” በሚል ርዕስ ባለፈው ሚያዚያ ወር ከወጣው ሰፊ ፅሁፍ የተወሰዱ ናቸው። የእንግሊዝ ፓርላማ ሪፖርት ውስጥ፤ “The Obama Doctrine” የተሰኘው ፅሁፍ ተመርጦ በተደጋጋሚ መጠቀሱ አይገርምም። ለምን በሉ። በ54 ገፅ የተዘጋጀው የእንግሊዝ ፓርላማ ሪፖርትና የኦባማ ዶክትሪን የተሰኘው ፅሁፍ ይመሳሰላሉ። በቃላት ብዛትና ርዝመት ብቻ አይደለም የሚመሳሰሉት - በይዘትና በቅኝት ጭምርም እንጂ።
የእንግሊዝ ፓርላማ ሪፖርት፣ “የጣልቃ ገብነት ቀብር” የታወጀበት ሰነድ እንደሆነ ተነግሮለታል። “The Obama Doctrine” በሚል ርዕስ ዘ አትላንቲክ መጽሄት ላይ የወጣው ሰፊ ዘገባ  ደግሞ፣ “ጣልቃ መግባትን እርም ብያለሁ” የሚል የኦባማ ስሜት በተደጋጋሚ የተስተጋባበት አስገራሚ ፅሁፍ ነው።
በአንድ በኩል በአፍሪካና በአረብ አገራት ዙሪያ እየተስፋፋ የመጣውን አሳሳቢ ቀውስ በደንብ ለመረዳት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት ምን ያህል ግራ እንደተጋቡ... በደንብ ለመገንዘብ የሚፈልግ ሰው፤ ሁለቱን ሰነዶች ማንበብ አለበት።
“Shit Show” - ባራክ ኦባማ
የሊቢያው ዘመቻ ሙሉ ለሙሉ የኪሳራና የውድቀት ዘመቻ መሆኑን የገለፁት ባራክ ኦባማ፤ ትርምስ ብቻ ነው የተረፈን ሲሉ ተናግረዋል። ሊቢያን ለማዳን የተካሄደው የጣልቃ ገብነት ዘመቻ፣ በተራ ቋንቋ “Shit Show” ብለውታል - ኦባማ። ምን ማለት ነው? እልፍ አጋፋሪ ወዲህ ወዲያ ውር-ውር ሲል፤ ቁምነገር የሚሰራ ይመስላል፣ ግን ወከባ ብቻ ነው። ከመደናበርና ከመቅበዝበዝ ያልተለየ፣ ዝብርቅርቁ የወጣ አስቀያሚ የተሳከረ የትርምስ ድግስ...  “Shit Show”።
ድግሱ የተሳከረው፣ በሊቢያ ብቻ አይደለም። ከዚያ በፊትም፣ ኢራቅን ከአምባገነኑ ሳዳም ሁሴን መንጋጋ በማላቀቅ፣ የዲሞክራሲና የብልፅግና፤ የሰላምና የነፃነት አርአያ ለማድረግ የተጀመረው ድግስ፣ ውሎ ሲያድር እየተዝረከረከ፣ እየተበላሸና እየተሳከረ የትርምስ ድግስ ሆኖ ቀርቷል። የአፍጋኒስታንም እንዲሁ። የየመንም ተመሳሳይ ነው። ይሄ ሁሉ ተጠራቅሞ፣ የሊቢያ ሲደመርበት፤... ባራክ ኦባማ፣ ከእንግዲህ ተጨማሪ “Shit Show” ከመፍጠር መቆጠብ፤ መመሪያዬ ሆኗል አሉ። “Don’t do stupid shit” በሚል መመሪያ።
የባራክ ኦማባን የቋንቋ አጠቃቀም የተመለከቱ በርካታ ፖለቲከኞች፤... “የቺካጎ ነገር!” በማለት ቅሬታቸውን ይገልፁ ይሆናል። ግን ችግር የለውም። ፕሬዚዳንቱ በተራ የጎዳና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን፣ በጨዋ ቋንቋም ሃሳባቸውን አስረድተዋል። በርካታ አገራትን እያዳረሰ የሚገኘው ቀውስ ለጊዜው መፍትሄ እንደሌለው ኦባማ ጠቅሰው፤ የአሜሪካ መንግስት ጣልቃ በመግባት የሚያመጣው ለውጥ የለም። ይልቅስ፣ ገሸሽ ብንል ነው የሚያዋጣን ብለዋል - (Don’t do stupid shit እንደማለት ነው)።
ለመሆኑ፣ የዘመናችን ቀውስ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ የማያገኘው ለምንድነው? ኦባማ፣ የቀውሱ ሦስት ዋና ባህርያትን ይጠቅሳሉ -
የሃሳብ (የተሳሳተ የጭፍንነትና የአክራሪነት አስተሳሰብ)፣
የኑሮ (ኑሮን ለማሻሻል እድል በማይፈጥር ኢኮኖሚ ሳቢያ የሚበራከት ቅሬታ)
የማንነት (የግል ማንነትን የሚያጠፋና በጠላትነት የሚያቧድን ዘረኝነት)።  
እንደ ሊቢያ የመሳሰሉ የአፍሪካና የአረብ አገራትን ለመቃኘት ብንሞክር ምን አይነት ክስተቶች እንደሚያጋጥሙን፣ ባራክ ኦባማ በራሳቸው አንደበት ይዘረዝራሉ።
የመሻሻልና የመበልፀግ እድልን ለሕዝባቸው መፍጠር ያልቻሉ መንግስታትን ታያላችሁ።
ነውጠኛ የአክራሪነት ጭፍን ርዕዮተ-ዓለምን ታያላችሁ - ለዚያውም በኢንተርኔት የማህበራዊ ድረገፆች አማካኝነት የጦዘ።
ስልጡን የፖለቲካ ልምድ በራቃቸው በእነዚሁ አካባቢዎች፣ ገናና መንግስት ሲፍረከረክ፣... ጎራ ለይቶ በጠላትነት የመቧደን ዘረኝነት፣ ብቸኛ የመሰባሰቢያ መንገድ ሲሆን ታያላችሁ።
እና ምን ይሻላል? በቃ ተስፋ የለውም? በደፈናው ተስፋ የለውም ለማለት አልፈለጉም - ኦባማ።
አዎ፣ የሰው ልጅ፣ እየወደቀና እየተነሳ፣ በረዥም የዘመናት ታሪክ፣ የነውጠኝነትና የጠላትነት ዝንባሌዎችን እየገራ፤ በኑሮና በጤና፣ እንዲሁም በእርስበርስ ግንኙነት እየተሻሻለ መጥቷል። ነገር ግን፣ እየተሻሻለ የመጣው ስርዓት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኋሊት ሊመለስ እንደሚችል በግልፅ እየታየ መሆኑን ባራክ ኦባማ ከነምክንያቱ ለማስረዳት ይሞክራሉ። ለምሳሌ በበርካታ የአፍሪካና የአረብ አገራት ውስጥ፣ ለዜጎቻቸው የመሻሻል እድል መፍጠር ያልቻሉ መንግስታት ሞልተው የለ? ይሄኔ፣ የኑሮ ችግር እየከበደ ወይም የመሻሻል ተስፋ እየተሟጠጠ፣ የዜጎች ቅሬታ ይበራከታል።
በእርግጥ፣ “የዚህ ዓለም ኑሮ፣ አላፊና ረጋፊ ነው” በማለት ብልፅግናን የሚያናንቁና ምናኔን የሚያንቆለጳጵሱ ሰዎች፣ በብዛት ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን፣ የኑሮ ችግር እየከበደ ሲመጣ፣ አብዛኞቹ የዘወትር ስበከታቸውን ይዘነጉታል። ብልፅግናን በመመኘት፣ የኑሮ ችግርን ማማረር ይጀምራሉ። “ከራስ ኑሮ በፊት፣ ለሌሎች ሰዎችና ለህዝብ ማሰብ!” እያለ የመስዋዕትነት አምልኮን የሚደሰኩር ሰውም፤ በብዛት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን፣ የራሱ ኑሮ ሲጎሳቆልበት፤ ዲስኩሩን ረስቶ፣ በምሬት ማጉረምረም፣ ከቻለም በቁጣ ማስገምገም እንደሚጀምር አትጠራጠሩ።
የተሳሳተ ወገኛ ስብከትና ዲስኩር፣ ምንም ውጤት የለውም ማለቴ አይደለም። ጭፍንነትን በማንገስ፣ የመፍትሄ ሃሳብ እንዳይመጣ እንቅፋት ይሆናል። ነገር ግን፤ የኑሮ ችግርንና ምሬትን አያስቀርም። የአገሬው ስብከትና ዲስኩር ምንም ሆነ ምን፤ የመሻሻል እድልን ለዜጎች መፍጠር ያልቻለ መንግስት ባለበት አገር ሁሉ፤ የዜጎች ቅሬታና ምሬት እያበጠ መምጣቱ አይቀሬ ነው። ከዚያስ?
“ጫናና ውጥረት ሲከብድ፣ የማህበረሰብ ስርዓት መፍረስ ይጀምራል” በማለት የተናገሩት ኦባማ፤ ከዚያ በኋላ... ምን እንደሚከሰት መዘዙን ይገልፃሉ - “Then the default position is tribe...” በማለት። ከጭፍን ስብከትና ዲስኩር የራቀ፣ ስልጡን የመፍትሄ አስተሳሰብ ካልመጣ በቀር፤... የኑሮ ቀውስ ወደ ጠቅላላ የሕይወት ቀውስ ያመራል። ጫናና ውጥረት ሲበረታ፤... በጉልበት ገናና የነበረው መንግስት መድከም ሲጀምር፤... የአገሬው ስርዓት ሲፍረከረክ፤... ያኔ፣ የብዙ ሰዎች መደበኛ አድራሻ፤... የብዙ ሰዎች “የፍጥርጥር መጠለያ”፣...  ዘረኝነት ሆኖ ያርፈዋል - ጎራ ለይቶ በጠላትነት መቧደን።
ይሄ በባራክ ኦባማ የቀረበው ሃሳብ፣ አዲስ አይደለም። “the default position”... የሚለው አገላለፅ፣ “the natural state” ከሚለው ነባር አባባል የተወሰደ እንደሆነ ራሳቸው ኦባማ ጠቁመዋል። እንዲያውም፣ “the natural condition” ከሚለው የፈላስፋው የቶማስ ሆብስ አባባል ጋር የተዛመደ ሃሳብ እንደሆነ ኦባማ ለመደበቅ አልሞከሩም። በሆብስ አስተሳሰብ፣ “the natural state” ማለት፣ ህግና ስርዓት ያልተበጀለት አኗኗር ማለት ነው - የአእምሮ ግንዛቤና አርቆ አሳቢነት ያልነካካው አኗኗር፣ ከሌሎች እንስሳት ያልተለየ፣ እርስበርስ የመበላላት፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ የአውሬ ‘ተፈጥሯዊ አኗኗር’! “እንደ ፍጥርጥሩ መኖር” ወይም “የፍጥርጥር ኑሮ” “ ልንለው እንችላለን።
እንዲህ አይነት የአውሬ አኗኗር፣ ለሰው ልጅ ትክክለኛ አኗኗር አለመሆኑን ሆብስ ሲገልፅ፤ “ሁሉም ሰው የሁሉም ሰው ጠላት የሚሆንበት” አኗኗር፣ ከፋታ የለሽ ጦርነት እንደማይለይ ያስረዳል - ሁሉም በሁሉም ላይ የሚዘምትበት ጦርነት! ያኔ፤ የሰው ሕይወት፣... በችጋር፣ በንክሻ፣ በጭካኔ የተሞላና በአጭር ተቀጭቶ የሚቀር ሕይወት... (...poor, nasty, brutish, and short) እንደሚሆን ሆብስ ይገልፃል - Leviathan በተሰኘው መፅሃፉ።
ባራክ ኦባማ፣ የአፍሪካና የአረብ አገራትን ቀውስ መፍታት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ የተናገሩበት አገላለፅን ደግሞ ተመልከቱ።
“I... believe that the world is a tough, complicated, messy, mean place, and full of hardship and tragedy...”  
“ዓለማችን፣... አደገኛ፣ ውስብስብ፣ ምህረት የለሽ የትርምስ ቦታ እንደሆነች አምናለሁ፤ ስቃይና የጥፋት ሃዘን የበዛባት”...
ኦባማ እንደሚሉት፤ በእንዲህ አይነቷ ዓለም ውስጥ፣ በየአገሩ የሚከሰቱ በርካታ አሳዛኝ ቀውሶች እጅጉን ልብ የሚነኩ ቢሆኑም፣ ጥፋትንና ስቃይን አቃልላለሁ እያሉ ሁልጊዜ ጣልቃ ለመግባት መሞከር፣ አያዋጣም - በከንቱ አብሮ ለመጥፋት ካልሆነ በቀር። በተለይ ደግሞ፤ የኑሮ ችግር ሲበረታና ነባሩ ስርዓት ሲብረከረክ፣ የኑሮ ችግርን የሚያቃልልና የመሻሻል እድልን የሚፈጥር የመፍትሄ ሃሳብ ከመፍጠር ይልቅ፤ በዘር የመቧደን ዝንባሌ እንደሚበዛ የገለፁት ኦባማ፤ በጎሳም ሆነ በሃይማኖት የመቧደን አባዜ እጅግ አጥፊ መሆኑን ይገልፃሉ - አሜሪካ ወይም ፕሬዚዳንቷ ሊፈውሱት የማይችል አጥፊ በሽታ። ኢራቅንና ሊቢያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካና የአረብ አገራትን  መጥቀስ ይቻላል።
አንዱ ወይም ሌላኛው አገር ቢቃወስ፣... ለአሜሪካ እጅግ ጠቃሚ አገር ቢሆን እንኳ፣ በዛሬው ዘመን ከአሜሪካ መፍትሄ መጠበቅ፣ ከንቱ እንደሆነ ኦባማ ይገልፃሉ “...there would still be little an American president could do to make it a better place”. ለምን? በጎሳ የመቧደን የዘረኝነት በሽታ የሚድነው፣ ራሳቸው ሰዎቹ በዘረኝነት ከመቧደን ሲቆጠቡ ብቻ ነው። አለበለዚያ፣ እርስበርስ ይጠፋፋሉ። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለዚህ መፍትሄ የለውም ይላሉ ኦባማ - “One of the most destructive forces... is tribalism—a force no president can neutralize”.
ለነገሩ፣ መፍትሄና ድጋፍ እንዲሰጡን የምንጠብቃቸው የአውሮፓና የአሜሪካ መንግስታት፤ በየራሳቸው አገር በብዙ ችግሮች ተጠምደዋል። ፋሪድ ዘካሪያ፣ ባለፈው እሁድ ባቀረበው የሲኤንኤን ሳምንታዊ ዘገባ እንደገለፀው፤ በነፃነትም ሆነ በኢኮኖሚ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ አገራት በሙሉ፣ ለመፍትሄ ያስቸገረ ውስብስብ ፈተና ውስጥ ናቸው። የኢኮኖሚ እድገት ተዳክሟል። የዜጎች ኑሮ እንደ ቀድሞው አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ኑሮን ማሻሻል እየቀረ ነው። በዚህም ሳቢያ፣ በመንግስት ላይ የዜጎች ቅሬታ በርክቷል። ከአስር ዓመታት በፊት፣ በሃያዎቹ ትልልቅ አገራት ውስጥ ስልጣን የያዙ መሪዎች በአማካይ፣ 60 በመቶ የሕዝብ ድጋፍ ነበራቸው። ዛሬ፣ የሕዝቡ ድጋፍ በጣም ቀንሷል - የአንዳንዶቹማ፣ በምርጫ አሸንፈው አመት ሳይቆዩ፣ የሕዝብ ድጋፋቸው ወደ 20 በመቶ እንደወረደ ፋሪድ ዘካሪያ ገልጿል።
እንግዲህ ከሰዎቹ በቀጥታ ሰምተናል - ከእንግሊዝ ፓርላማና ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት። እንደ ድሮ፣ የስልጣኔ ሃሳቦችን በፅናት ስላልያዙ፣ ሌሎች አገራትን ለማገዝ ይቅርና፣ የየአገራቸውን ችግር መፍታትም ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል። ስለዚህ...
ስለዚህ፣... ለኛ ያለነው እኛው ነን። ለቀውስ የምንዳረገው በራሳችን ስህተትና ጥፋት፣ ከቀውስ ወጥተን በመልካም ጎዳና ወደ ተሻለ ስልጣኔ ለመራመድ መፍትሄ ማበጀት የሚኖርብንም እኛው ራሳችን።
በራሳችን ጥፋት ወደ ቀውስ የምንገባው፡
የመንግስት ጥፋት - ዜጎች ኑሯቸውን የሚያሻሽሉበት እድል ለመፍጠር ከመትጋት ይልቅ፤ “የሚሊኒየም ግብ አሳክቻለሁ፤ ዩኤን ይመስክር...” ምናምን እያለ ይጫወታል። “የአካባቢ ጥበቃ... ከካርቦን ልቀት የፀዳ” እያለ ምናምን ሃብት በማባከን ይቀልዳል። የግል ቢዝነስን በሚያዳክሙ ነገሮች ላይ ደግሞ ይረባረባል። ይህን ጥፋት በፍጥነት ማቆም አለበት። እንዴት? የነፃ ገበያ አሰራርን በማስፋፋት። ዜጎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎችም፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ የጥፋት ተካፋይና ይሁን ባይ ከመሆን መቆጠብ አለባቸው።
መንግስት፣ ከየአቅጣጫው ተቃውሞ ሲበዛበት፣ እንደለመደው በሃይማኖትና በብሔር ብሄረሰብ መቧደንን የሚያበረታታ የፕሮፓጋንዳ አመሉን መተው አለበት። ዜጎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎችም፤ በየጊዜው የሚደራረቡ የኑሮ ችግሮችና ሌሎች ሸክሞች በከበዱ ቁጥር፤ ተቃውሞን ማሰማትና ለትክክለኛ መፍትሄ ድጋፍ መስጠትን እንጂ፤ በሃይማኖትና በብሄረሰብ መቧደንን ከመቀስቀስ፣ በዚህም ቀውስን ከማባባስ መቆጠብ አለባቸው። እንዴት? ለእውነታና ለአእምሮ ክብር በሚሰጥ፤ በግለሰብ ነፃነትና በግለሰብ ማንነት ላይ የተመሰረተ ስልጡን አስተሳሰብን በማስፋፋት!!          

Read 2980 times