Saturday, 01 October 2016 00:00

አገሪቱ ለይቶላት ካልተተራመሰች በቀር አንነቃም ማለት ነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(10 votes)

      በየአካባቢው የተቃውሞና የግጭት ማዕበል በተባባሰበት ሰሞን፣ ኢቢሲ በተከታታይ ያስተላለፋቸው ሁለት ዜናዎች፣ የአገራችንን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ያሳያሉ። ስብሰባ ላይ የሰነበቱ የኢህአዴግ መሪዎች፣ ስር ነቀል የመፍትሄ ውሳኔ እንዳስተላለፉ ይገልፃል የመጀመሪያው ዜና። በቂ የስራ እድሎች አለመፈጠራቸው የኛ ጥፋት ነው በማለት የተናገሩት የኢህአዴግ መሪዎች፣ በዚህም ሳቢያ፣ የስራ አጥነት ችግር የአገሪቱን ቀውስ የሚያባብስ ሆኗል ብለዋል። እናም፤ የስራ እድልን ማስፋፋትና ማሻሻል፣  አጣዳፊ ቁልፍ ተግባራችን ይሆናል ብለዋል - የኢህአዴግ መሪዎች።
በእርግጥ፣ የስራ እድልን እንዴት እንደሚያስፋፉና እንደሚያሻሽሉ በግልፅ አልተናገሩም። ቢሆንም ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ “በየአመቱ ሁለትና ሦስት ሚሊዮን የሥራ እድሎችን ፈጥረናል” ከሚለው ከንቱ ፕሮፓጋንዳ አረፍ ብለው፤ “በስራ አጥነትና በኑሮ ችግር፣ አገር እየተቃወሰ ነው” ብለው መናገራቸው አንድ ነገር ነው።   
ከዚህ ቀዳሚ ዜና በመቀጠል የመጣው ትልቁ የኢቢሲ ዜና፣ ምን እንደሆነ ላስታውሳችሁ። ‘ከፀሃይ ሃይል’፣ ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ጣቢያዎች እንደሚገነቡ ዜናው ገልፆ፣ ለዚህም ጨረታዎች እየተካሄዱ ናቸው ይላል። ታዲያ በደረቁ አይደለም። እንደ ድግምት፣ “አረንጓዴ ልማት”፣ “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “ከካርቦን ልቀት የፀዳ”... በሚሉ አጃቢ አባባሎች፣ ዜናውን ለማቆነጃጀት ጠብ እርግፍ ብሏል - ኢቢሲ።
ከፀሃይ ሃይል ኤሌክትሪክ? ይሄኮ ሌላ ትርጉም የለውም። በነፋስ ተርባይኖች ሳቢያ፣ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት፣ በከንቱ ሲባክንና ኤሌክትሪክ በየሰዓቱ ሲቆራረጥ እንዳየነው ሁሉ፤ አሁንም ተጨማሪ ብክነትና የኤሌክትሪክ ሃይልን የሚያቃውስ ተጨማሪ ችግር ይፈጠራል ማለት ነው። እንዲህ እየተቀለደ፣ የስራ እድል ሊስፋፋና ሊሻሻል አይችልም።
አዎ፤ እነ ዩኤን፣ “የነፋስ ሃይል”፣ “የፀሃይ ሃይል”፣ “ታዳሽ ሃይል”... ምናምን እያሉ፣ የአድናቆት ምስክርነታቸውን ያዘንቡልን ይሆናል። ነገር ግን፣ እውነታውን ሊቀይሩ አይችሉም። ለነፋስ ተርባይኖች ከወጣው ገንዘብ ውስጥ፣ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ያለ አንዳች ጥቅም ማባከን፣ ለዚያውም በድሃ አገር አቅም፣ በጣም የሚዘገንን ብክነት ነው። ማነፃፀር ትችላላችሁ። በሐዋሳ፣ ለ60ሺ ሰዎች የስራ እድል ለመክፈት ይረዳል የተባለለት የኢንዱስትሪ ፓርክ በ5 ቢሊዮን ብር ነው የተገነባው። የዚህ እጥፍ ነው በከንቱ የባከነው። እጅጉን የሚብሰው ብክነት ደግሞ፤ “ከፀሃይ ሃይል ኤሌክትሪክ ማመንጨት” ተብሎ ሲሞከር ነው።
እንዲህ ሃብት ሲባክንና በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሳቢያ ፋብሪካዎች ሲከስሩ፤ የስራ እድሎች ይመናመናሉ እንጂ አይስፋፉም።
አሁን የሁለቱን ዜናዎች ትርጉም ተመልከቱ። በአንድ በኩል፣ የስራ እድል ባለመስፋፋቱ ምክንያት አገር እየተቃወሰ ነው ተባለ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የስራ እድልን የሚያሽመደምድ የሃብት ብክነት፣ እንደ መልካም ተግባር ‘የምስራች’ ይወራለታል። ስራ አጥነት፣ አገሪቱን ለትርምስ እያጋለጠ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች፤ በእንዲህ አይነት አሳፋሪ የጥፋት መንገድ ሲጓዙ ምን ይባላል?    
የኢህአዴግ መሪዎች፣ የአገሪቱን ችግር፣ ገና በቅጡ አልተገነዘቡትም ፤... አደጋው፣ ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ፣ ዛሬም አልተረዱትም ማለት ነው። ለነገሩ፣ ብዙዎቹ ተቃዋሚዎችም፣ “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “ከካርቦን ልቀት የፀዳ”፣ “አረንጓዴ ልማት” በሚሉ ሰበቦች የሚባክነውን ሃብት ሲተቹ አልያም ሲቃወሙ አላየሁም። ባይገነዘቡት ይሆናል።
ከአስር ዓመት በፊት፣ የሃብት ብክነት ሲጀመር፣ ውሎ አድሮ መዘዝ እንደሚያመጣ፣ ያኔውኑ ባይገባቸው ላይገርም ይችላል። ለአመታት የተጠራቀመው ቅሬታ ፈንድቶ፣ አገሬው ከዳር ዳር ለወራት ሲመሳቀል ካዩ በኋላስ? በቃ፣ ለይቶለት ትምስምሱ እስኪወጣ ድረስ፣ በዚሁ የብክነት ጉዞ ለመቀጠል ነው ያሰቡት?
ይሄ፣ ገና ስም ያልወጣለት የወንጀል አይነት መሆን አለበት። ግን ይህ ብቻ አይደለም ችግሩ። በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ሲፈፀሙ የቆዩ ብክነቶችና ስህተቶችም ጥቂት አይደሉም። ኢንቨስተሮች እንዲሰሩ ከመፍቀድ ይልቅ፣ መንግስት በድሮው ‘የሶሻሊዝም አባዜ’፣ የስኳር አገዳ እርሻና የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶችን በደርዘን ለማስገንባት፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ቢሊዮን ብሮችን አባክኗል - ያለ ውጤት።
የጅምላ ንግድ ውስጥ እገባለሁ፤ የብረታብረት ፋብሪካዎችን እገነባለሁ፤ የኬሚካል፣ የሳሙና ምናምን እየተባለ፣ ብዙ ሃብትና ጊዜ ጠፍቷል። መንግስት፣ በማንኛውም ሰበብ፣ ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ ሲያቦካ፣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ፣ ውጤቱ ተመሳሳይ እንደሆነ፣ በብዙ አመታትና አገራት ታይቷል። ውጤቱ የሃብት ብክነት፣ ከዚያም የስራ እድል እጦት፣ ከዚያም የዜጎች ቅሬታና ተቃውሞ፣... ከዚያም፣... በተለይ፣ ችግሩ በጊዜ ካልተፈታ፣ አገራዊ ቀውስ ነው።
ይህ አልበቃ ብሎ፤ መንግስት ያንንም ያንንም እየነካካና እየተነኮሰ፣ ነገር ሲያበላሽም አይተናል - ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የአዲስ አበባ የታክሲ ወረፋ መመልከት ትችላላችሁ። ከ12 ሺ በላይ፣ ነጭ በሰማያዊ የተቀቡ ታክሲዎች፣ አዲስ አበባ ውስጥ አገልግሎት ይሰጡ ነበር - ከአስር ዓመት በፊት። ዛሬ የታክሲዎቹ ቁጥር ከ6ሺ በታች እንደወረደ፣ ከመንገድ ትራንስፖርት አመታዊ ምዝገባ የተገኘ መረጃ ያሳያል። የዚህ ጥፋት ዋና ተጠያቂ መንግስት ቢሆንም፤ ብቸኛው ተጠያቂ ግን አይደለም። ታክሲዎችን ከገበያ የሚያስወጣ፣ አላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥር በላይ በላዩ እየተደራረበ የመጣው፣ በአብዛኛው ሕዝብ የቁጥጥር ጥማትና ውትወታ ጭምር ነው - የዋጋ ቁጥጥር፣ የስምሪት ቁጥጥር፣ የፌርማታ ቁጥጥር...። ከዚያስ?
የትራንስፖርት እጦት ሲባባስ፣ ለመንግስት ሰራተኞች አዳዲስ አውቶቡሶች ተገዙ። ሃምሳ እና ሰባ ሰራተኞችን ጥዋት ወደ ስራ ያደርሱና ተገትረው ይውላሉ። በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር የወጣባቸው አውቶቡሶች፤ እንዲህ ሲባክኑ፣ ምን አይነት ቀልድ ነው?
ምን ይሄ ብቻ!
የትራንስፖርት እጥረትን ለማቃለል፣ ‘ከካርቦን ልቀት የፀዱ’ ብስክሌቶችን ለመግዛት ሚሊዮን ብሮችን መመደብ! እንዲህ አይነት ብክነት፣ ኢትዮጵያን ብቻ የሚያጠቃ በሽታ አይደለም። በቅርቡ፣ ተመሳሳይ ፕሮጀክት በደቡብ አፍሪካ፣ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት እንዲቋረጥ ተደርጓል። የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ነገር ግን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ የሃብት ብክነትን እንደዋዛ የማይመለከቱና ቁምነገረኛ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰዎችን አላጣችም። እጅግ ድሃ የሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ ግን፣ “መንግስትም ያው! ተቃዋሚም ያው! አብዛኛው ህዝብም ያው!” እየሆነ ነው።
አውቶብሶች ብቻ የሚጓዙበት ልዩ መንገድ ይገነባል ተብሎ እቅድ የሚወጣውና ብዙ ሚሊዮን ብር የሚመደበው፤ በምን አይነት ስካር እንደሆነ እንጃ። ግን፣ “እንዴት ነው ነገሩ!” ብሎ ድምፁን ያሰማ ተቃዋሚ ፖለቲከኛና ፓርቲ አጋጥሟችኋል? ለዚያውምኮ መንገደኛ በሚበዛበት አካባቢ አይደለም የአውቶብስ መንገድ የሚገነባው። ለነገሩ ምንም መንገደኛ ቢበዛ፣ ከመገናኛ እስከ ቦሌ፣ አልያም ከሜክሲኮ እስከ መካኒሳ ድረስ ቢሆን እንኳ፣ ለዚያ መንገድ ብቻ ሺ አውቶቡስ ሊመደብ እንደማይችል ግልፅ ነው። እና፣ በአምስት በአስር ደቂቃ አንድ አውቶቡስ እንዲሽከረከርበት ብቻ፣ መንገድ ይገነባል? በዚያ ላይ ግራና ቀኝ የሚጓዝ ትራንስፖርትን በማስተጓጎልም፣ ተጨማሪ ችግር ይፈጥራል።
ሰዎች፣… የማስተዋልና የማገናዘብ ጉዳይ እየተረሳ፤ ብዙ የአገራችን ነገሮች፣ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት... ፍሬንና መሪ እንዳጣ መኪና፣ ግራ ቀኝ እየተንገራገጩ፣ ወደማያምር መጨረሻ መንደርደር አብዝተዋል።   
በዚያ ላይ፣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በላይ የሆነና ከልክ ያለፈ የገንዘብ ሕትመት አለላችሁ። በየአመቱ ብር እየረከሰ፣ ዋጋ እየናረ፣ ኑሮ እየተወደደ፣ የብዙ ዜጎች ሕይወት ከአመት አመት ያናጋል። ከተሞች ላይ ብቻ አነጣጥሮ ለአመታት እየከበደ የመጣው የታክስ ጫናም ቀላል አይደለም። የአለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአስር አመታት ውስጥ፣ በአማካይ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች፣ ቅንጣት ታክል የገቢ እድገት አላገኙም። ታዲያ፣ የዜጎች ቅሬታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየተጠራቀመ፣ የተራራ ያህል መግዘፉ ምን ይገርማል?
ይልቅስ፣ አስገራሚው ነገር፣ ለቁጥር የሚታክቱት የኑሮ ችግሮችን ከምር አስተውሎና መርምሮ፣ በቅጡ አገናዝቦና ተንትኖ... በጉልህ እንዲታዩና መፍትሄ እንዲያገኙ ያለመታከት የሚጥር ሰው፣ ምሁር፣ ፖለቲከኛ፣ ፓርቲ በብዛት አለመታየቱ ነው።
አዎ፣ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የስኳር ፕሮጀክቶች፣ ያለ ውጤት ለአመታት የመጓተታቸውና የመዝረክረካቸው ነገር፣ አንድ ሰሞን ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር። ነገር ግን፣ ብዙም አልቆየም። ጉዳዩ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከጨዋታ ውጪ ሆኗል። ለምን?
“እገሌ መቶ ሺ ብር ዘረፈ፣ እገሊት በሙስና አንድ ሚሊዮን ብር አፈሰች”... ቢባል እንደ ጉድ የሚያወራጨን ሰዎች፤... ያለ ስርቆትና ያለ ሙስና፣ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት በከንቱ ቢባክን፣ ያን ያህል አይከነክነንም። የሆነ ሰው በሆነ መንገድ የተጠቀመ ሲመስለን ያንገበግበናል። በትክክል ያልተሰራ መስኖ በጎርፍ ሲወሰድ፣ አዳዲስ የመንግስት መኪኖች ያለ አገልግሎት ሲበላሹ፣ ግንባታ እየተጓተተ የወለድ ክፍያ ሲከማች... በዚህም ሳቢያ የቢሊዮን ብሮች ሃብት ሲባክን ግን ቅንጣት አይቆጨንም - ብር ሰርቆ ወይም በሙስና የተጠቀመ ሰው ከሌለ ችግር የለም።
ለነገሩ እንደ ጉድ ቢያንገበግበን እንኳ፣ ትርጉም አይኖረውም። መንግስት የሚጀምራቸው የቢዝነስ ፕሮጀክቶች፣ መቼም ቢሆን ከብክነት ድነው አያውቁም። የመንግስት ሰራተኛ ወይም አለቃ ሆናችሁ አስቡት። ሃብት ቢባክንም ሆነ ባይባክን፤ ፕሮጀክት ቢሳካም ሆነ ባይሳካ፣ በኑሯችሁ ላይ የሚያመጣው ለውጥ እንደማይኖር አስታውሱ። ከወር ደሞዛችሁ ያለፈ ተጨማሪ ክፍያ አታገኙም፤ ከወር ደሞዛችሁ ላይ የሚቀነስ ሳንቲም አይኖርም። የመንግስት ስራ እንዲህ ነው። ለዚህም ነው፤ ከመጓተትና ከመዝረክረክ፣ ከብክነትና ከሙስና የማያመልጠው። መንግስት፣ ደርዘን የስኳር ፕሮጀክቶችን ሲጀምር፣ አደጋው የማይታየን ከሆነ፣ ወይም እንደ ትልቅ ቁምነገር ቆጥረን “አበጀህ” የምንል ከሆነ፤... ሃብት ሲባክን ለማየት መዘጋጀት አለብን። ሃብት ሲባክን ደግሞ፣ የስራ እድል እጦትና የኑሮ ችግር እንደሚበረታ ግልፅ ነው።
ከላይ የተጠቀሱ ዋና ዋና የኢኮኖሚና የኑሮ ችግር መንስኤዎችን ተመልከቷቸው።
አንደኛ፤...መንግስት፣ በየጊዜው የቢዝነስ ፕሮጀክቶችን እዚህና እዚያ እየገተረ፣ ከፍተኛ የሃብት ብክነትን ይፈጥራል። በወዲህ በኩል፣ ለሚጓተቱት ፕሮጀክቶች፣ በየዓመቱ ተጨማሪ በጀት ለመመደብ፣ ገንዘብ ሲያትም፣ ብር እየረከሰ፣ ኑሮ እየተወደደ፣ የዜጎች ሕይወት ይሸረሸራል። በሌላ በኩል፣ በፕሮጀክቶቹ ምክንያት ብዙ ሃብት ሲባክን፣ ኢንቨስትመንት እየተዳከመ፣ የስራ እድል ይጠፋል።      
ሁለተኛ፤... በየአገሩ የሚታይ የዘመናችን ልዩ ስካር ደግሞ አለላችሁ - የአካባቢ ጥበቃ፣ ከካርቦን ልቀት የፀዳ፣ አረንጓዴ ልማት... በሚሉ ሰበቦች፣ ብዙ ሃብት ይባክናል፤ ኢንቨስትመንት ይደናቀፋል። የስራ እድል ይጣበባል።
ሦስተኛ፤... መንግስት ቢዝነስ ውስጥ በቀጥታ እየገባ ሃብት ከማባከኑም በተጨማሪ፣ በአዲስ አበባ ታክሲዎች ላይ እንዳደረገው፣ በአላስፈላጊ ቁጥጥሮች አማካኝነት የግል ቢዝነሶችን ያዳክማል። በዚህም፣ ኢንቨስትመንትንና የኢኮኖሚ እድገትን እያደናቀፈ፣ የስራ እድል ፈጠራን ያኮላሻል።
እነዚህ ሶስት ችግሮች፣ የመንግስት ብቻ ጥፋት ቢሆኑ ኖሮ፣ መፍትሄያቸው ከባድ ባልሆነ ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው? ብዙዎቻችን እንደ ጥፋት አንቆጥራቸውም። እንዲያውም፤ መንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶችን እያዘጋጀ ግንባታ ሲጀምር፣ የግል ቢዝነሶችንም በቁጥጥር ሲያስጨንቅ ስናይ፣ ቅሬታ የለንም። አንድም በይሁንታ እናልፈዋለን። አልያም፣ በድጋፍ እናጨበጭባለን።
የጥፋት መንስኤ የሆኑትን ችግሮች፤ እንደ መልካም ተግባር የምንቆጥራቸውና የምንደግፋቸው ከሆነ፤ መፍትሄ ለማበጀት ይቅርና፣ ተቃውሞ ለማሰማትም እንቸገራለን። ለዚህም ነው፤ ብዙዎቹ ተቃውሞዎች፣ ውለው ሳያድሩ፣ መልካቸው ሲቀየር የምንታዘበው። በኑሮ ችግርና በስራ እድል እጦት ሳቢያ የተቀሰቀሰ ተቃውሞ፣ ብዙም ሳይቆይ፣ በዘር ወይም በሃይማኖት የመቧደን ቅስቀሳ በሚያራግቡ ሰዎች ተጠልፎ፣ ወደተጨማሪ ጥፋት ይንሸራተታል። ኧረ፣ እባክህ መንግስት አስተውል። ኧረ ሰዎች እናስተውል።

Read 6487 times