Saturday, 01 October 2016 00:00

ሳውላ - “የመሠረተ ልማት ያለህ!” እያለች ነው!!

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹እኛ ያሉብን ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ በዋነኛነት መንገድ ነው፤ መብራትና ውሃም የለንም”

    ዕድሜ ጠገብ ናት፡፡ ከተቆረቆረች ብዙ ዕድሜ እንዳስቆጠረች ይናገራሉ፤ በጋሞ ጎፋ ዞን የሳውላ ወረዳ ነዋሪዎች፡፡ የወረዳው ዋና ከተማ ብትሆንም መሠረተ-ልማት አያውቃትም ማለት ይቻላል፡፡ መንገድ የላትም፣ ውሃ የላትም፣ መብራት የላትም፤… ሕዝቡ በጣም እየተሰቃየ ነው ሲሉ ነዋሪዎች በምሬት ይናገራሉ፡፡
የደቡብ ክልል ኃላፊዎች ዋና ከተማ ሲደርሱ፣ ሕዝቡ ጥያቄ ማቅረቡ ሰልችቶት አልተወም። ኃላፊዎቹም ቃል ይገባሉ፡፡ ‹‹በእውነት ነው እምላችሁ፤ አሁን ይሠራላችኋል፤ በቅርቡ ይጀመራል፤ በሁለት ዓመት ውስጥ እፎይ! ትላላችሁ፣… ›› በማለት የተለያዩ የመደለያ ተስፋ እየሰጡ በዚያው ‹‹የውሃ ሽታ›› ሆነው ይቀራሉ ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡ ‹‹መንገድ አሁን ይሰራላችኋል፣ መብራት በቅርቡ ይገባላችኋል፣ የውሃ ጥያቄ አንገብጋቢ ስለሆነ ቅድሚያ ይሰጠዋል፣… ሲሉን፣ ከአንዴም ሁለት በሬ አርደን ሥጋ አብልተን፣ ጥጥ ፈትለን ቡሉኮ ሰርተን አልብሰን ሸኝተናል፡፡ አንድም ግን ቃሉን ያከበረ ባለሥልጣን አላየንም›› ይላሉ የሳውላ ነዋሪዎች፡፡
በዚያ አካባቢ ወረዳዎች የንግድ ምርት (ካሽክሮፕ) አምራቾች ናቸው፡፡ ለውዝ፣ ቡና፣ ጥጥ፣ አርቲ (ቅመማ ቅመም)፣ ፍየል፣ ዶሮ፣ በሬ፣ ማር በብዛት ይመረታል፡፡ ለቡና ቁርስ የሚቀርበው ለውዝ ነው፡፡ እንግዳ ቢመጣባቸው እንደ ክብር ዕቃ የሚሸልሙት ቡሉኮ  ነው፡፡ ለምግብ የሚያቀርቡት ሥጋ፣ ማር፣ ብርዝ ወይም ጠጅ ነው፡፡ ግን መሠረተ ልማት የመነፈጋቸው ምስጢር ምን ይሆን?
አቶ ሙሉ በለጠን በዛላ ወረዳ አስተዳደር የተዘጋጀውን የመስቀል በዓል ሲያከብሩ ነው ያገኘኋቸው፡፡ ምን ችግር እንዳለባቸው ሲገልጹ፣ ‹‹እኛ ያለብን ዋነኛ ችግር መንገድና መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሌላ ችግር የለብንም፡፡ በእኛ ወረዳ፣ በቆሎ፣ ለውዝ፣ አርቲ፣ ቡና፣ ጤፍ --- በብዛት ይመረታል። ከብትም በብዛት ይደልባል፡፡ ፍየሎችም አሉ፡፡ በሳምንት ሁለት ወይም ሶስት መኪና ከብት ተጭኖ ይወጣል፡፡ (አንድ መኪና 10 ከብቶች ይይዛል) በወር ከስምንት ወይም ከ12 መኪና በላይ ጭኖ ይወጣል። ሌሎች ምርቶችም እየተጫኑ ይወጣሉ፡፡ አካባቢው የንግድ ነው፡፡ መንገድ ግን የለውም፡፡ የሚሰማን አጣን እንጂ እስከ ዛሬዋ ዕለት የመንገድ ጥያቄ እያቀረብን ነው፡፡
በቅርቡ ከጎፋ አርባ ምንጭ ድረስ አላለቀም እንጂ መንገድ እየተሠራ ነው፡፡ ከጎፋ እስከ ወላይታ ያለው 132 ኪ.ሜ መንገድ አልተሠራም፤ ፒስታ (የጠጠር መንገድ) ነው›› በማለት ገልጸዋል፡፡
አቶ ባህሩ የዛላ ወረዳ፣ እንደገራ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ ገበሬ ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው በጣም ሄዷል፣ በግምት 85 ዓመት ይሆናቸዋል፡፡ ሰው ቃለ-መጠይቅ ሳደርግ አይተው ከኪሳቸው አንድ ዙሪያውን በሙሉ የተጻፈበት ወረቀት አውጥተው ሰጡኝ፡፡ ምንድነው? ስል ጠየኳቸው፡፡ ማመልከቻ እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ ወረቀቱን ትቼ ቅሬታቸውን በቴፕ ተቀበልኳቸው፡፡ በተሰባበረ አማርኛ እንዲህ ሲሉ ያሉባቸውን ችግሮች ነገሩኝ፡፡
‹‹እኛ ያሉብን ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ በዋነኛነት መንገድ ነው፡፡ መብራትና ውሃ የለንም፡፡ ውሃ አንዳንድ ቦታ ቢኖርም በደንብ አይዳረስም፡፡ የከብቶች በሽታ በብዛት አለ፡፡ ዘንድሮ ሀብታም የሆነ ሰው ከብቶቹ አልቀውበት ድሃ ሊሆን ይችላል፣…›› በማለት በአካባቢው የሚታዩትን ዋነኛ ችግሮች ነገሩኝ፡፡
የመንገድ ችግር እንኳንስ ነዋሪዎቹን እኛንም ክፉኛ አስመርሮናል፡፡ ከወላይታ ሶዶ 9፡15 አካባቢ ተነስተን 132 ኪ.ሜትር ኮረኮንች ብንለው ብንለው አላልቅ ብሎን፣ ከምሽቱ 3፡40 ሳውላ ከተማ ደረስን። ሳውላ ከተማ የንግድ ምርቶች (ካሽክሮፕ) በብዛት የሚመረቱባት ስለሆነ በርካታ የጭነት መኪናዎች ይጎበኛታል፡፡ በዚህ ላይ ከቱሪስት መስህቦች አንዱ የሆነው የማዜ ፓርክ የሚገኘው በዚሁ መንገድ ላይ ነው፡፡ ፓርኩን ቱሪስቶች እንዲጎበኙትና ገቢም እንዲገኝ መንገዱ ወደ አስፋልትነት ሊቀየር ይገባል፡፡ የቅቤ፣ የቡና፣ የኮረሪማና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ባለቤት የሆነችው የቁጫ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው ‹‹ሰላም ከተማም›› የምትገኘው በዚሁ መንገድ ላይ ነው፡፡ አካባቢው ካለው የተለያዩ ጥቅሞች አኳያ የክልሉ መንግሥት ለመንገድ ግንባታ ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ከወላይታ እየተርገፈገፍን ሳውላ ደርሰን፣ እየተርገፈገፍን ተመለስን፡፡

Read 1552 times