Monday, 03 October 2016 07:58

አብዮት የወለደው ሳይንስ

Written by  በደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)

     በ1960ዎቹ መባቻ ላይ የሳይንሱ ዓለም አንድ ዱብዕዳ አስተናግዶ ነበር፡፡ ለብዙ ዘመናት ቆርቦ የኖረበትን ስርዓትና ደንብ ከሥሩ የሚመነግል አብዮታዊ ምልከታ በቶማስ ኩን አማካኝነት ተቀጣጠለ፡፡ የቶማስ ኩን “ዘ ስትራክቸር ኦፍ ሳይንቲፊክ ሪቮሉሽን” ግሩም ድርሳን  ለኅትመት ብርሃን በበቃበት በዚያ ዘመን፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍ በተሰማሩ ጉምቱ ልሂቃን ዘንድ የፈጠረው ጫጫታ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡
ኩን በዚህ ዘመን ተሻጋሪ ድርሳኑ፣ አብዮትን ከፖለቲካ አፍ ላይ ነጥቆ ለሳይንስ ይሸልማል። መጽሐፉ ገና ከደጃፍ የሚቀበለን በአብዮታዊ መስተንግዶ ነው፡፡ ጥቂት ገጾችን ገፋ አድርገን ወደ ውስጥ እንደዘለቅን፣ የሳይንሱ ዓለም ቀኖና የተቀለሰበት ወጋግራ የቆመበት መሬት እየከዳው፣ አንድ በአንድ ሲናድ ማስተዋል እንጀምራለን፡፡ ጭብጡን ብዙም ሳናብላላ ከአፋፉ ላይ ቆመን የሥር ነቀል ችቦው ወጋገን ለአይናችን ይታየናል፡፡
ይህ በ230 ገጾች የተቀነበበው ድንቅ መጽሐፍ፤ በውስጡ ተመንዘረው የማያልቁ ጽንሰ ሐሳቦችን፣ ምናብን የሚያበሩ ጭብጦችን በአስራ ሶስት ምዕራፎች ሰንቆ ይዟል፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፉ ከታተመ ግማሽ ክፍለ ዘመንን ቢያስቆጥርም በጊዜ ርቀት የማይበርድ ትኩሳትን እንደታቀፈ፣ እነሆ እስከ ዛሬው ዘመን ድረስ የመወያያ ርዕስ እንደሆነ ሊዘልቅ ችሏል፡፡
ሳይንስ በታሪክ መነጽር ሲመረመር
የሳይንሱ ዓለም ተለምዶአዊ የታሪክ አረዳድ የተቀየደው በዱላ ቅብብሎሽ ስልት ነው፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሲወርድ ሲዋረድ ካለንበት ዘመን የደረሰው አንዱ የጎደለውን በአንዱ ላይ እየጨመረ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህንን እውነታ ዕውቀት በምንገበይባቸው ሳይንሳዊ ድርሳናት ላይ በጉልህ ሠፍሮ እናገኛለን፡፡ በእዚህ ታሪካዊ ቅኝት መሠረት፣ የትኛውም ሳይንሳዊ ግኝት ዘረ-መል የሚመዘዘው፣ ከእርሱ ቀድመው ለፍሬ ከበቁ ንድፈ-ሐሳቦች ዝርያ ነው፡፡ ለምሣሌ በዱላ ቅብብሎሽ አረዳድ መሠረት፣ አልበርት አንስታይን ስለ ቁስ አካል የቀመረው ንድፈ ሐሳብ፣ የአይዛክ ኒውተን ንድፈ ሐሳብ ቅጥያ ይሆናል፡፡ ይህንን አካሄድ ተመርኩዘን የሳይንስን ታሪክ የምንተነትን ከሆነ፣ የኒውተንና የአንስታይን ንድፈ-ሐሳባዊ ትንተና የእርስ በእርስ ቁርኝት በመጨመር መንገድ /linear method/ የተሳሰረ እንደሆነ እንረዳለን ማለት ነው፡፡
ቶማስ ኩን በእንዲህ ዓይነት ስነልቦናዊ ቅኝት ላይ ዳሱን የጣለውን ሳይንስ በመኮነን ነው ምልከታውን የሚጀምረው፡፡ ይህ የተንሸዋረረ የሳይንስ ታሪክ አረዳድ መዘዙ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ አጥብቆ ይሞግታል፡፡ እውነተኛ የሳይንስ ግኝቶችን ታሪክ በቅጡ ባለመረዳት ምክንያት በፈጠራ በበለጸጉ ልሂቃን ምትክ በቃል የሚያነበንቡ የመከኑ ፊደላዊያን በየዕውቀት መቅሰሚያ አውድ ላይ ለመሰየም በቅተዋል፡፡    
በአብዛኛው ዕውቀት የሚገበይባቸው የትምህርት ተቋማት መማሪያ መጽሐፍት ውስጥ የታጨቁት ቁምነገሮች የቀለም ቆጣሪውን ምናብ አያበረቱም፡፡ በረብ-የለሽ ጭብጦች ተዥጎርጉረዋል። ፍጻሜያቸው ተገማች የሆኑ መርሆዎችና ቀመሮች ላይ ዕውቀት ቀሳሚው ስልጡን እንዲሆን ነው የሚፈለገው፡፡ የሳይንሳዊ ግንኙነቶች እውነተኛ ምንጭ ላይ እንዲመክር እንዲዘክር የሚፈቅድ የመማር ማስተማር ከባቢ ነጥፏል - ይላል፡፡
ላትራል ቲንኪንግ የሚል አዲስ የአስተሳስብ ስልትን ለዓለም በማበርከት የታወቀው ጉምቱ ልሂቅ ኤድዋርድ ዲቦኖ፤ “ዋይ ሶ ስቱፒድ” በሚለው ድርሳኑ ላይ ከላይ ከተነሳው ጭብጥ ጋር የሚያያዝ ግሩም ሃሳብ አቅርቧል፡-
Schools waste two thirds of talent in society and universities sterilize the other third. The apparent purpose of education is so to convince two thirds of the students that they really are stupid.
ገና በአፍላነት ቀለም ለመቁጠር የምንሰደድባቸው አስኳላዎች የሕይወታችንን ዳጎስ ያለውን ክፍል ሰልበው፣ ቀሪውን ሲሶ እጅ በግብር ለሚመስሏቸው ተቋማት ያስረኩብናል፡፡
እርግጥ ነው፣ ዘልማዳዊው የትምህርት ስርዓት እንደ መንፈሳዊ ቃል አይነኬ ጭብጦችን በአእምሮ አሳቁሮ፣ ቀሪውን የዕውቀት ጉብዝና ዘመናቸውን የሚያዘግሙ ልሂቃንን መፍጠር ዋንኛ ተግባሩ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ የተቀበሉትን የሚያከማቹ እንጂ በተቀበሉት ላይ የሚያምጹ ባለ ብሩህ አዕምሮ  ልሂቃንን ለዓይነ ሥጋ አያበቃም፡፡ ልክ እንደ ፋብሪካ ምርት በቅርጽና በይዘት ወጥ የሆኑ ቀለም ቆጣሪዎችንን መፍብረክ ተቀዳሚው አላማ ነው፡፡ በሁሉም ጽንሰ ሐሳብ ላይ አራት ነጥብን አኑሮ፣ የመጠየቅ ፍላጎትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቆልፋል፡፡ ይህ ነው መደበኛው የትምህርት ባህል። የዚህ ሁሉ የችግር ማጠንጠኛ ሄዶ ሄዶ፣ እውነተኛ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ሥረ መሠረት በቅጡ ለመፈተሽ ተነሳሽነት ከማይፈጥር ዳተኛ የዕውቀት አቀሳሰም ልምድ ላይ ያርፋል፡፡   
አብዮትና ሳይንስ ምንና ምን ናቸው?
አብዮትን የፖለቲካ የበኽር ልጅ ብቻ ያደረጋት ማን ነው? ብሎ ይሞግተናል፤  ኩን፡፡ አብዮት ልጆቿን ትበላለች የሚለው መፈክር ለሳይንሱም ዓለም ይሠራል፡፡ የሳይንስ አብዮት የሚበላው ግን ያረጀ ያፈጀውን ሳይንሳዊ አሠራር ነው፡፡ በአሮጌው ትቢያ ላይ አዲሱ ግኝት ይቀለሳል፡፡ ልክ እንደ ፖለቲካዊው ምህዳር ሁላ የሳይንሱ ዓለም በመሬት አንቀጥቅጥ አብዮት ሲታመስ ነው የኖረው፡፡ ሳይንስ እንደ ቀስት ወጥ በሆነ የዕድገት ሐዲድ ላይ አይወነጭፍም። ከዚህ ይልቅ በስር ነቀል ለውጥ እየታገዘ፣ ያረጀ ያፈጀውን አሠራር ግብዓተ ቀብር ፈጽሞ፣ አዲስ ሳይንሳዊ ግኝትን ለዓይነ ሥጋ ያበቃል፤ ይለናል ኩን፡፡
“ሳይንሳዊ ግኝቶች እውን የሆኑት በስር ነቀል አብዮት ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ኩነቶችን አብነት ማድረግ ይቻላል፡፡ የአንስታይን የቁስ አካል ቀመር ከኒውተን ይልቅ ለአሪስጣጢለስ የቀረበ ነው፡፡ በዘመን ስሌት ወይም በመጨመር መርህ ከሄድን ግን የአንስታይን አተያይ ኩታ-ገጠም መሆን የነበረበት ከኒውተን ጋር ነበር“
 ካርል ማርክስ በዳስ ካፒታል የኅብረተሰብን አወቃቀርና የፖለቲካ አብዮትን አይቀሬነት እንዳወጀው ሁሉ፣ ኩን የሳይንሱ ዓለም ለዘመናት ሲነጉደበት የኖረው ሐዲድ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነና በሥር ነቀል ለውጥ እየታጀበ ያለንበት ዘመን እንደደረሰ ያሳየናል፡፡ የረጋ ውቂያኖስ ለመታደስ ማዕበልን በብርቱ እንደሚናፍቅ ሁሉ፣ በአንድ ዓይነት አመለካከት ሲከወን የኖረው ሳይንስ፤ አብዮትን እንደ ተስፋይቱ ቀን በብርቱ ይጠባበቃል፡፡ የስነ-ክዋክብት ጥናት እስከ መካከለኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሲገዛበት የነበረው ሕግ - ጂኦሴንትሪክ ወይም መሬትን የጋላክሲ ማዕከል አድርጎ በሚያስቀምጥ የተወላገደ ንድፈ-ሐሳባዊ አረዳድ ነበር፡፡ ይህንን ንድፈ-ሐሳባዊ ትንተና ኮፐርኒከስ ከመቀናቀኑ በፊት በሳይንሱ ዓለም እንደ አድባር ዋርካ እየተመለከ ለዘመናት ነግሶ ኖሯል፡፡ ኮፐርኒከስ ሄሊዮሴንትሪክ በሚለው ጽንሰ-ሐሳቡ፣ መሬትን ከተሰጣት ያልተገባ ዙፋን ላይ በማውረድ እውነተኛውን መንበር ለፀሐይ በመለገስ፣ሁሉም ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ እንጂ በመሬት ዙሪያ አይዞሩም የሚለውን ሳይንሳዊ ግኝት ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋወቀ፡፡ በዚህም መሠረት፣በስነ-ክዋክብት ምርምር መስክ አዲስ አብዮት ሊቀጣጠል ችሏል፡፡ ከእርሱ ለጥቀው ለመጡትም ሳይንቲስቶች ማለትም ለጋሊሊዮና ኒውተን ፋና ወጊ ለመሆን በቅቷል፡፡
የኩን አብዮት የሚቀጣጠለው ፓራዳይም በሚባል ድንግል ጽንሰ-ሐሳብ መሪ ተዋናይነት ነው፡፡ የትኛውም ሳይንሳዊ ዲሲፕሊን የሚዘወርበት አስኳል መርህ ፓራዳይም ተብሎ ይጠራል፡፡ በእዚህም ሳይንሳዊ መርህ /ፓራዳይም/ አማካኝነት ብዙ ቋጠሮዎች ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ አንድ የሕክምና ባለሙያ የልብ ሕመምን ለመመርመር የሚጠቀምበት ሳይንሳዊ መርህ አለ፡፡ ይህ ሳይንሳዊ መርህ /ፓራዳይም/ በሙያው ላይ የተሰማሩ ጠበብቶች በአንድ ወቅት ተመራምረው ያኖሩት ሕግ ነው፡፡ ነገር ግን  መፍትሄ አመንጪው ሳይንሳዊ ቀመር ከጊዜ በኋላ እንደ ተርኪስ ባቡር ቀጥ ይላል፡፡ የልብ ሕመም መንስኤውና ምልክቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ በመሄዱ ምክንያት ሲሰራበት የኖረው ሳይንሳዊ መርህ አቅሙን ከሚገዳደሩ እክሎች  ጋር ፊት ለፊት መላተም ይጀምራል፡፡ ሳይንሳዊው መርህ ለእክሎቹ እልባት በመስጠት ፋንታ የበይ ተመልካች ሆኖ ያርፈዋል፡፡ በዚህ ወቅት ነው  አዲስ ሳይንሳዊ ግኝት /ፓራዳይም ሽግግር/ ግድ የሚሆነው፡፡ ፓራዳይምን በቅጡ ለመረዳት የሚከተለውን ተጨባጭ ምሳሌ እንመልከት፡-
በዘመናችን ኢቦላና ዚካ ቫይረስ፣ ከምድር ገጽ ላይ መጥፋት ያልቻሉ የሰው ልጅ ጤና ጠንቆች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በጤናው የምርምር መስክ በሚተገበረው ሳይንሳዊ መርህ /ፓራዳይም/ አማካኝነት ለጠንቆቹ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ሳይንስ እዚህ ጋ እጅ ሰጥቷል ማለት ነው፡፡ በሽታዎቹን ለማጥፋት አሁን ከሚሰራበት ሳይንሳዊ መርህ ከፍ ያለ ግኝትን ግድ ይላል፡፡ በመሆኑም ይህ መፍትሄ ማበጀት የተሳነው ሳይንሳዊ አሰራር ተወግዶ በምትኩ አዲስ ግኝት እውን ሲሆን አብዮቱ ግቡን እንደመታ ይቆጠራል፡፡    
ግርምቢጥ እውነታ
የኩን መጽሐፍ አወዛጋቢ ጽንሰ ሐሳቦችን በማስተዋወቁ ረገድ አይታማም፡፡ በተለይም አዲሱ ሳይንሳዊ ግኝት ከአሮጌው ጋር ተነጻጽሮ በተዋረድ ሊቀመጥ አይገባም የሚለው ትንትና፣ ከብዙ ልሂቃን ጉሮሮ ለመውረድ ያልቻለ ጭብጥ ነው፡፡
የድሮውን በአዲሱ ስንተካ ንጽጽራዊ መለኪያ እንደምንከተል የታወቀ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ ማድረግ ተገቢ መመዘኛ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ፀሐይ በመሬት ዛቢያ ዙሪያ ትሽከረከራለች የሚለው ሳይንሳዊ ትንተና፣ መሬት በፀሐይ ዛቢያ ዙሪያ ትዞራለች በሚል አዲስ ሳይንሳዊ አረዳድ ሲተካ፣ ንጽጽራዊ መለኪያ የማይቀር ሃቅ ይሆናል፤ ይላሉ የኩን ተቀናቃኞች፡፡
 ነገር ግን ልሂቁ በዚህ ትንተና አይስማማም፡፡ የፊቱም ሆነ አዲሱ ሳይንሳዊ አሰራር ዕውነታዎችን የሚያዩበት መነጽር ተለያየ እንጂ አንዱ ከሌላው የሚልቅበት ተፈጥሮ የለውም ይላል። ለዚህ ግርንቢጥ ጽንሰ-ሐሳባዊ ትንታኔ የሰጠው ስያሜ ኢንኮመሰረብሊቲ የሚል ነው፡፡ ኩን ኢንኮመሰረብሊቲን በማስተዋወቁ የመጨመር ግንዛቤን የተመረኮዘውን ዘልማዳዊውን የሳይንስ ታሪክ አረዳድ እንደ ማምከኛ ቢጠቀምበትም፣ በሌላ ጎን የተነሳበትን ጠንካራ መንደርደሪያ ሐሳብ ልፍስፍስ አድርጎበታል፡፡
በዚህ ጽንሰ-ሐሳብ ምክንያት መጽሐፉ ለሕትመት ብርሃን ከበቃበት ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ ብዙ ትችቶችን አስተናግዷል። ይህንንና ሌሎች የውዝግብ በርን የከፈቱ ጽንሰ ሐሳቦችን የበለጠ ግልጽ ለማድረግና ያራመደውን አብዮታዊ አቋም ለማጠናከር በመጽሐፉ የመጨረሻ ክፍል ላይ መጠነኛ ማብራሪያ /Post Script/ በማከል፣ አነጋጋሪው መጽሐፍ “ዘ ስትራክቸር ኦፍ ሳይንቲፊክ ሪቮሉሽን”  በ1970 ዓ.ም ዳግም ለሕትመት ሊበቃ ችሏል፡፡

Read 4181 times