Saturday, 01 October 2016 00:00

መስቀል ወ ‹ይሁዳ›

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

‹‹ነገር ግን እስራኤላዊያን ሰውን በስቅላት አይገድሉም ነበር››

   ዛሬ መስከረም 21 ቀን የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አመታዊ ንግስ ነው፡፡ ‹‹የአማኑኤል ግማደ መስቀሉ፡ ግሸን ነው አሉ›› ይላሉ ተጓዥ ምእመኑ። ‹‹ግሸን፤ ጌሰ ፡ ገሰገሰ ከሚለው ቃል በጊዜ ብዛት የወጣ ነው፡፡›› ብለውኝ ነበር፤ ከአመታት በፊት በመስቀለኛው ተራራ አምባ ያገኘሁዋቸውና በዚያ ስፍራ ብቻ የሚገኘውን፤ ከአጼ ዘርዐ ያዕቆብ ተጽፎ ለትውልድ የተላለፈውን፡ በየአመቱ በዚህ ወቅት እየወጣ የሚነበበውን የ‹ጤፉት› መጽሀፍ ምስጢር በወጉ ከሚተነትኑት ብዛታቸው በጣት ከሚቆጠሩ አበው ሊቃውንት አንዱ የሆኑት፡ የሀዲስና ዝማሬ መዋሲት መምህር ሊቀ ትጉኃን የማነ ብርሀን አዲሴ። መገስገሱ ስለምን ነበር ?
‹‹አጼ ካሌብ የናግራንን ሰማእታት ለመታደግ በዘመቱ ጊዜ ካገኟቸው ከግሪካዊው ካህን ከአባ ፊሊክስ/ፍቃደ ክርስቶስ ጋር ከናግራን ተራራ፣ ዛሬ በግሸን የሚገኙትን የቅድስት ድንግል ማርያምንና የመድኃኒአለምን ሁለት ጽላቶች ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ እግረ መንገድም ንጉሡ ስለ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በምስር (ግብጽ) ምድር መገኘት ሰሙ፡፡››
ባሳለፍነው ሳምንት መስከረም 16 ሰኞ እለት ዋዜማው፤ በዩኔስኮ በማይዳሰስ Intangible ቅርስነት ከሦስት አመት በፊት በተመዘገበው የመስቀል ደመራ ስርአት የተከናወነውና ማክሰኞ እለት መስከረም 17 ቀን የተከበረውን የአመታዊውን የመስቀል ክብረ በአል፤ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው መስቀል መገኘት ታሪክ ከብዙ በጥቂቱ በጨረፍታ ለማየት ያህል . . . በ326 ዓ.ም በዘመኑ ኃያል ገዢ የነበረው የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒ፤ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ በመንፈስ ምሪትና በአዛውንቱ አባ ኪራኮስ ምክርም ከኢየሩሳሌም ከተማ ወጣ ብላ፤ መስከረም 16 እንጨት አስደምራ በላዩ ላይ እጣን ስትጨምርበት፤ የደመራው ጪስ ወደ ላይ ወጥቶ ያረፈበትን ኮረብታማ ስፍራ መስከረም 17 ቀን ማስቆፈር ጀምራ፣ በሰባተኛ ወሩ መጋቢት 10 ቀን መስቀሉን ከተቀበረበት አስወጣችው፡፡ ቆይቶም፤ መስቀሉን የአለም ገናና ነገሥታት ከአንዱ አገር ወደ ሌላው በኃይል ሲናጠቁት፤ የጠቡን መክረር ለማስቆም የኢየሩሳሌም፡ ቁስጥንጥንያ፡ አንጾኪያ፡ ኤፌሶን፡ አርመንያ፡ ግሪክ፡ እስክንድርያ...አገራት መስቀሉንና ሌሎች የክብር ንዋየ ቅዱሳትን በእጣ ሲካፈሉ፤ ለአፍሪካ የደረሰው የቀኝ ክንፉ ግማደ መስቀል ወደ ግብጽ እስክንድርያ ተወሰደ፡፡
‹‹ አጼ ካሌብ መስቀሉን እንዲሰጧቸው አለዚያ ግን የአባይ ወንዝን እንደሚገድቡት ለምስር /ግብጽ በዛቻ አስጠንቅቀው ነበር፡፡ በእርሳቸው በተተኩት ልጃቸው በአጼ ዳዊት መስቀሉ ከግብጽ ሲመጣ፤ መሀል ሀገር ሳይደርስ አጼ ዳዊት በድንገት ኑቢያ/ሱዳን ምድር ያርፋሉ፡፡ ልጃቸው አጼ ዘርዐ ያዕቆብ በተራቸው መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው ቤተ መቅደስ አሰርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ ፤ የራእይ ቃል በህልም እየመጣ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል!›› - መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አስቀምጥ! ይላቸው ጀመር፡፡ ከተከታዮቻቸው ጋር ሆነው መስቀለኛውን ስፍራ ፍለጋ መላውን ኢትዮጵያ ሲያዳርሱ ቆይተው በመጨረሻ፤ በወሎ አምባሰል (የማር አምባ) ተራራ አናት ላይ በልዩ አፈጣጠሩ መስቀለኛ ሆኖ ወደሚታየው ተአምረኛ ስፍራ አጼ ዘርዐ ያዕቆብና እህታቸው ንግሥት እሌኒም እየገሰገሱ መጥተው፤ ግማደ መስቀሉን  በዚህ አኖሩት፡፡››
ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም፤ ለብዙ ዘመናት፤ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ነገሥታት የሚጎበኙዋትና ልጆቻቸውንም እውቀት እንዲቀስሙ የሚልኩባት ስፍራም ነበረች፡፡ ለእመ አምላክ አመታዊ ንግሷ በዛሬዋ እለት እልፍ አእላፍ ምእመናን በስፍራው ለበረከት የሚገኙበት ክብረ በአል፤ ጉዞው በአቀበት መንገድ ላይ በመሆኑ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጓዝ ሰው፤ ›የዛሬን ልመለስ እንጂ ሁለተኛ አልመጣም› ሊል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ገና ቁልቁለቱን ወርዶ፡እናትና ልጅ ወዲያና ወዲህ ፈንጠር ብለው በቆሙበት ድንገት መሀላቸውን ገምሶ ባለፈ ደራሽ ውኃ ተለያይተው ቀሩ የሚባልባት ‹‹ተለያየን›› ወንዝን እልፍ ሲል፤ በከፍተኛ ጉጉት ለቀጣዩም አመት ስለመሄድ መመኘቱ አይቀርም። ‹‹የግሸን መንገድና የሴት ልጅ ምጥ አንድ ነው›› ይባላል ከነተረቱም፡፡
+       +       +
‹‹በእስራኤል ዘንድ ሰው የሞት ፍርድ ከተፈፀመበት በኋላ ሬሳው ለማስጠንቀቂያ ከዛፍ ላይ ይሰቀል ነበር፡፡‹ ነገር ግን እስራኤላዊያን ሰውን በስቅላት አይገድሉም ነበር፡፡ ዘዳ 21፡21-23፤ ኢያሱ 10፡26፡፡›› የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ‹‹ስቅለት›› ለሚለው ቃል ፍቺ በሰጠበት ገጹ (82-83) ላይ ያሰፈረው  ነው፡፡ በምዕራፍና ቁጥር ብቻ የተዘረዘሩትን ማጣቀሻዎችንም ጨምረን እንያቸው።
‹‹የከተማውም ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፣ እንዲህም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታርቃለህ፥ እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ። ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ፥ እንዲሞትም ቢፈረድበት፥ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው፥በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር፤ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው።›› ኦሪት ዘዳግም 21፡21-23 ‹‹ከዚህም በኋላ መትተው ገደሉአቸው፥ በአምስቱም ዛፎች ላይ ሰቀሉአቸው፤ እስከ ማታም ድረስ በዛፎቹ ተሰቅለው ቆዩ›› መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 10፡26፡፡
ሮማውያን በብዙ ስቃይ እንዲሞት የተፈረደበትን ሰው በተለይም ደግሞ ዐመፀኞችን ይሰቅሉ ነበር። ለምሳሌ አራት አመት ከክ.በ ሁለት ሺህ ሰዎች በይሁዳ አገር ተሰቅለዋል፡፡ በ66 ዓ.ም ሦስት ሺህ ስድስት መቶ አይሁድ በስቅላት ተቀጥተዋል፡፡ በክርስቶስ ዘመን አራት አይነት መስቀሎች ነበሩ  +  T  X  1 ፡፡ ክርስቶስ የተሰቀለበት የመጀመሪያውን ይመስላል፡፡
ሰው በስቅላት ሲሞት ብዙ ጊዜ የሚከተሉት ነገሮች ይፈጸሙበት ነበር፡፡ 1. ከመሰቀሉ በፊት ይገረፋል - ‹‹...ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ።›› ማቴ 27-26፡፡ 2. መስቀሉን ወይም የመስቀሉን ግንድ ተሸክሞ ከከተማ ወደ ውጪ ወዳለው የመሰቀያ ቦታ ይወሰዳል - ‹‹ ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ። ዮሐ 19፡17-19፡፡ 3. የስቃይ ማደንዘዣ መጠጥ ለሚሰቀሉት ይሰጥ ነበር፡፡ 4. በመስቀል ላይ በምስማር ይቸነከራል ወይም በገመድ ይታሰራል። 5. ከበደለኛው ራስ በላይ የሟቹ ወንጀል ተጽፎ ይለጠፋል፡፡ ጲላጦስ በክርስቶስ የመስቀል ሞት የፈረደበት አይሁድ ‹‹ተሳድቧል›› በሚለው ክሳቸው  ምክንያት ሳይሆን ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ›› ነኝ ስላለ የቄሣር ተቀናቃኝ ነው በማለት ነበር፡፡ 6.የተሰቀለውን ሰው ልብስ ወታደሮች እንዲካፈሉት ይደረጋል፡፡  7. የተሰቀለው ሰው የሚሞተው ደሙን በማፍሰስ ሳይሆን በልቡ ድካም ነው፡፡ የሚሰቀለው ሰው ብዙ ጊዜ በ2ኛው ወይም በ3ኛው ቀን ይሞት ነበር። - ‹‹ጲላጦስም አሁኑኑ እንዴት ሞተ ብሎ ተደነቀ፥ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ቆይቶአልን? ብሎ ጠየቀው›› ማር. 15፡44፡፡ ወዳጆች እንዳያወርዱት መስቀሉ በወታደሮች ይጠበቃል፡፡››
በእስራኤል ዘንድ ያልነበረውን የስቅላት የሞት ቅጣትን ጨምሮ ከላይ የተዘረዘሩት ክንዋኔዎች የሚፈጸሙት በዘመኑ ገዢዎች በሮማውያን እንደነበር ሁሉ፤ ባንፃሩ የስቃይ ማደንዘዣ መጠጥን ለሚሰቀሉት የሚሰጠው በኢየሩሳሌም የነበረው የሴቶች ማኅበር ነበር፤ በመጽሐፈ ምሳሌ 31፡6 የተጻፈውን በማሰብ - ‹‹ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥ ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፡፡››
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኀበር፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ ክርስቶስ መስቀል የአዲስ ኪዳን ጸሀፊዎችን ሀሳብ ያሰፈረበት ዝርዝር ደግሞ እንዲህ ይላል ...‹‹ መስቀል የመዳን ቃል ነው፡፡ መስቀል የማስታረቅ ቃል ነው፤ በሰዎች መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሷልና - ‹‹እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ፤ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ፡ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፡ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።›› ኤፌ.2፡14-16፡፡ መስቀል የቤዛነት ቃል ነው፤ መስቀል የቅድስና ቃል ነው...››
+       +       +
ጥጦስን መሰል ሮማውያን ግን (እንዲሁም ሌሎችም) ቆይተው ደግሞ ገዢዎቹ አባትና አያቶቻቸው፣ ንጹኃን አይሁዳውያንን በስቅላት ሲለሸልሹበት ከኖሩት ራሳቸው የሰቀሉት የአዳኙ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተቆርቋሪ መስለው፡ የስቅለቱን አንድምታ በሚያጎድፍ የከፋ ጥፋት አሁንም እግዚአብሔር በመረጣቸው  አይሁዳውያን ሕዝብ ላይ ሲነሱ እናገኛቸዋለን፡፡
‹‹በተለያየ መልኩ አይሁዳውን በተለያዩ ሕዝቦች እጅግ ዘግናኝ ስደት ደርሶባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ፡ እነርሱ ታሪክን በሚመለከቱበት መልኩ ይበልጥ ስደትና እንግልት ያደረሱባቸው ክርስቲያኖች እንደሆኑ ነው የሚያስቡት፡፡ ይህን እምነታቸውን ከማስተባበል ወይም የተጋነነ ነው ከማለታችን በፊት እስቲ ለዚህ መሰረት የሆኗቸውን ጥቂት ምክንያቶች ከታሪክ እንመልከት፡፡ በመካከለኛው ዘመን ቅድስት አገርን ‹‹ነጻ ለማውጣት›› መስቀል ጦረኞች ባደረጉት ዘመቻ ወንድ፡ሴት፡ ህጻን፡ ሽማግሌ፡አሮጊት ሳይመርጡ በአውሮፓ የነበሩ በመቶ የሚቆጠሩ አይሁድ ማኅበረሰቦችን ጨፍጭፈዋል፡፡ ኢየሩሳሌምን ከተቆጣጠሩ በኋላም፡ እስከዚያ ድረስ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ብዙ ደም አፍስሰዋል፤ ከእነርሱ በላይ ጭፍጨፋ ያካሄደ ሰው ቢኖር በቲተስ (ጥጦስ) የተመራው የሮም ሰራዊት ብቻ ነው፡፡ በጣም የሚያሳፍረው ደግሞ ይህን ሁሉ ያደረጉት በክርስቶስ ስምና መስቀልን እንደ ዓርማ ይዘው መሆኑ ነው፡፡
በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ በአውሮፓና በሩስያ ቁጭራ ሰፈሮች ነበሩ የአይሁድ ማኅበረሰብን የዘረፉ፡ ቤቶቻቸውንና ምኩራቦቻቸውን ያቃጠሉ፡ ሴቶቻቸውን አስገድደው የደፈሩ፡ ለመከላከል የሞከሩትንም የገደሉ፡ የክርስቶስ ስቅለት ምልክት ያለበትን ዓርማ በያዙ ቄሶች የተመሩ አድመኞች መሆናቸው ሌላው እውነት ነው፡፡ ድርጊታቸውን ትክክለኛ ለማድረግ የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ፤ ‹‹የክርስቶስ ገዳዮች ስለሆኑ›› የሚል ነበር፡፡ በኋላም ይህ ትውስታ ገና ከአእምሯቸው ሳይወጣ፡ አይሁዳውያንን ጨርሶ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ናዚዎች ባደረጉት ጭፍጨፋ፣ ስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያን ተገድለዋል፡፡ ለዚህ ተግባራቸው ማስፈጸሚያ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ነበር የተጠቀሙት፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ናዚዎች በአይሁዳውያን ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ለመቃወም በአውሮፓ ከነበሩ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ እንኳ ድምፁን አላሰማም፡፡ በአይሁዳውያን ግን ይህ የክርስቲያኖች ዝምታ በድርጊቱ ከመስማማት ተለይቶ አይታይም፡፡››
የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ፕሮፌሰር የነበሩትና ቀሪ ዘመናቸውን ሁሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ አገልግሎት ያዋሉት፡ የበርካታ መጻሕፍት ደራሲው እንግሊዛዊው ዴሪክ ፕሪንስ፤ ‹‹ለእስራኤል ያለብን እዳ›› በሚል አርእስት በprayer for Israel በታተመው ጽሑፋቸው መሀከል የተጠቀሰ ነው፡፡
ዴሪክ ፕሪንስ ሲያብራሩም፤ ‹‹በ16ኛው ክ/ዘመን የበለጸገ ባሕል፡ በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀ ምድር ጦርና መርከበኛ ሰራዊት እንዲሁም በሁለቱም ንፍቀ ክበብ የተዘረጋ ግዛት እንደነበራት እንደ ስፔንና ምናልባት በሰው ልጅ ታሪክ ግዙፍ የሆነ ግዛቷን በማስከበር ሁለቱን የአለም ጦርነቶች በድል እንደተወጣችው፡ ሆኖም ግን በ1947-48 የእስራኤልን መንግሥት ምስረታ የተቃወመችው የራሴ የትውልድ አገሬ እንግሊዝን መሰል እጅግ ገናና የነበሩ የአለም መንግሥታት - Empires እስራኤልን በተቃወሙ ጊዜ እንዴት ተንኮታኩተው እንደወደቁ...›› እያሉና ተጨባጭ ታሪካዊ ማስረጃዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሳ ለመሳ (‹‹ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፡ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ፡፡›› ኢሳ 60፡12) እያገናዘቡ፤ይህን መለኮታዊ ጸጋ ባለማስተዋል፡ እግዚአብሔር ከአይሁዳውያን ጋር የገባውን ዘለአለማዊ ቃል ኪዳን ባለመረዳት፤ በመስቀል ስም የተፈጸሙ ግፎችን በዘረዘሩበት ጽሑፋቸው ውስጥ፤ ‹‹የዓለም ሕዝቦች በሙሉ ክቡር የሆነውን መንፈሳዊ ስጦታ ያገኙት ከአይሁዳውያን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን፡ አረቦችን፡ አፍሪካውያንን፡ አውሮፓውያንን፡ ሩሲያውያንን፡ አሜሪካውያንን ወይም ቻይናውያንን ጨምሮ ይህ ሐቅ መላው ሕዝብን ይመለከታል፡፡ ከዚህም የተነሳ በዋጋ ሊተመን የማይችል መንፈሳዊ ዕዳ ወይም ውለታ ለአይሁዳውያን አለብን›› ብለው አጽንኦት ከሰጡዋቸው ጥቅሶች መካከል ሁለቱ ... ‹‹ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ›› ዮሐ. ራእይ 5፡5 እና ኢየሱስ በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ሴት የነገራት ‹‹ እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን።›› ዮሐ. 4፡22 ናቸው፡፡ ‹‹መዳን ከአይሁድ ነውና›› ሲል ምን ማለቱ እንደ ሆነ መረዳት በጣም ጠቃሚ ነው። ይህ የማይካድ ታሪካዊ ሐቅ ነው፡፡ አባቶችን፡ ነቢያትን፡ ሐዋርያትን፡ መጽሐፍ ቅዱስንና አዳኝ የሆነውን ክርስቶስን ያገኘነው ከአይሁዳውያን ነው። ከነዚህ ነገሮች ውጭ ድነት በፍጹም የማይታሰብ ነገር ነው!›› ብለዋል አዛውንቱ ፕሪንስ፡፡
+         +         +
‹‹ስለ አይሁዳውያን ሕዝቦች የተሳሳቱ አስተምህሮዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በስህተት ሰርገው የገቡ ናቸው፡፡ ሂትለር እንኳ ‹እኔ የቀጠልኩት ቤተ ክርስቲያን የጀመረችውን ነው እያለ ነበር አይሁዳውያንን የጨፈጨፈውና ‹በዜጎቹ ጉያ ካስታቀፈውና በአለም ዙሪያ ሕዝቦች ልብ ከፀነሰው የጸረ - ጽዮናዊነት Anti Semitism የእፉኝት እንቁላሉ፤ ጸረ ሰላም፡ አጥፊ ዘሩ  መርዛማ ተናዳፊ ስብእናዎችን የቀፈቀፈው›፡፡ ጌታችን ግን የፍቅር፡ የሰላም፡ የርህራሄ አምላክ ነው፤ እንጂ በፍጹም ‹በኔ ስም አሰቃዩ፡ ዝረፉ፡ አሳድዱ፡ አግልሉ፡ ግደሉ› አላለንም! አይሁዳዊያን ሕዝቦች በእደ ጥበባት፡በእርሻ፡ በሳይንስና ምርምርና ዘርፈ ብዙ ሞያዎች በሚያሳዩት የላቀ ተግባር ለአለምና ለመላው የሰው ልጆች ካበረከቱዋቸው የትየለሌ ትሩፋቶች ባሻገር፤ በመንፈሳዊው አለምም ስለ ዘላለማዊ የቃል ኪዳን በረከታቸውም ማመስገን ይገባናል፤ እንጂ፤ የአብርሀምን አምላክ እያመለኩ የአብርሃምን ዘር መጥላት ከቶ እንዴት ይቻለናል! እስራኤላውያን ባለውለታዎቻችን ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርቶች፡ ኢትዮጵያዊውን የንግሥት ሕንደኬን መልእክተኛ ጀንደረባውን ባኮስን ያጠመቀውን ፊሊፖስን ጨምሮ፤ የአዲስ ኪዳንን 2/3ኛ የፃፈልን ሐዋርያው ጳውሎስ፡...ቅድስት ድንግል ማርያምም ሁሉም አይሁዳዊያን ናቸው፡፡ እናም እርሱ ራሱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአይሁድ ወገን ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለራሱ የመረጠውን ዘር መቼም ቢሆን አይተወውም - ቃሉ እንዲል ... ‹‹አንተ በፍጥረቱ የበረሀ ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፤ ይልቁንስ እነዚያ በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም?›› ሮሜ 11-24፡፡ ሂትለር ሞተ እንጂ ዛሬም ድረስ በአለም ሚዲያዎች እስራኤልን በመንቀፍና በማጥላላት ...ወዘተ ለጥፋት የሚንከላወሰው ክፉ መንፈስ ከናካቴው  አልተቀበረም፡ አላከተመምና ክርስቲያኖች ከእንግዲህ ወዲህ ልንነቃ ፡ ከዚህ ቀደም በክርስትና ስም በስህተት ስለተደረጉት አስጸያፊ የጥፋት ተግባራትም ልንፀፀት ይገባናል፡፡ በተቻለን አቅም ሁሉም፡ እስከ ዛሬ ድረስ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ (ቡዳ፡ጠይብ፤ሞረቴ በማለት፡ ከአያት ቅድማያቶቻቸው በወረሱት የአይሁድ እምነታቸው ጽናት በማሸማቀቅ፡ ንብረታቸውን በመውረስ፡ ከጥንት ምኩራባቸውና መኖሪያ መሬታቸው በማፈናቀል፡ በማግለል፡ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት በማድረስና በጭካኔ በመግደልም ጭምር...ወዘተ) በአይሁዳውያን ሕዝብ ላይ ለደረሰው/ላደረስነው ታሪካዊ በደል፤ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ወይም በቡድንና በየግላችን ንስሀ ገብተን፤ በየበኩላችን ዘወትር ለእስራኤል ብንጸልይ መልካም ነው፤ ለበረከትም ይሆንልናልና፤ ‹‹የሚወዱሽ ሁሉ ይበልጽጉ›› መዝ. 122፡6 እንዲል ህያው ቃሉ፡፡›› ይህን መሰል በጎ ሀሳብን ያስተላለፈው፤ ከአራት አመታት በፊት በአፍሪካ ህብረት በተደረገው ‹‹ክርስቲያን የእስራኤል ወዳጆች›› Christian friends of Israel ሴሚናር ላይ የተሰራጨው - Let’s learn from History የETN ህትመት ነው፡፡ ‹‹ከታሪክ እንማር››፤ የመጀመሪያ ገጹ መክፈቻ ጥቅስ ያደረገውና በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍ. ም. 12 ቁ. 3 የተፃፈው ‹‹ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፤ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ›› በረከትን የምንሻ ከሆነ እስራኤልን መባረክ እንደሚገባን መታዘዛችንን አመልካች ዘላለማዊ ቃል ኪዳን መሆኑን እናስተውልም ዘንድ በጽኑ ያሳስባል፡፡
እስካሁን በአለም ዙሪያ በቻይንኛ፡ በፊኒሽና በእብራይስጥ የተተረጎመውና በቅርቡ በአማርኛ ቋንቋ ‹‹በነቢያቱ አንደበት›› በሚል አርዕስት ለህትመት የበቃው The Prophets Speak በ41ኛው ገጹ ላይ ሕዝቡንና አሕዛቡን  በአንድ የሰላም ምስራች የዋጀውን የወንጌል ቃል አስፍሯል፡፡ ኤፌ.2፡17-18 - ‹‹መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ (አሕዛብ) ሰላምን፤ ቀርበው ለነበሩትም (አይሁድ) ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።››  
በይሁዳ ቤተልሄም የተወለደው ‹‹የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ››፤ ‹‹የዳዊት ዙፋን ወራሽ››፤ ‹‹የዳዊት ሥርና ዘር››፤ ‹‹ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፤ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፡፡›› . . . ከይሁዳ ወገን የሆነው፤ በገና ደርዳሪው፤ የእስራኤል ንጉሥ፤ ‹ልበ አምላክ› ዳዊትም በመዝሙሩ መካከል ከምድሪቱ አገራት ሁሉ መርጦ (መዝ. 68፡31) እንዲህ ይላል ... ‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› አሜን፡፡

Read 5725 times