Print this page
Saturday, 01 October 2016 00:00

ተሃድሶ የሚያስፈልገው “ተሃድሶ”

Written by  ክብሮም ዘቢብ
Rate this item
(5 votes)

     መንግስት እንደገና እታደሳለሁኝ ማለቱ የዘወትር ዜና ሆኗል፡፡ ተሃድሶው ዳግመኛ ከመባሉም ሌላ “ጥልቅ ነው” መባሉን ተከትሎ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ በዓይነትና በይዘት፣ በትርጉምና በፍልስፍና ቢለያይም የተሃድሶ አስፈላጊነት ሁሉንም ወይም አብዛኛውን ዜጋ ያስማማል፡፡
መንግስት ችግሬን በተሃድሶ አስተካክላለሁኝ እያለ በስብሰባና በሰበብ ተወጥሯል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ በ93 ዓ.ም ተሃድሶ ማድረጉንና ከተሃድሶ በኃላም በለውጥ መንበሽበሹን በኩራት ይናገራል፤ ከ15 ዓመታት በኃላ ዳግመኛውን ተሃድሶ  “በቅርብ ቀን ይጠብቁ” እያለ ነው፡፡ በዚህ ተሃድሶ ኪራይ ሰብሳቢነት የተባለን በሽታ መላና መድሃኒት እንደሚፈጠርለት  ሲነገር ቆይቷል፡፡ ያ ሆኖ ሳለ፣ ይህ ተሃድሶ የሚሉት ነገር ለንግግር የቀለለ፣ ለተግባር የከበደ (better said than done) ይመስላል፡፡ ከድግስና ከስብሰባ ብዛት ተሃድሶ ማለት ተሰብስቦ መጨፈርና መጠጣት የሚመስለው አይጠፋም። ከሴራና ከመጠላለፍ ብዛት ተሀድሶ ማለት ተቀናቃኝህን ድራሹን ማጥፋት የሚመስለውም አይጠፋም፡፡ ከፕሮፓጋንዳና ከፖለቲካ ብዛት 93 ላይ ተሃድሶ ነበር የሚል የዋህ አይጠፋም፡፡ ከተቃውሞና ከስሜት ብዛት አንዱን ፅንፍ ዘቅዝቆ በሌላኛው ፅንፍ መቆም ተሃድሶ የሚመስለውም ይኖራል፡፡ ከችግርና ከመከራ ብዛት መሪውን  ማጥፋት እውነተኛ ተሃድሶ ነው የሚልም ሊኖር ይችላል፡፡ ከራስ ወዳድነት ብዛት ራስን መሾም አልያም የራሴ የሚሉትን ሰው ወደ ዙፋኑ ማፈናጠጥ እፁብ ድንቅ የሚመስለውም ይኖራል፡፡ ከአውራ ፓርቲ መርህና ምኞት አንፃር አንድን ፓርቲ ለዘላለሙ ማንገስ ይቻላል የሚል ተስፈኛም ይኖራል ብሎ መጠርጠር ጠቃሚ ነው። እውነተኛ ተሃድሶ ግን ከዚህም በላይ ነው። እውነተኛ ተሃድሶን ካለ መደማመጥና መከባበር፣ ካለ ሳቅና ነፃነት፣ ካለ ጤናና ዳቦ ማሰብ አይቻልም። እንዴት ቢባል፡
“ራሳቸውን የሚያዳምጡ ታላቆች ናቸው፤ ሌሎችን የሚያዳምጡ ደግሞ ይበልጥ ታላቆች ናቸው” ኒቼ ዛራቱስትራ
ራስን ማዳመጥ መልካም ቢሆንም ሌሎችን ማዳመጥ ደግሞ ይበልጥ መልካም መሆኑን ኒቼ ይናገራል፡፡ ይህ አባባል በተለይ በመሪነት ያሉትን ይመለከታል፡፡ የአንድ መሪ ተቀዳሚ ተግባሩ ሌሎችን ወይም የሚመራውን ማድመጥ መሆን አለበት፡፡ ሌሎችን ማዳመጥ ሲችል፣ ስኬቱን ማየትና  ውድቀቱንም መለየትና ማረም ይችላል። ባሁኑ ወቅት በርካታ ዜጎች ለሞት፣ ለጉዳትና ለስደት መዳረጋቸው ማንም የሚያውቀው እውነት ነው። ሆኖም ግን መንግስት የችግሩን ስረ-ምክንያት ለማወቅ ህዝቡን ከማድመጥ ይልቅ በስመ ተሃድሶ መሰብሰብን አብዝቷል፡፡ የችግሩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔው አካል የሆነውን ህዝብ ማድመጥ ካልተቻለ “ተሃድሶውም” ሆነ ስብሰባው ትርጉም አይኖረውም፡፡ ህዝብ ማለት የሚፈልገውን ከማለት በላይም እያደረገ ስለሆነ፣ የህዝቡን ስሜት ለማወቅ አይከብድም፡፡ በጀሮው መስማት ያቃተው መንግስት፤ በዓይኑም እየሰማ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አስቸጋሪው ምዕራፍ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ምዕራፍ መንግስት አፈቀላጤዎቹን እንጂ ህዝብን መስማት እንደማይፈልግ ወይም እንደማይችል ያሳየበት ደረጃ ነው፡፡ እናም፣ ተሃድሶ ሲባል እርስ በርስ ተድበስብሶና ተሞጋግሶ ማለፍን ሳይሆን የህዝቡን ስሜት ማንበብና መመለስን ይጠይቃል፡፡
 “ቁጣን ወደ ሳቅ፣ እሳትን ወደ ብርሃን” የመቀየር ጥበብ
የተሃድሶና የሪፎርሜሽን እንዲሁም የ18ኛው ክ/ዘመን እኩያ ተደርጎ ይወሰድ የነበረው ቮልቴር፤ በምጡቅነቱ ይታወቃል፡፡ ይኸው ሰው፣ ከአስተሳሰብ ጥልቀቱ የተነሳ   ቁጣን ወደ ሳቅ፣ እሳትን ወደ ብርሃን የመቀየር ችሎታ ያለው ሰው ነበር ይባልለታል፡፡ እርግጥ ነው ጥበብ ለተሰጠው የሚከብድ አይደለም። ቁጣ ባለበት ሁሉ የቁጣውን ምንጭ አውቆና ለይቶ፣ ወደ መልካም ነገር መለወጥ ይቻላል፡፡ የቁጣው ምክንያት የመልካም አስተዳደር ችግር ብቻ ሳይሆን የመልካም ፖለቲካ እጦት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የቁጣው ምክንያት የዲሞክራሲ መጥፋትና የቢሮክራሲ መብዛት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የህዝብን ችግር ለመፍታት እንቅልፍ በማጣት ፈንታ፣ በህዝብ ፊት እንቅልፍ የሚያዳፋው ፓርላማ መኖሩ ነው የሚያስቆጣው፡፡ መንግስት ህዝብን መፍራት ሲገባው፣ ህዝብ ካድሬን እየፈራ ነው የተቸገረው፡፡ በድምሩ፣ የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የነፃነት እጦት ህዝቡን ያስቆጣው መሆኑ ግልፅ ሲሆን ቁጣውን ወደ ሳቅና ፈገግታ፣ እሳቱን ደግሞ ወደ ብርሃንና እፎይታ መቀየር ሲቻል ታደስን ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በዜናና በመግለጫ፣ በድንፋታና በእርግጫ ብዛት አይደለም፡፡ ይህ የሚሆነው ሁሉንም ጫፎች አድምጦና ሁሉንም አሳትፎ መፍትሔ የማበጀት “ማንዴላዊ; ድፍረት ሲኖር ነው፡፡
“የቻይናው ዶክተር” ለአራት ኪሎም፣ ለጥቁር አንበሳም ያስፈልጋል!
ከሺ ዓመታት በፊት በቻይና ላይ አንድ አብዮታዊ ተሃድሶ ተደረገ፡፡ አብዮት ለሚለው ቃል አዲስ ካለመሆናችን ብዛት፣ ወይ ትምህርት ቤት አልያም አደባባይ እናስብ ይሆናል፡፡ ከአብዮት፣ ከአብዮታዊ እርምጃ፣ ከአብዮት ጠባቂና ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ መብዛት፣ የመደንዘዛችንና የመደነዛችን ጉዳይ ሲታሰብ የቃሉን ትርጓሜ እንዳያምታታ ስለሚያሰጋ፣ አብዮት በሚል ፋንታ ለውጥ ብንለው ሳይሻል አይቀርም፡፡ እናም፣በለውጡ መሰረት አንድ ዶክተር የሚከፈለው የተመደበለት ደንበኛ ጤነኛ እስከሆነ ድረስ ነው፡፡ የደንበኛው ጤና በጨመረ ቁጥር፣ የሃኪሙ ገቢ ያድጋል። ደንበኛው ጤናው የሚታወክ ከሆነ ደግሞ የዶክተሩ ኪስ ይታወካል፡፡ የአተት ዓይነት ወረርሽኝ ከተስፋፋማ፣ የሀገሪቱ ዶክተር “ባንክራፕሲ” ውስጥ ገብቶ የከተማ ሴፍቲኔት ተረጂ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሀኪሙ  ዋና ትኩረት በህመም ሳይሆን በጤና ላይ ይሆናል፡፡ የደንበኛው ጤና እስካልተስተካከለ፣ የተከበረው ሙያ ባለቤት ስለሆነ ብቻ የሚያገኘው ኪሳራ እንጂ ትርፍ አይኖርም፡፡ ትርፍን ማግኘት ቢሻ ጤና የተትረፈረፈበት ማህበረሰብ መፍጠር ላይ ይበረታል፤ የደከመበትንና የተሰጠውን ሙያ ለህመም ሳይሆን ለጤና ያውላል። የሀገራችን የጤና ፖሊሲ÷ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚልም ሰምቶ ይሆናል፡፡
በቻይና ህክምና፣ የህይወት ሳይንስ (the science of life (ayurveda) መባሉ ለምክንያት መሆኑ ነው፡፡ አንድ ዶክተር የሰው ህይወት መጠበቅ እንዳለበት ሁሉ አንድ መንግስት ሀገርን የመጠበቅ ግዙፍ ግዴታ አለበት። የአንድ ዶክተር መሳሳት ታማሚውን እንደሚገድል፣ የአንድ መንግስት ስህተት ሀገርን ይገድላል፡፡ የቻይናው ዶክተር በጤነኛው ልክ እንደሚከፈለው ሁሉ የአራት ኪሎው መንግስትም እንዲሁ መሆን ነበረበት፡፡ ዶክተሩ በታማሚ ብዛት እንደሚከስር ሁሉ መንግስትም በሀገሪቱ ጤንነት ይለካል፡፡
በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች የሰላም ስጋት ገብቷቸዋል። ተጨንቀዋል፡፡ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተቃውሞ ጩኸቶች ይሰማሉ፡፡ በተለያዩ ቦታዎች የሰዎች መሞት፣ የመንግስትና የህዝብ ግጭት፣ ስደትና መፈናቀል መኖሩ መደበኛ ዜና እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተነሱ የተቃውሞ ክንዶች፣ የህዝብ ብሶት የሚያክም መጥፋቱን ያሳያሉ፡፡ የማያስተኛ ችግርና ጉዳይ ባለባት ሀገር፣ የሀገሪቱ ዋነኛ ሆስፒታል በሆነው ፓርላማ የሚገኙ ሀኪሞች በታማሚዎች ፊት ማንኮራፋታቸው የህዝብ  ጤናን አውኳል፡፡ ታማሚው እየተሰቃየ ባለበት ሁኔታ የሀኪም እጦት፣ ሞትንና ስቃይን ያስከትላል፣ እያስከተለም ነው፡፡
ዲሞክራሲ ብሎ ነገር በማይታይባት፣ እስርና እንግልት በበዛባት፣ ሙስና መታገል ከጥቅስና መፈክር ባለፈ የሚያስፈራ በሆነባት፣ ሹመኛው የቻለውን በሚዘግንባት ኢትዮጵያ ላይ ህዝብ ቢቆጣ አይገርምም። ይገርም የነበረው ባይቆጣ ነው፡፡
እንደ ዜጋ የተሰማህን ስትገልፅ የተለያዩ ስያሜዎች ሊያሰጥህ ይችላል፡፡ ይሁንና፣ ማንም ቢሆን ቤቱ ሲፈርስ አይታገስምና በኢትዮጵያ ጉዳይ፣ በሀገር ጉዳይ፣ በህዝብ ጉዳይ፣ በራስ ጉዳይ ድርድር የለም፡፡ በተለይ ደግሞ አማትሮ የሚመለከታት ሌላ ሀገር ለሌለችው ሰው፤የሀገር ጉዳይ የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነትን ጥቅም ለሚረዳ ሰው፣ የሀገር ጉዳይ ከወንበርና ከጥቅም በላይ ነው፡፡ የሶርያን የዘወትር ሰቀቀን ለተመለከተ ሰው፤የአንድነትና የፍቅር ጉዳይ ተቀዳሚ የቤት ስራ ነው። በጠላት የተከበበችው ኢትዮጵያን ላሰበ ሰው፤ የውስጥ ነፃነትና ዲሞክራሲ የምግብ ያህል ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት የጋራ ነው፤አንድነት ያሸንፋል!!

Read 3845 times