Print this page
Monday, 03 October 2016 08:07

ባለመኝታው የባቡር ትራንስፖርት በቅርቡ ሥራ ይጀምራል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

 ወደ ባቡር ሲገቡ በሚያዩት የመቀመጫ ጥራት ዓይንዎን ማመን ይቸግርዎታል፡፡ በስተቀኝ በኩል ባለው መቀመጫ ሦስት ሰዎች ወደ ፊት፣ ሦስት ሰዎች ወደ ኋላ እያዩ ፊት - ለፊት ይቀመጣሉ፡፡ በመኻላቸው ላፕቶፕ አውጥተው ወይም እየጻፉ የሚሄዱበት ጠረጴዛ አለ፡፡ በስተግራ ሁለት ሰው ወደ ፊት፣ ሁለት ሰው ወደ ኋላ የሚያስቀምጥ የሶፋ መቀመጫ አለ፡፡ በአራቱ ሰዎች መኻል የተቀመጠ ጠረጴዛ አለ፡፡ በቀኙና በግራው መቀመጫ መኻል መተላለፊያ አለ፡፡
ባቡሩ 41 ጎታች ፉርጎዎች አሉት፡፡ ተጎታቹ ካርጎዎች 1110 ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 30 የመንገደኛ ተጎታች ፉርጎ አላቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 20ዎቹ ፉርጎዎች ከ112-118 ሰዎች ይጭናሉ፡፡ ከ30ዎቹ ውስጥ 8ቱ ባለ አልጋ ናቸው፡፡ አራቱ ፉርጎዎች እያንዳንዳቸው 64 መንገደኞች ይጭናሉ፡፡ ሌሎች አራት ፉርጎዎች ደግሞ እያንዳንዳቸው 34 መንገደኞች ይይዛሉ፡፡ በአንድ ጊዜ 50 ሰዎች መያዝ የሚችሉ ሁለት ካፊቴሪያ ፉርጎዎች አሉ፡፡ ድንገት ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ቢፈጠር (መብራት ቢቋረጥ) ተብሎ መጠባበቂያ የሚሆኑ 6 ጎታች ባቡሮች አሉ፡፡ ትኬት የቆረጠ መንገደኛ እንደ ድሮ መቀመጫ ለማግኘት በሩጫ አይሽቀዳደምም፡፡ ወንበሮቹ መጫን ከሚችሉት በላይ ቲኬት አይቆረጥም፡፡ እያንዳንዱ መቀመጫ ደግሞ ቁጥር አለው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ መንገደኛ በቆረጠው ቁጥር ወንበር ላይ ስለሚቀመጥ መሸቀዳደም አያስፈልግም፡፡ እያንዳንዱ ተጎታች በር ላይ ደግሞ የጋዜጣና የመጽሔት ማስቀመጫ አለ፡፡
ሁለት ተጎታቾች ደግሞ ባለመኝታና ባለደረጃ ናቸው፡፡ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ አላቸው፡፡ መንገደኞች ቲኬት ሲቆርጡ ከፈለጉ አንደኛ ደረጃ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ብለው መቁረጥ ይችላሉ፡፡ አንደኛው ደረጃ መዝጊያ በር አለው፡፡ ከፈለጉ መጻፊያ ጠረጴዛም መኻላቸው አለ፡፡ 2ኛ ማዕረግ ባለ ተደራራቢ አልጋ ሲሆን በር የለውም - ክፍት ነው፡፡
የዛሬ ሳምንት በርካታ የአገር ውስጥ ሚዲያ ተቋማትና የውጭ አገር ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ከፉሪ-ለቡ ተነስተን እስከ አዳማ (ናዝሬት) ድረስ ጉብኝት አድርገን ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጣቢያ ሰበታ ሲሆን ፉሪ-ለቡ 2ኛው ጣቢያ ነው፡፡ የሰበታ-መኢሶ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መኮንን ጌታቸውና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ ስለ ባቡሩ አጠቃላይ ሁኔታ ገለጻ እያደረጉልን ተጓዝን፡፡
ይህ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የሚዘልቀው የባቡር መንገድ፣ በሁለቱ አገሮች ትብብር የተሠራ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከሰበታ-ደወሌ-ጂቡቲ ድረስ ያለው 656 ኪ.ሜ ርቀት የሠራች ሲሆን ጂቡቲ ደግሞ ከድንበሯ እስከ ወደቡ ያለውን 100 ኪሜ ያህል ሰርታለች፡፡ የባቡር መንገዱ ግንባታ 3.4 ቢሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን 70 በመቶው ከቻይናው ኤግዚን ባንክ የተገኘ፣ 30 በመቶ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ድንበር ተሻጋሪ ስለሆነ የአዲስ አበባ ጂቡቲ ምድር ባቡር ፕሮጀክት በሁለቱ መንግሥታት በጋራ እንደሚቋቋም፣ የማኔጅመንት ኮንትራት ተሰጥቶ ከ3-6 ወር የሙከራ ጊዜ እንደሚኖር፣ ከዚያም ዓለም አቀፍ የባቡር ህብረት መጥቶ ሁሉንም መስፈርቶች ሟሟላቱን ካረጋገጠ በኋላ፣ የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት እንደሚሰጥ ኢ/ር መኮንን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ በ42 ወራት መጠናቀቁን የጠቀሱት ኢ/ር መኮንን፤ የባቡሩ ከፍተኛ ፍጥነት በሰዓት 120 ኪ.ሜ፣ የዕቃ መጫኛው በሰዓት 90 ኪ.ሜ እንደሚበር፣ቀደም ሲል ከአ.አ-ጂቡቲ 7 ቀን ይፈጅ የነበረውን ጉዞ ከ10-12 ሰዓት ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የባቡር መስመሮች ኔትዎርክድ (የተሳሰሩ ናቸው) ያሉት ኢንጂነሩ፤የአዲስ አበባ-ጅቡቲ መስመር ከወደብ ጋር ይገናኛል፡፡ ወደ አገሪቱ ሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ የሚደረገው የባቡር ጉዞ ከአዋሽ ይጀምራል፡፡ ከዚያም ወልዲያ (ሃራ ገበያ) አሳኢታ፣መቀሌ እያለ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ከሰበታ-መኢሶ ያለው 342 ኪ ሜትር ርዝመት መንገዱ 61 ድልድዮችና 434 የውሃ መውረጃ ቦዮች እንዳሉት የጠቀሱት ኢ/ር መኮንን፤ በሩሲያ፣ በቻይናና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲቪል፣ መካኒካልና ኤሌክትሪካል ኢንጂነሮች በመሰልጠንና ከቻይናዎቹ ጋር በመሥራት ወደፊት ራሳችንን ችለን ልንሰራ የምንችልበት ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ቀስመንበታል፡፡ 128 አሰልጣኞችም ወደ ቻይና ተልከው ሰልጥነው ተመልሰዋል፡፡ አሁን ወደ አገር ውስጥ የገቡት እጅግ ዘመናዊ ባቡሮች ከቻይና የመጡ ናቸው፡፡ ወደፊት ተሳቢ ፉርጎዎቹን እዚሁ አገር ውስጥ ለመስራት ዕቅድ አለ በማለት አስረድተዋል፡፡
እንዶዴ ባቡር ጣቢያ የጭነት ጣቢያ ነው፡፡ ባቡሮቹ እቃ የሚጭኑትም ሆነ የሚያራግፉት 8 ኪ.ሜ ገባ ብለው ነው፡፡ እዚያ የሰራተኞች መኖሪያም አለ፡፡ እዚያው እየሰሩ እዚያው ይኖራሉ፡፡ 1110 የዕቃ መጫኛ ፉርጎዎች አሉ፡፡ ፈሳሽ፣ ደረቅ፣ የከብት፣ ብትን ጭነት፣ ለሥጋ፣ ለአትክልት፤ ለአበባ ደግሞ ማቀዝቀዣ ያላቸው 10 ፉርጎዎች አሉ፡፡
አንዱ ፉርጎ 7 ቶን የማንሳት አቅም አለው፤ሁለት መኪና የሚያነሳውን ያህል ማለት ነው፡፡ ጭነት የሚጭኑትን 30 ፉርጎዎች የሚጎትተው አንድ ጎታች ፉርጎ ነው፡፡ የፉርጎዎቹ ብዛት የሚወሰነው ባለው የጭነት ልክ ነው፡፡ በአጠቃላይ 1110 ዕቃ መጫኛ ፉርጎዎች በአንድ ጊዜ ሥራ ላይ ቢውሉ፣ 3500 ቶን የማንሳት አቅም አለው በማለት አቶ ደረጀ ተፈራ ገልጸዋል፡፡
የዚህ የባቡር ፕሮጀክት ታላቅ ምስጢር የገቢና የወጪ ንግዱን በጣም ፈጣን ከማድረጉም በላይ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ነው ያሉት አቶ ደረጀ፣ 17ሺህ ኢትዮጵያውያን ከሰበታ እስከ ደወሌ ግንባታው እስኪያልቅ ድረስ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል አግኝተዋል፡፡ በዚህ ሥራ እውቀትና ልምድ የገበዩት በአሁኑ ወቅት ወልዲያ - ሃራ ገበያ፣ መቀሌ እየሰሩ ነው፡፡ የጋራ የሆነ ኩባንያ ሲቋቋም ደግሞ ከ2600 እስከ 6000 ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ያገኛሉ፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም በንግድ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ይደረጋል ሲሉ አብራርተዋል አቶ ደረጀ ተፈራ፡፡  

Read 2174 times