Monday, 03 October 2016 08:15

ቶዮታ በመኪና አምራች ኩባንያዎች ውድድር ቀዳሚነቱን ይዟል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የጀርመኑ ቮልስዋገን እና የጃፓኑ ቶዮታ እየተቀያየሩ ሲመሩት በዘለቁት የዘንድሮው የአለማችን ታላላቅ የመኪና አምራች ኩባንያዎች ውድድር ከሰሞኑ ቶዮታ መሪነቱን መያዙን ፎርብስ መጽሄት ዘገበ፡፡
ቶዮታ በዘንድሮው የፈረንጆች አመት ያለፉት ስምንት ወራት ብቻ 6.69 ሚሊዮን መኪኖችን አምርቶ ለአለም ገበያ በማቅረብ መሪነቱን መያዙን የጠቆመው ዘገባው፣ በተመሳሳይ ጊዜ 6.69 ሚሊዮን መኪኖችን ለገበያ ያቀረበው የጀርመኑ ቮልስዋገን በሁለተኛነት እንደሚከተል ገልጧል፡፡
የሶስተኛነት ደረጃን ይዞ የሚገኘው የአሜሪካው ጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ በ2016 የመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት 6.3 ሚሊዮን መኪኖችን አምርቶ ለአለም ገበያ ማቅረቡ ተነግሯል፡፡ ቶዮታ እና ቮልስዋገን እያንዳንዳቸው በየአመቱ 10 ሚሊዮን መኪኖችን አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡበት አቅም ላይ እንደደረሱ ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል ያለው ፉክክር መቀጠሉንና በቀሪዎቹ ወራት የመሪነቱን ስፍራ ይዞ የሚቀጥለውንና የአመቱ የዓለማችን ትልቁ የመኪና አምራች የሚሆነውን ኩባንያ ለመገመት አዳጋች እንደሆነ ገልጧል፡፡

Read 1271 times