Monday, 03 October 2016 08:16

የኬንያ የኦሎምፒክ ቡድን መሪ፣ 256 ሺህ ዶላር በመዝረፍ ተከሰሱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ባለፈው የሪዮ ኦሎምፒክ፣ የኬንያን ልኡካን ቡድን በመምራት ወደ ብራዚል ያቀኑት ስቴፈን አራፕ ሶይ፣ ለቡድኑ አባላት የውድድር ቆይታ ከተመደበው ገንዘብ 256 ሺህ ዶላር ዘርፈዋል በሚል ናይሮቢ በሚገኝ ፍርድ ቤት ክስ እንደተመሰረተባቸው አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የኦሎምፒክ ቡድን መሪው ወደ ብራዚል በተደረገው ጉዞ ለሚመለከታቸው የአገሪቱ የመንግስት አካላት ሳያስታውቁ ይዘውት የወጡት 234 ሺህ ዶላር የገባበት አልታወቀም፤ በተለያዩ አጋጣሚዎችም 22 ሺህ ዶላር የመንግስት ገንዘብ ዘርፈዋል የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ግለሰቡ ባለፈው ረቡዕ ናይሮቢ በሚገኘው ፍርድ ቤት ቀርበው የቀረበባቸውን ክስ ያደመጡ ሲሆን፣ የተጠቀሰውን ገንዘብ አልዘረፍኩም ሲሉ ክደው መከራከራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ሌሎች ሁለት የኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን ባለስልጣናትም ናይኪ ኩባንያ በስፖንሰርነት ለቡድኑ ያበረከተውን ትጥቅ ሰርቀዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ በእለቱ ክደው መከራከራቸውን አመልክቷል፡፡
የኬንያ የኦሎምፒክ ኮሚቴና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ባለስልጣናት በሪዮ ኦሎምፒክ በሙስና እንደተጠረጠሩ ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው አመትም የአገሪቱ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና ገንዘብ ያዥ 700 ሺህ ዶላር ያህል በመዝረፋቸውና ሌሎች የሙስና ወንጀሎችን በመስራታቸው ከስራ ገበታቸው እንደተሰናበቱና ምርመራ እንደተደረገባቸው ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1065 times