Monday, 03 October 2016 08:16

የቀድሞው የእስራኤል መሪ ሺሞን ፔሬዝ አረፉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ከእስራኤል መስራች አባቶች አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸውና አገሪቱን በፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስተዳደሩት የኖቤል የሰላም ተሸላሚው ሺሞን ፔሬዝ ባደረባቸው ህመም በተወለዱ በ93 አመታቸው ባለፈው ረቡዕ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ተዘግቧል፡፡
ከፍልስጤም ጋር የሰላም ድርድር እንዲደረግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እ.ኤ.አ በ1994 የኖቤል የሰላም ሽልማትን የተቀበሉት ፔሬዝ፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት በልብ ህመም ተጠቅተው ቴል አቪቭ አቅራቢያ ወደሚገኝ ሆስፒታል የገቡት ፔሬዝ፣ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ባለፈው ረቡዕ ማለዳ ማረፋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ባወጡት መግለጫ፣ በፔሬዝ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸው፣ ፔሬዝ በእስራኤልና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን እስከ እለተ ሞታቸው ያለመታከት የሰሩ ባለ ራዕይ መሪ ነበሩ ብለዋል፡፡  
የሽሞን ፔሬዝ ህልፈተ ህይወት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ቢል ክሊንተን፣ ቭላድሚር ፑቲን፣ ቶኒ ብሌር፣ ፍራንኪዮስ ሆላንዴ እና ጀስቲን ትሬዱን ጨምሮ በርካታ የአለማችን አገራት የቀድሞና የወቅቱ መሪዎች የሃዘን መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ ፔሬዝ ሰላምን በማስፈን ረገድ ያበረከቱትን ጉልህ ሚና አድንቀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በበኩላቸው፣ ሽሞን ፔሬዝ በእስራኤልና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ሰላም ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ መሪ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የሁለትዮሽ መፍትሄን በማመንጨት የአገሪቱ ዜጎች ከፍልስጤማውያንና ከአካባቢው አገራት ጋር በሰላም እንዲኖሩ ለማስቻል የለፉ ታላቅ ሰው ነበሩ ሲሉ አሞግሰዋቸዋል፡፡
ሃማስ በአንጻሩ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ የፔሬዝን ህልፈተ ህይወት በደስታ እንደተቀበለው ገልጾ፣ ሰውዬው ወንጀለኛ መሆናቸውንና ፍልስጤማውያንም በግለሰቡ ሞት ጥልቅ ደስታ እንደሚሰማቸው ማስታወቁን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1923 የተወለዱት ሽሞን ፔሬዝ፣ በ1959 ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርጠው የእስራኤል ፓርላማ አባል መሆናቸውን ያስታወሰው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ፣ ከ1984 እስከ 1986 እንዲሁም ከ1995 እስከ 1996 ለሁለት ጊዜያት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከ2007 እስከ 2014 ደግሞ ፕሬዚዳንት በመሆን ማገልገላቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያና የፋይናንስ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉት የሽሞን ፔሪዝ የቀብር ስነስርዓት የአለማችን ታላላቅ መሪዎች በተገኙበት ትናንት በእየሩሳሌም ተፈጽሟል፡፡

Read 1607 times