Monday, 03 October 2016 08:18

32 ሺህ ሰዎችን ያሰረቺው ቱርክ፣ ማሰሯን እንደምትቀጥል አስታወቀች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 መንግስት ተጠርጣሪዎች በመብዛታቸው አዳዲስ ፍርድ ቤቶችን እየገነባ ነው

       በቱርክ ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ 32 ሺህ ሰዎችን ያሰረው የአገሪቱ መንግስት፣በቀጣይም ሌሎች ተጨማሪ ሰዎችን እንደሚያስር ማስታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የአገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር በኪር ቦዝዳግ ከኤንቲቪ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በሃምሌ ወር አጋማሽ ከተሞከረው መፈንቅለ መንግስት ጋር ንክኪ አላቸው በሚል የተጠረጠሩ 70 ሺህ ያህል ሰዎች ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ 32 ሺህ ያህሉ እንደታሰሩና በቀጣይም ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች እንደሚታሰሩ ተነግሯል፡፡ ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል የተጠረጠሩት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ምርመራውን በወቅቱ ለማጠናቀቅ አዳጋች በመሆኑ፣ የቱርክ መንግስት የተጠርጣሪዎችን ጉዳይ የሚመረምሩ አዳዲስ ፍርድ ቤቶችን እየገነባ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ማስታወቃቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡ 270 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት በዳረገውና ባለፈው ሃምሌ ወር አጋማሽ ላይ ተሞክሮ በከሸፈው የቱርክ መፈንቅለ መንግስት፣ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ከስራ ገበታቸው መባረራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 2047 times