Monday, 03 October 2016 08:25

የፋሽን ኤክስፖ ማክሰኞ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

      የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ አልበሳትና አምራቾች ማህበር በጋራ ያዘጋጁት የጨርቃጨርቅና አልበሳት የፋሽንና የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ማክሰኞ ከ4፡00 ሰዓት ጀምሮ ይከፈታል፡፡ ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚህ ኤክስፖ ላይ ጥጥ አምራቾች፣ ጨርቃጨርቅ አምራቾችና የዘርፉ ቴክኖሎጂ አምራችና አስመጪዎች፣ የቤት ማስዋብ ኢንዱስትሪ ዲዛይነሮች፣ ቡቲኮች፣የመስተንግዶና ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪዎች በአጠቃላይ ከ180 በላይ አለም አቀፍ የዘርፉ አምራቾች ስራዎቻቸውን ለዕይታ እንደሚያበቁ አዘጋጆቹ ሀሙስ ረፋድ ላይ በሳሮማሪያ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
 በኤክስፖው ላይ ከ25  ከተለያዩ የዓለም አገራት፡- ከኬኒያ፣ ጃፓን፣ ደቡብ አሜሪካ፣ ቻይና ዚምባብዌ፣ ህንድ፣ ኔዘርላንድ፣ አሜሪካ፣ ሲሪላንካ፣ ባንግላዲሽ፣ ከእስራኤልና ሌሎች አገራት የሚመጡ አምራቾች ይካፈሉበታል ተብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ይሄው ኤክስፖ በአዲስ አበባ ተካሂዶ፣ውጤታማ እንደነበርና ዘንድሮም መቀጠሉን የተናገሩት አዘጋጆቹ፤ የኤክስፖው የአፍሪካ ተወካይ በሆነችው ኢትዮጵያ በየአመቱ እንደሚካሄድ ጠቁመው፣ይሄም የአፍሪካን ዲዛይነሮች አልባሳት፣ጨርቃጨርቅ አምራቾችና በአጠቃላይ ዘርፉን ያሳድጋል ተብሎ እንደታመነበት ገልጸዋል፡፡
በኤክስፖው በየቀኑ የፋሽን ትርኢቶች የሚቀርቡ ሲሆን በዘርፉ ባሉ ችግሮች፣ በዓለም ተሞክሮዎችና መፍትሄዎች ዙሪያ ውይይት እንደሚካሄድ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡

Read 881 times