Monday, 03 October 2016 08:28

የጎደሉ ገፆች - ምልዐት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

ጃፋር ሱቅ አንድ ሶስቴ ተመላለስኩ - የትዕግሥት ማሞን መጽሐፍ ፍለጋ! … “ቁጭት” የሚለው መጽሐፍዋ ውስጥ ያየሁዋቸው ቁንጅናዎች፣ ብርሃናቸውን ያፈካውን የውበት ኩል አድምቃው ይሆን? አፍዝዛው? በሚል ጉጉት - ጠበቅሁዋት፡፡
ቅዳሜ መጽሐፍዋን እንደሸመትኩ መንገድ ለመንገድ፣ ታክሲ ውስጥ፣ ከዚያም ቤቴ ጋደም ብዬ አነበብኳት፡፡ …. “ትናንትና ዛሬ” … የሚለውን ሳነብ ስሜታዊ ሆንኩ፡፡ ነፍሴ ነደደች፣ እንባዬ መጣ፡፡ የደስታ እንባ!! … የልቤን ጀርባ፣ በሚያቃጥል ጅራፍ፣ በሚጣፍጥ ዜማ ገረፈችው!
ዛሬ ግን
ባለ ቀን ተጭኖት ተላልፎ ተሰጠ አቅም ጉልበት
አጣ፣
ሐገር እንደሌለው ወገን እንደሌለው
እሜዳ ተሰጠ፡፡
ማንም ታሪክ አልባ ታሪኩን ሲያጠለሽ፣
ስሙን ከል ሲቀባ፣
ዕዩልኝ ወንዱን ልጅ ዘራፉን በትኖ፣
   እንደሴት ሲያነባ፡፡
ዛሬ ላይ ተቀምጠን የትናንትን ኑረት የኋሊት
ሽተናል፤
ለስማችን ጥልሸት ቀና ምንልበት
ትንሳኤ ናፍቀናል፡፡
የታል ዳኛ ሙሴ፣ ሙሴ ያስፈልገናል፣
አለን ብለን እያልን በዓለም ፊት ወድቀናል፡፡
እስቲ አንድ አርኬ/አንጓ ልጨምርበት …
ዛሬ …
ከተስፋ ቃርሚያ ላይ ሩቅ ማስላት አይሎ ፣
መሻቱን ቢነፈግ በኖረ ኩራቱ በክብሩ ዕጣ ጥሎ፣
እንደተለቀመ እንደ ስንዴ እንክርዳድ፣
የትም ተበትኖ በሐሩር በንዳድ፣
ሐገር እንደሌለው፣
ወገን እንደሌለው፣
እናት እንደሌለው፣
አባት እንደሌለው፣
ተመልካች እንዳጣ … በረሀ ወደቀ፣
ለካስ ስም ባዳ ነው፡፡ “ሐበሻ ነኝ” ማለት …
ካፉ ተነጠቀ፡፡
ሀሳቡ ቁሥልን በዶሮ ላባ ጠምቆ ውሃ እንደማጠብ ነው፣ እያመመ ደስ ይላል፡፡ አሰነኛኘቱ፣ በእጅጉ የተሳካ ነው፡፡ ምጣኔውን ስትለካ፣ ብዙ ቦታ ላይ ቤት አመታትዋ፣ ጠንካራ ድምፅ ያላቸውን አናባቢዎች በመጠቀም ስለሆነ፣ “ጧ!” ብሎ የሚፈነዳ፣ ዜማና ድምቀት አለው፡፡ ለአፅንኦት የተጠቀመችባቸው ደጊመ - ቃላት፣ ደግሞ ከልብ ትርታና ቅዝዝ ካለ የእንባ ስሜት ጋር ሆነው በልብ ስሮች ቁልቁል ይወርዳሉ፡፡ … ጠብታቸው ይሰማል፣ ግዝፈታቸው ያጎብጣል! … በሀሳብ፣ ኮሳሳ ቃላት ዘውድ ደፍቶ፣ ማንገስ እንደሚቻል ያሳያል፡፡
ትዕግስት ማሞ በፍቅር ግጥሞች፣ ለኔ የተለየ ጣዕም ያላት ናት፡፡ በፊት የወደድኩላትም ያንን ነበር፡፡ ለነፍስ መዘመር ትችላለች፤… ውስጥ ያለውን የፍቅር ወንዝ ጠልፋ፣ በቦይ ወደየ እርሻችን ስታመጣው፣ ሁዳዳችን ውስጥ ያሉት አዝርእት እየረሰረሱ፣ ደስ በሚል ነፋሻ ነፋስ - “እዜፒዩ!” እያሉ ያጎነብሳሉ፡፡ ትዕግስት ውስጥን ትፅፋለች … ግንዱን ብቻ ሳይሆን የሥሩን ሥር!
… የለህም አውቃለሁ፣ አልመጣም ደፍሬ፣
ላልተሰጠኝ ህይወት፣ ብቻዬን ሌጣዬን፣
እርቃኔን አድሬ፡፡
ደ’ሞ ወረድ ብላ እንዲህ ታፈሰዋለች፡-
… አንተ ሐገር ነጋ ወይ፣ ነገን ማሰላሰል፣
ገብቶሀል ትርጉሙ፣
ወይስ ልክ እንደኔ የትናንት ትውስታው፣
የትናንት ህመሙ፣
ነፍስህን ሰቅዞ ይኮረኩርሀል?
ንገረኝ የኔ ዓለም ልብህ ምን ይልሀል?
መንጋትና መምሸት በፍቅር ቀን ለብቻ ነው፡፡ … የጠሉትን ገመድ በጥሶ የሚጥል አንጀት የጠፋ ቀን፣ የንጋቱ ነገር ሆድ ይፍጀው ነው፡፡ ትርጉሙ አይደረስ! የትየለሌ ነው፡፡ “ንገረኝ የኔ ዓለም ልብህ ምን ይልሀል? … ልብ እንደ ስልክ አይጠለፍ ነገር! ገፀ ባህሪዋ … ገፀ ባህሪውን፣ በምናብ ትቧጥጠዋለች … ትፈልገዋለች …. ስሜቱን ለማወቅ ትማስናለች! … የተለየችውን ሰው ዛሬም “የኔ ዓለም!” ማለቷ ይገርማል፡፡ … የማንም ዓለም አይደለም፣ የሷ ዓለም ነው!! … ትዕግስት እንደ እኛ ሀገር ገጣሚያን ስለ ፍቅር ስታወራ አትግደረደርም! … ከይሉኝታ ነፃ የወጣች፣ የራሷ ባንዲራ ያላት ናት፡፡ ያመኑበትን፣ ነገር መፃፍ እንዲህ ነው፡፡ ብርሃኑ ገበየሁ እንዳለው፤ የኛ ሀገር ደራሲያን አደባባይ ላይ አይናፋር ናቸው፡፡ … የጓዳውን ባናውቅም!
“የእብዱ ሰው ስንኞች” ብዙ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ ጉዳዩ ቅርባችን ባለው የታክሲ ሰልፍ ላይ የታከከ ቢሆንም ራቅ ብሎ ላየው፣ አድማሱ ብዙ ይከነዳል፡፡ አተያዩም ጥልቅ ነው፡፡ አንድ አንጓ እንይላት፡-
ይኼ ሰልፈኛ ግን …
ባደባባይ ውርደት፣ ስድብ ተከናንቦ፣
ከሚያውቀው እውነት ላይ ትዝታን ደርቦ፣
             ዐይኖቹን ያሻሻል…
ፈሪ ደንቡ አይደለ እየደጋገመ ነገር ያበላሻል፣
  እውነት ያጠለሻል፡፡
በሚገርም ፍሰት ይቀጥላል ግጥሙ፡፡ … የግጥም አንዱ ብቃትና ውበት ይህ ነው፣ የምናውቀውን ነገር፣ በማናውቀው መንገድ፣ ማምጣት! … መከሸን፣ ማጣፈጥ! ትዕግስት በነገር ሁሉ ጨምራለች፡፡      
እኔ ወደ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ግጥሞች ሸሽቻለሁ፤ እንዲህ ብዬ
ተረት ተረት በይኝ፤ አንድጂው እሳቱን፤
የልቤን ውስጥ ሀዘን አራግቢው ብሶቱን፤
ሀዘኔ-ተረቴ
ተረቴ- ሕይወቴ
የአያት-ቅምአያቴ
የእናትና- አባቴ
ውስጥን የሚያነድድ፤ ግጥም ነው፡፡ ጋሽ ስብሀት ልቦለድ እንደ ተረት ቢፃፍ ያለውንም አሥታወሰኝ፡፡ የትዕግስት ግጥሞች ቆሠቆሱኝ፡፡ ባላሰብኩት ልክ! ልቤ ክንፍ ካወጣ በኋላ መሥከንም፤ማረፍም አልቻልኩም!... (ትዕግስት በሩቁ ላያት እንዲህ ያገር ሕመም የሚያማት፤ እንዲህ የወገን እንባ የሚያማስላት አትመስልም፡፡… ግን እንዲህ ናት!..)
ብዙ ቦታ ለዛ ባለው ጥበብ፣ የደበበ ሰይፉን ሃሳብ የተጋራች ትመሥላለች፡፡ አትሣቅስ በሉኝ /ግዴለም ከልክሉኝ/ የፊቴን ፀዳል/ አጠልሹት በከሰል/ የግንባሬን ቆዳ /ስፉት በመደዳ፤ /ጨጓራ አስመሰሉት፡፡
ግዴለም፡፡
አትጫወት በሉኝ /ዘፈኔን ንጠቁኝ፡፡
ግዴለም፡፡
ብቻ አታልቅስ አትበሉኝ አትጩህ አትበሉኝ፡፡
ገጣሚዋ አሁን ያለውን አገራዊ ስሜት ተጋርታለች፡፡ ዶክተር ሳሙኤል ጆንሰን እንዳለው ካልሆነ በቀር፣ ወጣቷ ገጣሚ ብርቱ የጥበብ ሥራ ሰርታለች፡፡ ዓይኖችዋ በጥልቀት፣ ልቧ በርቀት ማትሯል፡፡ … “All perhaps are more willing to honor past than present excellence›› ነበር ያለው ጆንሰን፡፡ እውነት ለመናገር አሁን አሁን ራቅና ጠለቅ ያለ አተያይ ያላቸው ወጣት ገጣሚያን እያገኘን ነው፡፡ ትንሽ ቢያነብቡ፤ ቢጨምሩበት፤ ‹‹በቃኝ›› ብለው ራሳቸውን ሰማይ ባይሠቅሉ፣ ከቀድሞ የበለጠ የጥበቡ ሠፈር እንደሚደምቅ፤ ድንኳኑ በፌሽታ እንደሚሞላ እምነት አለኝ፡፡
‹‹ታብዳለች ፒያሳ›› ስለ ከተሞችና ሰፈሮች ከተፃፉት የሌሎች ገጣሚያን ስራዎች በለጥ ያለ ውበትና ድምቀት አላት፡፡ ሃሳብና ሽርሽሯን ጨምሮ ምሠላው ያማረና ድንቅ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
የተሳያት ጠሐይ፣ ቦታውን ለምሽት፣ ለቆ
ለመሰወር
ከተፈጥሮ ጋራ፣ ድርድር ላይ ነበር
ቀኑ ቅዳሜ ነው…
የምሽቱ ንፋስ፤ የኮረዶች ጠጉር እያዘናፈለ
ምድርን ከሀሩር ጋር፤ ለማቆራረጡ ደርሶ ብቅ
እንዳለ..
ሒያጅ መጪ በዛባት እግር በረከተ፣
ኩርፊ ዝምታዋ፤ በሳቅ በፈገግታ፤ ድንገት
ተከተተ፡፡
የግጥሟ መደምደሚያው አንጓ እንዲህ
ይቀጥላል…
ፍቅር ባቦዛቸው፤ በሽንፈታም ዐይኖች…
ብርሐኗን ለኩሳ፤
በናፍቆት ያጌጠ፤ ክት ልብሷን ለብሳ፤
ቅዳሜ ከሆነ…
ጨርቋን ትቀዳለች፤ ታብዳች ፒያሳ
ቅዳሜ-ፒያሳ እንዲህ ትቀብጣለች እንዲህ
ታብዳለች፡፡
‹‹የጎደሉ ገፆች›› ደራሲ በግጥሞቿ ትልልቅ ሀገራዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን አንስታለች፡፡ ኢ.ኤ.ግሪኒንግ እንደሚሉት፤ የቅዳሜዋን ፒያሳ በሙዚቃና በሥዕል አድምቃ አቅርባለች፡፡ ግጥሞቹ ውስጥ የሕይወት አበቦችና እሾሆች አሉ፤ ያበደ ፍቅር፤ የመረረ- ሀዘንም ተካትቷል፡፡
ከዚህ ሌላ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ የታተመው ግጥም፤ ፉከራ ይመሥላል፤ በማን ላይ እንደሆነ ባላውቅም ‹‹ሀበሻን አትድፈሩ!›› ይላል፡፡ ምናልባት አሁን መንግስት ከሚያሳየው ጡንቸኝነት ጋር ይያያዝ ይሆን?
በጉልበታችሁ ታምናችሁ
በመሣሪያችሁ
ክምር ብዛት
ሐበሻን ያህል ጀግና ሕዝብ
ኢትዮጵያን ያህል ግዛት
መድፈር ካሻችሁ ግና
ያው ሜዳውም ፈረሱ
ለኢትዮጵያዊ ብርቁ አይደለም
ሥጋ ቆርሶ ደም ማፍሰሱ፣… እያለ ይቀጥላል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ መጽሐፉ በሁለት አፍ የተሳሉ ሰይፎች ያሉበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲያው ክንፋቸውን የዘረጉ ደካማ ግጥሞችም አሉበት - እንደ “የጎደሉ ገፆች” አይነት! ይህ ደግሞ የየትኛውም ገጣሚ ችግር ነው፡፡ ብቻ ትዕግስት ከቀደመው ሥራዋ ይልቅ በውበት ማለትም በቅርፅና በይዘት ደምቃ መጥታለች፡፡ ይመቻት!

Read 1363 times