Monday, 03 October 2016 08:31

የደራሲነት ምርጫና ጭንቀቱ!!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 (የራስ ተሞክሮ)

      ስለ አጭር ልብ ወለድ መፃፍ ፈለግሁኝ፡፡ ስለ አጭር ልብ ወለድ ከመፃፍ፣ አጭር ልብወለድ መፃፍ ይቀለኛል፡፡ መጀመሪያ ያነበብኩትን አጭር ልብ ወለድ ከማስታወስ፣ መጀመሪያ የፃፍኩትን አጭር ልብ ወለድ ማስታወስ ይቀለኛል፡፡
አዲስ ነገር የምፈልግበት ጊዜ ነበር፡፡ የተወሰኑ የእንግሊዝኛ አጭር ልብ ወለዶች ለመፃፍ ሞክሬ፣ግን እኔ እንደምፈልጋቸው አልሆኑልኝም፡፡ ያነበብኳቸው መፅሐፍት እየጎተቱ ያስቸግሩኛል፡፡ ደግሞ ፀሐፊ/ደራሲ እሆናለሁ ብዬ ቆርጫለሁኝ፡፡ የቀድሞ ስራዬን ለዚህ ድፍረት ስል ትቼዋለሁ፡፡ አስታውሳለሁኝ በጣም የትግል ጊዜ ነበር፡፡ የጥርጣሬ ጊዜ ነበር፡፡ “ነኝ ወይንስ አይደለሁም? መፃፍ እችላለሁ ወይንስ አልችልም?” … ሁሉም ነገር ጥርጣሬ ብቻ ነበር፡፡ ግን እርግጠኝነትም አለ፡፡ እርግጠኛ ባልሆን እርግጠኛ የነበረውን ስራዬን አልተውም፡፡
“It’s a shot in the dark” እንደሚለው ነው ቡካውስኪ፡፡ … “ወርውር የእጅህን ዘገር/የህሊናህን ዘር/ ይዘኸው እንዳትቀር” የሚለው የደበበ ሰይፉ ቁራጭ ግጥምን እንደ አዝማች እደጋግማለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ ፈርተውኛል፡፡ ተጠራጥረውኛል፡፡ አባቴ አንድ ቀን አስቀምጦ መከረኝ፡፡ ስለ ብዙ ደራሲዎች ህይወት ዘረዘረልኝ፡፡ ብዙዎች ደራሲ እንሆናለን ብለው ባክነው ነው የሚቀሩት ------ they end up being bums … ምናምን ሲለኝ ትዝ ይለኛል። ግን ማስፈራሪያው ቢያስፈራራኝም፣ ህይወቴ ትርጉም የሚኖረው ሳልፈራ ከቀጠልኩ ብቻ ነው ብዬ ገገምኩኝ፡፡
ቤተሰቤ በአጠቃላይ በንባብ ባህል ውስጥ የሚመላለስ ቢሆንም … የሌሎችን ልፋት በድርሰት መልክ ማንበብ እንጂ … ደራሲ ሆኖ አስነብባለሁ የሚል አቋምን ለማስተናገድ ዝግጁ አልነበረም፡፡ “ሞክር እና እየው” በሚል ተዉኝ፡፡
የፅሁፍ አለም አስፈሪው ጨለማ በመኝታ ቤቴ ውስጥ ቢሰፍንም … መፅሐፍ ገልጬ ሳነብ መጠነኛ ብርሐን እፈጥራለሁ፡፡ የሆነ ሀሳብ ብልጭ ሲል ለመፃፍ ስታገል፣ ጥርጣሬዬ ለጊዜውም ቢሆን ይወገዳል፡፡ ትግል ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ እንዳይኖር ግን ከጧት እስከ ማታ በትግል ውስጥ እደበቃለሁኝ።
የጥንቱ የስራ ዓለም ጓደኞቼን ራቅኋቸው። የድሮው አለም ለፅሁፍ ግብአት እንዲሆነኝ እንጂ እንድኖርበት አልፈልግም ብዬ ወስኛለሁ፡፡ አዲስ ድልድይ ለመስራት የድሮውን አፈረስኩት፡፡  እንድፅፍ ሲያበረታታኝ የነበረ አንድ ፈላስፋ ወዳጅ ነበረኝ፡፡ ፀሐፊ ሆኖ እኔ እንድፅፍ ሲገፋፋኝ በነበረ ጊዜ፣ እኔ ደብዳቤ እንኳን መፃፍ የማልደፍር ሰው ነበርኩኝ፡፡ ጓዜን ጠቅልዬ ወደ ፅሁፍ ስገባ፣ ፀሐፊ የነበረው ጓዴ መፅሐፍን ማምለክ አቁሞ፣ ብር ማምለክ መጀመሩን በይፋ አስታወቀኝ፡፡ እምነቴን እንዳይበክለው ካፈረስኩት ድልድይ ጋር እሱንም አስወገድኩት፡፡
በህይወቴ እንደዚያ ያነበብኩበት ዘመን የለም። ሌላ አማራጭም አልነበረኝም፡፡ የማላነብ ከሆነ መፃፍ ነበረብኝ፡፡ የማልፅፍ ከሆነ ስለ ፀሐፊዎች ህይወት ማወቅ ነበር ፍላጎቴ፡፡ የጃክ ለንደንን አጭር ልብ ወለዶች ከመውደድ ወደ መጥላት ገባሁኝ። ከአጭር ልብ ወለዱ ይልቅ “ማርቲን ኤደን” የተባለውን ብቸኛውን ረጅም ድርሰቱን ሳነብ ብዙ ፅናትን ፈጠረልኝ፡፡ “ማርቲን ኤደን” የአንድ ደራሲ ታሪክ ነው፡፡ ተነባቢ ለመሆን የሚያደርገውን ውጣ ውረድ፣ ከህይወቱ ጋር ቀይጦ የሚተርክ መፅሐፍ ነበር፡፡ ልክ ለእኔ የተፃፈ ድርሰት እስኪመስለኝ ተዋጥኩበት፡፡
የጃክ ለንደን አጫጭር ልብ ወለዶችን የጠላሁበት ምክኒያት ለአንባቢ እንጂ ለደራሲ የሚሆኑ ስላልነበሩ ነው፡፡ በህይወት ስቃይና በተፈጥሮ ጭካኔ ስር ስለሚፍጨረጨሩ ሰዎች ገድል ነው  የሚተርኩት። የህይወት ተሞክሮው በጉዞ ገድሎችና በአደገኛ የህይወት ጠርዝ ላይ ተፈትኖ የኖረ ሰው የሚፅፋቸው ታሪኮች ናቸው። የእሱ ታሪክን እንደ አንባቢ ሆኜ ሳየው፣ ነፍስን ሰቅዞ የሚይዝ የአድቬንቸር ፊልም ነው፡፡ ግን የእኔን አለም አይወክልም፡፡ የእኔ አለም ከመኝታ ቤቴና ከመፅሐፍቴ የበለጠ ገድል የሌለበት ነው። ተጉዤ አላውቅም፡፡ ጀብድ ፈፅሜም አላውቅም። ለነገሩ የመጓዝም ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ እኔ የጉዞ ማስታወሻ ፀሐፊ መሆን እጣ ፈንታዬ አይደለም ብዬ ደምድሜያለሁ፡፡ ስለዚህ ጃክ ለንደንን ጠላሁት። ሪያሊዝም የሚፅፉትንም ጠላሁዋቸው፡፡ አዲስ አማራጭ መፈለግ ነበረብኝ፡፡ ስለ ተራ ሰዎች መፃፍ እችላለሁ፡፡ የማውቃቸው ሰዎች ከተራም የበለጠ የወል ናቸው፡፡ የሚያወሩትን፣ የሚያስቡትን፣ የሚኖሩትን ----- ልፅፈው ይቅርና ልብ ብዬ ሳያቸው እንኳን ነፍሴ ትፀየፋለች፡፡
አቅጣጫ ማግኘት ነበረብኝ፡፡ የራሴን ድምፅ መፍጠር ነበረብኝ፡፡ ጭንቁ የሚቻል አይደለም። ጭንቅ ውስጥ እንደነበርኩ ግን የሚገባኝ አሁን ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስታውስ ነው፡፡ ደግነቱ በወቅቱ ለእኔም አይታወቀኝም ነበር፡፡ ኪሎ ስቀንስም ልብ አልልም፡፡ ያኔ ኤችአይቪ የሚፈራበት ዘመን ነበር፡፡ ግን አይታወቀኝም፡፡ …. ማማጥ ብቻ ነበር ሥራዬ፡፡
ይሄ ጽሁፍ ልብ ወለድ ይመስላል አይደል። ወደ ኋላ ተመልሰን በድጋሚ ህይወታችንን ከተመለከትነው እኮ ታሪካችን በራሱ ጊዜ ልብ ወለድ ሆኖ ይገኛል፡፡
አንድ ዓመት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቆየሁኝ፡፡ እህቴ የገዛችልኝ ሙሉ እሽግ የወረቀት ጥራዝ በመፃፍ አለቀ። ብዙ እፅፋለሁ ግን የነጠረው ውጤት ጥቂት ነው፡፡ ክረምት መውጫው ላይ አልሰር ያዘኝ፡፡ ጨጓራዬ ደማ፡፡ ደም አስታወከኝ … ራሴን ስቼ ሆስፒታል ገባሁኝ፡፡ ደም አዋጥተው ሰጡኝ፡፡ ያው ድኜ ወጣሁ፡፡ ምናልባት የሰጡኝ ደም እንደሆነ ባላውቅም … ከሆስፒታል ወጥቼ ሳገግም፣ ከመስከረም ፀሐይ ጋር አዲስ የምናብ አቅም በውስጤ ሲበራ ድንገት ይሰማኝ ጀመር፡፡
ከመስከረሙ ፀሐይ ጋር አንድ ቀደም ሲል ሰው ያስተዋወቀኝን ጋዜጠኛ በመንገድ ላይ ባጋጣሚ አገኘሁት፡፡ ቤቱ ወስዶ አብረን ቃምን፡፡ እንደኔው የሚፅፍ ሰው … እና ከፅሁፉ ጋር ለመሞት የቆረጠ አምሳያዬን ለመጀመሪያ ጊዜ አገኘሁኝ፡፡ ጋዜጠኛው ዘና ያለ ነው … በአላማና ግብ የተወጠረ አይደለም። ታላቅ ደራሲ በአንዴ ካልሆንኩ ብዬ፣ በጭንቀት አልሰር መያዝ የዋህነት መሆኑን ተገነዘብኩኝ፡፡ ሁሉም ነገር ቀስ በቀስ የሚመጣ ነው፡፡
በሦስት ወር ታላቅ ድርሰት ካልፃፍኩ ብሎ ነገር የለም፡፡ ጋዜጠኛው ቤት ሌሎች ሁለት ልጆች አይጠፉም፡፡ አንዱ ገጣሚ ነው፤ ሌላኛው … እንደ ሀያሲ፣ እንደ ባህታዊም ያደርገዋል፡፡ ለብቻ ከሚደረግ ትግል ይልቅ የማህበሩ ይቀላል፡፡ መናበብም ይኖራል። የባህሪይ ብቻ ሳይሆን የወረቀትም መናበብ፡፡ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በእንግሊዝኛ እንጂ በአማርኛ ፅፌ አላውቅም፡፡
“አማርኛ ወንዝ የማያሻግር ቋንቋ ነው” ብለን ከቀድሞው ፈላስፋ (በኋላ ነጋዴ) ጓዴ ጋር እንፎክር ነበር፡፡ እንደ አዲስ እምነቴን ለማደስ፣ አማርኛን ማንበብ ያዝኩኝ፡፡ ንባቤ ለዘመናት ሳይሆን አቅሜን ምዘና ነበር፡፡ የአዳም ረታ “ማህሌት”ን … እና በፋሲል ይትባረክ የተተረጎመውን የዶስቶይቪስኪ “የስርቻው ስር መጣጥፍ”ን ከሌላው ለይቼ ወደድኳቸው፡፡ ሁለቱንም የማምለክ ፍላጎት ግን ባልታወቀ ምክኒያት አልነበረኝም፡፡
የመጀመሪያ የአማርኛ መጣጥፍ ፅፌ፣ ለማህበሩ አባላት አስነበብኳቸው፡፡ ገጣሚው መጣጥፉን መውደድ ብቻ ሳይሆን ከዚያ ላይ እየጠቀሰ፣ በወሬ መሀል እንደ ማስረጃ ሲያነሳሳው፣ ያ የድሮው ፍርሐቴ የልብ ልብ ተሰማው፡፡ ከዚያ በኋላ መጣጥፍ መፃፍ ላይ በረታሁኝ፡፡ መፃፍና ለእነዛ መሰሎቼ አስነብቤ ጭበጨባን ማግኘት እንጂ ሌላ ግብ ለጊዜው አልታየኝም፡፡
ለጋዜጣ ለምን አትሰጥም? የሚል ግፊት የመጣውም ከዚሁ ቡድን ነው፡፡ ጋዜጦች አጭር ልብ ወለድ እንደሚያስተናግዱና ‹‹አዲስ አድማስ›› ተብሎ የሚጠራ ጋዜጣ፣ የርቅቀት ጫፍ መሆኑ ሁሉም በጊዜው ይስማማበት ነበር፡፡ ከቡድኑ መሀል ባይሆንም አንድ ጓደኛቸው፣ ሳይንስ አምድ ላይ ስለ ‹‹አክሊሉ ለማ›› ጽፎ እንደተስተናገደለት፣ ልጁን እንደ ጀግና ክበው ነገሩኝ፡፡
አጭር ልብ ወለድ በአማርኛ ለመፃፍ ገና ሩቅ መሆኔ ይገባኛል፡፡ ጅማቴን ለማጠንከር ስል የእንግሊዝኛ ልብ ወለዶችን ወደ አማርኛ መተርጎም ጀመርኩኝ፡፡ ትርጉም ራሱን የቻለ ውበት እንዳለው የገባኝ፤ በተመስጦ ስተረጉም ውዬ፣ ከሀያ ገፅ በላይ ፅፌ እንቅልፍ የሚገላግለኝ ጊዜ ስለነበር ነው፡፡ በእጄ ብዙ ልብ ወለድ ቢኖሩኝም- በአልፍሬድ ሂችኮክ ብራድ ስር የሚታተሙ ‹ሚስትሪ ማጋዚን› ላይ የወጡ ብዙ የፍርሀት  ታሪኮችን ወደ አማርኛ ማዞር ያዝኩኝ፡፡
ለ“አዲስ አድማስ” ልብ ወለድ ከመስጠቴ በፊት በጋዜጣው ላይ የወጡትን አጭር ልብ ወለዶች  ደርድሬ በማንበብ ራሴን አዘጋጀሁ፡፡ የፀሐፊዎቹን ስም አልይዝም፡፡ ትኩረቴ የልብ ወለዱ አቅም ላይ ብቻ ነበር፡፡ ለአቅመ “አዲስ አድማስ” እስክደርስ… ተመሳሳይ ይዘት ያለው ‹‹ኔሽን›› የሚባል ጋዜጣ ትኩረቴ ውስጥ ገባ፡፡ “ኔሽን” ላይ ‹‹ሉቂያኖስ››  በሚል ስም የሚፅፈውን ልጅ የእይታ አዲስነት ማድነቅ ጀመርኩኝ፡፡ ልጅ በእውቀቱ ስዩም ስለመሆኑ በጊዜው ምንም መረጃ  አልነበረኝም፡፡
የተረጎምኩትን ልብ ወለድ በአዲስ ሉክ በጥንቃቄ ገልብጬ፣ ወደ ጋዜጣው የዝግጅት ክፍል ሄድኩኝ፡፡… “ማርቲን ኤደን” በሚል ርዕስ፣ ጃክ ለንደን ጻፈው ያልኩት ወጥ ልብወለድ ላይ ደራሲ ለመሆን አሳሩን የሚበላው ገፀ ባህርይ፤ ፅሁፉን ለጋዜጣ ሲያስገባና “rejection slip” ሲሰጠው ነው መፅሐፉ የሚተርከው፡፡ እኔም የማርቲን ኤደን እጣ ፈንታ ይገጥመኛል ብዬ ደምድሜ ነበር ፅሁፌን ያስገባሁት። መቶ ጊዜ ለመመላለስ ዝግጁ ነበርኩኝ፡፡
ግን የሰጠሁት የትርጉም አጭር ልብ ወለድ በተመሳሳይ ሳምንት ጋዜጣው ላይ ወጣ፡፡ ማመን አልቻልኩም፡፡ በውስጤ የነበረውን ኩራት የማጋራው ሰው  ናፈቀኝ፡፡ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ሰው ማግኘት ፈለኩኝ፡፡ ገንዘብ ግን አልነበረኝም። ጋዜጣዬን ይዤ ተቀመጥኩኝ፡፡ እገልጠዋለሁ። አነበዋለሁ፡፡ ስሜ ከፅሁፉ በላይ አለ፡፡ ለልብ ወለዱ የካርቱን ስዕል ተስሎለታል፡፡ ትንግርት ሆነብኝ፡፡ በቀጣዩ ሳምንት የአጭር ልብ ወለድ እሩምታ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ለቀቅሁኝ፡፡ ግን ያስገባሁት አልወጣም፡፡ ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ የማርቲን ኤደን ዕጣ ፈንታ በእኔ የመጀመሪያ ስኬት ተሽሯል፡፡
ምናልባት ወጥ ልብ ወለድ ይሆናል የሚፈልጉት በሚል መፃፍ ጀመርኩኝ፡፡ ግን መፃፍ ስጀምር… የልብ ወለዶቹ አቅጣጫ አዲስነት፣ በጋዜጣ ከማውጣት ስኬት በላይ ይማርከኝ ጀመር፡፡… የጥበብ ጓደኞቼም ሙከራዎቼን ክበው/ከምረው በራስ መተማመን አሳበጡኝ፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት አጭር ልብ ወለድና አንድ መጣጥፍ መፃፍ አለብኝ ብዬ ወሰንኩኝ፡፡ አንዳንዴ ግን ከውሳኔዬ በላይ የምጽፍበትም ጊዜ ነበር፡፡….
ይህ አመት ለእኔ ድምፄን ያገኘሁበት አመት ነው ብዬ ስለማስበው…. ትቶብኝ የሄደው ብርሀናማ ትዝታ ተራ ቦታ የሚሰጠው አይደለም፡፡ ግን ይኼ አመት እኔ የድርሰት ድምፄን ያገኘሁበት ነበር ብልም… በሀገሪቷ ታሪክ ግን አስገራሚ ቁጥር ያለው ህዝብ ድምፁን ለምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥቶ የተነጠቀበት ተብሎ የሚታወስ ታሪካዊ አመት ነው። ዓመቱ 1997 ነበር፡፡  
የፖለቲካ ውዝግቡ ሳይረብሸኝ መሰረታዊ ብዬ የማስባቸውን የልብ ወለድ ንድፎች የፃፍኩበት ወቅት ነበር፡፡ 97 ለመላው ኢትዮጵያ ሌላ ትዝታ ቢኖረውም፤ ለእኔ ግን ‹‹የንፋስ ህልም እና ሌሎች የምናብ ታሪኮች›› የሚለውን ከ97 አምስት አመታት በኋላ ያሳተምኩትን መፅሐፍ ጥንስስ ያቦካሁበት ልዩ አመት ነበር፡፡
ታዲያ አሁን ይኼንን ታሪክ ለምን ልብ ወለድ አስመስዬ ፃፍኩት? ለብልሃቴ ብዬ ነው፡፡ ‹‹የንፋስ ህልም›› በድጋሚ ታትሞ ገበያ ላይ ለመውጣት ዝግጅቱ ጦፏል፡፡ ይሄን መረጃ ለናንተ ለውድ አንባብያን ለመጠቆም የዘየድኩት መላ ነው፡፡ መፅሐፉን ማንበብ ከመፅሐፉ ጀርባ ያለውን ታሪክ አይነግርም፡፡
(በፊልም The making of the film እንደሚሉት መሰለኝ) እኔ ግን ‹‹የንፋስ ህልም›› አፃፃፍን ከፅሁፉ ነጥሎ መደበቅ ንፉግነት ስለመሰለኝ እነሆ ብያለሁኝ። መጽሐፉ እስኪወጣም መዳረሻ ይሆናችኋለሁ፡፡

Read 1927 times