Sunday, 09 October 2016 00:00

ለፖለቲካዊ ችግሮች - ፖለቲካዊ ውይይት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

በአገሪቱ ለተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምሁራን፣ፖለቲከኞች፣ ዕውቅ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች የመፍትሄ ሃሳብ የሚሉትን መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሃሳባቸው ጆሮ አግኝቷል ወይ ለሚለው እርግጠኛ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ውጤቱን በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የመፍትሄ ሃሳቦቹ ቀውሱ እልባት እስኪያገኝ ድረስ መቀጠል አለባቸው፡፡ መንግስት በአዲሱ ዓመት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት በመጀመር፣ሰላምና መረጋጋት ያሰፍናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህላችንም እንደሚጎለብት እምነታችን ጽኑ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ለዛሬ የፖለቲከኞችን እንዲሁም ምሁራንን አስተያየት አጠናቅሯል፡፡
የዚህ ውይይት ዓላማ፣ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሸራሸር መፍትሄ ማፈላለግና መጠቆም ነው፡፡ በአገራችን ለተከሰተው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ወይም አስተያየት አለን ለምትሉ ወገኖች መድረኩ ሁሌም ክፍት ነው፡፡

“ጥልቅ ውይይት ቁጣን ያስተነፍሳል”

ተሻገር ሺፈራው

እኔ አስተያየቴን የምሰጠው፣ ከሙያዬ አኳያ የግሌን አስተሳሰብ ነው፡፡ በሌላ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችም እንዲሁ ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ እንደየሙያቸው ሊመለከቱት ይችላሉ። በአገራችንም ሆነ በውጭው ዓለም ህዝቡ የሚጠቀምባቸው የመገናኛ ብዙኃን አሉ፡፡ እነዚህ የመገናኛ ብዙኃን የሰከነ የውይይት መድረክ ለመሆን መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ጊዜው ስጋትና አለመረጋጋት የሰፈነበት ስለሆነ፣ ይህንን ተከትሎ ስሜታዊና ነገሩን የሚያባብስ ዘገባ ለመስራት የሚያነሳሳ ሁኔታ አለ። ነገር ግን በተቻለ መጠን በሳልና የሰከኑ ዘገባዎችን ለህዝቡ ማቅረብ ይገባል፡፡ ስሜት ቀስቃሽና ቁጣ የሚያነሳሱ መሆን የለባቸውም፡፡ ዘገባዎቹ ሰዎች ማሰብና መወያየት፣ ከስጋቶቹ በስተጀርባ ሊመጡ የሚችሉ ነገሮችን መገመትና ራሳቸውን በሰከነ ሁኔታ መምራት እንዲችሉ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መገናኛ ብዙኃን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ማወያየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገሮችን ከመሸፋፈን ይልቅ ግልፅ አውጥቶ፣ በስፋትና በሰከነ ሁኔታ መወያየት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። እንዲህ ዓይነት ውይይቶች ሲካሄዱ ወደ ቁጣ፣ ረብሻና ጥቃት የሚወስደንን መንገድ እንዘጋዋለን፡፡ ውይይት የችግሮች ሁሉ መፍትሄ ነውና፡፡
አቅምና ጉልበት ያላቸው ወገኖች፣የውይይት በር መዝጋት የለባቸውም፡፡ አቅም ያላቸው ስል … ህብረተሰቡን አንቀሳቅሰው፣‹‹እንዲህ አድርግ፤ እንዲያ አታድርግ›› ብለው ማዘዝ የሚችሉ ማለቴ ነው፡፡ ህዝብን ማንቀሳቀስና መምራት ቀላል አቅም አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግስት ቁሳዊ ሀይል አለው፤ነገር ግን ያንን ቁሳዊ ሀይል ከመጠቀም ይልቅ የማሳመንና ችግሩን የመፍታት አቅሙን ይበልጥ አጠንክሮ መሄድ ነው ያለበት፡፡ የመለወጥና የመታደሱን ነገር፣ ከንግግር ባለፈ ተግባራዊ አድርጎ፣ ህዝቡ በሚፈልገው መጠንና ደረጃ ላይ መገኘት አለበት፡፡ ያን ጊዜ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ቁጣ መቀልበስ ይቻላል፡፡ ይሄ ሁሉ ግን የሚከናወነው ከውይይቱ ጎን ለጎን መሆን አለበት፡፡ ውይይቱ ይካሄዳል፤መቀየር ያለባቸው ነገሮችም አብረው ይቀየራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
የህዝባዊ ቁጣው መነሻ እንደሚመስለኝ፣ለብዙ ጊዜ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ክምችት ውጤት ነው። ጠቅለል ባለ መልኩም እንዳየነው፤ መንግስትም እንዳመነው፤ የመልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲ እጦትና ሌሎችም የመብት ጥያቄዎች ለቁጣ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ያሉ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን፣ህዝብ መናገር የሚፈልገውን ያህል የሚያናግሩ አይደሉም፡፡ የሚጠበቅባቸውን እያደረጉ ባለመሆኑም፣የህዝቡን ድምፅ ማሰማት አልቻሉም፡፡ ቁጣ የሚመነጨው ደግሞ ከመታፈን ነው፡፡ ህብረተሰቡ ግልፅ ውይይት እንዲያደርግ፣ ሀሳቡን በነፃነት እንዲያንሸራሽር መንግስት ዕድሉን ሊያመቻችለት ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ነውጥና ቁጣ ሊበርድ ይችላል፡፡ ሁለተኛው ነገር ተቃውሞና ቁጣ በሚነሳበት ሰዓት፣ መንግስት የሃይል እርምጃ መውሰድ የለበትም፡፡ ሰዎች ከህግና ከፍርድ ውጭ የሚገደሉበት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም። በሌላ በኩል የህዝብ ተቃውሞም ቢሆን ጥፋት የተቀላቀለበት ከሆነ በእኔ እምነት ተቀባይነት የለውም፡፡ አገርን፣ ሀብትንና ንብረትን ወደ ማፍረስ የሚያዘነብል ነውጥ፣ ምንም ትርፍ የለውም፡፡ ከዚህ አንጻር ተቃውሞና አመጽ የሚመሩ ወገኖች ጉዳዩን በጥሞና ሊያዩት ይገባል፡፡
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፤ መገናኛ ብዙኃን ህዝቡ እንዲወያይና ሀሳቡን እንዲገልፅ በቂ ዕድል ስላልሰጡት፣ አሁን ማህበራዊ ሚዲያዎች፡- እነ ፌስ ቡክ፣ ቲወተርና መሰል ሶሻል ሚዲያዎች አማራጭ መተንፈሻዎች ሆነው ህዝቡን ማንቀሳቀስ ችለዋል። ቀደም ባለው ጊዜ ማለትም ከኢንተርኔት ዘመን በፊት፣ በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን መወያየት ሳይቻል ሲቀር የውስጥ ለውስጥ ድብቅ የጋዜጣ ዝውውሮች ነበሩ፡፡ በእነዚህ የውስጥ ለውስጥ ጋዜጦች የተለያዩ ወገኖችን የማወያየት ስራ በድብቅ ይሰሩ ነበር። አሁን ግን ዘመኑ (ቴክኖሎጂው) ያንን ችግር በእጅጉ ቀርፎታል፡፡ አሁንም መደበኛ መገናኛ ብዙኃን ይህን ማድረግ ሲያቅታቸው፣ ኢ-መደበኛ ወደሆነው (አሁን መደበኛ እየሆነ ነው) በመሄድ ህዝቡ እንደ ልቡ ይወያያል ይነጋገራል፡፡ ይህ ዘመኑ የፈጠረለት አማራጭ ነው፡፡ ሶሻል ሚዲያው ታዲያ ከመገናኛ ብዙኃንነቱ ባለፈ እንደ ሚያስተላልፈው መልዕክትና ይዘት፣ ወደ ነውጥ ሊያመራ የሚችል እንቅስቃሴም ይፈጥራል። ይህ ማለት ከፍተኛ አቅም አለው ማለት ነው፡፡
ይህ እንዳይሆን የህዝብ ጥያቄዎች በግልፅ በአደባባይ እየወጡ መነገር አለባቸው፤ ሁሉም ነገር ለውይይት ከፍት መሆን አለበት። ያለምንም ጥርጥር ውይይት ቁጣን ያስተነፍሳል። ውይይቱን ተከትሎ ግን ተግባራዊ ለውጥ መምጣት አለበት። የኮሙኒኬሽን ስራና ከፍተኛ ውይይት ማድረግ ለወቅቱ የአገሪቱ ችግር አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

==================================

“ለምንድን ነው ለህዝብ እድል የማይሰጠው?”
አያልነህ ሙላት (ደራሲና ጸሃፌ-ተውኔት)

ይህን ሃሳብ የማቀርበው ማንንም ሳይሆን ራሴን ብቻ ወክዬ ነው፡፡ ችግሩ ምንም የሚያጠራጥር ነገር አይደለም፤ በህዝብና በመንግስት መካከል የተፈጠረ ነው፡፡ በህዝብና በመንግስት መካከል የተፈጠረን ችግር፣መንግስት አስታራቂ ሆኖ፣ራሱ ሊሸመግል የሚችልበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ቅራኔው በሁለቱ መካከል ነው፡፡ እንደኔ፣ ቅራኔውን ሊፈታ የሚችለው ህዝቡ ራሱ ይመስለኛል፡፡ ህዝብ በኢትዮጵያ ባህል ውስጥ ለዘመናት የተቃረኑ ችግሮችን ሲፈታ የኖረ ነው፡፡ የአካባቢ ሽማግሌ እያለ የተፈጠሩ ችግሮችን በሙሉ ሲፈታ የኖረ ነው። አሁንም ይሄ እድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ መንግስት ከጣልቃ ገብነት ታቅቦ፣ ችግሮቹን ራሳችሁ ፍቱ ቢል፣ መፍትሄውን አቅርቦ ችግሩን ሊፈታ የሚችል፣ የበቃ ህዝብ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይሄን ችግር ምሁራን ብቻቸውን ሊፈቱት አይችሉም፡፡ የኛ ምሁራን ከራሴ ጀምሮ የተቃኘነው በአውሮፓ ስርአተ ትምህርት ነው፡፡ ይሄ ስርአተ ትምህርት ደግሞ ከኢትዮጵያ ባህል ጋር አላገናኘንም፤ነጥሎን ነው የኖረው፡፡ የኛ ባህል ወዲያ ማዶ፣ህብረተሰቡ ያለው ወዲህ ማዶ ነው፡፡ የምናገለግለው ላስተማረን ፈረንጅ እንጂ ህብረተሰባችንን አናውቀውም። ብናውቀው ኖሮ 5 ሺህ ዓመት የታረሰበትን ማረሻ፣ ዘመናዊ እናደርግ ነበረ፡፡
 ዛሬ እኔ አያልነህ ሙላት፣ ስለ ታላላቅ የአውሮፓ ደራሲያን አመት ሁለት ዓመት የማስተምር ሰው፣ስለ እማሆይ ገላነሽ ሁለት ደቂቃ ንግግር አድርግ ብባል አልችልም፡፡ እኔ ነኝ ታዲያ የዚህን ህዝብ ችግር ልፈታ የምችለው? ህዝቡን ሳላውቀው፣ ችግሩን ሳላጠና፣ ከህዝቡ ተምሬ መልሼ ሳላስተምረው፣ በምን መልኩ ነው መፍትሄ የምሰጠው? ችግሩስ የሚገባኝ? ስለዚህ መፍትሄው የሚገኘው ከህዝቡ ነው፡፡ መንግስት ከዚህ ውስጥ እጁን ማውጣት አለበት፡፡ ከራሱ ካድሬዎችም መፍትሄ ከማፈላለግ ይታቀብ። ግን ለምንድን ነው ለህዝቡ እድል የማይሰጠው? ለምንድን ነው ህዝቡ እንዲህ የሚፈራው? ለምንድን ነው  እንደፈለገ የመናገር ነፃነት አግኝቶ፣ እንዲወያይ የማይደረገው?
 ኢሬቻ በዓል ላይ የታየውም ይሄው ነው፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ከህዝቡ በስተቀር ማንም የመንግስት ተወካይ ወይም ሌላ አካል መገኘት አልነበረበትም፡፡ ህዝቡ ነፃነቱ ቢሰጠው ኖሮ፣ ችግሩ ይፈጠራል ብዬ አላምንም፡፡

===============================


“ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ መንግስት መቀጠል አይችልም”
ሀብታሙ አያሌው (ፖለቲከኛ)

እነዚህ በህዝቡ ጎልተው ፊት ለፊት የወጡት አጀንዳዎች የመነሻ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ዋናው መሰረታዊው ነገር፣ህዝቡ ግልፅ የሆነ ስርአተ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋል፡፡ ዋናው ጥያቄ ይሄ ነው። ከዚህ በኋላ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ መንግስት መቀጠል አይችልም፤ የስርአት ለውጥ መምጣት አለበት የሚል ጥያቄ ነው የተነሳው፡፡ መንግስት ራሱ እንዳመነው፤ በ25 ዓመታት ውስጥ መልካም አስተዳደር ማምጣት አልቻለም፡፡ በ25 ዓመታት ውስጥ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ኖሮ፣ህዝቡ እኩል ተጠቃሚ መሆን አልቻለም፡፡ በትምህርት ተደራሽነት፣ በመሰረተ ልማት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ያሉ ችግሮች የታወቁ ናቸው፡፡ ጥቂቶች በሙስና ሰማይ ጠቀስ ፎቅ እሚሰሩበት ሀገር ሆኗል፡፡ የህዝቡ ጥያቄ እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች የያዘ፣ የስርአት ለውጥ ጥያቄ ነው፡፡
ነገር ግን መነሻ ምክንያት ያስፈልግ ነበርና፤ለአማራ ክልል - ወልቃይት፣ ለኦሮሚያ ክልል ደግሞ ማስተር ፕላን ሆነ፡፡ ከወልቃይት በፊት የቅማንት ህዝብ ጥያቄ ነበር፡፡ ቀጥሎ የወልቃይት ጥያቄ ወደ መድረኩ መጣ። የወልቃይት ጥያቄ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ በየአቅጣጫው ጥያቄው ነበር። በማያሻማ መንገድ ኢህአዴግ ከመግባቱ በፊት ወልቃይት ከጎንደር ጋር የቆየ ስለመሆኑ የታሪክ እውነታዎች ያስረዳሉ። ድንበሩ ተከዜ ነው ተብሎ በታሪክ ተመዝግቧል። ህውሓት ደግሞ ወልቃይትን በትግል ሳለ ለሁለት አላማዎች ይፈልገው ነበር። አንደኛ፤ የትግራይ ክልል በትግሉ ወቅት የመሬት እጥረት ስለነበረበት፣  ቦታውን ወታደሩን ለማስፈሪያነት ተጠቀሙበት፡፡ 30ሺህ ወታደር ነው ያሰፈሩበት፡፡ በ1981 ህውሓት በትግራይ የመሬት ስሪት ክፍፍል ሲያደርግ፣ ከ18 ዓመት ዕድሜ በላይ ለሆኑ መሬት ሲያከፋፍል ነበር፡፡ በ1983 ደግሞ ከ16 ዓመት በላይ የሆነውም ተሰጥቶታል፡፡ በትግሉ ወቅት ይዘውት የመጡትን ወታደሮችስ የት ያድርጉ? ለዚህ ነው ወልቃይት ላይ ወታደሮችን ያሰፈሩት። ወታደሮቹ ከሰፈሩ በኋላ ብዙዎቹ ትግርኛ ተናጋሪ ስለሆኑ፣ መሬቱም ለኛ ይገባል በማለት የሆነው ሆኗል። በትግሉ ወቅትም ወደ ሱዳን ለመውጣት ወልቃይት ወሳኝ ቦታ ነበር፡፡ ከእነዚህ የፖለቲካ አላማዎች አንጻር ነው ወልቃይት ወደ ትግራይ የተጠቃለለው፡፡
25 ዓመት የት ነበሩና ነው ዛሬ ጥያቄ የሚያነሱት? ይባላል፡፡ እኔ እስከምረዳው፣ባለፉት 25 ዓመታት በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይቀርቡ ነበር፡፡ ጠያቂዎቹ ብዙ መከራና ስቃይ ሲደርስባቸው ነበር፡፡ ሌላው በጣም አስገራሚው ነገር ከወልቃይትም አልፈው አንድ ግጨው የምትባል አነስተኛ ወረዳ አለች፡፡ ህውሓት ይህቺን ወረዳ ለመውሰድ ሲዳዳው ነው በህዝቡ ውስጥ ሲብሰለሰል የነበረው ጥያቄ እየሰፋ የመጣው፡፡ ህውሓት እስከ ቤኒሻንጉል ድረስ በርካታ የመስፋፋት ሰፈራዎችን አከናውኗል፡፡ ከዚህ በመነሳት የህውሓት የመስፋፋት ዘመቻ የፈጠረው ችግር ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ኦሮሚያ ላይ ያለው የህዝብ ጥያቄ አሻሚ አይደለም፡፡ ከቀዬአቸው ተነስተው የት እንደደረሱ የማይታወቁ ብዙ የኦሮሞ ገበሬዎች አሉ፡፡ ይሄ ችግር የመነጨው ከመሬት ፖሊሲው ነው፡፡ ግለሰቦች መሬቱ የነሱ ቢሆን በሚያዋጣቸው ዋጋ፣ ከገዥው ጋር ተደራድረው፣ በሚጠቅማቸው መንገድ መሸጥ ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን መሬት የመንግስት ነው በሚለው ፖሊሲ፣ ገበሬው እዚህ ግባ በማይባል ካሳ ከቀዬው ይፈናቀላል፡፡ መንግስት ከገበሬው በካሬ ሜትር 10 ብር የገዛውን፣ በካሬ ሜትር 5 ሺህና 6 ሺህ ብር ይሸጠዋል፡፡ መንግስት ያለ አግባብ የነጋዴ ቅርጽ በመያዙ የኦሮሞ አርሶ አደር ተጎድቷል፣ማህበራዊ ትስስሩ አደጋ ላይ ወድቋል፤የሚል አቤቱታ በየጊዜው ይቀርብ ነበር፡፡ አንድ ከተማ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ሊሰፋ ይችላል ነገር ግን በሚስፋፋበት ቦታ ያለው ማህበረሰብ ማን ነው? ከቦታው ጋር ያላቸው ቁርኝት ምንድን ነው? የሚለው መታየት ነበረበት፡፡
ኢህአዴግ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ሲመጣ አንድ መመሪያ ነበር። መመሪያውን ፈጥነው አጥፍተውታል፡፡ መመሪያው፤ ለምሳሌ ከካሳንችስ የሚነሳ ሰው ቢበዛ ከ1.5 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ አይሄድም ይላል፡፡ እዚያው በለመደው አካባቢ እንዲቀመጥ ነበር  ዓላማው፡፡ ነገር ግን በ1997 ከፍተኛ ማኅበራዊ ትስስር ያለው የአዲስ አበባ ሁኔታ ስላሰጋቸው፣ ኮንደሚኒየም ግንባታ በሚል ይሄን መመሪያ አጥፍተው፣ ህዝቡን አሁን ባለው መልኩ በታትነውታል፡፡ ኦሮሚያ ላይ የአርሶ አደሮቹ ጉዳይም ከዚህ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ለችግሩ ተገቢ ምላሽ አለመስጠታቸው ሲብላላ የነበረ ጥያቄ፣ ምክንያት ይዞ እንዲፈነዳ ሆኗል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ ህዝብ ብሶቱን በተቃውሞ ሲገልጽ፣ መንግስት አግባብ ያለው ምላሽ እንደ መስጠት ሃይል ተጠቀመ፡፡ የሃይል አማራጭ ደግሞ መቼም መፍትሄ አይሆንም፡፡ በዚህ መንገድ ተቃውሞን ዝም ማሰኘት ቢቻል እንኳ ህዝብና መንግስት አብረው እየኖሩ ነው አያስብልም። የሚሻለው መንገድ አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦች በመቀየስ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ነበር፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ይሄን ማድረግ አልቻለም። ብዙ ሰው ሞቷል፤ ቆስሏል፡፡ በኢሬቻ በአልም አስከፊ እልቂት ደርሷል፡፡ ህዝቡ ለምን ተቃወመ በሚል፣በሚሊዮን በሚቆጠር ህዝብ መሃል፣ ያውም መንቀሳቀሻ በሌለበት ገደላማ ቦታ፣አስለቃሽ ጭስ መተኮስ አልነበረበትም፡፡
ለችግሮቹ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የፖለቲካ ለውጥ ነው፡፡ ማርሽ መቀየር አለበት፡፡ በመጀመሪያው ማርሽ መሄድ አይቻልም፡፡ ህዝብ ለመወያየት እንዲችል መድረኮች ክፍት መሆን አለባቸው፡፡ መንግስት ወታደሮቹን እያሠማራ፤ ህዝብም ወደ አደባባይ እየወጣ ብሶቱን በገለጸ ቁጥር፣ በህዝቡና በመንግስት መካከል ያለው ቅራኔ እጅግ እየሰፈ ይሄዳል፡፡ ጉልበት መፍትሄ አይሆንም፡፡ የህዝብን የስልጣን ሉአላዊ መብት ማክበር ነው መፍትሄው። መጀመሪያ አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ችግሩ የራሳችን ነው” ብለው የኦሮሞን ህዝብ ይቅርታ እስከ መጠየቅ ሲደርሱ፣ ጥሩ ለውጥ ሊመጣ ነው ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ውሎ ሳያድር ግን የፀጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃ እንዲወስዱ ማዘዛቸውን ተናገሩ፡፡ ይሄ እጅግ ተቃራኒ የሆነ ነገር ነው፡፡ ኢህአዴግ ሌላው ቀርቶ የኮንሶን የ“ዞን እንሁን” ጥያቄን እንኳ በአግባቡ መፍታት ያልቻለ ድርጅት ነው፡፡ ሃገሪቱ በእውነቱ አደገኛ ሁኔታ ላይ ነች፡፡ ምክክር በእጅጉ ያስፈልጋል። ውይይት መጀመር አለበት፡፡
አለበለዚያ አደጋው ከፊታችን ነው ያለው፡፡ የኢህአዴግ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ባይፈቅድም፣ “ስልጣን እለቃለሁ” እስከ ማለት መድረስ አለበት፡፡ “የህውሓት የበላይነት ይቁም” የሚለው ጥያቄ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፡፡ በፖለቲካው፣ በፀጥታው ዘርፍ፣ በመከላከያው፣ በኢኮኖሚው የህወሓት የበላይነት በግልጽ ይታያል፡፡ መፍትሄው ፖለቲካዊ ንግግርና ውይይት መጀመር ነው፡፡


==============================

“መፍትሄው ሥልጣን ለህዝቡ መመለስ ነው”

አቶ ተማም አባቡልጋ (የህግ ባለሙያ)


በአማራም በኦሮምያም በሌሎች አካባቢዎችም ያሉ ተቃውሞዎችና ግጭቶች መነሻ ምክንያታቸው በህገ መንግስቱ ላይ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ይላል፡፡ (አንቀፅ 8) ይሄ ወደ ተግባር አለመቀየሩ ነው፡፡ ህዝቡ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ ያለመከበሩ፤ የስልጣን ምንጭ ያለመሆኑ፣ በአጠቃላይ ህዝቡ በህገ መንግስቱ የተሰጠውን የስልጣን ባለቤትነት በተግባር ማጣቱ የፈጠረው ችግር ነው፡፡
መንግስት ደግሞ ለነዚህ ችግሮች የሚሰጣቸው ምላሾች፣የበለጠ ከመፍትሄው የሚያርቁና ነገሩን የሚያባብሱ ናቸው፡፡ 25 ዓመት ሙሉ ያየነው ሃቅ፣ ኢህአዴግ ለችግሮች ሁነኛ መፍትሄ የሚሰጥ ድርጅት አለመሆኑንና ችግርን በችግር የሚያጠፋ ድርጅት መሆኑን ነው፡፡ እሳትን በጭድ የሚያጠፋ ድርጅት ነው፡፡ አሁን እየወሰደ ያለው እርምጃም ለዚህ ምስክር ነው፡፡  እንደውም ፍፁም ከመፍትሄው የሚያርቅና ራሱን የመግደያ መንገድ ላይ ያለ ይመስለኛል። ሀገሪቷን በእውቀትና በእውነት መምራት ሁነኛ መፍትሄ ነው። ሀገሪቷ የምትመራው ግን በሙከራ ነው፡፡ አሁን የሚያዋጣው እውነቱን መነጋገር ነው። እስካሁን የተሄደበት መንገድ አላዋጣም ተብሎ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ተደርሷል፡፡
ከዚህ በኋላ ወዴትም መሄድ ስለማይቻል፣ ወደ እውነቱ መመለስ ነው የሚያዋጣው፡፡
“ሀ” ብሎ 1983 ዓ.ም ከነበረበት ቦታ ተመልሶ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ እውነተኛውን የስልጣን ባለቤትነት ለህዝብ መልሶ፣ እንደ አንድ በሀገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ድርጅት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚወዳደርበትን ሁኔታ ፈጥሮ፣ በተግባር ሀገሪቱን ለህዝቡ መመለስና የህዝቡን ውሳኔ መስማት ነው መፍትሄው፡፡
ከዚህ በኋላ ወዴትም መሄድ የሚቻል አይመስለኝም (dead end) የመስመሩ ማለቂያ ላይ ነው ያለው። ወዴትም መመለስ አይቻልም፤ ወደ ኋላ ካልሆነ በስተቀር፡፡


=============================

“ለኢህአዴግ ዋስትና ሰጥተን ስልጣን መልቀቅ አለበት”

ዳንኤል ሺበሺ (ፖለቲከኛ)


ህዝባዊ እንቅስቃሴዎቹ ጠንካራና ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ተማሪውም ገበሬውም ሌላውም የተሳተፈበት በመሆኑ በይዘቱ ጥልቀት ያለው ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ በአንፃሩ ከቻርተሩ ጊዜ ጀምሮ ህዝብ ያላመነበትን ነገር እየፈጠረ፣ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አለመግባባቱ ነበር፡፡ ሥልጣን ላይ የቆየው በጉልበት ነው የቆየው፡፡ ለህዝብ ተቃውሞ መቀስቀስ መንስኤው፡- ጭቆና፣ አምባገነንነት፣ አድሎና ሙስና ነው፡፡ ህዝብ ያላመነበትንና ያልመከረበትን እንዲሁም የጋራ መግባባት ያልተደረሰበትን ነገር በሃይል ሲተገበር ነው የከረመው፡፡ ይሄ ደግሞ እንደማያዋጣ ስናሳስብና ስናስጠነቅቅ ነበር፡፡ የተቃውሞ ድምጾችን ሳይሰማ በመቅረቱና ጭቆናው፣ ሙስናውና በደሉ በመባባሱ ነው፡፡ መንግስት በአንፃሩ እየወሰደ ያለው የመፍትሄ እርምጃ፣ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ አይነት ነው፡፡ መድሐኒቱ ሌላ በሽታው ሌላ እንደ ማለት፡፡ ፈፅሞ ከችግሩ ጋር አይገናኝም፡፡ መንግስት በ100 ፐርሰንት ድምጽ ተመርጫለሁ ባለ ማግስት ነው ተቃውሞው የተቀሰቀሰው፡፡
አንድ ሰው ከአንድ ማህበረሰብ ከተገደለ ህብረተሰቡ ያኮርፋል፡፡ የግድያ መፍትሄ፣ ይሄ ነው ችግሩ፡፡ ሃይል በየትኛውም ሃገር ውጤት አምጥቶ አያውደቅም። ከድጡ ወደ ማጡ ነው የሚወስደው። ኢህአዴግ የሲዲ ማጫወቻውን መቀየር አለበት። ህዳሴ ብለው እስካሁን ምንም ያደረጉት ነገር የለም። ስለዚህ ይሄ መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም። ብዙ ሰዎች የሽግግር መንግስት ወይም የአደራ መንግስት ይቋቋም፣ ድርድር ይካሄድ ይላሉ፡፡ እኔ መነጋገሩና መደራደሩ ላይ ችግር የለብኝም፤ ግን መደራደር ያለብን ከኢህአዴግ ጋር ለመቀጠል አይደለም፡፡ አነሰም በዛ ኢህአዴግ ባለፉት 25 አመታት፣ ብዙ ጥሩም መጥፎም ነገር ሰርቷል፡፡ ስለዚህ ይሄን እውቅና ሰጥተን፣ ዋስትና መስጠት አለብን፡፡ ላካበቱት ሃብት ሁሉ ዋስትና ሰጥተን መነጋገር አለብን። ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ ስልጣን በአግባቡ መልቀቅና ስልጣን ይገባናል ያሉ ሰዎች ተወያይተው እንደረከቡ ማድረግ አለበት። ኢህአዴግ ምንም አይነት ተሃድሶ ቢያደርግ ውጤት ሊመጣ አይችልም፡፡ ዋስትና አግኝቶ መልቀቅ አለበት፡፡

===============================

“ተቃዋሚ መሆን ወንጀል መምሰል የለበትም”

አቡበከር አለሙ
(የቀድሞ “የሙስሊሞች ጉዳይ” መፅሄት አምደኛ)

እንደሚታወቀው ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ገጥሞን በማያውቅ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግስትም ያለውን ችግር በተወሰነ ደረጃ አምኗል፡፡ ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ኢትዮጵያ ሀገራችን፣ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንዳለች ይረዳል፡፡ ይሄ ሁኔታ  ተባብሶና ስር ሰዶ ከቀጠለ፣ ሀገራችንን የጥፋት አዘቅት ውስጥ የሚከት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ጊዜያት እንዳየነው፣ የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለሞቱት ወገኖቻችን የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን እገልፃለሁ፡፡
ይሄ ነገር ስር ሰዶ ወደሚፈራው ነገር እንዳያመራ፣አራት መፍትሄዎችን ልጠቁም እወዳለሁ፡፡ በሂደት የሚፈቱ ነገሮች እንዳሉ ሆኖ፣እነዚህ ግን አስቸኳይ መፍትሄዎች ናቸው። ባለው ህገ መንግስትና በህገ መንግስታዊ ስርአት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን፣ መፍትሄዎችን የግድ ማምጣት አለብን፡፡ ይሄን መፍትሄም በዋናነት ማምጣት የሚችለው ሀገሪቱን እየመራ ያለው ኢህአዴግ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ፈረንጆቹ፤ The ball is on your hand እንደሚሉት፣ በዋናነት የመንግስት ሥራ ነው፡፡  
በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉንም ወገን ያካተተ ብሄራዊ እርቀ ሰላም ማውረድ ያስፈልጋል፡፡  መንግስት በአዋጅ ደረጃ ይሄን ጥሪ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ማቅረብ አለበት፡፡ ሀገሪቱ የሁላችንም ነች፤ ሰላሟና ደህንነቷ ተጠብቆ ፣የጀመረችው ልማት እንዲቀጥል ከተፈለገ መንግስት የእርቀ ሰላም መድረክ ማመቻቸቱ የበለጠ ተጠቃሚ ያደርገናል፡፡ ነገሮችም ተባብሰው አቅጣጫ አይስቱም፡፡ ስለዚህ መንግስት ሆደ ሰፊ ሆኖ መስራት አለበት፡፡ የሀገርን የግዛት አንድነት የመጠበቅ ኃላፊነት በመንግስት እጅ እንደመሆኑም፣ ተነሳሽነቱን መውሰዱ ተገቢነት አለው፡፡ ይሄ ጉዳይ ከበፊትም ጀምሮ ብዙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሲጠይቁት የነበረ ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የበለጠ እንዲከበርና ስር እንዲሰድ ከማድረግ ባልተናነሰ፣ የጋራ እሴት የሆነው ኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲጎለብትና እውነተኛ ቦታውን እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ህገ መንግስቱ የስልጣን ባለቤት የሚያደርገው ብሄር ብሄረሰቦችን ነው፡፡ ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መደረጉ ተገቢ ነው፤የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የፌደራል ስርአቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የዘጠኙ ክልሎች ብሄሮች እውነተኛ ስልጣን ኖሯቸው፣ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ልዩነትን ልንክድ አንችልም፤ ያለና የሚኖር ነው። ያኔ ከነበሩ ትውልዶች ጀምሮ የተነሳ ጉዳይ ነው። ይሄ የሚካድ አይደለም፡፡ የበለጠ ስር መስደድ ነው ያለበት፤ ሆኖም ግን ከዚሁ ባልተናነሰ መልክ በጋራ እሴታችን፣ ኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ሊሰራ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲባል በነገስታቱና በደርግ ሞዴል ሳይሆን 21ኛውን ክ/ዘመን በሚመጥን መልክ መጎልበት አለበት፡፡ በንጉሱ ዘመን ኢትዮጵያዊነት በአንድ ወገን ነበር ሲቀነቀን የነበረው፡፡ የአንድ ብሄር የበላይነት፣ የአንድ ሃይማኖት የበላይነት ሲቀነቀን ነበር፡፡ ደርግ ደግሞ ሁሉንም የጨፈለቀ፣ብዝሃነትን የደፈጠጠ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን ክ/ዘመኑን የሚመጥን ደረጃ ላይ መድረስ አለብን፡፡
በሶስተኛ ደረጃ በነፃነት የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ በጥቅሉ በኢፌድሪ ህገ መንግስት የሠፈሩ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለ አንዳች መሸራረፍ መተግበር አለባቸው፡፡ ሰው የፈለገውን በነፃነት ይናገር፣ ይፃፍ፣ ይሰብሰብ፣ መሣሪያ እስካልታጠቀ ድረስ ሠላማዊ ሰልፍ እንደፈለገ ያድርግ፤ በቃ የተለመደ ነገር ይሁን፡፡ ይሄን ማድረግ አስፈሪ አይሁን፡፡ ሰው ለመናገር ከፈራ፣ እኔ አሁን በእናንተ ጋዜጣ ላይ ሃሳቤን በምገልጽበት ሰአት፣ መንግስት ምን ያደርገኛል ብዬ መፍራት የለብኝም። መናገር አስፈሪ ነገር አይሁን፤ መፃፍ አስፈሪ ነገር አይሁን፣ መሰብሰብና ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ አስፈሪ ነገር አይሁን፡፡ ህገ መንግስቱ ውስጥ የሠፈሩ እንደመሆናቸው፣ ያለመሸራረፍ በተግባር ይተርጎሙ። የህትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ለሁሉም ክፍት ይሁኑ፡፡ ኢቢሲም፣ አዲስ ዘመንም ሊሆን ይችላል፤ የህዝብ እንጂ የአንድ ወገን ሃሳብ አስተናባሪ ብቻ አይሁኑ፡፡ ይሄ በተግባር የሚገለጽ ከሆነ፣ ሃገሪቷን እንታደጋለን ብዬ አስባለሁ።
 በአራተኛ ደረጃ፣ መንግስት፤ ሰዎች ወደ አመፅና ረብሻ አንዳይሄዱ ከፈለገ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው የሰፋ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በቃ ተቃዋሚ መሆን ወንጀል መምሰል የለበትም፡፡ የአንድ መንግስት ተቀናቃኝ መሆን እንደ ወንጀል መታየቱ መቆም  አለበት፡፡ ሁከትና ረብሻ እንዳይኖር ሠላማዊ መድረኮች እስከ ጥግ መከፈት አለባቸው፡፡ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች የመጫወቻ ሜዳ ካላገኙ፣ ዜጎች ወደ ተስፋ መቁረጥ ሊሄዱ ይችላሉ። ያኔ አማራጩ አመፅ ይሆናል፡፡ ችግሮች የሚፈቱት በትጥቅ ትግል ነው ወደሚል አስተሳሰብ ሊገፉ ይችላሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ሃገራችን ሌላ አዙሪት ውስጥ የሚከት ነው፡፡
በቅርብ ያሉትን እነ ሶርያ፣ የመን፣ ሊቢያን አይተን አልቅሠን፣ አዝነን ተቆጭተን ሳናባራ፣ በሃገራችን ላይ እንዲደገም አንፈልግም፡፡ ማንም ጤናማ ህብረተሰብ ይሄን አይፈልግም፡፡ ይሄ ግን ባለመፈለግና በምኞት ብቻ ሳይሆን በድርድር፣ በውይይት፣ በመግባባት ብቻ ነው ማስቀረት የሚቻለው፡፡ መንግስት ከታጠቁም ካልታጠቁም ወገኖች ጋር እርቀ ሰላም እስካወረደ ድረስ ውይይት ቢኖር እፎይታ ይፈጥራል፡፡ ህዝቡም ከዚህ ውጭ የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ነገሮች ከተስተካከሉ ገበሬውም ወደ ግብርናው፣ ተማሪውም ወደ ትምህርቱ፣ ሰራተኛውም ወደ ስራው ነው የሚሄደው፡፡ ይሄ ካልሆነ ወደ ሁከትና ረብሻ መኬዱ አይቀርም፡፡ መንግስት አሁን የውጭ ኃይሎች እጃቸውን እንዳያስገቡ ስጋት ይኖረዋል፤ነገር ግን ይሄ እንዳይሆን ሰላማዊ መድረኮች መፈጠር አለባቸው፡፡
አሁን አየሩን ሞልቶ የምናየው ዘርና ብሄር ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ቅስቀሳ መቆም አለበት፡፡ ጤናማ አይደለም፡፡ ወደ ውድመትና እልቂት ነው የሚያደርሰን፡፡ መንግስታት ያልፋሉ፤ዘላለማዊ መንግስት የለም፤ከአላህ መንግስት በስተቀር፡፡ ዘላለማዊ ሊሆን የሚለው ህዝብና ሀገር ብቻ ነው። ስለዚህ የዘር ጥላቻ ቅስቀሳ መቆም አለበት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ስንባል በጥብቅ ትስስር ውስጥ የምንኖር ህዝቦች ነን፤ተገማምደናል ተዋልደናል። በጥብቅ ስብጥር ውስጥ ያለን ህዝቦች ስለሆንን ባህሪያችንም ለፀብ እድል አይሰጥም፡፡ ባለው የዘር ቅስቀሳ ወደ እርስ በእርስ ግጭት የሚገባ ከሆነ አላህ አይበለውና ከሩዋንዳም ልንብስ እንችላለን፡፡ ስለዚህ አሁኑኑ ዘረኝነት መቆም አለበት፡፡

Read 4699 times