Sunday, 09 October 2016 00:00

የዓለም አቀፍ ቅርሶች ምዝገባ ተውኔትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

Written by  ሰውየለም አገሬ
Rate this item
(10 votes)

     የቅርስ ጥናትና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 209/1992 በአንቀጽ 3፣ ንዑስ አንቀጽ 5 እንዳሰፈረው፣ ግዙፍነት የሌለው ቅርስ ማለት በእጅ ለመዳሰስ የሚያዳግት ነገር ግን በአይን ለማየት፣ በጆሮ ለመስማት የሚቻል፣ ልዩ ልዩ ትርኢትና ጨዋታ፣ ስነቃል፣ የሃይማኖት፣ የእምነት፣ የጋብቻ፣ የሀዘን ሥነሥርዓት፣ ሙዚቃ፣ ድራማና ሌሎች ተመሳሳይ ባህላዊ እሴቶች ፣ ወግና ልማድን የያዘ ቅርስ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 2003 በፀደቀው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን በአንቀጽ 2 መሠረት፣ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ማለት ማህበረሰቦች፣ ቡድኖች፣ በተወሰነ ደረጃ ግለሰቦች ባህላዊ ቅርሳቸው አድርገው የተቀበሏቸው ድርጊቶች፣ ውክልናዎች፣ መገለጫዎች፣ እውቀት፣ ክህሎት እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዙ መሣሪያዎች፣ ቁሶች፣ ደጥበባትና ባህላዊ ስፍራዎችን የሚያካትት ነው፡፡  ኮንቬንሽኑ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ፡-  ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ ማህበረሰቦችና ቡድኖች፣ ለአካባቢያዊ ሁኔታዎች ምላሽ ለመስጠት ከተፈጥሮና  ከታሪክ ጋር በሚያደርጉት መስተጋብር፣ በቋሚነት የተፈጠረ የማንነት ስሜትንና ቀጣይነትን የሚገልጽ፣ የብዝሀ ባህልና multicaultural የሰው ልጅ ፈጠራና ክብርን የሚያስተዋውቅ እንዲሁም ከዚህ ኮንቬንሽን አንፃር”ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር የማይፃረር የህዝቦች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች እርስ በርስ ተከባብረው የሚኖሩበትና ከዘላቂ ልማት ጋር የማይፃረር ነው” በማለት ሰፋ ያለ ፅንሰ ሀሳባዊ ግንዛቤ ሊያስጨብጥ የሚችል ትርጉም ሰጥቶታል፡፡
ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ፡- ማህበረሰቦች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ባህላቸው አድርገው የተቀበሏቸው ትግበራዎች፣ ውክልናዎች ፣ መገለጫዎች እውቀት፣ ክህሎት እንዲሁም ከእነዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሣሪያዎች፣ ቁሶች፣ እደጥበባትና ባህላዊ ሥፍራዎችን የሚያካትት ነው፡፡ ኢንታንጀብል የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ታንጀብል ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ተቃራኒ ሲሆን ትርጉሙም በመንካት፣ በመዳሰስ፣ በመጨበጥ ሊታወቅ ወይም ሊለይ የማይችል ማለት ነው፡፡
ወደ ተነሳሁበት የዓለም አቀፍ ቅርሶች ምዝገባ ተውኔትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ርእስ ልመለስ፡፡ ላለፉት አምስት ስድስት ዓመታት ማለትም የሐረር ጀጎል ግንብና የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዓለም መካነ ቅርስ World Heritage List  መመዝገብን ተከትሎ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃንና ቅርሶችን ለማስመዝገብ እንንቀሳቀሳለን በሚሉ  ክልሎች እጅግ የጦዘ የህዘብ ግንኙነት ስራ ከመሰራቱ ባሻገር፣ ሰሞኑን በብሄራዊ ደረጃ ያሉና የክልል መገናኛ ብዙኃን በእሬቻ ክብረ በዓል የተከሰተውን ሁነት ተከትሎ በተለያዩ መንገዶች የዓለም ቅርስ ምዝገባ ጉዳይ እጅግ በተጋነነ መልኩ ሲዘግቡ ተስተውሏል። የአዘጋገቡ ስርዓትም ፖለቲካዊ ቅኝት የተላበሰ ከመሆኑ ባሻገር የዓለም ቅርስ ምዝገባና ፖለቲካ በተለይ በኢትዮጵያ ፈር እየለቀቁ በመምጣታቸው ስርዓትና ደንብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የዓለም መካነ ቅርስ አመዘጋገብ የራሱ የሆነ ሂደት አለው፡፡ ቅርሶች በአካባቢ (region)  በአገር አቀፍ (National) ደረጃ ከወጣላቸው በኋላ የሚመዘገቡ ሲሆን በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፤ በየትም ዓለም የሌለ ዓለም አቀፍ ቅርሶችን በየዓመቱ እመዘግባለሁ የሚል ቡድን በማቋቋም በወቅታዊነት ሊሰራ የሚችለውን ስራ  ማለትም ካሉን ቅርሶች የተወሰኑት ብቻ ምናልባትም የዓለም አቀፍ ቅርስን መስፈርት አሟልተው ሊገቡ እንደሚችሉ እየታወቀ፣ ቋሚ የሆነ የስራ ክፍል በማቋቋም በ GTP ሰባት ቅርሶችን በዓለም መካነ ቅርሶች ውስጥ  አስመዘግባለሁ በማለት በዕቅድ ይዟል፡፡ የዚህ እቅድ ሃሳብ አመንጪዎች ሰባት አይደለም አንድ መካነ ቅርስ በዓለም የቅርስ ማህደር ውስጥ ለማስገባት የሚወስደውን ጊዜ ጠንቀቀው እያወቁ፣ ይህንን ዕቅድ ይዘው  ወደ ክልሎች በመሄድ ሁኔታው የተለየ መልክ እንዲይዝ አድርገዋል፡፡ የክልል ባለስልጣኖችም፤ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ዕቅድ በመጥቀስ፣ እነርሱም በተራቸው ለሚመሩት ህዝብ በ‹‹ዩኔስኮ እናስመዘግባለን›› እያሉ፣ ህዝቡ ቅርሱን ከራሱ ባህላዊ ፋይዳ አንፃር ሳይሆን ከዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ምዝገባ አንፃር እንዲመለከተው አድርገዋል፡፡ የዚህ አስቂኝ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ከሆኑት ሰዎች አንድ የሙያ ማህበር መሪ፣ ከሁለት ዓመት በፊት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ደደቢትን ሲጎበኙ፣ በቴሌቪዥን መስኮት፣ ‹‹ደደቢት በዓለም የቅርስ ማህደር እንዲመዘገብ እንሰራለን›› ሲሉ ተደምጠዋል። ‹‹የዓለም ቅርስ አስመዘግባለሁ›› የምትለዋ ያልተገባ ፖለቲካዊ ቃል  ህዝባችንን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰደው ከመሆኑ ባሻገር፣ የገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የህዝቡን ስስ ብልት ማማለያ ማድረጋቸው፣ ሃገሪቱን ብዙ ከማስከፈሉ በፊት እርምጃ መወሰድ ተገቢ ነው። በዓለም የቅርስ ማህደርነት የሚመዘገቡ ቅርሶች የሚገቡበት መንገድ የተለያየ ነው፡፡
እጅግ ውስብስብ የሆነው፣ ቅርስን በዓለም መካነ ቅርስ ማህደር World Heritage List  መዝገብ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ማህደር የተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች 9 ናቸው። ኮንሶ በዘጠነኛነት ሲመዘገብ ለማስመዝገብ የወሰደው ጊዜ፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ከ15 ዓመት በላይ ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሶበታል፡፡ የተመዘገበውም በማግባባት (lobby) ነው፡፡  ያ ሁሉ ልፋት ተለፍቶበትም የመመዝገብ እድሉ እጅግ የጠበበ ነበር፡፡ ይህንን እውነታ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ኃላፊዎች ሲናገሩ አይደመጥም። መካነ ቅርሶች ሊመዘገቡ የሚችሉት ዩኔስኮ ያስቀመጣቸውን 10 መስፈርቶች በሚገባ አሟልተው ሲገኙ እንጂ  ምሁራን ተሰባስበው እጅግ የረቀቀ ጥናት በማቅረባቸውም አይደለም፡፡ ቅርሶች በዓለም መካነ ቅርስ ማህደር ሊገቡ የሚችሉት አስሩ መስፈርቶች መሟላታቸውን ከዩኔስኮ በሚመጡ ባለሙያዎች ሲያረጋግጡ ብቻ ነው፡፡  ሌላው ቅርሶች የሚመዘገቡበት መስፈርት በዓለም ወካይ ቅርስ ማህደር (representation list) ነው፡፡ ይህ እጅግ በጣም ቀላል የሆነ፣ መጠይቅ (questionnaire) በመሙላት የሚሰራ ነው፡፡ በዚህ መዝገብ የሚሰፍሩ ቅርሶች ሊዳሰሱ የማይችሉ የሰው ልጅ ወካይ ቅርሶች ናቸው፡፡ ይህንን ቅፅ መሰረት በማድረግ፣ በአንድ አመት ውስጥ በዛ ያሉ ወካይ ቅርሶችን በዩኔስኮ የዓለም የቅርስ ማህደር እንዲመዘገቡ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በዚህ ሂደት ቅድሚያ አግኝቶ ወደ ዩኔስኮ የተላከው የኢትዮጵያ ቅርስ የኦሮሞ የገዳ ስርዓት ነበር፡፡ ገዳ ከአስር አመት በፊት ሰነዱ ተልኮ ለምን ሳይመዘገብ ቀርቶ እንደተመለሰ የክልሉ ባሀልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ጠንቀቀው የሚያውቁት ጉዳይ ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት፣ Ilmma Gatta ጥርስ አብቅሎ ስለሚወለድ ልጅ የተጠቀሰውና በገዳ የሴቶች ተሳትፎ እንደሌለ ተገልፆ ሰነዱ ለዩኔስኮ በመላኩ ነበር፡፡ ዩኔስኮም ሴቶችን የማያሳትፍ፣ ሕፃናትን የማያከብር ዲሞክራሲያዊ ሊያሰኘው አይችልም በሚል ሰነዱ ተመልሷል፡፡ የዚህን ሰነድ ከአስር አመት በፊት መመለስ አንዳቸውም የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስራ ኃላፊዎችም ሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትንፍሽ አላሉም፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም ይሁኑ የኦሮሞ ህዝብ ስለዚህ ሂደት አልተነገረውም። ከዓመታት ዝምታ በኋላ ገዳን የማስመዝገብ እንቅስቀሴ ተጀመረ፡፡ የሴቶች ውክልና ገዳ ውስጥ ስለመኖሩ፣ የአርሲ ሴቶች ሲንቄ እንዲካተት ተደረገ። ኢሬቻም የገዳ አንድ አካል ሆኖ ተካተተ፡፡ ኢሬቻ እንደ መስቀል በዓል አከባበር  በራሱ ቆሞ በዩኔስኮ መመዝገብ የሚችል፣ የኦሮሞ ማህበረሰብ በአደባባይ አምላክን የማመስገን ስርዓት (ritual festival) ነው፡፡ ሆኖም  የገዳ ስርዓትን ለማስመዝገብ ሲባል በአንድ ሰነድ ተካቷል፡፡ እንግዲህ ዩኔስኮ የቀረበለትን ሰነድ ገምግሞ፣ ውሳኔውን በቅርቡ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ ከውሳኔው በፊት ግን ፖለቲከኞች ከውስጥም ከውጭም እንዲንጫጩ በር የከፈቱት፣ የባህልን ስሱነት እየተገነዘቡ ህዝቡን ወደ አልተፈለገ ድምዳሜ እንዲደርስ እያደረጉ ያሉ መገናኛ ብዙሐን፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስራ ኃላፊዎች፣ ሃይ ሊባሉ የግድ ነው፡፡
የማይዳሰሱ ቅርሶች፤  የሰው ልጅ ከእለት ተእለት መስተጋብሩ በሚኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ የተወው የማንነቱ አሻራ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ እውቀት፣ እምነቶች፣ በእለት ተእለት እንቅስቃሴው የፈጠረው የስነጥበብ ውጤቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ናቸው፡፡ ቅርስ የሰው ልጅ  ኑሮውን ለመምራት የሚገለገልባቸውን ቋንቋዎች፣ ወኪሎች፣ የስነምግባር እሴቶች የሚያጠቃልል ሲሆን ባህላዊ ቅርስ ከህብረተሰብ ጋር በህብረ-ተዛምዶ የሚገለፅ ነው፡፡  ከህብረተሰቡ ውጭ ለብቻው የራሱን ህልውና ጠብቆ መኖር የሚችል አይደለም፡፡ ቅርስ  የአንድ ማህብረተሰብ ንብረትና መለያ፣ የማንነቱ አሻራ ያረፈበት መግለጫው፣ የአንድ ማህበረሰብ ድምር የተግባር ውጤት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ከህብረተሰቡ ጋር ለብዙ ሺህ ዓመታት አብረው የኖሩና የሚኖሩ፣ ያሉና የነበሩ፣ ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው፡፡ ዩኔስኮ ትናንት ስለተፈጠረ በዩኔስኮ ማህደር መመዝገባቸው ወይም አለመመዝገባቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ፋይዳ ከቶውንም ሊያደበዝዝ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ቅርሶቹ የተፈጠሩት ዩኔስኮ እንዲመዘግባቸው ተብሎ ሳይሆን ማህበረሰቡ ማንነቱን ሊገልፅበት፣ ሊኖርበት፣ ለትውልድም ለማስተላለፍ ስለሚፈልግ ነው፡፡ በዩኔስኮ ሰነድ ውስጥ ቅርሶችን ማስመዝገብ ማለት ‹‹የእኔ ቅርስ ዓለምአቀፋዊ ፋይዳ አለውና የዓለም ህብረተሰብ እያገዘኝ እንከባከበዋለሁ፤ እጠብቀዋለሁ፤›› የሚል ቅርሶችን በዓለም ህብረተሰብ ዘንድ ዕውቅና አሰጥቶ ‹‹ባጠፋው ብሰርዘው ባበላሸው የዓለም ህዝብ ይፍረድብኝ›› ከማለት የዘለለ ምንም ፋይዳና ትርጉም የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ባህል እንደ ሸቀጥ በቱሪዝም ስምና ሰበብም የሚቸበቸብ እቃ አይደለም፡፡
  የመስቀል በዓል አከባበር እንደ ምሳሌ  
ክርስትና ዓለምአቀፍ ሃይማኖት ነው  (universal)፡፡  ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስ  ማህደር ያስመዘገበችው ክርስትናን ወይም ሃይማኖትን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስ ማህደር ያስመዘገበችው የመስቀል በዓል አከባበርን እንጂ መስቀልንም አይደለም፡፡ ምክንያቱም መስቀልም በምልክትነት ዓለም አቀፋዊ ወይም ዩኒቨርሳል በመሆኑ ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ሃይማኖት ነው ሲሉ ይደመጣል፤ ከላይ እንደገለፅኩት መስቀል የተመዘገበው ከአዲግራት ደቡብ ኢትዮጵያ ድረስ ባለው ማህበረሰብ ኢትዮጵያ አቀፍ ሆኖ  ነው። የመስቀል በዓል በዓልም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሁሉም የኢትዮጵያ የህብረተስብ ክፍል የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
የመስቀል በዓል አከባበር የምዝገባ ሂደት በተመለከተ ብዙ ውጣ ውረዶች ታልፈዋል። ከእነዚህም አንዱ መስቀልን እንዴት አድርገን በህብረባህላዊ አመለካከት /በህዝቦች መካከል/ ማህበራዊ ጥምረት እንዲፈጠር፣ አድርገን ማስመዝገብ እንችላለን የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ የሚገኙ የካቶሊክ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች፣ መስቀል በዓለም የቅርስ ማህደር እንዲመዘገብ በፊርማቸው ጭምር በማረጋገጣቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነትና ፆታ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳን በውስጣቸው ከፍተኛ መከባበር፣ ‹‹የአንዱ ዕውቅና የእኔም እውቅና ነው›› የሚል የእኔነት ስሜት በውስጣቸው የዳበረ፣ የራሳቸውን ባህልና ማንነት የሚጠብቁ፣ ለሺዎች ዓመታት ሳይከፋፈሉ በማህበራዊ ጥምረት /social cohesion/ የኖሩ፣ የብዙ ቋንቋና ባህል ውህዶች ሆኖም አንድ ብሔር ናቸው፡፡
ከላይ በመስቀል አመዘጋገብ ሂደት እንደታየው፣ ቅርሶች ከምንም ተፅዕኖ ተላቀው በህብረተሰቡ ይሁንታና ፈቃድ ያለ አንዳች ፖለቲካዊ ተፅዕኖ፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ብዝሀ ባህል አካል ሆነው እንዲቀጥሉ መፍቀድ ወሳኝ ነው፡፡
እና ምን ይደረግ?
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ባለስልጣናት፣ ለህብረተሰባቸው ቃል ከሚገቡበት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ‹‹ቅርሶችን በዓለም የቅርስ ማህደር እናስመዘግባለን›› የሚለው ነው፡፡ ይህንን ሲናገሩም አስረግጠው ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ወይ በሚቀጥለው ሳምንት እያሉ፡፡ በመሆኑም በህብረተሰቡ ዘንድ ‹‹ቅርሱ በዩኔስኮ ካልተመዘገበ ቅርስ አይደለም›› ወደ ሚል አስተሳሰብ እንዲገባ እያደረጉ ነው፡፡ በዘርፉ በባህልና ቱሪዝም ሴክተር ያሉ የህዝብ ግንኙነት አካላት ሳይቀሩ ስለ ዩኔስኮ አሰራር የጠለቀ እውቀት ያላቸው አይመስሉም። በዚህም የተነሳ ስስ የሆነና የህብረተሰብን ስሜት በቀላሉ ሊያስቆጣ ወይንም ሊያሳዝን በሚችል ርእሰ ጉዳይ ተደጋጋሚ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ሲሰጡ ይታያል፡፡ ‹‹እናስመዘግባለን›› የሚሉ ክልሎችም ይሁኑ ህብረተሰቡ ያልተረዳው በዓለም መካነ ቅርስና በዓለም ወካይ ቅርስ መሃከል ያለውን ልዩነት ነው። በዓለም ወካይ ቅርስ አንድን ቅርስ ለማስመዝገብ ምንም ዓይነት የተወሳሰበ ሳይንስ የለውም፡፡ እጅግ ፈታኙ የማስመዝገብ ሂደት ከላይ እንደጠቀስኩት፤  ቅርስን በዓለም መካነ ቅርስ ማህደር ማስመዝገብ ነው፡፡  
በዓለም ወካይ ቅርስ አንድን ቅርስ ለማስመዝገብ፣  አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ከዩኔስኮ ድረ ገፅ ላይ በቀላሉ ሊያገኘው የሚችል አይሲኤች ዜሮ ሁለት የሚባል ፎርም መሙላት ነው፡፡ ድረ ገጹ ላይ በዓለም ወካይ ቅርስ አንድን ቅርስ ለማስመዝገብ ‹‹Instructions for completing Form ICH-02››
የሚሉትን መመሪዎች በመከተል የምዝገባውን ሂደት ማካሄድ ይቻላል፡፡
ይህንን የጠያቂዎች የምዝገባ ስራ በበላይነት የሚያስተባብረው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ነው፡፡ የሂደቱን ጅማሮም ሆነ ፍፃሜ በቅርብ የሚከታተል አካል ነው፡፡ ሆኖም የህዝብን አስተሳሰብ፣ ስሜት፣ ዝንባሌ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴቶችን፣ የአንድ ማህበረሰብን መለያ…  በእጃችን ላይ በሌለ የዩኔስኮ ውሳኔ ‹‹ሁሉንም ቴክኒካዊ ጉዳዮች ስላሟላን መመዝገቡ አይቀሬ ነው›› በማለት ለሚዲያ ፍጆታ ማዋሉ፣ የህብረተሰቡ መለያ የሆነው ቅርስ ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ከማድረጉም በላይ በመመዝገብና ባለመመዝገብ ሂደት ውስጥ ድንገት ውሳኔው እንደተጠበቀው ባይሆን ሊያስከትል የሚችለውን ፖለቲካዊ ጠባሳ ሁሉም ወገን ሊያጤነው ይገባል፡፡  
ባህል ሚኒስቴር በዚህ ረገድ በደርግ ጊዜ ከነበረው የባህል ሚኒስቴር በእጅጉ ወደ ኋላ የቀረ ነው፡፡ በሜትር አርቲስት የዓለም ሎሬት  አፈወርቅ ተክሌ፣ በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ በእነ አርቲስት እሸቱ ጥሩነህ፣ በታዋቂው ፀሀፌ ተውኔት መንግስቱ ለማ፣ በእነ ደራሲ አያልነህ ሙላት፣ በእነ አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ…. ይመራ የነበረው የድሮው ባህል ሚኒስቴር፤ አሁን የቀድሞው ግርማ ሞገሱ አለ ለማለት ያዳግታል።  የአሁኑ ሚኒሰቴር መስሪያ ቤት በስብሰባ፣ ጭፈራና በተለያዩ የአበል  ሁነቶች የተጠመደ ነው ቢባል ማጋነን ይሆን?
የዛሬው ባህል ሚኒስቴር ቅርስ ትናትና ጥበቃ  በክልሎች  በመምህርነት ስራ ረዥም ጊዜን አሳልፈው፣ በተጓዳኝ ኑሮን ለመለወጥ ኢህአዴግን የተቀላቀሉ አባል የነበሩ ወይም የሆኑ መምህራን ስብስብ ነው የባህል ሚኒስቴር ያቋቋመው አንድ የገዳ አስመዝጋቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ መግለጫውም፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተደርጎ መቅረቡ ትንሽ ገርሞኛል፡፡ ዩኔስኮ በምዝገባ ሂደቱ በኢትዮጵያ በኩል የሚያውቀው ተጠሪ አካል (state party) የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንን ሲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ራሱን ባለቤት አድርጎ መቅረቡ ከኮሜዲዎቹ አንዱ ነው? ከሰሞኑ አስቂኝ ትእይንቶች ሌላው በቢሸፍቱ ‹‹የጦር ሄሊኮፕተር ወደ በዓሉ የጠራሁት እኔ ነኝ›› ማለታቸው ነው፡፡ ዩኔስኮ በባህላዊ ክብረ በዓል ላይ የጦር ሄሊኮፕተር፣ የጦር መሳሪያ፣  ፖለቲካዊ ባነር ወይም መገለጫ እንዲኖር እንደማይፈቅድ አያውቁም ማለት ነው? ጦር የተሰካበት ዱላ እንኳን መታየት የለበትም፡፡
ይህንን እንዴት ሊዘነጉት ቻሉ? የመመዝገቡ ብስራት መቼ በይፋ ተነገረና ነው ሄሊኮፕተር ለመጥራት የሄዱት? ይህ በተባለ ማግስት የክልሉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ‹‹ገዳ በዓለም የመጀመሪያው ዲሞክራሲ ነው›› ሲሉ በሬዲዮ ፋና ተገኝተው ከክልሉ ባህል ቢሮ ኃላፊ ጋር መግለጫ፤ ሰጥተዋል፡፡
እንደ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው መግለጫ  ሌሎች በንጉስ በሚተዳደሩበት ዘመን ‹‹እኛ ዲሞክራሲ ነበረን›› ብለዋል፡፡ ጥሩ ነው እሰየው!! ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ‹‹ዲሞክራሲ ከረዥም ጊዜ ሂደት በኋላ የሚመጣ ነው›› እያለን ባለበት ጊዜ፣ ገና በውስጣችን እንዳልሰረፀ እየነገረን ባለበት ወቅት እሳቸው አባል የሆኑበት ኢህአዴግ፤ ከኦሮሞ ገዳ ዲሞክራሲ  ምን እንደተማረና ምን መማር እንዳለበት  መምክር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ይህን መሰል ዲሞክራሲያዊ ባህል እያለው አፍሪካ ለምን ከዚህ ትምህርት መውሰድ እንዳልቻለች መሪዎቻችንም ሊነግሩን የግድ ነው።
በነገራችን ላይ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ባህላዊ መድረኩን ለፍላጎታቸው ማዋላቸው በዩኔስኮ አይደገፍም፡፡ ስፍራው አባገዳዎች እንዳሉት፤ የእርቅ የሰላም እንጂ የፖለቲካ መነታረኪያ መድረክ መሆኑ ባህላዊ ፋይዳውን በእጅጉ ይጎዳዋል፡፡ ገና መቼ ተነጋገርን? በሚቀጥለው ሳምንት ስለ የመስክ ተወካይ (antiquity officer) አሰራር እናወራለን፡፡ የሳምንት ሰው ይበለን!!


Read 8544 times