Sunday, 09 October 2016 00:00

ራስ ካሣ ኃይሉ ስደተኛው መጽሐፋቸውና ፍልስፍናዊ ቀመራቸው

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(4 votes)

      ቤተ ትምህርቱ ከቤተ ክህነቱ በመመንጨቱ፣ ቤተ ክህነቱም ለቤተ መንግስቱ የቀኝ እጅ በመሆኑ፣ ቀደም ባለው የሀገራችን ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ የምንጠራቸው አብዛኞቹ ጎምቱ ስሞች፣ የቤተ-መንግስትንና የቤተ-ክህነትን ጃኖ የደረቡ ጸሐፍት ናቸው፡፡ ከእኒህ ውስጥ በአማርኛ የፈጠራ ጽሑፍ ቀዳማይ የሆነውን “ጦቢያ”ን የጻፉት አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ፣ የቤተ-ክህነትን ትምህርት ልቅምጭ ያደረጉ የቤተ-መንግስቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡
የዘመናዊ ትምህርትን ብርሃን በኢትዮጵያ ለማብራት ተግተው ሲጽፉ የነበሩትና በትምህርት ሚኒስቴርም ውስጥ ከፍ ባለው ዙፋን ላይ ለመቀመጥ የበቁት ከበደ ሚካኤልም እንዲሁ ናቸው፡፡ ሌላም ጎምቱ ደራሲ አሉ፤ ሀዲስ ዓለማየሁ። በቤተ-ክህነት ዕውቀታቸውና በቤተ-መንግስቱ ስልጣናቸው ይታወቃሉ፡፡ እኒህ በስም ያነሳኋቸው በተለይ የሚታወቁት ዘመን አመጣሹን የሥነ-ጽሑፍ ዘውግ ተከትለው በመጻፍ ሲሆን ብዙዎቹም የፈጠራ ጽሑፍ የሚከትቡ ነበሩ፡፡
ማህተመስላሴ ወ/መስቀል ደግሞ ሌላ ገጽታ የነበራቸው የቤተ-ክህነትና የቤተ-መንግስት ባለሟል ነበሩ፡፡ የልጆች ምክር የሚሆን የሀገር ባሕል ተረት መጽሐፍ ከማሳተም አልፈው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚገልጽ ደጓሳ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ “ዝክረ ነገር” የተሰኘው መጽሐፋቸው ‹ኢንሳይክሎፒዲያ› የሚባለውን የውጭዎቹን መጽሐፋዊ እሳቤ ለመተካከል የተሞከረበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የፍልስፍና ትምህርት ታሪክ ውስጥ ታላቅ ስም ያላቸው እጓለ ገ/ዮሐንስም የቤተ-ክህነቱ ውጤት ናቸው፡፡ ስነ-መለኮታዊውን ትምህርት ከጀርመን ዘመናዊ የፍልስፍና ትምህርት ጋር አዳቅለው፣ የበሰለ ፍልስፍናዊ ዕይታን መፍጠር የቻሉ ሰው ናቸው፡፡ አሁንም ድረስ አንባቢያን እያደኑት ያለው “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” የተሰኘ መጽሐፋቸው (ንግግራቸው) የእሳቸውን ፍልስፍናዊ ምጥቀት የሚያሣይ ነው፡፡
ኅሩይ ወ/ሥላሴ ደግሞ ትውልድ መቅረጽን በመመኘት፣ የቅዱሳን መጽሐፍትን ውስጠ- ምሥጢር በሚገባና በሚጥም ተረክ፣ ‹ኤሊጎሪ› ድርሳን እየከሸኑ ትውልድን መግበዋል፡፡ “ወዳጄ ልቤ”፣ “ስኳርና ወተት”፣ “ለልጅ ምክር ያባት ስጦታ”፣ “የጽዮን ሞገስ ጋብቻ” እና የመሳሰሉ መጽሐፎቻቸው፣ ልጆችን በመንፈሳዊ አስተሳሰብ ቀርጾ፣የጥሩ ምግባር ባለቤት ለማድረግ ያለሙ  ይመስላሉ፡፡ ዛሬ ከእኒህ ደራሲ ዓላማ ጋር መሳ ለመሳ የሆነ ዓላማ ያነገቡ አንድ ደራሲን ህይወትና ስራ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ።
 የትውልዳቸው ቀን ህዳር 3 ቀን 1873 ዓ.ም ነው፡፡ በልጅነታቸው ዓለምን ጠልተው የምንኩስና ህይወትን ተመኝተው፣ የታጨችላቸውን ወ/ሪት አልቀበልም እስከ ማለት ደርሰው ነበር። አስቀድሞ በመንፈሳዊ ህይወት ጥላ ስር መሆናቸውን የጠላው ባይኖርም፣ ምንኩስናውን የወደደላቸው ግን አልነበረም፡፡ እናም የመጀመሪያው ግሳጼ ከእምዬ ምኒልክ ደረሳቸው፡፡ ምንኩስና የሚሉትን ትተው፣ ለወግ ለማዕረግ እንዲበቁና የታጨችላቸውንም ወ/ሪት አሜን ብለው እንዲቀበሉ አሳሰቧቸው፡፡ ይህንን ንጉሣዊ ግሳጼ መግፋት ያልሆነላቸው ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ፤ በ1895 ዓ.ም ልዕልት ጽጌ በሻህን ሊያገቡ ችለዋል፡፡ ከዚያም አስራ አንድ ልጆችን አፍርተው፣ የተመኙትን የምንኩስና ሕይወት በ1920 ዓ.ም ተቀላቅለዋል፡፡  
ልዑል ራስ ካሣ በህይወት ዘመናቸው አስራ ሁለት መጻሕፍትን አሰናድተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ “ስለ አባት እናት”፣ “ምርጥ ቃላት”፣ “ጊዜ ጥበባት”፣ “ጣዕመ ጸሎት”፣ “ጣፋጭ ጥበብ”፣ “አጭር ጸሎት”፣ “ከሁሉ አይነት”፣ “አበራ ወንጌል”፤ እንዲሁም የአራት ቋንቋዎች (እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛና አማርኛ) የንግግር መማሪያ መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡  የሁሉም መጽሐፎቻቸው መሠረታዊ ትኩረት፣ ስነመለኮታዊ ምጥቀትና መንፈሳዊ ፍጽምና ይመስላል፡፡ እነሆም ዛሬ ከእኒህ ሁሉ ውስጥ የፍልስፍና ቀለም ያለውን ስደተኛውን መጽሐፋቸውን እንመለከታለን፡፡ “ፍኖተ አእምሮ” የሚል ርእስ ያለው ይኸው መጽሐፍ፤ ‹የእውቀት ጎዳና› የሚል የግእዝ ምላሽ የሚመስል ንዑስ ርዕስ አለው፡፡ በዚህ መጽሐፍ “የመግቢያ መንገድ” ውስጥ እንዲህ የሚል  ሰፍሯል፡-  ‹‹ፍኖተ አእምሮ (የእውቀት ጎዳና) የተሰኘው ይሄ መጽሐፍ፤ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ በ1918 ዓ.ም ለመጻፍ ጀምረውት በ1922 ዓ.ም ፈጽመውት፣ በዘመኑ በነበረው በደህና ቁም ጽሕፈት አስገልብጠውታል››
የዚህ መጽሐፍ የስደት ታሪክ የሚጀምረው በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ሀገራችንን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረበት ወቅት ነው፡፡ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ፤ በጊዜው በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦር ሲቀላቀሉ፣ የትግሬ ጦር ግንባር ጠቅላይ አዛዥ ሆነው ነው፤ ያኔ ይህንን መጽሐፋቸውንም ይዘውት ዘመቱ፡፡
በማይጨው ጦርነት የተፈጠረው በተፈጠረ ጊዜ፣እንደ ንጉሡ ልዑል ራስ ካሣም ስደትን ሲመርጡ፣ ያኔ ይሄ መጽሐፋቸው ከእሳቸው ተለይቶ ነበር፡፡ ላስታ ውስጥ የቀረው  መጽሐፉ፤ በአንድ ታማኝ አሽከራቸው አማካኝነት በእንክብካቤ ተይዞ፣ ከአቢቹ ጦር ጋር ፍቼ ላይ ዘምተው ለነበሩት ሁለቱ የልዑሉ ልጆች ማለትም ለደጃዝማች አበራ ካሣና ለደጃዝማች አስፋወሰን ካሣ ያስረክባል፡፡
የዚህ መጽሐፍ ታሪክ ሰፊ ነው፡፡ ሁለቱ ደጃዝማቾች አባታቸው በብዙ የለፉበት ይህ መጽሐፍ በክብር እንዲቀመጥ በማሰብ፣ አዲስ አበባ በሚገኘው ቀራኒዮ (አባታቸው ባሠሩት ደብር) እንዲቀመጥ አደረጉ፡፡ ይሁንና በ1929 ዓ.ም ሁለቱ የልዑሉ ልጆች በጠላት ጦር ተገደሉ፡፡ መጽሐፉም የቤተክርስቲያን ንብረት ሲዘረፍ አብሮ ተዘረፈ፡፡ የተዘረፉት ንብረቶችም እዚህና እዚያ ሲጣሉ፣ ለገበያ ሲቀርቡና ሲቸበቸቡ፣ በቀለ የተባለ የልዑሉ አሽከር ይህንን መጽሐፍ አይቶ ሊያልፈው አልቻለም፡፡ ለመጽሐፉ የተጠየቀውን ዋጋ ከፍሎ ሁነኛ ቦታ ላይ ያስቀምጠዋል፡፡ ለአምስት ዓመታት በእንግሊዝና በእየሩሳሌም በስደት የኖሩት ልዑሉ፤ ወደ ሀገራቸው (ከንጉሡ ጋር) ሲመለሱ፣ ይሄ አሽከራቸው መጽሐፉን ሊያስረክባቸው በቃ፡፡ ልዑል ራስ ካሳ፤ በ1949 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት እስኪለዩ ድረስ መጽሐፉ እንዲታተም ፈቃድ አልነበራቸውም፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ ግን ይሄ መጽሐፍ የታተመ ሲሆን በህይወት እያሉ መጽሐፉ እንዳይታተም የፈለጉት ከትህትናቸው የተነሳ መሆኑን የሚያምኑ ብዙ ናቸው፡፡
301 ገጾች ያለው መጽሐፉ፤ በ37 ምእራፎች መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን ይዟል፡፡ የአጻጻፍ ስልቱ መጽሀፍ ቅዱሳዊ ምክሮችን በመተንተን ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ይሔም እነ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ ከተጠቀሙበት አምሳላዊ ወይም ኤሊጎሪካል አጻጻፍ የተለየ ያደርገዋል። እንደ መጽሀፍ ቅዱስ፤ በምዕራፍና በቁጥር እየሸነሸኑ፣ ከመጻፋቸውም በላይ ሊያብራሩ የሚያስቡትን ነገር ጥያቄ ብለው በጥያቄ ይጀምሩታል፡፡ ምላሽ ብለውም ትንታኔያቸውን ያስቀጥላሉ፡፡ አስተምህሮው ወይም የአስተምህሮው መሠረት መንፈሳዊ ይሁን እንጅ መጽሐፉ ዓለማዊ ሕይወትን እንዴት በእርጋታ፣ በጣዕምና በስኬት መምራት እንደሚቻል የሚያስረዳ ነው፡፡ ሳምንት ፍልስፍናዊ ቀመራቸውን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ያሰንበተን!

Read 3729 times